Monday, 24 December 2018 08:22

አቶ አምዶም በጭብጨባ ስለታፈነው ሃሳባቸው ይናገራሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 · “እኔ ያንን ሁሉ ሰምቻቸው፣እነሱ አምስት ደቂቃ እንኳ መቋቋም አልቻሉም”
    · “ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ከሁሉም በላይ የታፈነው በትግራይ ነው”
    · “በትግራይ ህወሓትን መቃወም ከባድ ዋጋ ያስከፍላል”

    ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ በመቐሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተካሄደው ውይይት፤ በህወሓት ላይ የሰላ ትችት የሰነዘሩትና ሃሳባቸው በጭብጨባ የታፈነባቸው የ”አረና” የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገ/ሥላሴ፤ ከአዲስ አድማስ ጋር አጭር የስልክ ቆይታ አድርገዋል፡፡ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አጠናቅሮታል፡፡


    በኮንፈረንሱ ላይ የተሳተፉት ተጋብዘው ነው?
ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው በመቐለ ዩኒቨርሲቲና በትግራይ ክልል መንግስት ነው ተብሏል፡፡ በዋናነት የተዘጋጀው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ለፓርቲያችን ሶስት ሰዎች እንዲሳተፉ የሚጠይቅ ግብዣ ቀረበልን፡፡ ግብዣውን ተቀብለን ከሁለት ጓደኞቼ ጋር በኮንፈረንሱ ላይ ለመሳተፍ ተገኘን፡፡ በኮንፈረንሱ ሰዎች በሰፊው እየተሳተፉና ሃሳብ እየሰጡ ነበር፡፡ እኔም እድል ተሰጥቶኝ ለመናገር ስሞክር አቋረጡኝ፡፡
እንዴት ነው ንግግርዎ እንዲቋረጥ የተደረገው? ማይክራፎን የማጥፋት ሁኔታ ነበር የሚባለው እውነት ነው?
ማይክራፎን አልጠፋም፡፡ ሁሉም እንደተመለከተው፣ በጭብጨባ ነበር ሃሳቤን ለማቋረጥ የሞከሩት፡፡ ይሄን ደግሞ ያስጀመሩትና የመሩት አቦይ ስብሃት ናቸው፡፡ እሳቸው ሲጀምሩ፣ ለዚህ ተዘጋጅቶ የነበረ ካድሬ፣ ያለ ማቋረጥ ወደ ጭብጨባ ነው የገባው። ጉባኤው  የአንድ ቀን ተኩል ነበር፡፡ የእነሱ ሰዎች ያለ ገደብ እስኪበቃቸው ተናግረዋል፡፡ ለኔ ንግግር የተሰጠኝን አምስት ደቂቃ እንኳ በአግባቡ ሳልጠቀም ነው ያቋረጡኝ፡፡ እኔ ያንን ሁሉ ሰምቻቸው፣ እነሱ አምስት ደቂቃ እንኳ መቋቋም አልቻሉም፡፡
ሃሳብ የማፈኑን ድርጊት የተቃወሙ  አልነበሩም?
አቶ በረከት መድረክ ላይ ሆነውም ድርጊቱን ተቃውመዋል፡፡ ሃሳብን ማፈን ትክክል አይደለም ብለው፣ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ ካድሬዎቹ ግን ምንም አልመሰላቸውም፡፡ ምሁራኑ ግን በድርጊቱ አዝነው አይቻለሁ፡፡ ከአዳራሽ ከወጣን በኋላ በተፈጠረው ድርጊት ያዘኑ በርካታ እንደሆኑ ተገንዝቤያለሁ፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የሚንጸባረቁት ሃሳቦች ምን ዓይነት ነበሩ?
ብዙም የተለየ ሃሳብ የለም፡፡ ለኔ የተመቸኝና ጥሩ ሃሳብ አቅርበዋል ብዬ የምጠቅሳቸው፡- ሌ/ጀነራል ፃድቃንና ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት ናቸው። ተቀራራቢ ሃሳብ ነበር ያቀረቡት፡፡ ይሁን እንጂ የኔ ንግግር በካድሬዎቹ አልተወደደም፡፡
ሃሳብዎ  ከተቋረጠ በኋላ በውይይቱ ቀጠሉ ወይስ አቋርጠው ወጡ?
እስከ መጨረሻው ድረስ ቁጭ ብዬ ተከታትያለሁ፤ አላቋረጥኩም፡፡
በመቀሌ በተደጋጋሚ  ከተካሄዱ  ውይይቶች ምን ታዘቡ?
ከዚህ ቀደም ከነበሩ የፖለቲካ አቋሞችና አካሄዶች የተለየ ሃሳብ ሲንፀባረቅ አላስተዋልኩም፡፡ ውይይቶቹ  ጠንከር ያለ ሃሳብ አይስተናገድባቸውም፡፡ በጣም ልምጥምጥነት ያላቸው ውይይቶች ናቸው፡፡ እስካሁን የተለየ ሃሳብ አላገኘሁም፡፡  
ብዙ ጊዜ የውይይት አጀንዳ የሚሆነው ምንድን ነው?
የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚል ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ሶሽዮ-ፖለቲካዊ ሁኔታንም ለመቃኘት የሚሞክር ነው፡፡ በሀገሪቱ የተፈጠሩ የፖለቲካ ችግሮች ከምን መጡ በሚልም፣ የመፍትሄ ሀሳቦች የመፈለግ አዝማሚያ ነበራቸው፡፡ መፍትሄ ተብለው የሚቀርቡት ሃሳቦች ግን አዲስ ነገር የላቸውም። ያው ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውሉ ናቸው፡፡ በተለይ በህወሓት የሚዘጋጁት ለራሳቸው ጥቅምና ፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳ የታለሙ ናቸው፡፡ የተለየ ነገር የላቸውም፡፡
በትግራይ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ምን ያህል ይከበራል?
በአሁኑ ወቅት ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ከሁሉም በላይ የታፈነው በትግራይ ነው፡፡ ህዝቡ ሃሳቡን መግለፅ አይችልም፤ እንደታፈነ ነው ያለው፡፡ የተለየ ሃሳብ የሚያስተናግድ አማራጭ ሚዲያ የለም፡፡ ህብረተሰቡ እንዳይናገር ታፍኗል፡፡ ያው ትግራይ እንደ ቀድሞው ነው፤ አዲስ ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ እስረኞችም በትግራይ እስካሁን አልተፈቱም፡፡ በሁሉም መልኩ ያለው አፈና አሁንም ቀጥሏል፡፡   
የትግራይ ፖለቲካ ወዴት እያመራ ነው ይላሉ?
እዛው ነው ያለው፡፡ ወዴትም አላመራም፤ነገር ግን ህውሓት የመገንጠል አጀንዳን አሳብባ ስልጣኗን ማጠናከር ትፈልጋለች፡፡ ይሄን ፍላጎቷንም እያየን ነው። ህውሓት ከሌለ የትግራይ ህዝብ እንደማይኖር ተደርጎ ነው፣ ህዝቡ ላይ ፍርሃት የሚነዛው፡፡ ይሄው ነው አሁን በትግራይ ያለው ፖለቲካ፡፡ ህብረተሰቡ ግን እኔ እስከተረዳሁት፣ የመገንጠልም ሆነ ከኢትዮጵያዊነቱ የመላቀቅ ሽራፊ ፍላጎት የለውም፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ ፅኑ ህብረተሰብ ነው፡፡
ከጉባኤው በኋላ የደህንነት ስጋት አላደረብዎም? እንደውም ታስረዋል የሚል መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቶ ነበር---
ያው የመጣ ይምጣ ብለን ነው፡፡ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ከፈለጉ ደብድበው ሆስፒታል ያስገቡናል። ይሄ ደግሞ የተለመደ ነው፡፡ የመጣውን ለመቀበል ሁሌም ዝግጁ ሆነን ነው የምንታገለው፡፡ እኔ ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ተደብድቤ፣ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኝ፣ ሆስፒታል ገብቻለሁ፡፡ ጓደኞቻችን ደግሞ ከኔም በላይ ጉዳት የደረሰባቸው አሉ፡፡ የህይወት መስዋዕትነትም የከፈሉ አሉ፡፡ በትግራይ ህወሓትን መቃወም ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እስካሁን ግን (ረቡዕ ነው ቃለ ምልልሱ የተደረገው) ያጋጠመኝ ነገር የለም፡፡ ታሰረ የተባለውም ስህተት ነው፡፡
በሃሳብ አፈናው ዙሪያ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከተሰጡ አስተያየቶች ምን ተገነዘቡ?
አፈናውን እንደተጋሩት ተረድቻለሁ፡፡ ችግሩ እንደገባቸውና ችግራችንን ሌላውም እንደሚጋራን ነው የተገነዘብኩት፡፡ ትግራይ ከፍተኛ አፈና ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ሚዲያዎች ይሄን ነገር ትኩረት ሰጥተው መመልከት አለባቸው፡፡ ከአፈና እንድንወጣ አማራጭ ሃሳብ የምናቀርብባቸው መድረኮች ያስፈልጋሉ፡፡ ይሄን ዕድል ቢፈጥሩልን መልካም ነው፡፡   

Read 5898 times