Saturday, 19 May 2012 12:17

የልማት ተነሺዎች ቤታችን በላያችን ላይ ፈረሰ አሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

ከልጆቼ ጋር ዝናብ እየደበደበኝ ነው - ወ/ሮ ዘውድነሽ

ቆሻሻ እንኳን በክብር ነው ተከፍሎ የሚደፋው

ሁለት ሰዎች በድንጋጤ ወድቀው ተጐድተዋል

አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ሠፈር” ለበርካታ ዓመታት ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አፀደ ተሰማ”  በ4ብር ተከራይተው በሚኖሩባት አንዲት የቀበሌ ክፍል ቤት ውስጥ 10 የቤተሰብ አባላት ያስተዳድራሉ፡፡ አካባቢው ለልማት ስለሚፈለግ ቤቱን ለቀው እንዲወጡ የሶስት ቀናት ጊዜ ቢሰጣቸውም መኪና ባለማግኘታቸው አንድ ቀን እንዲጨመርላቸው መጠየቃቸውን ወ/ሮ አፀደ ይናገራሉ፡፡ አፍራሽ ግብረ ሃይሎቹ ግን አሻፈረን አሉኝ የሚሉት ነዋሪዋ “ እግራቸው ስር ተደፍቼ ለመንኳቸው “ እነሱ ግን ደፈርሽን በማለት ጭርሱኑ አንድ ቀን ቀነሱብኝ ብለዋል- እያነቡ፡፡ እቃ የሚጭኑበት መኪና የሚያገኙት እሁድ እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ አፀደ” ግብረ ሃይሎቹ እስከ እሁድ እንዲታገሷቸው ተማጥነዋል፡፡

ቀበሌው ቀደም ሲል ቤታችሁ የሚፈርሰው የተሰጣችሁ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ስትገቡ ነው ብሎአቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ቆሻሻ እንኳን የምንጥለው በክብር ከፍለን ነው ያለችው ወ/ት እቴነሽ አበራ በበኩሉዋ “ እኛ ግን ክብራችን ተዋርዶ በላያችን ላይ ቤታችን ፈርሷል ስትል በምሬት ተናግራለች፡፡ ሌሎች ነዋሪዎች ከዓመት በፊት በክብር ቤታቸውን ለቀው እንደወጡ የተናገሩ አንድ ነዋሪ” እስካሁን ቦታው ታጥሮ ቆሻሻ መጣያ መሆኑን በመጥቀስ” ለአንድና ለሁለት ቀን ቢታገሱን ምን ይሆናሉ ሲሉ ግራ በመጋባት ጠይቀዋል፡፡  የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ዘውድነሽ ወልዴ” ከእናትዋ ጋር ተጠግታ ነበር የምትኖረው፡፡ አሁን ግን የእናቴ ቤት ፈርሷል ትላለች፡፡ እናት ባለአንድ መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ቢደርሳቸውም ገና ተሰርቶ ስላላለቀ መውደቂያ የለንም ብላለች፡፡ ወ/ሮ ዘውድነሽ ኤችአይቪ በደሟ ውስጥ ስላለ ተጠልላ እንድትኖር ደብዳቤ እንደተፃፈላት ገልፃ “ቀበሌው ተለዋጭ ቤት የለኝም በማለት ያለችበትን ቤት ጣሪያ ስለነቀለባት የቤቷን ጣሪያ በላስቲክ ለመክደን መገደዷን ትናገራለች፡፡ “ከልጆቼ ጋር ዝናብ እየደበደበኝ ነው” ብላለች - ወ/ሮ ዘውድነሽ እያለቀሰች፡፡  በአሁኑ ሰአት እየፈረሰ ያለው የቀበሌ ተከራዮች ቤት ብቻ  እንደሆነ የነገሩን ነዋሪዎቹ” ቤቶቹ ሲፈርሱ ሁለት ህፃናት ፍርስራሽ ወድቆባቸው መፈንከታቸውን እንዲሁም ሁለት በእድሜ የጠኑ አዛውንት እራሳቸውን ስተው መውደቃቸውን ገልፀውልናል፡፡  ቤታቸው በመፍረሱ ምክንያት ሜዳ ወድቀዋል የተባሉ አንዲት  ነዋሪን  ብቅል ተራ አካባቢ አግኝተን ልናነጋግራቸው ብንሞክርም “ምንም ነገር መናገር አልፈልግም” መውደቂያ የለኝም” በማለት ቅሬታቸውን ገልፀውልናል፡፡ ነዋሪዎቹ ባሰሙት ቅሬታ ዙሪያ የቀበሌውን ስራ አስኪያጅ ለማነጋገር ብንሞክርም ለዚህ ዕትም ሊደርስልን አልቻለም - ረQም ስብሰባ ስላለብኝ በሚቀጥለው ዕትም ሰፊ ማብራሪያ እሰጣለሁ በማለታቸው፡፡

 

 

 

 

Read 16712 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 12:44