Print this page
Tuesday, 01 January 2019 00:00

የአማልፊዋ ወጣት

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(6 votes)

 ከኡማ ጋር አስር ሰአት ላይ ቀጠሮ ነበረኝ። እዛው እስዋ የምትማርበት ኮሌጅ አጠገብ ያለ ፌርማታ ጋ ነበር የተቀጣጠርነው፡፡ ዘወትር ወደምንሄድበት መናፈሻ፣ በዘጠኝ ቁጥር አውቶብስ ለመሄድ ነው ያሰብነው፡፡ ወርቃማ ፀጉርዋንና ውብ ሰማያዊ አይኖችዋን ለማየት ከመጓጓቴ የተነሳ ዘጠኝ ሰአት ተኩል ነበር የደረስኩት። ቦታው ጭር ያለ ሲሆን ብዙ የመኪና ግርግር አይታይበትም፡፡ በምስራቅ ሳንላጀሮ፣ በደቡብ ኮንካ ዲማሬኒ፣ በሰሜን ምስራቅ ራቬሎ ማናሮ የሚያዋስናት አማልፊ ኮስት፤ በሎሚ እርሻዎቿም ትታወቃለች፡፡ ከኡማ ጋር ከተዋወቅን ዘጠኝ አመታት ቢያልፉም፣ የፍቅር ግንኙነት
የጀመርነው ግን ከአንድ አመት በፊት ነበር፡፡ ያን ቢጫ ቱታዋን ለብሳ ስፖርት ስትሰራ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት፡፡ አንድ ሸበቶ ፀጉር ያላቸው በደንብ የለበሱና ከዘራ የያዙ አዛውንት መጥተው አጠገቤ ተቀመጡ፡፡ ዕድሚያቸው በግምት ወደ ስድሳ አምስት ይጠጋል። ነጭ ሙሉ ሱፍ፣ ከቡናማ ሸሚዝ ጋር አስማምተው ለብሰዋል፡፡ ወርቃማ ህብር ያለው ቢራቢሮ ከረቫት አስረው፣ ነጭ ባርኔጣ ደፍተዋል፡፡ ጫማቸው በደንብ የተወለወለ ሲሆን የሥነ ፅሑፍ ተማሪ በመሆኔ ሰውየው ሰብአዊ ፍጡር ብቻ ሳይሆኑ ገፀ ባህሪ ጭምር መስለው ታዩኝ፡፡
ምን ዓይነት ገፀ ባህሪ ይሆኑ፡፡ በጣም ሃብታምና የተካበደ ሳይሆን ቀለል ያለ አኗኗር የሚመሩ፡፡ እንዲህ ዓይነት አለባበስ ለብሶ አውቶቡስ የሚጠብቅ
ሰው አይቼ ስለማላውቅ ነው፣ ስለሳቸው እንዲያ የገመትኩት፡፡  
“ሶስት ቁጥር አውቶቡስ አልፋለች?” ሲሉ ጠየቁኝ፡፡
“ከመጣሁ ጀምሮ አላለፈችም” መለስኩኝ፡፡
“ከመጣህ ስንት ጊዜ ሆነህ?”
“ወደ ሃያ ደቂቃ ገደማ” በጥያቄው እየተገረምኩኝ፡፡
“ሶስት ቁጥርን ነው የምትጠብቀው?”
“አይ እኔ እንኳን ዘጠኝ ቁጥር ነው የምጠብቀው”
ሁለታችንም ዝም ብለን ተቀመጥን፡፡ ያጋጣሚ ነገር ሆነና፣ ወዲያው ዘጠኝ ቁጥር አውቶቡስ መጣችና ፌርማታው አጠገብ ቆመች፡፡ ሰውየው ዞር ብለው
አዩኝና፤ “መጣችልህ” አሉኝ፡፡ አዛውንቱ ያልገባቸው ነገር አለ፡፡ እኔ ኡማን ሳልይዝ አልሄድም፡፡
“አይ ትለፈኝ” አልኩኝ፤ በመጠኑ አፈር እያልኩኝ፡፡
በሩን ዘግቶ ሄደ፡፡
“እንግዳ ነገር ነው” አሉ፡፡
“አይ የምጠብቀው ሰው ስላለ ነው” አልኩኝ ፍርጥም ብዬ፡፡
“ሴት ናት?” ፈገግ አሉ፡፡
“እ…አዎ” እያመነታሁ፡፡
“እንግዲያማ እንዳንተ አይነት ጀግና ወጣት፣ እንዴት መንገድ ፌርማታ ላይ ሊጠብቅ ይችላል?”
እኔ ስለ ሰውየው ስገምት፣ ሰውየው ግን ስለኔ ማወቃቸው ገረመኝ፡፡
“አያስደንቅም፡፡ ሁላችንም ያለፍንበት ነው፡፡ ወጣት ወንዶች---ማለት እንዳንተ አይነት ተማሪ፣ የገንዘብ ችግር ሊኖርበት ስለሚችል፣ ፍቅረኛውን ፌርማታ
ጋ ቢቀጥር አያስገርምም”
 እዚህ ላይ እንኳ ተሳስተዋል፡፡ ባይበዛም የተወሰኑ ሺ ሊሬዎች ይዤ ነበር፡፡
“ቀድመህ መገኘትህ ትክክል አድርገሃል፡፡ በምንም መንገድ ሴትዋን ማጣት የለብህም፡፡ አንዴ ካጣሃት እንደገና ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው” አሉኝ፡፡
“እንዴት?”
“እኔ ላይ ስለደረሰብኝ ነው፡፡ እንደምታውቀው አማልፊ በሎሚ እርሻዎችዋ ትታወቃለች፡፡ እና ወሲብ የጀመርኩት በአስራ ስድስት አመቴ ነበር፤ አስራ ዘጠኝ አመት ከሞላት የጎረቤት ልጅ ጋር፡፡ መጀመሪያ እንደ ጓደኛ ነበር የምንተያየው፡፡ አንድ ቀን ቤቷ ስሄድ ቤተሰቦችዋ ሁሉ እቤት አልነበሩም፡፡” አሉና ጭልጥ ብለው በሃሳብ ተጓዙ፡፡
“ከዚያስ?” ጠየቅኩኝ፤ቀጣዩን ለመስማት እየጓጓሁ።
እንደመባነን አሉና፤ “ና አንድ ነገር ላሳይህ አለችና፣ ከመደርደርያው ላይ አንድ ግማሽ የደረሰ የጂን ጠርሙስ አንስታ፣ ሁለት ብርጭቆ ላይ ቀዳች፡፡
ከዚያም ሁለት ትልልቅ አረንጓዴ የሎሚ ፍሬዎችን ቆርጣ ከጨመቀችበት በኋላ ብርጭቆዋንና ብርጭቆዬን አጋጨች፡፡ ጠጣሁት፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሰውነቴን ሁሉ
ሲነዝረኝ ተሰማኝ፡፡ ከት ብላ ሳቀችና እንደገና ብርጭቆዎቻችን ሞላችና አሁንም ሎሚ ቆርጣ ከጨመቀች በኋላ እንደገና አብረን ጨለጥነው፡፡ ከዚያ በኋላ
ራሴን ያገኘሁት የሷ አልጋ ላይ ነበር፤ ሁለታችንም እርቃናችንን ሆነን፡፡ እንደዚያ አይነት ወሲብ በመላው አለም ተደርጎ የሚያውቅ አይመስለኝም--”
ብለው ትካዜ ውስጥ ገቡ፡፡  
“እባክዎትን አያቋርጡ” ለመንኳቸው፡፡
“እንደነገርኩህ ዋናው ነገር ሴትዋን ማጣት የለብህም፡፡ በፍቅር ከነፍን፡፡ ሁልጊዜ ከወሲብ በፊት ጂን በሎሚ መጠጣት አይቀሬ ሆነ፡፡ በሁለተኛው አመት ኔፕልስ ኮሌጅ መግባት ነበረብኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለሶስት አመት መለያየት የግድ ነበር፡፡ ከሶስት አመታት በኋላ እኔ የአስራ ዘጠኝ አመት፣ እሷ የሃያ ሁለት ዓመት ጎረምሶች ሳለን፣ ኔፕልስ መጣችና ተገናኘን፡፡ የደረሰችው በእኩለ ሌሊት ስለሆነ ሱቆችም ሱፐር ማርኬቶችም ዝግ ነበሩ፡፡ አንድ ክፍት ግሮሰሪ ብቻ ነበር፡፡ ለረዥም ሰዓት ተቃቅፈን ከተሳሳምን በኋላ ልጋብዛት ወደ ግሮሰሪው አመራን፡፡ የሚበላ ነገር ቀማምሰን፣ ጂን በሎሚ አዘዝን፡፡
“ጂን ቢኖርም ሎሚ ግን እንደሌለ አስተናጋጅዋ ነገረችን፡፡ ጂኑ ተቀዳና ቀመስኩት፡፡ አጥወለወለኝ። እሷንም ሳያት ፊትዋ ኮሶ መስሏል፡፡ ሁለታችንም ተግባባን፡፡ መጣሁ አልኩና ወጣሁ፡፡ ወዴት ነህ ብላ አልጠየቀችኝም፡፡ ምክንያቱም የት እንደምሄድ ታውቃለች፡፡ ክፍት ሱቅ ፍለጋ ማሰስ ጀመርኩ፤ ሁሉም ዝግ ነበር፡፡ ከሩቅ አንድ የበራ መብራት አየሁ። ልቤ እየመታ በፈጣን እርምጃ መራመድ ጀመርኩ። ወደ መብራቱ እየቀረብኩ ነው፡፡ ስደርስ የሱቁ በር  ከውጭ በትላልቅ የሰረገላ ቁልፎች ተከርችሟል፡፡ ከዚያ ሱቅ ውጭ ከተማው ሁሉ ኦና ሆኖ ጭር ብሎ ነበር። እንኳን ክፍት ቤት ሊኖር ቀርቶ የሰው
ዘር የለም። በፍርግርጉ የብረት መዝጊያ በመስተዋቱ ውስጥ የሱቁ ሸቀጣሸቀጦች ሁሉ ይታዩኛል፡፡ የወተት ተዋፅኦ፣ ልኳንዳው፣ ለስላሳ መጠጡ፣ አልኮሉ፣ ፍራፍሬው---ከሁሉም በላይ ግን በግምት ሁለት ሳጥን የሚሆን ትኩስ ትላልቅ አረንጓዴ ሎሚዎች---” አሉና ፈዘው ቀሩ፡፡
በመገረም አፌን ከፍቼ ቀርቻለሁ፤ “ከዚያስ?” አልኩኝ፤ በደከመ ድምፅ፡፡
“ሎሚዎቹን እያየሁ ፈዝዤ ቀረሁ፤ በሎሚዎቹ ውስጥ ግን እሷን ነበር የማየው፡፡ አይኔ እንባ አቅርሮ እዛው እንደተገተርኩ ሁለት ፖሊሶች መጡ፡፡
“ምን ታረጋለህ?” ጠየቁኝ፡፡
“ሎሚ ልገዛ ነበር” መለስኩ፡፡
“ተዘግቷል! ቀጥል!”
እያዘንኩ ተመለስኩ፡፡ ግሮሰሪው ውስጥ ቁጭ ብላ ነበር፡፡ ምንም ሳንነጋገር አንገታችንን ደፍተን ወደ ማደርያችን ሄድን፡፡ በነጋታው ጠዋት የማይታለፍ የስራ ቀጠሮ ስለነበራት አማልፊ መመለስ ነበረባት፡፡ ምንም ፍቅርም ወሲብም ሳንሰራ እንቅልፍ በአይናችን ሳይዞር ነጋ፡፡ ጠዋት ላይ ሸለብ አደረገኝ፡፡ ስነቃ አልጋው ላይ የለችም፡፡ ኮሞዲኖው ላይ ግን አንድ ወረቀት ነበር፡፡ ነገሮች ሲመቻቹ እመጣለሁ፡፡ ጠብቀኝ ይላል፡፡ የኮሌጁ ትምህርት ብዙ ስላልተሳካልኝ ወደ ንግድ ገባሁ፡፡ አንድ ሱቅ ተከራየሁ፡፡ እቃ ስሞላ የመጀመሪያው ዋናው ነገር ግን ሎሚ ነበር፡፡ ሱቁ እየተስፋፋ መጣ፡፡ ትርፉ በጣም እየጨመረ
ስለመጣ፣ አሉ ከተባሉ የሎሚ ገበሬዎች እየወሰድኩ ሎሚ አከፋፋይ ሆንኩኝ፡፡ አማልፊ መጣሁና ብዙ ሄክታር መሬት የሎሚ እርሻ. አለማሁ። … እዚሁ
አማልፊ የሎሚ የታሸገ መጠጥ ፋብሪካ የከፍትኩት በዚያን ጊዜ ነበር…”
ሶስት ቁጥር አውቶብስ መጥታ ፌርማታው አጠገብ ቆመች፡፡
“ልጄ አደረቅኩህ ሰላም ዋል፡፡” አሉና ፈጠን ብለው ወደ አውቶቡሱ ውስጥ ገቡ፡፡ የታሪኩን መጨረሻ ለማወቅ ተከትያቸው ወደ አውቶቡሱ ልገባ ስል፤“ቻዎ …” አለችኝ ኡማ፤ ዞር ብዬ ሳያት ጉርድ ቀሚስ ለብሳ፣ ሎሚ እየመጠጠች ነበር፡፡
አንዴ እሷን፣ አንዴ ሽማግሌውን አፈራርቄ ተመለከትኩ፡፡ ፈገግ ብለው እያዩኝ ጣታቸውን እሷ ላይ ቀሰሩ፡፡ “ዋናው ነገር ሴትዋን ማጣት የለብህም” እያሉ እንደሆነ ገባኝ፡፡
እኔና ኡማ ፌርማታው ጋ ተቀምጠን ዘጠኝ ቁጥርን ስንጠብቅ፣ አዛውንቱ የሎሚ ከበርቴ ለመሆን ያደረሳቸውን ጉዳይ እያሰብኩ ነበር፡፡ እንዲያ ተዘጋጅተው
ግን ያቺ የሚጠብቋት ሴት መጥታላቸው ይሆን? አልኩ፡፡---         

Read 3603 times