Saturday, 26 May 2012 11:07

እምነትና አማኞች - ሦስት ሐሰሳ ሙሴ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(0 votes)

“How Small Sinai appears

When Moses stand up on it”

(Heinrich Heine)

ሔነሪክ ሔይንን “አፌ ቁርጥ ይበልልህ” ባልነው ነበር የኛ የአነጋገር ዘዬ ግራ እንዳያጋባው ፈርተን ተውነው እንጂ፡፡ ደግሞም ከትክክል በላይ የሆነ ገለፃ ነው ስለሙሴ የቀረበው፡፡ ሲና ተራራ ላይ ሙሴ ሲገኝ ተራራው በንፅፅር ከታላቁ ሰው እንዴት እንዳነሰ ለማየት አይነ ህሊናን መክፈት ይበቃል፡፡ ሲና ምስኪኑ ተራራ ሙሴን ሲያይም ይሆናል የተሸማቀቀው፤ ገና ሳይወጣበት፣ እምጵፅ - ለሲና!የሙሴ ታላቅነት (The Towering figure of Moses ይሉታል ፈረንጆቹ) ያፈዘዛቸው፣ ያነሆለላቸውና እንደ ሲና በረሃ የራሳቸውን ትልቅነት ያስረሳቸው ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ20 ተወልዶ በ50 ዓ.ም የሞተው የአሌክሳንደሪያው ፈላስፋ philio አንዱ ነው፡፡ “Life of Moses” የሚል የተደጐሰ መፅሐፍ አበርክቷል፡፡ ሙሴን “ታላቁ” እያለ የመጥራትን በር የከፈታት እሱ ነው፡፡ እነሆ እኛ ተቀበልነው፣ ከምስጋና ጋር፡፡ ለphilio ሙሴ ፈላስፋ ነው፡፡ የተጓዘውም የፍልስፍናን መንፈሳዊ መንገድ ነው፡፡ ከድንቁርና ፈርኦናዊ ባርነት) እስከ መገለጥ (ተስፋይቱ ምድር) ጀምሮ ጨርሶታል - ያለ አንዳች ቅብብል፡፡ ዘይገርም!በpsychoanalysis የምታውቀት Sigmund Freud ደግሞ የphilioን መቋጫ ይቃወማል፡፡

“Moses and Monotheism” በተሰኘ መፅሐፉ፤ ሙሴ philio እንዳለው አንድ ሳይሆን መንታ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ ነፃ አውጥቶ እስከተወሰነ ሸኝቶ አብቅቷል ወይም ሞቷል፤ ሁለተኛው ሙሴ ከዚያ ይቀጥላል፡፡ የፈረንጅ ነገር! የደረጀውን ነገር አፍርሶ አዲስ ረጋሰራሽ ነገር ለመትከል መጣሩ አያስገርምም? ደግሞም’ኮ የባሰ አታምጣ ማለት ደግ ነገር አይመስላችሁም? ምክንያቱም እንደ Eduard Meyer ያለ የታሪክ ተመራማሪ ሊጥልብን ይችላላ፡፡ ማነው እሱ ደሞ? ምን አለ? ለምትሉ ብቻ ይሄን አንብቡ!

 

“Moses was not a historical personality”

ጨርሰው ሳይነጥቁን ቀጥታ ወደ ሙሴ ታሪክ፡፡የአማልክቶቹ “ዘመነ-መሣፍንት” ከፋፍለህ ግዛ እና ትእቢት በታላቁ ሙሴ ቆራጥ እርምጃ እንዲሁምየማያወላውል አመራር ከዓለም ላይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲደመሰስ ተደረገ፡፡ ይሄን ጊዜ ሙሴ ባይነሳ አማልክቱን ለመለማመን ውድ ልጆቻችንን ሳይቀር እሳት ውስጥ በመጨመር መስዋእት እናደርግ ነበር፡፡ እግዚኦ! ደግነቱ ሙሴ ተነሳልን እንጂ፡፡አማልክቶቹ ሙሴ መጥቶባቸው እስኪርበደበዱ ድረስ ብዙ የሙሴ አይነት “የአንድ አምላክ ሰባኪያንን” (monotheism) ፀጥ አሰኝተዋል፡፡ “History of Religion” የተሰኘ መፅሐፍ በግብፅ በባቢሎንና በኢራን ውስጥ የአማልከቱን ጀሌ ከእምነት ስፍራ ለማስወገድ እና አንድ አምላክን ለመተካት ሙከራ መደረጉን ይነግረናል፡፡ አልተቻለም እንጂ፡፡ የየአማልክታዊ ጉልቱ ቀሳውስት በጅማሬ አስቀሩት፡፡ (አብዮታዊው ዘገባ “ቀለበሱት” ይላል) ሙሴን ግን አልቻሉትም፡፡ አማልክቱ መጥፊያቸውን በጉያቸው ሸሽገው አሳደጉ እንበል?እስራኤላውያን ባርነትን የጠሩዋት በገዛ እጃቸው ነው፡፡ ከኬብሮን ቆላ፣ የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸውን ዮሴፍን ለእስማኤላውያን አሳልፈው በመሸጣቸው መዘዝ መላ እስራኤላውያን የግብፅ ባርነት መጣባቸው፡፡ ባርነቱ የከፋው በዳግማዊ ራምሴስ ዘመን ሲሆን ከፍተኛ የጉልበት ሥራና ወንድ ልጅ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ማእቀብ ተጣለባቸው፡፡ “የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ወንዝ ጣሉት፤ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በህይወት አፅኑአት ብሎ ህዝቡን ሁሉ አዘዘ” እንዲል፡፡ሙሴ የተወለደው፣ ወንድ ሆኖ ከህብሩ መፈጠር የሞት ፍርድ በተበየነበት (አብዮታዊው ዘገባ “ቀውጢ”ይለዋል) ጊዜ ሲሆን ከሥጋ ዘመዶቹ ጋር የቆየው ለሦስት ወር ጊዜ ብቻ፤ አልተቻለምና በቅርጫት ተደርጐ በወንዝ ላይ ተለቀቀ፡፡ ያገኘችው የፈርኦን ልጅ ናት፡፡ ደንገጡሯን ልካ ባስመጣችው ጊዜ ቆንጆ ወንድ ልጅ! አሳደገችዋ!!እንደ ሙሴ ህይወት ሁሉ ስሙም ሁለት አይነት ፍቺ አለው፡፡ በአሳዳጊዎቹ በግብፆች ከሄድን “ሙሴ” (moses) ወንድ ልጅ ማለት ነው፡፡ ግብፆች ከሙሴ የተመለከቱት ወንድ ልጅ መሆኑን ብቻ ነውና በቀላሉ “ማሞ” አሉት፡፡ “The Bible as History” መፅሐፍ እንደሚነግረን “ሙሴ” የሚለው ስም የሥጋ ዘመዶቹ በሚናገሩበት ስርዎ ቋንቋ “አወጣ፣ ወሰደ፣ አስወገደና በኃይል ነቀለ” የሚል ፍቺ አለው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ግብፆችና እስራኤሎች እንደየፍጥርጥራቸው ሥሙን ሲጠሩት ደስ እየተሰኙ መሆኑ አይደንቅም?ከመደነቃችን ስንመለስ ደግሞ ይሄ ምርምር ተዘጋጅቶ ይጠብቀናል፡፡ ሙሴ በዚች ምድር ላይ ከመከሰቱ ከአንድ ሺህ አመት አስቀድሞ እንደተፃፈ የተገመተ የድንጋይ ጥርብ ታሪክ ተገኘ፡፡ የተገኘው ፅሁፍ ከባቢሎናውያን አፃፃፍ መግነን በፊት ጥቅም ላይ ይውል የነበረ cuneiform ነው፡፡ “የሳርጐን አፈታሪክ” (Sargon legend) በሚል ይታወቃል፡፡ የAKKad ስርዎ መንግሥት መስራች የንጉስ ሳርጐን ታሪክ ተቆንፅሎ ሲተረጐም እንዲህ ይነበባል (በተርጓሚዎቻችን ላይ እምነታችንን ጥለን)“እኔ ሳርጐን ነኝ፣ ባለ ሃይል ንጉስ፣ የአካድ ንጉስ፣ እናቴ የኦኒቱ ካህን ነበረች፣ አባት የሚባል አላውቅም… እናቴ በምስጢር አርግዛ በምስጢር ወለደችኝ… በውሃ ዳር ቄጠማ የተበጀ ትንሽ ሳጥን ውስጥ ከተተችኝ፡፡ ወንዙ ላይ አኖረችኝ… ወንዙም እያንሳፈፈ ወደ አኪ ወሰደኝ፡፡ የወንዙን ውሃ እየመራ አትክልት በማልማት የሚተዳደረው አኪ አንስቶ እንደ ልጁ አሳደገኝ፡፡”የፈረንጆችን ተንኮል ለተረዳ ነገሩ ይቀልለታል፡፡ ጠጋ-ጠጋ እያሉ ያሉት ሙሴን “ቅጂ” ወደማድረግ ነው፡፡ ማን ቢሰማቸው፡፡ የጀመርንበትን ጥቅስ አንዴ አስታውሰናቸው እንቀጥላለን እንጂ “How Small Sinai appears when Moses stand up on it!” በዚህ አፍ ካሲያዝን ዘንዳ ስንቀጥል:-መጀመሪያ ወደ ግብፅ ያቀናው ዮሴፍን ጨምሮ ከያዕቆብ ጉልበት የወጡ ልጆቹ ሰባ-ሰባት ሆነው አልቀሩም፡፡ እጅግም በዙ ተባዙም ግብፅንም ሞሉዋት፡፡ ግብፃውያንንም ሊያሳስቧቸው፣ ሊያሰጓቸው ጀመሩ፡፡ በዚህ መካከል እንግዲህ ዳግማዊ ራምሴስ በግብፅ ነገሰ፡፡ መፅሐፉ “በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሳ” የሚለው እሱ ዳግማዊነታቸው እስራኤላውያንን የማስጨነቅ ስትራቴጂ ነደፈ፡፡ በግብር፣ በጉልበት ሥራ፣ ፊቶም እና ራምሴን የተባሉ ማጐሪያ (Concentration Camp) መሰል መኖሪያ አካባቢን መከለልን ያጠቃለለ የማስጨነቅ ስትራቴጂ፡፡ ምን አለፋን በቀላሉ ዳግማዊ ራምሴስ ቀዳማዊ ሂትለር እንደማለት ነው፡፡በዚህ መካከል ደግሞ የዳግማዊነታቸውን ስትራቴጂ ድባቅ የሚመታ ሌላ የእስራኤል አምላክ ስትራቴጂ መነደፉን ልብ እያልን፡፡ ሙሴን ከተገፉት እስራኤላውያን እንዲፈጠር ማድረግ፣ እንዳይገደል መከላከል፣ እናቱ በቄጠማ ሳጥን አድርጋ በወንዝ ላይ እንድትለቀው ልቧን ማደንደን፣ የፈርኦን ልጅ ልጁን ስታገኝ ልቧ ወከክ እንዲል ማለዘብ፣ እንዲያድግና እስራኤሎችን እንዲታደግ ማድረግ የእስራኤል አምላክ ስትራቴጂ ነው፡፡ሙሴ በመጨረሻው ፍልሚያ ታጥቆ ፈርኦን ፊት በመቅረብ በቆራጥ ወኔ “ህዝቤን ልቀቅ” ሲል የሰማኒያ አመት ጐልማሳ ነበር፡፡ (ጐረምሳ አለማለታችን፣ አለማጋነን መፈለጋችንን ይጠቁማል) በሽርኩ እግዚአብሔር አማካሪነት “ልቀቅ” ይላል፡፡“አልለቅም” ልቡ በእግዚአብሔር መደንደኑን ያላወቀው ምስኪኑ ፈርኦን ይመልሳል፡፡ ምድረ ግብፅ በምድረ ጓጉንቸር ትመታለች፡፡ የንጉሱ ሌማት አልቀረም፡፡ “እለቃለሁ” ይላል ፈርኦን፡፡ “የጓጉንቸሩን ዝናብ አባራልኝ፣ የእንቁራሪቱን ደራሽ ገድብልኝ”“ደግ” ይላል ሙሴ፡፡ በፀናች እጅ ካልሆነ ፈርኦን እስራኤላውያንን እንዳይለቅ ቢያውቅም ቅሉ የጓጉንቸሩን ወረራ ይገታለታል፡፡ እንዲያ-እንዲያ እያለ በግብፅ ምድር ብዙ ድንቅና ተአምራት ይበዛሉ፡፡ ውሃው ተለውጦ ደም ይሆናል፣ ቅማል ይፈላል፣ በረዶ ይወርዳል፣ በዝንብ መንጐች ይወረራል፣ ሻህኝ የሚያወጣ ቁስል ይመጣል፣ ጨለማ ይሆናል፣ የበኩር ልጆችን የሚቀስፍ መአት ይወርዳል፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ መአተ-መአታት በኂላ የፈርኦን ደንዳና ልብ ለጊዜው ለዝቦ እስራኤላውያንንከነሀብታቸው ይለቃል - ኋላ ሊከተላቸው፣ ሊያሳድዳቸው፤ የተከፈለው ባህር እስኪከደንበት፡፡ ውሃውን ያቅልልለት፣ አሜን!!

 

 

Read 2335 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 11:14