Saturday, 26 May 2012 11:51

ፖላንድን በሳምንት ጉብኝት

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(0 votes)

ወደ ፖላንድ የመሄድ እድሉን ያገኘሁት በአዲስ አበባ የሚገኘው የፖላንድ ኤምባሲ ባዘጋጀው የጋዜጠኞች ጉብኝት ፕሮግራም አማካኝነት ነበር - ከሳምንት በፊት፡፡ ቦሌ አየር ማረፊያ  ተጓዥ መሆኔን አረጋግጬ” ሻንጣዬን አስመዝኜ ከላኩ በኋላ በኢሚግሬሽን በኩል የሚፈለገውን ፎርም ሞልቼ” ተራዬ ሲደርስ አንዱ መስኮት ጋ ቆምኩ፡፡ የስራ ኃላፊው ፓስፖርቴን ከተቀበለኝ በኋላ ይዞት ወደ አንድ ቦታ ሄደና ተመለሰ፡፡ “ለምንድን ነው የምትሄጅው?” የሚል ነበር ቀጣይ ጥያቄው ፡፡ “ለጉብኝት!” አልኩት፡፡ ቀና ብሎ አየኝና “ለጉብኝት ልትሄጂ አትችይም!” አለኝ፡፡ “ዘንድሮ ፖላንድ ከዩክሬን ጋር የአውሮፓ የእግር ኳስ ጨዋታን ስለምታስተናግድ ጋዜጠኞች ዝግጅቱ ምን እንደሚመስል እንዲያዩ የፖላንድ ኤምባሲ ስለጋበዘን ነው” ብዬ በዝርዝር አብራራሁለት፡፡

በንቀት ቀና ብሎ አየኝና “እስከዛሬ የሄድሽባቸው አገሮች ግን ይሄን አያሳዩም” አለኝ፡፡ ፓስፖርቴ ላይ የጋና እና የሱዳን ቪዛ ነው ያለው፡፡ የጥያቄው አዝማሚያ ስለገባኝ “ፊት ለፊትህ ያለው ኮምፒዩተር ላይ የጉዞ ታሪኬ ፋይል ካለህ አሜሪካንም ሄጄ መጥቻለሁ” ይሄ አዲስ ፓስፖርት ስለሆነ ነው…” ስለው “በህልምሽ ነው” ሲል ተሳለቀብኝ፡፡ ሳቄ ቢመጣብኝም አልሳቅሁም፡፡ በንግግሩ ማፈሬን ግን አሳይቼዋለሁ፡፡ እንዲህ ነው መንገደኞችን እየተቀበለ የሚያስተናግደው? እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ ስንቱን እንዲህ አሸማቆ ይሆን ስል አሰብኩ፡፡ የቀጠረው መስሪያ ቤትም ሊያፍር ይገባዋል፡፡

የፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ ጥንታዊ እና አዲስ ከተማ በሚል ለሁለት ትከፈላለች፡፡ ጥንታዊዋ ከተማ ዋርሶ ውስጥ መታየት አለባቸው ከሚባሉ ቦታዎች አንዷ ስትሆን” ዘጠና በመቶ የሚሆነው የቀድሞ ይዞታዋ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወድሟል፡፡ አብዛኛው ነገር ከጦርነቱ በኋላ እንደ አዲስ የተገነባ ሲሆን በዩኔስኮ የአለም ቅርስ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡

በ1885 ዓ.ም በኮንስታንቲ ሄግል የተቀረፀችው ግማሽ ሰው ግማሽ አሳ ምስል (ሜርሜይድ) የዋርሶ ከተማ ምልክት ስትሆን ትልቁ የሜርሜይድ ሐውልት የሚገኘው በጥንታዊቱዋ ከተማ ነው፡፡ በፖላንዳውያን አፈታሪክ” ሜርሜይድ ከባህር ተነስታ አሁን ጥንታዊው ከተማ የሚገኝበት ስፍራ እረፍት ለማድረግ መጥታ ቆመች፡፡ ቦታውን ወደደችውና ለመቆየት ወሰነች፡፡ ነገር ግን እሷ ከተማ ውስጥ ስትቆይ በአቅራቢያው የሚኖሩ አሳ አጥማጆች እንግዳ ነገሮች ማየት ጀመሩ፡፡ ማዕበል አስቸገራቸው፡፡ የአሳ ማጥመጃ መረቦቻቸውም ተቀዳደው ያጠመዱትን አሳ መልሰው ለባህሩ ያቀብሉባቸው ጀመር፡፡ ይህን መአት ያመጣችባቸውን ሜርሜይድ ለመበቀል ተነሱ፡፡ ነገር ግን ዝማሬዋን ሲሰሙ በፍቅሯ ወደቁ፡፡ የማታ ማታ አንድ ሀብታም ነጋዴ አጠመዳትና በእንጨት በተሰራ ጐጆ ውስጥ አስቀመጣት፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳትቆይ የሚያሳዝን ለቅሶዋን የሰማ ወጣት” ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር ነፃ አወጣት፡፡ እሷም ከዛን ጊዜ ጀምሮ ከአሳ አጥማጆቹ ጋር ለመተባበር ቃል ገባች፡፡ ጋሻ እና ጦር ታጥቃም ዋርሶንና ነዋሪዎቿን መጠበቅ ጀመረች፡፡ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሜርሜይድ የዋርሶ ከተማ መለያ ምልክት ሆነች፡፡ በጣም ታዋቂው የዋርሶው ሜርሜይድ ሀውልት በጥንታዊው ከተማ ቢገኝም ከተማዋ በሜርሜይድ ምስል የተሞላች ነች፡፡አዲሱ የዋርሶ ክፍል ከ1952-1955 በሶቪየት ህብረት የተገነባው ሰማይ ጠቀስ የባህልና የሳይንስ ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉን ጆሴፍ ስታሊን ለፖላንዳውያን በስጦታ አበርክቶታል፡፡ ህንፃው የኮሙኒስት ስርአትና ሶቪየት ህብረት በፖላንድ ላይ የነበራቸውን የበላይነት ያስታውሳል፡፡  ሲኒማና ቲያትር ቤቶች፣ ሙዚየሞች፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ የኤግዚቢሽን ቦታዎችን አካትቶ የያዘ ነው - ህንፃው፡፡

የእውቁ ሙዚቃ አቀናባሪ የፍሬድሪክ ሾፐን ሙዚየምም ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ በሙዚየሙ የሾፐን ከ7ሺ በላይ ሙዚቃዎች፣ ደብዳቤዎች፣ ጌጣጌጦች፣ዳያሪዎች ወዘተ ይገኛሉ፡፡ የሾፐንን ስራዎች የማሰባሰብ እንቅስቃሴ የተጀመረው በ1889 ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሙዚየሙ በፍሬድሪክ ሾፐን ኢንስቲትዩት ስር ይተዳደራል፡፡ የዋርሶ የአውሮፕላን ማረፊያ በስሙ የተሰየመለት ሾፐን” ሙዚየሙን ዩኔስኮ በአለም ቅርስነት መዝግቦለታል፡፡

በሙዚየሙ ውስጥ ሾፐን ለተለያዩ ሰዎች የፃፋቸው ደብዳቤዎች ይገኛሉ፡፡ በሙዚየሙ ውስጥ በተቀመጡት ኮምፒዩተሮችም የፈለጉትን ሙዚቃ መርጠው ማዳመጥ ይችላሉ፡፡ አስጐብኚያችን ከተማውን እያዞረች ስታሳየን በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩት ጉዳዮች ሁለተኛው የአለም ጦርነትና አይሁዳውያን በጀርመኑ ሂትለር የደረሰባቸው ስቃይ ናቸው፡፡

ፓርላማው በጦርነቱ ወቅት ወድሞ ምንም ሳይሆኑ የተረፉት ምሰሶዎቹ ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን የሚታየው ፓርላማ በነዚያ ከውድመት በተረፉ ምሰሶዎች እንደ አዲስ የተሰራ ነው፡፡ ከመካከለኛው ዘመን የሚጀምረው የፖላንድ የፓርላማ ታሪክ “ በአሁኑ ጊዜ  በየአራት አመቱ ምርጫ ያካሂዳል፡፡ በየሁለት ሳምንቱ ደግሞ መደበኛ ስብሰባ ያደርጋል፡፡ ፓርላማው 460 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አንድ የግል ተመራጭ እና አንድ የጀርመን አናሳዎችን የሚወክሉ ተመራጮች ይገኙበታል፡፡ የፓርላማውን አዳራሾች በጐበኘንበት ወቅት እንደተመለከትነው”የፕሬዚዳንቱ መቀመጫ ጋዜጠኞችና ሌሎች እንግዶች በሚቀመጡበት ጋለሪ ላይ ተከልሎ ይገኛል፡፡ በፓርላማው ውስጥ ያሉት የተለያዩ አዳራሾች የሚለዩት እስካሁን ባገለገሉ አፈ ጉባኤዎች ሀውልት እንደሆነም ከአስጎብኚያችን ገለፃ ለመረዳት ችለናል፡፡

ዋርሶ በስነጥበብ የተዋበች ከተማ ነች፡፡ ህንፃዎቿ እጅግ ውብ ናቸው፡፡ ከመካከለኛው ዘመን እስከ አሁን ድረስ ያሉትን የተለያዩ ዘመናት የስነ ህንፃ አሰራሮች ታንፀባርቃለች፡፡ ከተማዋ  በአመት ውስጥ የተለያዩ የስነጥበብና የሙዚቃ ዝግጅቶች ያሉዋት ሲሆን ፋሲካ ሁለት ሳምንት ሲቀረው የሚካሄደው በቤቶቨን የተሰየመ ኮንሰርት አንዱ ነው፡፡ ሌላው የሞዛርት ፌስቲቫል (የበጋ የጃዝ ኮንሰርት) ሲሆን በሾፐን የተሰየሙ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ጨምሮ በዓመት ውስጥ አስራ ሦስት ቋሚ ኮንሰርቶች ይካሄዳሉ፡፡

አሁን የበጋ ወቅት (summer) እየገባ ነው፡፡ ከዩሮ 2012 ዝግጅት ጋር ተዳምሮ ዋርሶ ሞቅ ደመቅ ብላለች፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በአገሪቱ የሚገኙ ሙዚየሞች በሙሉ ተከፍተዋል፡፡ ኮንሰርቶች ተጀምረዋል፡፡ እኛ በታደምንበት ኮንሰርት የክላሲካል ሙዚቃ ኮምኩመናል፡፡ ሙዚቃው፣ ተጫዋቾቹ፣ ታዳሚው፣ ሁሉ ነገር ውብ ነበር፡፡ ለሙዚቃ ተጫዋቾቹ ያለማቋረጥ ማጨብጨብ ማለት አድናቆት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ሙዚቃ ተጫወቱልን ብሎ እንደመጠየቅ ነው፡፡ በአቅራቢዎቹና በታዳሚዎቹ መሀል ምንም አይነት የቃላት ልውውጥ የለም፡፡ አቅራቢዎቹ የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸውን እንደያዙ ታዳሚውን “እናመሰግናለን እባካችሁ ይብቃን” የሚል መልዕክት ባዘለ ገፅታ ይመለከታሉ፡፡ ታዳሚው ደግሞ ያለማቋረጥ ያጨበጭባል- እባካችሁ ተጫወቱልን እንደማለት፡፡ ከዚህ በሁዋላ ሙዚቀኞቹ ምንም ምርጫ የላቸውም፡፡  አንድ ሁለት ሙዚቃ ይጨምራሉ፡፡ በመጨረሻ ግን ሺህ ጊዜ ጭብጨባው ቢቀልጥም አመስግነው ይወጣሉ፡፡

ከኮንሰርት መልስ እራት በልተን ስንወጣ” በከተማዋ ሦስት የተለያዩ ቦታዎች ረጃጅም ሰልፎች አየንና አስጐብኚያችንን “ምንድነው?” አልናት፡፡ “ቆይ እናየዋለን” አለች፡፡ ከፊት ቀደም ቀደም ብላ በመሄድም በአካባቢው ላይ የነበረ አንድ ፖሊስ አናገረች፡፡ “አይ መግቢያው በዛ ነው” ብሎ ጠቆማት፡፡ ለካስ በመውጪያው በኩል ነው ልታስገባን የሞከረችው፡፡ “ይሄ እንግዲህ  የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ቤት ነው፡፡ ዛሬ የፕሬዚደንቱን ቤት መጐብኘት የሚፈልግ ሰው ሁሉ መጎብኘት ይችላል፡፡ ሰልፉ ረጅም ነው እንጂ እኛም እንጐበኝ ነበር” አለችንና ሳንጎበኘው ጉዞ ቀጠልን - ወደሌላ ጉብኝት፡፡ ትንሽ እንደሄድን የጠቅላይ ሚ/ሩ ቤትም በተመሳሳይ  የጐብኚዎች ሰልፍ መጨናነቁን አስተዋልን፡፡ ፓርላማውም እንደዛው፡፡ በቃ የጉብኝት ምሽት ልትሉት ትችላላችሁ፡፡

ፖላንድ ከዩክሬን ጋር በአንድነት የምታስተናግደው ዩሮ 2012 እየተቃረበ ነው፡፡ የዋርሶ ስታዲየም፣ ሆቴሎች፣ መዝናኛ ቦታዎች ወዘተ--- ሁሉም ዝግጅታቸውን እያጧጧፉ ነው፡፡ ፖላንድ አዘጋጅ አገር በመሆኗ የተሰጣትን 4 ቢሊዬን ዩሮ  ከጨዋታው ጋር የተገናኙ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያከናወነችበት  ሲሆን 20 ፈጣን አዳዲስ ባቡሮች፣ አንድ ሺህ አዳዲስ አውቶቡሶች አዘጋጅታለች፡፡ ለጨዋታው ወደ ሁለት ሺ የሚጠጉ የውጪ ዜጐች ዋርሶ ይገባሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ከፖላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከእኛ ጋር ለመገናኘት የመጡት ሰው በጣም አስገርመውኛል - የተዋወቁን ጥርት ባለ አማርኛ ስለነበር፡፡ “ኢትዮáያ ነበሩ ወይ?” ስንል ጠየቅናቸው፡፡ አንዴ ለሶስት ወር ያህል” ሌላ ጊዜ ደግሞ ለሶስት ቀን በአገራችን ቆይታ እንደነበራቸው ነገሩን፡፡ ይሄ ደግሞ እንደሳቸው አማርኛውን ለሚያቀላጥፍ ሰው ፈፅሞ በቂ ጊዜ ሊሆን አይችልም፡፡ ታዲያ ይሄ የመንዝ የመሰለ አማርኛ ከየት መጣ? አልናቸው - ፖላንዳዊውን የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ሰራተኛ፡፡ በዋርሶ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ቁዋንቁዋዎች ክፍል አማርኛ በመማር ላይ እንደሆኑና ትምህርቱን ሲያጠናቅቁ ለፖላንዳውያን ተማሪዎች የአማርኛ ሰዋሰው እንደሚያስተምሩ ደንቀፍ እንኩዋን ሳያደርጋቸው አወጉን፡፡

 

 

Read 3597 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 11:55