Monday, 28 January 2019 00:00

ዴዝዴሞና

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(9 votes)

 ከረፋፈደ  በኋላ ነበር የትያትር ቤቱ የኋላ ረድፍ ላይ ቦታ ይዞ የተቀመጠው፡፡ የያዘው ክፉ የፍቅር ልክፍት ነው በዚህ ቲያትር ቤት ውስጥ እንዲገኝ ያደረገው፡፡ ለሼክስፒር የተውኔት ድርሰቶች ፍቅርና ስሜት ኖሮት አያውቅም፡፡ እሱ ፍቅር የያዘው ከገፀባህሪዋ ስም ጋር ሞክሼ ስም ካላት የራሱ ዴዝዴሞና ጋር ነው፡፡ ክፉ የቅናት ዛር መንፈሱን ከተቆጣጠረው ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ እርዳታ ፍለጋ ሃኪም ጋር ሄዶ “ፓራኖያ አለብህ” ተብሏል፡፡ ከወንድ ጋር ያያት ሴት ሁሉ እስዋ ትመስለዋለች፡፡ ከንግግርዋ፣ ከአዋዋልዋ፣ ከአመሻሽዋ፣ ከአለባበስዋ፣ ከጓደኞችዋ፣ ከቤተሰቦችዋ፣ከትናንት ታሪክዋ ጋር የተገናኘ የቅናት መንፈስ ተጠናውቶታል። ስልክ ስታወራ በቅናት ልቡ ይመታል፡፡ ትንሽ ካመሸች ጓደኞቿ ጋር ሁሉ እየደወለ ወይም እየሄደ ሊሰልላት ይሞክራል፡፡ ባልና ሚስት ሳይሆኑ ሌባና ፖሊስ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በእንቅልፍ ልብዋ የሆነ ነገር ብታልጎመጉም፣ በሱ ነገር እየተጨነቀ፣ ፍችውን ለማወቅ ሲባዝን ያድራል፡፡
ለእሷ ካለው እውር ጭፍን ፍቅር የተነሳ “ኦቴሎ”ን ሊያይ ቲያትር ቤቱ የመጨረሻ ወንበር ላይ ቢሰየምም፣ መጋረጃው ተገልጦ ቲያትሩ የጀመረው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ነበር፡፡
ቃሲዮን ሲያይ፣ እጁን ቡጢ ጨበጠ፡፡ ይሄ ነው ሚስቴን ሲዳራ የሚያድረው እያለ ጥርሱን በቁጣ ያፋጫል፡፡ ኢያጎ ለኦቴሎ በመሰሪ ቋንቋው የዴዝዴሞናን አለመታመን በጆሮው ሲያንሾካሹክ፣ እሱም ከኦቴሎ ከራሱ በላይ ቁጣው ገነፈለ፡፡
ወደዚህ ቲያትር ቤት ለመግባት ዋና ምክንያቱ፣ ፍቅረኛው ትላንት በስልክ ከወንድ ጋር ስትቀጣጠር በመስማቱ ነው፡፡ ሁሉንም ንግግር  በትክክል ባይሰማም “ማዘጋጃ” እና “አስር ሰዓት” የሚሉት ቃላት ግን አላመለጡትም፡፡
ኦቴሎ በኢያጎ ስብከት በቁጣ ሲንጎራደድ፣ ድንገት አይኑ ውስጥ ገባች፡፡ ፊት ካለው ረድፍ ወንበር ላይ አንድ ጎረምሳ እጁን ትከሻዋ ላይ ጣል አድርጎ ተቀምጧል፡፡
እሷ ለመሆንዋ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ከአመት በፊት የገዘላትን ሻሽ አንገትዋ ላይ ጣል አድርጋዋለች፡፡ ረጅም ፀጉርዋንም ቢሆን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ እንዴት የሚስቱ ፀጉር ይጠፋዋል፡፡ ቢሆንም የማይቀና ጥሩ ባል ለመሆን በመሞከር፣ ስልኩን ከኪሱ አውጥቶ ቁጥርዋን መታ፡፡ ይጠራል፡፡ ግን አይነሳም፡፡ ሻሹን በደንብ አስተዋለ፡፡ ራሱ ነው፡፡ የሚያያት ከጀርባዋ ቢሆንም፣ ከት ብላ ስትስቅ፣ ሰውየውም አብሯት ሲስቅ ተመለከተ። አሁንም ደግሞ ደወለ፡፡ ሶስቴ ከጠራ በኋላ “የደወሉላቸው ደንበኛ ስልክ ጥሪ እያስተላለፈ ነው” አለች፤ ኦፕሬተርዋ፡፡
እሱ ላይ ስልክ እየዘጋች ከማንም ውርጋጥ ጎረምሳ ጋር ስታስካካ ሊታገስ አልቻለም፡፡ ሜሴጁን ማዥጎድጎድ ጀመረ፡፡
“አንቺ ውሻ፣ ሸርሙጣ፣ ድሮስ ማን ይፈልግሻል!” አንዱ ነው፡፡
ቲያትሩ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል፡፡ ኦቴሎም የዴዝዴሞና አልፍኝ ለመግባት እርምጃውን ጀምሯል፡፡
ሁለተኛውን ሜሴጅ ጻፈ፡፡
“በረጅም እንጨት አልነካሽም፡፡ ድሮስ እኔ አላቅሽም ወዘተረፈ …”
ለሃያ ደቂቃ ያህል ስምንት ሜሴጆችን አከታትሎ ቢጽፍም፣ የፍቅረኛው ሜሴጅ የመጣው ግን ዘጠነኛውን ሊጽፍ ሲያስብ ነበር፡፡
እንዲህ ይላል፡-
“ረስተኸው ይሆናል፡፡ እኔ ግን አልረሳውም። ዛሬ የተገናኘንበት ቀን ነበር፡፡ ልክ በዛሬው ዕለት፣ ከአራት አመታት በፊት፣ ምሽቱን ወጣ ብለን እንድናሳልፍ አስቤ ነበር፡፡ ስጦታም አዘጋጅቼልሃለሁ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ለገዛህልኝ ሻሽ እሺ ያልኩህ ጊዜ ትዝ ይልሃል፡፡ የኔ ፍቅር፤ የገዛሁልህን ሮሌከስ ሰዓት፣ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ ካለው ስዊዝ ሰዓት ቤት ውሰድ፡፡ የኔ ፍቅር ደህና ሁን፡፡
በፍጥነት ተነስቶ እየተንደረደረ፣ ወደ ፊት ወንበሮች አመራ፡፡ ሻሹን እያየ ወደሷ ቀረበ፤ አጠገብዋ ሲደርስ ፊትዋን በእጁ አዞረው። ዴዝዴሞና አልነበረችም፡፡ ሁለቱ ፍቅረኞች በድንጋጤ ፈጠው እያዩት ነበር፡፡
ኦቴሎ ዴዝዴሞናን ያነቀው በዚያ ቅፅበት ነበር፡፡

Read 3125 times