Saturday, 02 February 2019 15:03

ቃለ ምልልስ “ብሔራዊ መግባባት የሁላችንም ጉዳይ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 ነዋሪነታቸውን በለንደን ያደረጉት አቶ ስለሺ ጥላሁን፤ከግንቦት 7 ንቅናቄ መስራቾች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤትን ከፖለቲካ አጋሮቻቸው ጋር በማቋቋም በሊቀ መንበርነት ይመራሉ፡፡ በ26 የፖለቲካ ድርጅቶች ትብብር በአሜሪካ ሲያትል የተቋቋመው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመግባባትና እርቅ ኮሚቴ አስተባባሪው አቶ ስለሺ፤ በሙያቸው መሃንዲስ ሲሆኑ በቅርቡ ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም የሃገሪቱ
የፖለቲካ ኃይሎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀውን የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉባኤ ለማዘጋጀት ከኮሚቴው አባላት ጋር እየተንቀሳቀሱ
መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለመሆኑ የዚሀ ጉባኤ ዓላማ ምንድን ነው? በእርቅና መግባባቱ ላይ የሚሳተፈው ማነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡

     ብሔራዊ መግባባት ሲባል ምን ማለት ነው? በምን ጉዳይ ነው ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠረው?
የብሔራዊ መግባባት ጉዳይን ስናነሳ፣ በሃገሪቱ እስከ ዛሬ በርካታ መግባባት ላይ ያልደረስንባቸውን ጉዳዮች በማሰብ ነው። የመሬት ጥያቄ፣ የቋንቋ የማንነት፣ የሰንደቅ አላማ፣ የህገ መንግስት ጉዳይ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ህዝብን የስልጣን ባለቤት የማድረግ ጉዳይ፣ የምርጫ ጉዳይ፣ በዘር ወይም በጎሳ ሃገሪቱ በመደራጀቷ የዜጎች እንቅስቃሴና ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር ዋስትና ማጣት የመሳሰሉትም እንደ ሃገር አንድ መግባባት ላይ ልንደርስቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ አሁን በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ የለውጥ ኃይል አለ፡፡ የለውጥ ኃይሉ ያሳካቸው ወሳኝ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል የገጠሙት መሰናክሎችም አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች እንዴት ተወጥተን፣ ሃገርን ወደፊት ማሻገር እንችላለን ነው ዋነኛ ማጠንጠኛው፡፡
እስካሁን ለዚህ የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ የተደረጉ ዝግጅቶች ምን ይመስላሉ በእናንተ በኩል?
በውጪ ሃገር ሆነን በተከታታይ ውይይቶች ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ሃገር ውስጥ ካሉ ተወካዮች ጋርም ሰፊ ውይይት በቴሌ ኮንፈረንስ ስናድረግ ቆይተናል፡፡ መሪ እቅድ አውጥተናል፡፡ የሂደቱን ቅደም ተከተል ሰንደን አዘጋጅተናል፡፡ ለዚያም የሚሆን ፈንድ ተዋጥቷል፡፡ ትግሉ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሆነ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች (ከ50 በላይ) ናቸው የተሳተፉበት። የመጀመሪያ መለስተኛ ጉባኤ በራስ ሆቴል ተደርጓል፡፡ ቀጥሎ 100 የተለያዩ የሲቪክ ተቋማት የተሳተፉበት ጉባኤ ተደርጓል፡፡ አሁን ሁሉን አቀፍ ጉባኤ ለማድረግ ነው ጥረታችን፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት ድጋፍ ያስፈልጋል። እኛ ድጋፍ እንዲሰጡ ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ ምላሻቸውን እየተጠባበቅን ነው፡፡ ኤምባሲዎች ይሄን ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ጉባኤ በገንዘብ እንደግፋለን ብለው ነበር፤ ችግር የሆነብን መንግስት እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱ ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት የሁላችንም ጉዳይ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ የጀመራችሁት ነገር ካለ ቀጥሎበት ብለውናል፤ ነገር ግን መንግስታዊ ድጋፍ ነው የምንፈልገው፡፡
በመንግስት የተቋቋመ የብሔራዊ እርቅ ኮሚሽን አለ፡፡ የእናንተ በጐን ይሄን መድረክ ማዘጋጀት ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ኮሚሽኑ መቋቋሙን ሰምተናል፤ ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ፍኖተ ካርታውን አናውቀውም። ኮሚሽኑ ይዞት የተነሳው አላማ፣ እኛም እየሄድንበት ያለ በመሆኑ ጽኑ ድጋፍ አለን፡፡ ይሄ ኮሚሽን በዋናነነት የመንግስት ወይም የለውጥ ሃይሉ አቅጣጫ ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ሠላም እርቅና መግባባት አለበት ብለው የተነሱለት አላማ ነው፡፡ ይሄ እኛ ልናካሂደው ካቀድነው ጋር ምንም ተቃርኖ የለውም፡፡ መንግስትም ማካሄዱ፣ እኛም በሌላ መድረክ ማካሄዳችን ጉዳዩን የበለጠ ትኩረት የተሰጠውና ሁሉን አሳታፊ ያደርገዋል። ብሔራዊ መግባባትን የጠለቀ ለማድረግ መንግስት ብቻ ሳይሆን እኛም ሃላፊነት አለብን። ምናልባት ሁለቱ ተደምረው ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ ዋናው አላማው ግቡን ይምታ፡፡
ብሔራዊ መግባባቱ የሚፈጠረው በእነማን መካከል ነው? በፖለቲካ ልሂቃኑ? በህዝቡና በፖለቲካ ልሂቃኑ? በመንግስትና በህዝብ?
ይሄ ለውጥ ከመምጣቱ በፊት እኛ አሜሪካ ሲያትል ላይ ከሀገር ውስጥም ውጪ ያለን የፖለቲካ ሃይሎች ተሰባስበን ነው ጉዳዩን በዋና አጀንዳነት ያስቀመጥነው፡፡ በወቅቱ እኛ ጉባኤው ላይ እያለን ነበር አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ለቅቄያለሁ ያሉት፡፡ በወቅቱ የሀገሪቱ አቅጣጫ ወዴት ሊሄድ ይችላል የሚለው አስጨናቂ ነበር። ስለዚህ እዚያው እያለን ነው ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጣነው፡፡ በወቅቱ በመግለጫችን፣ የሽግግር መንግስትን አጀንዳም አካተናል፡፡ ግን በሂደት ዶ/ር ዐቢይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ሲመጡና እርምጃዎች ሲወስዱ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመለከት፣ በርካታ የሽግግር ጊዜ እድሎች አምልጠዋል፡፡ ለዚህ ነው የሽግግር መንግስት ካሁኑ ይቋቋም ያልነው። ነገር ግን በኋላ ላይ በሽግግር ሂደቱ ሊሳኩ የሚችሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በእነ ዶ/ር ዐቢይ አመራር ከሞላ ጐደል ተሠርተዋል፡፡ በወቅቱ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ብሔራዊ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የማለታቸው ሚስጥር በኋላ ላይ እየተፈታ መጥቷል፡፡
ሁላተንም እንደምናየው፤ የፖለቲካ ምህዳሩ ሠፍቷል፡፡ አሁን የፈለግነውን አጀንዳ ማራመድ እየቻልን ነው፤ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ አጀንዳን ጨምሮ፡፡
ስለዚህ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚለውን አጀንዳ ትታችኋል ማለት ነው?
አዎ! አሁን እሱ አጀንዳችን አይደለም፡፡ አሁን ዋነኛ አጀንዳችን፣ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ነው፡፡ በቀጣይ ምርጫ አለ፡፡ ከምርጫ በፊት ብሔራዊ መግባባትና እርቅ የስፈልገናል። በምርጫ ጉዳይ ውይይት ከመደረጉ በፊትም ብሔራዊ መግባባቱ ያስፈልገናል፡፡ በምርጫ ጉዳይ ብሔራዊ መግባባት ከፈጠርን፣ የእርስ በእርስ መጠራጠሩ ይቅርና ጠቅለል ባለ መልኩ፣ የህግና አሠራር ማሻሻያዎችን አቅርቦ፣ የተዋጣለት የምርጫ ስርአት መዘርጋት ይቻላል፡፡ ብሔራዊ መግባባት ሲባል የፖለቲካ ድርጅቶች መስማማት አይደለም፡፡ በአንድ ጉዳይ ቢያንስ የጋራ ግንዛቤ መያዝ ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ፓርቲዎች እርስ በእርስ እንዲዋሃዱ፣ እንዱጣመሩና እንዲቀናጁም ይረዳል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ መግባባት ስንል፣ የፖለቲካ ድርጅቶችንና ልሂቃኑን ማስማማት ሳይሆን በሀገር ጉዳይ የጋራ ግንዛቤ ይዞ፣ ልዩነትን ማራመድ መቻል ነው፡፡
ብሔራዊ መግባባት ከተፈጠረ በኋላ ብሔራዊ እርቅ ማድረግ አለበት፡፡ መግባባቱ በእርቅ መቋጨት አለበት፡፡ እርቅ ሲባል ወንጀል መደበቂያ አይደለም፡፡ እሱ በብሔራዊ መግባባት ጉባኤው አማካይነት መርማሪ ኮሚሽኖች ተቋቁመው ሊጣራ ይችላል፡፡ ይሄ የጉባኤው ውሣኔ ነው የሚሆነው፡፡
በዚህ የብሔራዊ መግባባት አጀንዳ ቅድሚያ የምትሰጡት ጉዳይ ምንድ ነው?
ብሔራዊ መግባባት የሚለው ጥቅል ሃሳብ ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ስንል ምን ማለታችን ነው? በጉባኤው እነማን ይሳተፋሉ? እነዚህን ዝርዝር ጉዳዮች በቀጣይ አዘጋጅተን ይፋ እናደርጋለን፡፡ ትኩረት የሚሰጣቸው አጀንዳዎችም፣ በቀጣይ በምናዘጋጀው ሰነድ ላይ ይፋ እናደርጋለን፡፡
የጉባኤው የጊዜ ገደብ፤ በስድስት ሳምንት ውስጥ ይካሄዳል የሚል ነው፡፡ አሁን የመጀመሪያ አጀንዳችን ይሄ ነው የሚለውን እኔ መናገር አልችልም፡፡ ይሄን የሚያዘጋጅ ኮሚቴ አለ፤ እሱ የሚያቀርበው መነሻ ሃሳብ ይወስነዋል፡፡
ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ውስጥ ብትሆንም በየቦታ ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ የብሔራዊ መግባባቱ አጀንዳ በቀጥታ እነማንን ታሣቢ ያደርጋል?
ግጭቶች አሳሳቢ ናቸው፡፡ እነዚህ ካልተፈቱ ወይም እንዲቀንሱ ካልተደረገ ምንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ አንዱ ትልቁ አጀንዳ፤ ይሄ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም በመንግስት አወቃቀር ውስጥ ዘጠኝ የክልል መንግስታት አሉ፡፡  አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች እነዚያ የክልል መንግስታት ውስጥ ገብተው ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ እንቅፋት እየገጠማቸው ነው።
ህዝቡም ችግር ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የጉባኤ ሂደት እነዚህ መሠረታዊ ችግሮች ምንጭና መፍትሔም ይፈተሻል፡፡ ከዚህ አልፎ የህገመንግስትም እጣ ፈንታ ላይ ውይይት ሊደረግ ይችላል፡፡ ቢያንስ ህገመንግስቱ ላይ የፖለቲካ ሃይሎች ያላቸውን አተያይ ቢያቀርቡና ሊሻሻሉ ሊለወጡም የሚገባቸውን ጉዳዮች ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡
አሁን ጉባኤውን ለማዘጋጀት በምትንቀሳቀሱበት ሂደት ውስጥ ምን ያህል የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው የሚሳተፉት?
በመጀመሪያ ሲያትል ላይ በነበረን ጉባኤ 26 የፖለቲካ ድርጅቶች ነበርን፡፡ ከሀገር ውስጥ እነ ሠማያዊ፣ መኢአድ ነበሩ፡፡ ከውጭ በትጥቅ ጭምር ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እነ አርበኞች ግንቦት 7 ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ሃገር ውስጥ ገብተን እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ በወቅቱ እኛ ሲያትል የመጀመሪያውን ስብሰባ ባደረግን ጊዜ በሌላ በኩል እነ ኦነግ፣ ኦብነግ ያሉበት የ11 ድርጅቶች ተመሳሳይ ስብሰባ ለንደን ውስጥ ተካሂዶ ነበር፡፡ እነሱም የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመው ነበር፡፡ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል ብለው የወሰኑበት ሁኔታም ነበር፡፡ እነሱ ያንን ማድረጋቸውን ካየን በኋላ ግንኙነት ፈጥረን ነበር፡፡ ወዲያው ሂደቶች ፈጣን ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ መሰባሰብ ተጀመረ፡፡ የፖለቲካ አሠላለፍም ለውጥ ታየበት።
በኋላ ሁለተኛው ሀገር ቤት ከመጣን በኋላ ሁላችንም የተገናኘንበትን ስብሰባ ነው ያዘጋጀነው፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ከ50 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግም ተገኝቶ ነበር፡፡ አቶ ዳውድ በእለቱም በጣም ገንቢ ሃሳብ ነበር ያቀረቡት፡፡ ለንደን ላይ የተሰባሰቡ አካላትም የዚህ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉባኤ አካል እንደሚሆኑ ነው አቶ ዳውድ ያረጋገጡት፡፡ ብሔራዊ መግባባቱ ወሳኝ እንደሆነ አቶ ዳውድ በእለቱ ተናግረዋል፡፡ ዛሬ ባደረግነው ስብሰባ ላይም ያልተገኙት ከመንግስት ጋር ተመሳሳይ ውይይት ስላለባቸው ነው፡፡ አሁን በዚህ የጉባኤ ሂደት ሁሉ ተሳታፊ ነው፡፡ ኦብነግ ተሣታፊ እንደሚሆን አረጋግጦልናል፡፡ የሚቀር አይኖርም ማለት ነው፡፡
ይሄን የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉባኤ ለማከናወን ከመንግስት ጋር እያደረጋችሁት ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?
ሲያትል ላይ ባለ ዘጠኝ ነጥብ አቋም ላይ ከደረስን በኋላ፣ በወቅቱ አቶ ሃይለማሪያም ከስልጣን ለቅቄያለሁ ስላሉ፣ ግንኙነት ስናደርግ የነበረው ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር ነበር፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሠፊ ውይይት ተደርጐ፣ እሳቸውም ደግፈውት ነበር፡፡ በኋላ ዶ/ር ዐቢይ ተመረጡ፡፡ እኛም የሽግግር መንግስት ጉዳይን ትተን ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ላይ አተኩረን፣ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ደብዳቤ ልከን ነበር፡፡ እስካሁን ግን ምላሽ አልተሠጠንም፡፡ በዋሽንግተን የፖለቲካ ድርጅቶች ከዶ/ር ዐቢይ ጋር  ያደረጉትን ስብሰባ እኛ ነን ያዘጋጀነው፡፡
እዚያ ላይ “እኔ አሸጋግራችኋለሁ ነው” ያሉት። ነገር ግን ብሔራዊ መግባባቱን ይቀበሉታል፤ ምላሽ ይሰጡናልም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከ50 ፓርቲ በላይ በተገኘበት የራስ ሆቴል ስብሰባችን፤ የኢህአዴግ ተወካይ ተገኝተው ነበር፡፡ ስለዚህ ሂደቱን ኢህአዴግም ይፈልገዋል ማለት ነው፡፡ የኛ አላማም ከጉባኤው ማንም እንዳይቀር ነው የምንፈልገው፡፡ እንደውም መንግስት በሠፊው በሂደቱ ገብቶ ቢመራውና ቢተባበረን ጠቃሚ ይሆናል፡፡
የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉባኤ የመጨረሻ ግቡ ምንድን ነው?
በ50 አመት ታሪክ ውስጥም ሊሆን ይችላል፤ እየተንከባለሉ መፍትሔ አልባ ሆነው፣ እዚህ የደረሱ ጉዳዮች በሙሉ ተነስተው መተማመን መግባባት ላይ መድረስ ነው - የመጨረሻ ግቡ፡፡ በሀገሪቱ ጉዳይ ከሰማይ በታች ያሉ ችግሮች በሙሉ ተነስተው የመፍትሔ አቅጣጫ ይሰጥበታል፡፡ የሚነሱ ችግሮችን በሙሉ ሰብስበን ተወያይተን፣ አጥብበን … አንዳች መግባባት ላይ መድረስ ነው፡፡ ከዚያ ወደ እርቅ መሻገር ነው፡፡ የብሔራዊ መግባባቱ ውሣኔ፤ ወደ እርቁ ይመራናል ማለት ነው፡፡ ጉባኤው ላይ አብዛኞቹ ከተስማሙ ለኢትዮጵያ ትልቅ እፎይታ ነው፡፡
ዋናው ግቡ ግን የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስ ማስቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያንም ወደ ላቀ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የማሸጋገር ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ሀገሮች ፍላጐት አለ፡፡ ለእነዘህ ሁሉ ሀገሪቱና ዜጐቿ ያላቸውን ዝግጅነት ማረጋገጫ ጉባኤ ነው የሚሆነው፡፡       

Read 4270 times