Print this page
Saturday, 02 February 2019 15:33

የጣት ውስጥ ‹ዳስተር›

Written by  ከዳግማዊ እንዳለ (ቃል ኪዳን)
Rate this item
(16 votes)

  በጊዜ ብዛት መደገፊያው ወደ ኋላ የተለጠጠው ሶፋ ላይ፤ ተኮራምቼ ከተቀመጥኩ ግማሽ ሰዓት ያህል አልፎኛል፡፡ በቁጭታዬ ከአንዳንድ ሰርጎ ገብ ሀሳቦች ውጪ አብዛኛውን ስለ ሶፋው መደገፊያ እንዲህ መለጠጥ በማሰብ ነው ያሳለፍኩት፡፡ የሶፋውን መደገፊያ ምን እንዲህ እንደለጠጠው እንጃ፡፡ መቼም ዕድሜ ብቻ አይሆንም፡፡ ደግሞ ዕድሜ ወደ ፊት ያጎብጣል እንጂ፤ እንዲህ ወደ ኋላ አይለጥጥም። ምናልባት ትዕቢት አድሮበት ሳይሆን አይቀርም። እቤቱ ውስጥ ካሉት ዕቃዎች ሁሉ በዕድሜ ትልቁና ለባለቤቱ ቅርብ የሆንኩ ነኝ ብሎ ሲንጠባረር ይሆናል፡፡ ምን ያድርግ! ከእርሱ ቀድሞ የተገዛው የጥጥ ፍራሽ፤ በስፖንጅ ፍራሽ ተቀይሯል፡፡
ቆይ በዕድሜው ዘልዛላነትና ለእኔ መቀመጫና ጀርባ ባለው ቅርበት እንዲህ የሚለጠጥ ከሆነ፤ እኔ ከእርሱ በዕድሜና ለራሴ ቅርብ በመሆን የምበልጠው፤ ምንድን ነው እንዲህ የሚያኮራምተኝ? ገዢነቴ ለታላቅነቴ ማረጋገጫ ነው፡፡ ግና ከእኔ በላይ ሶፋው ቅርብ ይሆን እንዴ? እንደዛማ ሊሆን አይችልም፡፡  
ሶፋው ላይ ተለጥጬና እግሮቼን አንፈራጥጬ ተቀመጥኩ፡፡ ደላኝ! የተለጠጠ ላይ ተለጥጦ መቀመጥ እንዴት ይመቻል፡፡ ከተደላደልኩ በኋላ አንዴ በረጅሙ ተንፍሼ፤ የተቃጠሉ ሀሳቦቼን ከውስጤ አስወጣሁና ወደ ውጪ ሲያዩ የቆዩት ዓይኖቼን፤ ክንፎቻቸውን አጥፌ፤ ወደ ውስጥ ማየት ጀመርኩ፡፡
ዓይኖቼን ከድኜ ወደ ውስጤ ስመለከት፤ በህሊናዬ አንዱ ጥግ ‹ኢዝል› ላይ የተሠቀለ አንድ ገብስማ (የጎለመሰ) ሰሌዳ ተመለከትኩ፡፡ ነገር ግን የትኛውን ጥግ (በግራ ይሁን በቀኝ) ይዞ እንደቆመ ልረዳ አልቻልኩም፡፡ ምናልባት ሰሌዳ መሀል እንጂ ጥግ ይዞ ቆሞ አይቼ ስለማላውቅ ይሆናል፡፡ ደግሞ ሰሌዳው ባዶ ነበር፡፡ እላዩ ላይ ተዘባርቀዉ ተጽፈዉ የነበሩትን ሀሳቦችን ተንፍሼ አወጣዋቸው እንዴ?
የተጨፈኑ ዓይኖቼን ከፍቼ አንድ እግሬን በአንዱ፤ ሁለተኛዉን በሌላኛዉ የዓይኔ መስኮት አሾልኬ፤ ሽቅብ ወደላይ በረርሁና እንደ ንስር ቁልቁል የሰሌዳውን አቅጣጫ ለማወቅ ዓይኖቼን ሰደድኩ፡፡ ሶፋዉ ላይ ተለጥጦ ተቀምጧል ያልኩት አካሌ፤ ሶፋ ላይ ሳይሆን፤ ሴት አያቴ ልጅ እያለች ቆማ እስክስታ ትለማመድበት የነበረ የጠፍር አልጋ ላይ ተጋድሞ፣ ትከሻውን እየሰበቀ ሲነጥር አየሁት፡፡ አካሌን ‹‹ሸክሽክ!›› ሲሉት ሰማሁ፤ የሞኒካ ሲሳይ ሴት አያት እያጨበጨቡ፡፡ ደንግጬ እንዳወጣጤ አንዱ እግሬን በአንደኛው ዓይኔ፤ ሁለተኛውን በሌላኛው አድርጌ፤ ዓይኖቼ ዉስጥ ተወርውሬ ከገባሁ በኋላ፤ የዓይኖቼን መስኮቶች ጠርቅሜ ዘግቼ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡ ከውጪ ይዣቸው የገባሁትን ሀሳቦች ግን ከትንፋሼ ጋር አብረው የወጡ አልመሰለኝም፡፡
ሰሌዳዉ አሁንም እቆመበት ተገትሯል። የቆመበትን አቅጣጫ ለማወቅ ያደረግሁት ጥረት ባለመሳካቱ ትንሽ ቅር ብሎኛል፡፡ ግን ደንግጫለሁ - ፈጥኜ መመለስ ነበረብኝ። ሰሌዳውን አተኩሬ ስመለከት ሀሳቦቼ አእምሮዬን ጸሐይ አድርገዉ ይሽከረከሩት ገቡ። ውስጤ ጻፍ፣ ጻፍ አለኝ። ጣቶቼን ዝቅ ብዬ ተመለከትኩ። ጠመኔ ለመጨበጥ ምንም ጉጉት አላሳዩም፡፡ ምናልባት ጠመኔ ስላላዩ ይሆናል ብዬ ጠመኔ ፍለጋ ዓይኖቼን ባንከራትትም፣ በሰሌዳው ዙርያ ስባሪ ጠመኔ እንኳን ላይ አልቻልኩም፡፡ ቆይ ጠመኔ ቢኖር እንኳን ምን ዓይነት ቀለም ያለው ጠመኔ ነው፣ በገብስማ ሰሌዳ ላይ መጻፍ የሚችለው? ይህን ማረጋገጥ የሚቻለዉ በሙከራ ብቻ ነዉ፡፡
ከዓይኖቼ ክዳኖች ጀርባ፤ ምናልባትም በሴት አያቴ የጠፍር አልጋ ላይ፤ በሞኒካ ሲሳይ ሴት አያት አጫፋሪነት፤ ከጉልበቱ ታጥፎ፤ በጀርባው ተንጋሎ እስክስታ የሚመታው አካሌ ያለበት ክፍል ውስጥ ጠመኔ ይኖር ይሆን እንዴ? ጠመኔ እንኳን ባይኖር፣ ከግድግዳዬ ቆርሼ የምወስደው፤ ቀለሙ እረግፎ ያገጠጠ ጀሶ ይኖር ይሆን? እሱ እንኳን ባይኖር፣ ትናንት ማታ ከገበያ ከገዛሁት እንጀራ ውስጥ ተቀላቅሎ የተጋገረውን ጀሶ፤ ጨምቄ አጥቼ ጠመኔ ማበጀቱ ይሳካልኝ ይሆን? ይሄንንም ጥያቄ ለመመለስ አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለኝ፡፡ እሱም ሙከራ ነው፡፡
ቆይ ጀሶውን ባገኝ እንኳን የገብስማው ሰሌዳ ጥቁር፣ ጥቁር አካሉ ላይ ብቻ ነው መጻፍ የምችለው እኮ! ለነጭ፣ ነጩ ማንደጃዬ ላይ የተረፈ ከሰል ካለ፣ መፈለግ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ በነጭ ጀሶና በጥቁር ከሰል በ‹ኢዝል› ላይ በተሰቀለ ገብስማ ሰሌዳ ላይ እያፈራረቁ ቃላት መሞነጫጨሩ፤ ከመጻፍ ወደ መሣል ሳያደላ አይቀርም፡፡
ጠመኔ ፍለጋ ተነሳሁ፡፡ የዓይኖቼን ቆቦች ከፍ አደረግሁና አንድ እግሬን በአንዱ፤ ሁለተኛውን በሌላው አሾለክሁና ወጣሁ፡፡ እስክስታ የሚመታውን አካሌን ፍለጋ ዓይኖቼን ስሰድ ጎረምሳው ወንድ አያቴ፤ አንዲት የገበሬ ሚስት ቤት ገብቶ ሲጫወት ሳለ፤ ለእርሻ የወጣው ገበሬ፤ ዕቃ እረስቶ በመመለሱ፤ መደበቂያ ፍለጋ ሲራወጥ አየሁት፡፡  የገበሬው ሚስት ለአፍታ ስታስብ ቆየችና አያቴን እንደ ሬሳ እመሬት አጋድማ፤ አጎዛ አልብሳው ስታበቃ፤ ደጋኗን አንስታ እላዩ ላይ ጥጥ መንደፍ ጀመረች፡፡ አያቴ ወባው እንደተነሳችበት የከባድ መኪና ሹፌር መንቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ የገበሬው ሚስት በአያቴ የእንቅጥቅጥ ስልት የተቃኘ ዜማን ማንጓራጎር ጀመረች፡-
‹‹የወንፈሌ ጥጥ
ተው አትንቀጥቀጥ
እርጋ!
ሊወጡ ነው ደጋ፡፡››
ገበሬው ማገሩን ፍለጋ የቤቱን ዕቃ ሲያተራምስ ቆየና ሚስቱን በቁጣ፣ ማገሩን የት እንዳስቀመጠች ጠየቃት፡፡ እሱ ማገር እየፈለገ ትዘፍናለች እንዴ? የገበሬው ሚስት በስሜት ሆና ኖሮ በዜማ መለሰች፡፡ እጇን ወደ ወፍጮዋ እየጠቆመች፡-
‹‹ያውና ማገሩ
ክፉ አትናገሩ
ያውና ወፍጮው ሥር
ያላዩት ይመስል››
ሴትዮዋ በእሷም ብሶ ባልየው ላይ ‹ጨቅጫቃ› የሚል ‹ታፔላ› ለመለጠፍ ስትሞክር፤ በነገረ ሥራዋ ተናድጄ እንዳወጣጤ፤ ወደ ውስጤ ተመልሼ ገባሁ፡፡ ገብቼ ሰሌዳው ፊት ከመቆሜ፤ ውስጤ ያለ ጠመኔ ገብስማው ሰሌዳ ላይ ይጽፍ ጀመረ፡፡ ቆይ ግን በገብስማው ሰሌዳ የሠራ አካላት ላይ እንዲህ ደምቆ የሚታይ ቀለምን ከየት አመጣ? እውነትም ያንኳኳ ይከፈትለታል፡፡ ለመጻፍ የጣረም ይጻፍለታል!፡፡
‹‹ሳሌምዬ በጣም ናፍቀሺኛል፡፡›› የሚል የሚያምር ፊደል አጣጣል የሚታይበት ጽሑፍ ሰሌዳው ላይ ሠፈረ፡፡ መናፈቄን ሳውቅ ደነገጥሁ። ድንገት መኖሩን እንኳን ያላወቅሁት ‹ዳስተር›፡-
‹‹መናፈቁን ናፍቅ! ግና የምን ማመን ነው? ‹በአፍ ያለ ይረሳል፤ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል› ሲባል አልሰማህም? የምን ጽፎ ማስቀመጥ ነዉ?›› ብሎ በቁጣ የተጻፈውን አጠፋዉ፡፡ ሰሌዳው ምንም እንዳልተጻፈበት ሁሉ አዲስ ሆነ፡፡ አሻራ እንኳን የማይተው ምን ዓይነት ሰሌዳ ቢሆን ነዉ? አሻራ እንኳን የማያስቀር ምን ዓይነት ‹ዳስተር› ነው?
‹‹እንዴ ናፈቀቺኛ! ስትናፍቀኝስ? ሰሞኑን በዓይኔ ስትሄድ ነዉ የከረመችው፡፡›› ሲል ውስጤ ‹ዳስተሩን› ሞገተው፡፡
‹‹ቆይ በዓይንህ ላይ ምን መንገድ አስጠረገህ? ‹ቤታቸውን ከፍተዉ ሰውን ሌባ ይላሉ› አሉ፡፡›› ‹ዳስተሩ› ይበልጥ ተቆጣ፡፡
‹‹በቃ ከናፈቀችኝስ!›› ውስጤ በእልህ ከ‹ዳስተሩ› በላይ ገዝፎ ሰሌዳው ላይ ‹ናፈቅሺኝ! ናፈቅሺኝ!› ሲል ፊደል ጣለ፡፡ ‹ዳስተሩ› ድርግም አድርጎ አጠፋውና በእልህ ውስጤ ላይ አፈጠጠ፡፡ ውስጤ መልጾ ጻፈው፡፡ ‹ዳስተሩ› መልሶ አጠፋው፡፡ በተደጋጋሚ እንዲያ ሆነ፡፡
አመመኝ - መጻፍ እየፈለጉ አለመጻፍ አመመኝ፡፡ ሰሌዳና መጻፍያ እያለ መጻፍ አለመቻል አመመኝ፡፡ የህሊና ሰሌዳ ላይ መጻፍ ካልተቻለ፣ ሌላ መጻፍ የሚቻልበት መንገድ መፈለግ አለብኝ፡፡ ለአፍታ ‹ዳስተሩ› ላይ አፈጠጥኩና አንድ ሀሳብ መጣልኝ፡፡ አብዮት፡፡ ከመጻፍና ለእራስ ከመንገር እንደውም ለእሷ መንገር፡፡ እንዴት? አዎ ማሰብ እና በህሊናዬ ማህደር ስሜቴን ማስፈር ካልቻልኩ፤ ከዳስተሩ የተረፉ ትርፍራፊ ስሜቶቼን ስልኬ ላይ እከትብና የጽሑፍ መልዕክት እልክላታለሁ፡፡ እሷም እንደኔ እያደረጋት ከሆነ በጎደለዉ ሞልታ ታነበውና  ሀሳቤን ትረዳለች፡፡
ሳላስበው በችኮላ የግራ ዓይኔን መዝጊያ ከፈትሁና ሾልኬ ወጣሁ፡፡ በግራ ዓይኔ በኩል መውጣቴን ተከትሎ ሰሌዳው በግራ በኩል ቆሞ እንደነበር ተገለጸልኝ፡፡ አካሌንም ልጥጡ ሶፋ ላይ ተለጥጦ ተቀምጦ አገኘሁት፡፡ አንድ እግሬን በአንዱ ዓይኔ፤ ሁለተኛውን በሌላኛው እያደረግሁ መውጣቴ ነበረ፣ ችግሩ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ እግሮቼን በሁለቱ የዓይኖቼ ቀዳዳዎች አሾልኬ ስወጣ፤ የዓይኖቼ መጋጠሚያ ቦጭቆ የሚያስቀረው አካሌ፤ በእውነትና በሌላኛው እውነት መሀከል ያለ ማዕዶት ነበር ማለት ነው፡፡ ግን ለምን ነበር በሁለቱ እግሮቼ፤ በሁለቱ ዓይኖቼ ሾልኬ ስወጣ የነበረው?
ስልኬን አወጣሁና የጽሑፍ መልዕክት መጻፍያ ሰሌዳውን አዘጋጀሁ፡፡ ከዛ ጠመኔ ጣቴን ተጠቅሜ ‹‹ሳሌምዬ ሰሞኑን በዓይኔ ስትሂጂ ነው የሰነበትሸው፡፡ ቆርጦልኛል ብዬ ብልም ሰሞኑን ይኸው በናፍቆትሽ እየተሰቃየው ነው፡፡›› ብዬ ጻፍኩና ‹ላክ› የሚለውን ልጫን ስል፤ መኖሩን እንኳን ያላወቅሁት፤ ጣቴ ውስጥ የነበረ ‹ዳስተር› የጻፍኩትን አጠፋው፡፡
ብደነግጥም በስህተት አጥፍቼው ይሆናል ብዬ እራሴን አሳምኜ እንደገና ልጽፍ ተነሳሁ፡፡ እንደውም ሀሳቤን አሻሽዬ ለመጻፍ እድል አገኘሁ ስል ተጽናናሁ፡፡ መጻፍ ጀመርሁ፡-
‹‹ያንቺ ነገር ቆርጦልኛል ካልሁኝ ቆየዉ፡፡ ‹ቆረጠልኝ› ማለት ግን ምን ማለት ነው? አውቀው የነበረ ቢመስለኝም አሁን ስትናፍቂኝ ትርጉሙ ተሰወረብኝ፡፡ ትርጉሙን ሳላውቅ ነዉ እንዴ ቆረጠልኝ ስል የከረምሁት? ግን መቁረጥ ምንድን ነዉ? ታድያ አሁን ምን ቀጠለው? የተቆረጠውን ምን ሰፋው? መንገድ ላይ ሳይሽ እንኳን እንደረሳሁሽ ያለፍኩሽ አሁን ለስልክ እንኳን እርቀሺኝ በምን ትዝ አልሺኝ? ምን ነበርስ ያስረሳኝ? ቆይ፣ ቆይ መርሳት እራሱ ምን ማለት ነው? ‹ሳይኮሎጂ› መርሳት የሚባል ነገር የለም የሚለው ስላንቺ ነው እንዴ? ስላንቺ ካልሆነ ካንቺ በፊት የነበሩትን እና ካንቺ በኋላ የተነሱትን እንዴት እረሳዋቸው? እሷን እንኳን እንዴት እረሳዋት? ቆይ አለማስታወስ፤ መርሳት ነው አይደለ? ካልሆነ ጉዴ ነው፡፡ ጊዜ እየጠበቁ በሚፈነዱ ቦንቦች ተከብቤአለሁ ማለት ነው፡፡ ሳሌምዬ ናፍቀሺኛል፡፡ ሳሌምዬ በዓይኖቼ ላይ እየሄድሽ ነው፡፡›› ‹ላክ› ከማለቴ በፊት ጣቴ ውስጥ ያለው ‹ዳስተር› የጻፍኩትን አጠፋሁ፡፡
አሁን በስህተት እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ‹ዳስተሮቹን› ግን ምን ነካቸው? እሷን በመናፈቄ የሚቀና፤ የትኛው ምቀኛ ያሠራብኝ ድግምቶች ናቸው? ድንገት ወንድ አያቴና ገበሬው፤ ሴት አያቴ እስክስታ ስትለማመድበት የነበረው የጠፍር አልጋ ላይ አስተኝተው፤ የገበሬው ሚስት አጎዛ አልብሳኝ፤ በደጋኑ ማሲንቆ እየገዘገዘች (ማሲንቆውን ከየት እንዳመጣችው እንጃ)፤ የሞኒካ ሲሳይ ሴት አያት እያጨበጨቡና እልል እያሉ፤ በቀኝ ዓይኔ በኩል፤ አንስተው ይዘውኝ ገቡና መሬቱ ላይ አስቀመጡኝ፡፡ ገብስማው ሰሌዳ በህሊናዬ ቀኝ ጥግ ‹ኢዝሉ› ላይ ተሰቅሎ ተገትሯል፡፡ እላዩ ላይ በርበሬ በሚመስል ደማቅ ቀለም አንዳች ነገር ተጽፏል፡፡ በርበሬው እሳት ላይ አንደተበተነ ሁሉ ይጨሳል፡፡ ሀሉም ተባብረው አንገቴን አንቀው ሲያበቁ፤ ዓይኖቼን ጎልጉለው አውጥተው፣ በበርበሬው ጽሑፍ ያጥኗቸው ጀመረ፡፡ በማያምር የፊደል አጣጣል ሰሌዳው ላይ ይሄ ተጽፏል…
አንደኛ፡- በበረደህ ቁጥር ድሮ ያሞቅህ የነበረን ሰው አታስታውስ፡፡ ያ ሰው የሄደ ጊዜ ተመልሶ መጥቶ እንኳን ለማያሸንፈው ለሌላ ዓይነት ብርድ አጋልጦ ነው የሄደው፡፡
ሁለተኛ፡- ለምን ጥላህ የሄደች መሰለህ? አሁንስ ምን የተለወጠ ነገር አለ?
ሦስተኛ፡- ደግሞ ምን አባህ ብለህ ነዉ የጻፍከ? ፍቅረኛ ለነበረች ሴት እንደዚህ ዓይነት መልዕክት ይጻፋል?
(ቦነስ) ምርቃት፡- ከሶፋው ይልቅ የዕድሜ ባለጸጋውና ላንተ ቅርብ የሆነው ባልንጀራህ እቤቱ ግድግዳ ላይ ይህን ጽፎ ለጥፏል፡፡
‹‹ከትናንት በስቲያ ሰጥታኝ፤ አኝኬ የተፋሁትጣዕሙን አጣጥሜ፤ እንደማስቲካ የጣልሁትፍቅሯ መልሶ ቢያምረኝ፤ ውስጤ ውስጧን ቢርበውእንደውሻችን መቻል፤ ትፋቱን እንደሚበላውከጣልኩበት አነፍንፌ፤ መልሼ ባጣጥመውጣዕሙ አልቆ ጎምዝዞ፤ ምሬቱ ሞልቶ ቢፈስየፍቅሬን ምላስ አቁስሎ፤ ከናፍሮቼን ቢጠብስመቻልን አስጠራሁና፤ ብጠይቀው ምስጢሩንትፋቱን ዳግም ሥራ ላይ፤ ያዋለበት ብልኃቱንለካ እርሱ እንደኔም አይደል፤ አንድም ምቀኛ የለው እርሱ አንዴ ከጀመረው፤ ትፋቱን ማንም አይነካው፡፡››

Read 3019 times