Monday, 11 February 2019 00:00

ቃለ ምልልስ አዛውንቱ ፖለቲከኛ … በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 - ሀገራችን የሁላችንም እንጂ የአንድ ቡድን አይደለችም
     - ኢትዮጵያ እናቴ ነች፤ ኢትዮጵያ ነች ወልዳ ያሳደገችኝ


    የ88 አመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አንጋፋው ፖለቲከኛ ቡልቻ ደመቅሳ፣ ከሰሞኑ በተካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ላይ የተሳተፉ ሲሆን ለመጀመርያ ጊዜ ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ተገናኝተው የመነጋገር ዕድል አግኝተዋል - ለአጭር ጊዜ ቢሆንም፡፡ ከጥቂት ዓመታት
በፊት ራሳቸውን ከፖለቲካ በጡረታ ያገለሉት አቶ ቡልቻ፤ በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት እውን የተደረገውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ በመጪው ምርጫ፣ ለፓርላማ ለመወዳደር መወሰናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳን በኢትዮጵያዊነት፣
በግጭቶች አፈታት እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡


     ከጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ጋር ተገናኝታችሁ ምን ተወያያችሁ?
ከዐቢይ ጋር የተገናኘነው በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ውይይት ያደርጉ ነበር፡፡ በዚያ ውይይት ላይ ተጋብዤ ነው የሄድኩት፡፡ በኋላም በሻይ እረፍት መሃል እኔና ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ብቻችንን ተቀምጠን፣ አጭር ውይይት ማድረግ ችለናል፡፡ በእለቱ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እኔን አክብሮ ለማናገር በመቻሉ  በጣም ነው ያደነቅሁት፡፡
ከዚህ ቀደም  ተገናኝታችሁ ታውቃላችሁ…?
በአካል ስንገናኝ የመጀመሪያችን ይመስለኛል። ነገር ግን ከዚህ በፊት በስልክ ተነጋግረናል፡፡ እሳቸው ወደ አሜሪካ ሲሄዱ፣ እኔ ደግሞ ወደ ሀገር ቤት እየተመለስኩ ነበር፡፡ ከመጡ በኋላ በስልክ ተገናኝተናል፡፡ በወቅቱ ሠላምታ ብቻ ነበር የተለዋወጥነው፡፡
በአሁኑ ግንኙነታችሁ ምን ተወያያችሁ?
በሃገሪቱ ጉዳዮች በሠፊዉ ተነጋግረናል፡፡ ስለ መጪው ምርጫ አውርተናል፡፡ እኔ ከዚህ ቀደም በመንግስት ስራ ላይ ነበርኩ፡፡ በጃንሆይ ጊዜ የገንዘብ ማኒስትር ነበርኩ፡፡ በኋላም በፓርላማ ቆይቻለሁ፡፡ ስለዚህ አሁንም በነበረችን አጭር ቆይታ አንዱ የተነጋገርነው ስለ እኔ ጉዳይ ነው። እሳቸው ያላቸውን አክብሮት ገልፀውልኛል። እኔም እንደዚያው፡፡ በመጪው ምርጫ ተወዳድሬ ፓርላማ መግባት እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በሚገባ ተነጋግረናል፡፡ ፍላጐቴን ገልጬላቸው፣ እሳቸውም እንደግፍሃለን፤ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርግልሃለን ብለውኛል። ሃሳቤንም ወደውታል፡፡ በርቱ ነው ያለኝ፡፡ በዋናነት የተነጋገርነው ይሄንን ነው፡፡ በተቀረ ስለ ሌላ የፖለቲካ ጉዳይ አልተነጋገርንም፡፡ ጊዜም አልነበረም፡፡ ለኔ ይሄ ትልቅ አስደሳች አጋጣሚ ነበር፡፡
በዚህ ዕድሜዎ  ለፓርላማ አባልነት እንዴት ለመወዳደር አሰቡ?
እኔ በህይወቴ ሙሉ በኦሮሞና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ነው ስሠራ የኖርኩት፡፡ ስለ ኦሮሞ ጉዳይ ብዙ ተነጋግሬያለሁ፡፡ ይሄ ማለት ስለ ሌላው ኢትዮጵያዊ በያገባኛል ስሜት አልተወያየሁም ማለት አይደለም፡፡ ለሁሉም በምችለው ስስራ ነው የኖርኩት፡፡ ከ65 አመት በላይ በዚህ ሥራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ አሁንም በዚህ ዙሪያ የምሠራቸው ስራዎች አሉኝ፡፡ በኦሮሞ ጉዳይ ብዙ ተናግሬያለሁ፡፡ አሁንም ኦሮሞ በኢትዮጵያዊነቱ ተደስቶ እንዲኖር የማውቀውን ሁሉ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ኦሮሞ በራሱ ሰርቶ፤ በራሱ ተማምኖ፣ ኢትዮጵያ ሀገሩን ወዶ ሠርቶባት፣ ደስተኛ ሆኖ እንዲኖር እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ አሁንም መስራት እፈልጋለሁ፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ፤ ኢትዮጵያ እንደ አንድ አፍሪካ ሀገር፣ በጣም ጐልታ አትታይም፡፡ ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት የነበራትን አስተዋጽኦ ያህል ጐልታ አትታይም፤ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡
ኢትዮጵያ አቅመ ሠፊ ናት፡፡ ብዙ ሃብት አላት። መሬቷ፣ የሰው ሃይሏ፣ ተፈጥሮዋ … በውስጡ ብዙ አቅም አለው፡፡ ይሄን አቅም ተባብሮ እንዴት ማበልፀግና ከድህነት ማላቀቂያ ማድረግ ይቻላል የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ታላቅነት የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ፓርላማ ገብቼ መመንዘር እፈልጋለሁ። ከሃብታም ሀገሮች ብዙ ተምረናል፣ ብዙ አይተናል፣ በስራ አጋጣሚ ብዙ ልምድ ይዘናል። ይሄን ልምድ ለማካፈል፣ ከዚህ በፊትም በፓርላማ ተገናኝቼ ስጮህ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሰሚ መንግስት እየተፈጠረ በመሆኑ፣ እነዚህን ሃሳቦች በሚገባ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ የሃገራችን አንድነት እንዳይናጋ፣ ህዝብ እንዳይበደል አሁንም ፓርላማ ተገኝቼ መሟገት፣ መከራከር እፈልጋለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ደግ ነገር እንዲደረግ እንጂ መጥፎ ነገር እንዳይደረግ መምከር እፈልጋለሁ፡፡ ለፓርላማ መመረጥ የፈለግሁት በእነዚህ ምክንያቶች ነነው።
የቀድሞ የፓርላማ ቆይታዎን ሲያስታውሱ ምን ይሰማዎታል?
በወቅቱ ብዙ ነገሮችን ተነጋግረናል፤ ብዙ ጉዳዮችን አንስተናል፡፡ ኢህአዴግ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዘመኑ ሃይለኛ አልነበረም፡፡ ለመማርም ዝግጁ ይመስል ነበር። አቶ መለስም ለመማር፣ ለማወቅ፣ ለመምራት ፍላጐት ያላቸው ይመስል ነበር፡፡ ነገር የተበላሸው በኋላ ነው፡፡ በኋላ የምንናገረው ሁሉ ጠቃሚ ሳይሆን አፍራሽ እየመሰላቸው መጣ፡፡ ቀስ በቀስ ክፋት እያየለ ሄደ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር የፓርላማ ቆይታዬ ያለፈው፡፡ እኔ በወቅቱ ለሀገሬ ይጠቅማል ያልኩትን ተናግሬያለሁ፡፡ ሠሚ ግን አላገኘም፡፡ ክፋት እያየለ ሲመጣም፣ ለፓርላማ መወዳደር አልፈልግም ብዬ ተውኩት፡፡ ወደ ምርጫ አልገባም ብዬ ነው ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጌ የተውኩት፡፡
አሁን የተሻለ ፓርላማ እንደሚፈጠር እርግጠኛ ሆነዋል ማለት ነው?
አዎ! ጥሩ ፓርላማ እንደሚፈጠር ተስፋ አድርጌያለሁ፡፡ አሁን ለመመካከር ለመነጋገር እድሉ ሰፊ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ተበድሏል ብለን በደሉንም ስንናገር ኖረናል፡፡ አሁን ደግሞ እኩል ቁጭ ብሎ ስለ ሁሉም ነገር መነጋገር የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ኦሮሞ ብዙ ህዝብ ነው፤ በዚያው ልክ ተገፍቶ ወደ ኋላ የቀረ፤ የተጐዳ ህዝብ ነው፡፡ እርግጥ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የተጐዳ ነው፡፡ ይሄኛው ቁጥሩ የበዛ ስለሆነ ነው በተለየ ያነሳሁት፡፡ አሁን ህዝብን ከጉዳት የሚያላቅቅ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ  ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ አንተ እንዳልከው ይሄ ተስፋ ነው ለምርጫ ለመወዳደር ያነሳሳኝ፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ትግል የደረሰበት ደረጃ እንዴት ይገለጻል?
አሁን ቢያንስ ኦሮሞ፤ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ሳይሆን ኢትዮጵያን መገንባት የሚችል መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ኦሮሞ ለኢትዮጵያ ይሠራል፣ ለኢትዮጵያ ይሞታል፤ ከዚህ ቀደምም ሞቷል፤ ስለዚህ ኦሮሞን እንደ ልዩ ህዝብ አድርገን አንየው፡፡ በኢኮኖሚ ደረጃ ዛሬና ትናንት የነበረው ይለያያል ማለት ያዳግታል፡፡ ሁሉም ነገር በጊዜው ነው የሚሻሻለው፤ የመሬት ጉዳይ አሁንም ብዙ ይቀረዋል፡፡ የህዝብን ኢኮኖሚ ለማበልፀግ ብዙ ስራ ይፈልጋል፡፡ ዋናው የአስተዳደሩ ጉዳይ መስተካከሉ ነው፡፡ እሱ አሁን በተጀመረው መልኩ ከተስተካከለ፣ የምንፈልገው ውጤት የማይመጣበት ምክንያት የለም፡፡ ነገሩን ማረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን ነች የሚለውን እምነት እንዲይዝ፣ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ሃገራችን የሁላችንም እንጂ የአንድ ቡድን ሃገር አይደለችም፡፡ የዶ/ር ዐቢይ ሃሳብ በጣም ጥሩ ነው፤ አንዳንድም በተግባር ያየነው ነገር አለ፡፡    
ለምሣሌ ያህል ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
የኤርትራ ጉዳይ በጣም አስደንቆኛል። ታሪክ የማይዘነጋው አስደናቂ ተግባር ነው። የፖለቲከኞች መፈታት፣ በውጭ የነበሩ ፖለቲከኞች በነፃነት ወደ ሀገራቸው መመለስ … ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እፎይ ነው ያለው። እፎይታ ነው የተሠማው፡፡ ይሄ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አንዳንዶች ይሄ እፎይታ አልገባቸውም ወይም አልተገለጠላቸውም ይሆናል፡፡ ግን እኔ የሚሠማኝ እፎይታ ነው። ለኔ ኢትዮጵያውያን ልዩ ህዝቦች ናቸው፡፡ መማር ማወቅ መሠልጠን የሚችሉ ናቸው፡፡ እኔ አሁን 88 አመቴ ነው፡፡ በዚህ እድሜዬ ብዙ የተማሩ፣ በእውቀት የመጠቁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ተፈጥረው አይቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለመማርም ለመሠልጠንም ለመበልፀግም ምቹ ነን፡፡ ያጣነው ይሄን የሚረዳ መሪ ነበር፡፡ አሁን ያን አይነት መሪ አግኝተናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ህዝቡ ተስፋ አለው፡፡ የዛሬ 50 አመት አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሄድ የተደነቅሁትን ያህል፣ አሁን በሀገሬ መደነቅ ጀምሬያለሁ፡፡ ለወደፊት የበለጠ መደነቃችን አይቀርም፡፡
ለእርስዎ ኦሮሞነትና ኢትዮጵያዊነት እንዴት ይገለጻል?
ሁለቱ ማንነቶች በፍፁም አንድ ናቸው - የሚምታቱ፣ የሚጋጩ፣ የሚጣሉ የማይፈላለጉ አይደሉም፡፡ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ጉራጌነት፣ ትግሬነት፣ ሶማሌነት፣ ሲዳማነት ስሞች ናቸው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ግን አይተኩም፡፡ እኔ አሁን ኒውዮርክ ሄጄ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል ነው ሰው የሚያውቀኝ፤ እንጂ ኦሮሞ ነኝ ብል ሰውን ማደናገር ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚያውቀው ኢትዮጵያን ነው፡፡ ኦሮሞ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው፣ ትልቅ ህዝብ ነው፡፡ በውጭ አለም ግን ትርጉም ያለው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡
በኦነግ እና ኦዴፓ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ሁኔታ እንዴት አዩት?
በእውነት ለመናገር ፀባቸው አስጨንቆኝ ነበር፡፡ አልቅሼ ሁሉ ነበር፡፡ በኦሮሞ ጉዳይ የተወጠርኩትን ያህል፣ የመንግስትና የኦነግ ሃይሎች ሲታኮሱ በእጅጉ ነው ያዘንኩት፡፡ እንዴት ወንድም ወንድሙን ይገድላል? እንዴት ለአንድ ህዝብ የሚታገሉ ሃይሎች እርስ በእርስ ይገዳደላሉ? የሚለው በእጅጉ ነበር ያስጨነቀኝ። ይሄን ጭንቀቴን በወቅቱ በሚዲያ ገልጬ ነበር። አሁን እግዚአብሔር ይመስገን፣ ሁሉም ነገር ጥሩ ሆኖ፣ ችግሩ ተፈቷል፡፡
ችግሩ ዳግም እንደማያገረሽ እርግጠኛ መሆን  ይቻላል?
አዎ ፈጽሞ ያ አይነት ችግር ተመልሶ አይመጣም፡፡ ምክንያቱም አሁን ሁሉም እውነተኛ ኢትዮጵያዊነትን እየተለማመደ ይሄዳል፡፡ በሂደት ደግሞ የበለጠ ኢትዮጵዊ እየሆነ ይመጣል፡፡ ያኔ ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡ ኦሮሞ ብቻ አይደለም፤ ሁሉም የላቀ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ውስጥ ይገባል፤ ኢትዮጵያ እናቴ ነች፣ ኢትዮጵያ ነች ወልዳ ያሳደገችኝ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ የሰው ሁሉ ህሊና ይጓዛል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ሁሉም በሂደት ከብሔር አስተሳሰብ፣ ወደ ከፍ ያለው የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ይሸጋገራል፡፡ ለምን እርስ በእርስ ቸር እንሆናለን? ለምን እርስ በእርስ እንጋባለን? ይሄ ሁሉ የሚሆነውና ሲሆን የኖረው በምክንያት ነው። ትርጉም አለው፡፡ አሜሪካ ስሄድ እኔ የምከበረው፣ በኢትዮጵያዊነቴ ነው፡፡ ይሄ ለኔ ትልቅ ትርጉም ነው ያለው፡፡
ኢትዮጵያዊነት የበለጠ እንዲበለጽግና እንዲጠልቅ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
በሁሉም መንገድና አቅጣጫ ኢትዮጵያዊነት ከፍ እንዲል ዘመቻ ማድረግ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ አደገች ሲባል ኦሮሞም አማራም ጉራጌም ወላይታም ሌላውም አደገ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ እድገት የሁላችንንም እድል ነው የሚያበለጽገው። በመንደር ከመከፋፈል ኢትዮጵያን ይዘን ወደ ብልጽግና መጓዝ አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ንብረት በሙሉ የኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ለምሣሌ ወያኔዎች ያቋቋሙት ኤፈርት አለ፡፡ አንድ ፈረንጆች ያጠኑትን ጥናት ስመለከት፤ ኤፈርት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ኩባንያዎች እጅግ በጣም ሃብታም ነው፡፡ በሌላውም እንዲሁ ሃብታም ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ናቸው። ሁሉም የኢትዮጵያ ንብረቶች ናቸው፡፡ ኤፈርትም በለው ሌላው በሙሉ የኢትዮጵያ ንብረት ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ንብረት በሙሉ የዜጐቿ ናቸው። መንግስትም ሆነ ቡድኖች የኔ ብቻ ነው ማለት አይቻላቸውም፡፡ ሁሉም ተገቢውን ታክስ መክፈል ይገባዋል፡፡ ያ ታክስ ለዜጐች መድረስ አለበት፡፡
ከለውጡ ጐን ለጐን የሰው ህይወት የሚቀጥፉ ግጭቶች ተበራክተዋል፡፡ መፍትሄያቸው ምንድን ነው?
በእርግጥ ይሄ ጉዳይ ትልቅና አሳሳቢ ነው። መፍትሄውን ለዶ/ር ዐቢይ ለመንገር ፈልጌ ነበር፤ ግን ጊዜ አልበቃንም፡፡ የችግር መፍቻ ዘዴውን ግን ጽፌ አስቀምጫለሁ፡፡
እባክዎ ይንገሩኝ?
ብዙ ሰው ይሄ ግጭት እንዴት ይፈታ የሚለው ያስጨንቀዋል፡፡ እኔም ያስጨንቀኛል፡፡ ከዚህ ጭንቀት በመነሳት ሁሌም አዲስ መፍትሔ ለማግኘት ሳነብ ሳሰላስል ነው የምውለው፡፡ አንዱ መፍትሔ መስሎ የታየኝ ለምሣሌ የኦነግ እና የመንግስት ፀብ የተፈታው በውጭ ሃይሎች ወይም በህግ ሰዎች ጣልቃ ገብነት አይደለም፡፡ በኦሮሞ አባ ገዳዎች አሸማጋይነት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ችግር ባለባቸው አካባቢ በሙሉ ከአካባቢው ወጣቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአካባቢው ተሠሚነት ያላቸው ግለሰቦችና ምሁራን የተውጣጣ የአሸማጋይ ቡድን ማቋቋምና፣ ቡድኑ በአካባቢው ባህልና ወግ መሠረት ችግር እንዲፈታ ማድረግ ይቻላል፡፡
የወልቃይት ጉዳይን እንደ ምሣሌ ብንወስድ፤ አካባቢውን በሚገባ የሚያውቁ ሽማግሌዎች፣ የባህል መሪዎች፣ የማህበረሰብ ተሠሚዎች፣ ወጣቶችና ምሁራን፤ ከሁለቱም ወገን በጋራ ማቋቋምና መንግስት እጁን ከዚያ ውስጥ አውጥቶ “በሉ እናንተ በዚህም በዚያም ብላችሁ ይሄን ችግር ፍቱት” ቢባል ማህበረሰቡ አብሮ የኖረ፣ የተዋለደ እንደመሆኑ ሳይውል ሳያድር ችግሩን ይፈታ ነበር፡፡ የሀገሪቱ ግጭቶች፤ ከሀገሪቱ አዋቂዎችና ሽማግሌዎች የሚያልፍ አይደለም፡፡
ለዚህ ደግሞ የኦሮሞ አባገዳዎችና ሽማግሌዎች ያደረጉት በቂ ምስክር ነው፡፡ ዋና ትልቅ ተግባር፤ ሽምግልናን ማጠናከር ነው፡፡ ሽማግሌዎቹን በየአካባቢያቸው ያለውን ችግር እንዲፈቱ መንግስት ራሱን ቢያገልል ጥሩ ውጤት ይመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን መሪውን እንደመረጠ ይሰማኛል። ምንም የምርጫ ወጪ ሳናወጣ፣ ህዝብ መሪውን መርጧል፡፡ እኔ መቼም ሌላ የምለው ነገር የለኝም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከእግዚአብሔር የመጣ ነው እላለሁ፡፡ ከአፄ ሀይለ ሥላሴ ወዲህ እኔ በመሪነት ደረጃ የማረከኝ ዶ/ር ዐቢይ ነው። ከጃንሆይ ጋር ለ10 አመት ያህል ሠርቻለሁ፤ እቀርባቸው ነበር። በጣም ትልቅ አሳቢ ሰው ነበሩ፡፡ በአዕምሮዬ ውስጥ እስካሁንም አፄ ኃይለሥላሴን እንደ ትልቅ ሰው አያቸዋለሁ። አሁንም ዶ/ር ዐቢይን ሳገኛቸው እንደዚያ አይነት ስሜት ተሰምቶኛል። ዶ/ር ዐቢይ ሃኪም አይደሉም፣ የህግ አዋቂ አይደሉም፤ በቃ እሳቸው መሪ ናቸው፡፡  በመሪነታቸው ዶ/ር ዐቢይ ትልቅ ሰው ናቸው። ዶ/ር ዐቢይን ሳነጋግራቸውም። ትክክለኛ መሪ እንደሆኑ በሚገባ ተረድቻለሁ። ከገጠር እስከ ከተማ ዶ/ር ዐቢይ በመሪነታቸው ይታወቃሉ። 10 አመት ያለ ትርጉም ከሚቀመጡ መሪዎች በተሻለ 10 ወር የቆዩት ዶ/ር ዐቢይ ተቀባይነትና እውቅና አግኝተዋል፡፡  
አሁን አብዛኛውን ጊዜዎን በምንድን ነው የሚያሳልፉት?
ጡረታ ከወጣሁ 10 አመት ይሆነኛል፡፡ አለም ባንክ ውስጥ ነበር ስሰራ ቆይቼ ጡረታ የወጣሁት። አሁን የጡረታ ጊዜዬን በብዙ ጉዳዮች ላይ እያሳለፍኩ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜዬን በማንበብና ስለ ሀገር ጉዳይ በማሰላሰል አሳልፋለሁ፡፡ በተረፈኝ ጊዜ ደግሞ ዘመዶቼን እጠይቃለሁ፡፡ እነሱም እኔ ጋ መጥተው ይጐበኙኛል፡፡ ከዚህ በፊት አንድ መጽሐፍ ጽፌያለሁ፤ አሁንም ሌላ ለመፃፍ እየሞከርኩ ነው። እኔ ሁልጊዜ እፀልያለሁ፡፡ ዘወትር ጠዋት እነሳና “እግዚአብሔር በሠላም ስላሳደረኝ አመሰግነዋለሁ። ቤታችን ስላልተቃጠለ ወይም ሌባ መጥቶ ስላልዘረፈን አመሰግነዋለሁ፡፡ ሀገሪቷም ደህና ስላደረች አመሰግነዋለሁ፡፡”
የጡረታ ክፍያ ከማን ነው የሚያገኙት?
የአለም ባንክና የተባበሩት መንግስታት ናቸው እንጂ እኔ ከኢትዮጵያ መንግስት የማገኘው ጡረታ የለም፡፡ ምክንያቱም እኔ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሰራሁት 20 አመት ገደማ ስለሆነ ለጡረታ አይበቃም፡፡ ያው የጡረታ ገንዘብ ብዙ አይደለም። ግን የምበላው የምዝናናበት አላጣም፤ ፈጣሪ ይመስገን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አነባለሁ፡፡ ከሰዎች ጋር በቤቴ፣ በሌላ ቦታ እየተገናኘሁ እጫወታለሁ፡፡
ቀጣይ ምርጫ የት ነው የሚወዳደሩት?
ባለፈው የተወዳደርኩበት ወለጋ ላይ ነው ለመወዳደር ያሰብኩት፡፡ በግሌ ነው የምወዳደረው፡፡
አፄ ኃይለ ሥላሴንና ዶ/ር ዐቢይን ለማመሳሰል ሞክረዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በምንድነው ነው የሚመሳሰሉት?
ጃንሆይ ለኔ ቅርብ ነበሩ፡፡ ሁልጊዜ ስለ መፋቀር፣ ስለ መከባበር፣ ስለ እርቅ ይናገሩ ነበር፡፡ ዶ/ር ዐቢይም ይሄን ሃሳብ ይናገራሉ። ዶ/ር ዐቢይ እኔን የማረከኝ በዚህ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ከሰው ጋር በሠላም መኖርን ነው የሚሰብከው፣ መነጋገር መቀራረብን ይወዳል። ምንም ቢሆን በጉልበት እንዲህ አደርጋለሁ፣ እንዲህ እናደርጋለን ሲል እስካሁን አልሰማሁም። ስለዚህ ዶ/ር ዐቢይ በፍቅርና በመቀራረብ የሚያምን ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴም እንዲህ ዓይነት በጐ ባህሪ ነበራቸው፡፡ እኔም ምታው! በለው! ማለት አልወድም፡፡ የፍቅርና ለስለስ ያለውን የሠላም መንገድ ነው የምወደው፡፡         

Read 3944 times