Saturday, 09 February 2019 13:09

“ዲሽ”

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(8 votes)

  ሰውየው የሽያጭ ሰራተኛ ነው፡፡ ቀኑን በሙሉ ሰዎችን ሲያግባባና ለቀጠረው ኩባንያ ገቢ ሲያስገባ ይውላል፡፡ ደሞዙ ግን አይበቃውም፡፡ ሌላ ስራ ቢያፈላልግም የሚቀጥረው መስሪያ ቤት አላገኘም፡፡ ምክንያቱም አንድም በትምህርቱ የገፋ ባለመሆኑና ሁለትም የተሟላ የትምህርት ማስረጃ ስላልነበረው ነው፡፡
በልቶ ጠጥቶ ጥቂት ከተዝናና በእጁ ላይ ገንዘብ አያድርም፡፡ እድሜው በሰላሳዎቹ መጨረሻ ላይ ሲሆን እሱ ከሚያሻሽጥበት መደብ ጐን፣ ሌላ መደብ ያላት የፀጉር ቅባቶችን የምታሻሽጥ ወጣት ሴት ከወደደ ሶስት ወራት አልፎታል፡፡
እየተሰራረቁ በአይን ከመተያየት ውጭ እና አልፎ አልፎ ከሚሰጣጡት የእግዚአብሔር ሰላምታ ውጭ ብዙም ንግግር የላቸውም፡፡ አንድ ምሽት እቃውን ሰብስቦ ለመሄድ ሲሰናዳ አጠገቡ ቆማ አገኛት፡፡ ሁልጊዜ የምትለብሰውን እዚህ ግባ የማይባል ቀሚስዋን ሳይሆን ግራጫማ ስስ ሹራብና ዳሌዋን አጉልቶ የሚያወጣ ጥቁር ሱሪ ለብሳ ነበር፡፡
እንዲህ ታምራለች እንዴ? ሲል አሰበ፡፡ አይንዋን እያሸች ነበር፡፡
“እስኪ እይልኝ ትንኝ ገባ አይኔ ላይ” በጥንቃቄ አይንዋን… ቅንድብዋን እየነካካ፣ ሸፋሽፍቷን እየከፈተ ቢያይ ምንም ምሽት የለም፡፡
“በደንብ አላየህልኝም” አለችና አይንዋን እያሸች ወደ ቦታዋ ተመለሰች፡፡ እንደለመደው ሰርቆ ሲያያት፣ ልብ የሚሰልብ ፈገግታ ሰጠችው።
ይህ በሆነ በሳምንቱም ቤቱ ይዟት ሄደ። ትዳራቸው ጣፋጭና በደስታ የተሞላ ሆነ። የሶስት ወር እርጉዝ ከሆነች በኋላ ስራዋን ማቆም እንዳለባት ተስማሙ፡፡ ቀኑን በሙሉ ሲሰራ ይውልና ማታ ቤቱ ሲመለስ በፍቅር ሲጫወቱ ያድራሉ፡፡ የቤት ኪራይ ከፍሎ፣ ለሁለቱ ምግብና የሚያስፈልጋቸውን አሟልቶ የተረፈው አራት ሺህ ብር ነበረው፡፡ ቀኑን ሙሉ ብቻዋን ባዶ ቤት በመዋዋል ልቡ ስለተነካ፣ ለስዋ ደስታ ቴሌቪዥንና ዲሽ ለመግዛት ወሰነ፡፡
“ዲሽ ልገዛልሽ አስቢያለሁ” አለ የሰጠችውን ድንሾ በስጋ ተስገብግቦ እየዋጠ፡፡
“በምን ገንዘብ?” ጥፍርዋን እየሞረደች፡፡
“አራት ሺህ ብር አለኝ”
“እና ለሌላ ለሚጠቅም ነገር ውል አይሻልም?”
“ብቻሽን ስትሆኝ ደስ አይለኝም”
በግዴለሽነት ትከሻዋን ሰበቀች፡፡
በሚቀጥለው ቀን ቲቪውንና ዲሹን አመጣ። ዲሹን ጣራ ላይ ለመስቀል ከጐረቤት መሰላል ከተዋሰ በኋላ ጣራው ላይ ወጣ፡፡
አሮጌው የቤቱ ቆርቆሮ በተጠላለፈ የኤሌክትሪክ ገመድ ተተብትቧል፡፡ በጥንቃቄ እየተራመደ ቆመና የጐረቤቱን ወጣት ልጅ “ዲሹን አቀብለኝ” አለው፡፡ በዚያች ቅጽበት አንዳች ንዝረት መላ ሰውነቱን አርገፈገፈውና ከጣራው ላይ ወድቆ መሬት ላይ ተፈጠፈጠ፡፡ ምን እንዳደረጉለት አይታወቅም፡፡ የነቃው ግን አልጋው ላይ ነው፡፡ ከጐኑ ተኝታ እያለቀሰች ነበር፡፡
“ምን ሆኜ ነው?” አላት፡፡
“ኤሌክትሪክ ነው፡፡ ይሄን ሰበበኛ እቃ አውጣና ጣል!”
ከሶስት ቀናት በኋላ ዲሹን እንዴት ጣራው ላይ እንደሚሰቅል ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ነገር ግን ምንም መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ያለው እድል ወደ ባለሞያ” መሄድ ብቻ ነበር፡፡  
ባለሞያው መሰላሉ ላይ ወጥቶ፣ ጣራውን በጥንቃቄ ከተመለከተ በኋላ “ሁለት ሺህ ብር ያስከፍላል” አለው - እጆቹን አጨብጭቦ እያረገፈ፡፡
“ሁለት ሺህ ብር ኬት አገኛለሁ?”
“ያም ቢሆን ህይወቴን ለአደጋ ሰጥቼ ነው፤ ስትፈልገኝ በዚህ ደውል” ብሎት ጥሎት ሄደ፡፡
የባለሞያውን ካርድ ይዞ ፈጦ ቀረ፡፡ መጀመሪያ ያደረገው ማስታወሻ ደብተሩ ላይ ብር የሚያበድሩትን ሰዎች ስም ዝርዝር መፃፍ ነበር፡፡ ሄኖክ አንደኛው ነው፡፡ ሂሩት ሁለተኛዋ ናት፡፡ ስድስት ሰዎች ፃፈና ቢሮዋቸውንና ቤታቸውን ማንኳኳት ጀመረ፡፡ በስንት ድካም ገንዘቡ ተገኝቶ ዲሹ ተተከለ፡፡ ተወዳጅዋ ሚስቱ አይንዋን ከቴሌቪዥኑ መንቀል ተሳናት። ከጣቢያ ጣብያ እየቀያየረች አክተሮቹንና ዘፋኞቹን ፈዛ ስትመለከት ታድራለች፡፡ ሳቅ ጨዋታዋና የሞቀው እቀፏ ቀስ በቀስ ወደ ዲሹ ሄዶ፡፡ ብቻውን አልጋው ላይ ሲገለባበጥ እያደረ የስዋን ተደናቂ አክተሮች መርገም ማደር ከጀመረ ሰነበተ፡፡ በመጨረሻ ፊትዋን አዙራ መተኛት ጀመረች፡፡
“ዲሹን ለመሸጥ አስብያለሁ” አላት ሰጠችውን ጨው የሌለው ሽሮ እየጎመዘዘው አፉ ላይ እያላመጠ
“ለምን?” ጥፍርዋን ቀለም እየተቀባች፡፡
“ገንዘቡን ለሌላ ለሚጠቅም ነገር ላውለው አስብያለሁ”
በግዴለሽነት ትከሻዋን ሰበቀች፡፡
ዲሹን የሚያወርደው ያው ባለሙያ ነው፡፡ ደወለለት፡፡
“ዲሹን አውርድልኝ” አለው፡፡
“ለምን?”
“አልፈልገውም፤ ልሸጠው አስብያለሁ ትገዛዋለህ?”
“ምን ያደርግልኛል?”

Read 2359 times