Saturday, 16 February 2019 13:47

ከ43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በፊት…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(7 votes)


       • በጃንሜዳው አገር አቋራጭ የኢትዮጵያ እጩ አትሌቶች ተለይተዋል
       • ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኬንያ ዝግጅት ግምት ተሰጥቷል
       • 310 ሺ ዶላር የሽልማት ገንዘብ ቀርቧል
       • በ42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች፤34 የወርቅ ሜዳልያዎች የኢትዮጵያ
       • የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ይቻላል ወይ


           በ36ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሲካሄድ የበርካታ ክለቦችን ትኩረት ስቧል፡፡ ለዓለም የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና እንደማጣርያ  ሲካሄድ  በወጣት ፤በአዋቂ እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ በሁለቱም ጾታዎች በአምስት የውድድር መደቦች ተከፋፍሎ ነበር፡፡
በ10 ኪሎ ሜትር  አዋቂ ወንዶች ውድድር ላይ አትሌት ሞገስ ጥኡማይ ከመሰቦ ሲሚንቶ ክለብ አንደኛ ሆኖ የጨረሰ ሲሆን ርቀቱን የሸፈነው 31 ደቂቃዎች 16 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነው፡፡ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከደቡብ ፖሊስ ክለብ  እንዲሁም አትሌት አንዷምላክ በልሁ ከሲዳማ ቡና ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን አግኝተዋል፡፡ በአዋቂ ሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት ደራ ዲዳ ከኦሮሚያ ክልል  ስታሸንፍ ርቀቱን  በ33 ደቂቃዎች 50 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በመሸፈን ሲሆን አትሌት ለተሰንበት ግደይ ከትራንስ ኢትዮጵያ እና አትሌት ዘነቡ ፍቃዱ ከኦሮሚያ ፖሊስ   ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል በወጣት ወንዶች የ8 ኪሎ ሜትር ውድድር  አትሌት ንብረት መላክ ከአማራ ክልል፣ ፀጋዬ ኪዳኑ ከመስፍን ኢንጂነሪግ እና ሚልኬሳ መንገሻ ከኦሮሚያ ክልል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ሲያገኙ፤ በወጣት ሴቶች የ6 ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ  አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሄር ከጉና ንግድ ሥራዎች፣ አለሚቱ ታኩ ከኦሮሚያ ክልልና ፅጌ ገብረሰላማ ከሱር ኮንስትራክሽን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል።በድብልቅ ሪሌ ውድድር ላይ የኦሮሚያ ክልል በአንደኛነት ሲጨርስ አዳማ ከተማ ሁለተኛ እንዲሁም የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ተከታታዮቹን ደረጃዎች ወስደዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን እንዳስታወቀው በ36ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የሜዳሊያ ውጤት ያስመዘገቡት እስከ አምስተኛ ደረጃ የጨረሱት፤ እንዲሁም በወጣቶች ምድብ በሁለቱም ጾታ እስከ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁና በመጋቢት ወር ላይ በዴንማርክ በሚካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የመሳተፍ እድል ይኖራቸዋል፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተመሳሳይ ከሳምንት በኋላ የሚደረገውን የማጣርያ ውድድር ያዘጋጀው በኤልዶሬት ስፖርት ክለብ ሜዳ ላይ ሲሆን መወዳደርያው  በየሁለት ኪሎሜትር የሚጠማዘዝ ፤ አስቸጋሪና እንቅፋቶች የበዙበት ሆኖ ከዴንማርክ አሩሁስ ጋር የሚቀራረብ መሆኑ ተገልጿል፡፡
43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በዴንማርክ አሩውስ
43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን በመጋቢት  ወር የምታስተናግደው  የዴንማርኳ ከተማ አሩውስ ስትሆን 70 አገራትን የወከሉ ከ700 በላይ አትሌቶች ይሳተፉበታል፡፡ ዴንማርክ ለሻምፒዮናው ያዘጋጀችው የመወዳደርያ ሜዳ በውድድር ታሪክ ዘመናዊው የተባለ ሲሆን በሳራ ንጣፍ በተሰራለት ሙዚዬም ውስጥም የሚያልፍ ይሆናል፡፡ በሻምፒዮናው እንደተለመደው ከፍተኛውን የውጤት ግምት የወሰዱት የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ቢሆኑም በተለይ ከኡጋንዳ እና ኤርትራ እንዲሁም ከቱርክ፤ ባህሬን፤ አሜሪካ፤ እንግሊዝ፤ አየርላንድ እና ከጃፓን አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል፡፡ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ባለፉት 42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በሁለቱም ፆታዎች በተለይ በረጅም ርቀት ከፍተኛ ውጤት ቢያስመዘግቡም በአጭር ርቀት ያን ያህል የበላይነት አልነበራቸውም፡፡ በረጅም ርቀት በአዋቂ ወንዶች ከ1981 እኤአ ጀምሮ እንዲሁም በአዋቂ ሴቶች ከ1991 እኤአ ጀምሮ፤ በወጣት ወንዶች ከ1982 እኤአ ጀምሮ  እንዲሁም በወጣት ሴቶች ከ1989 እኤአ ጀምሮ ሌሎች አገራትን ጣልቃ ሳያስገቡ በአሸናፊነቱ ላይ ተፈራርቀዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ለዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በድምሩ 310 ሺ ዶላር የሽልማት ገንዘብ አዘጋጅቷል፡፡  በግልና በቡድን  ከ1ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች የሽልማት ገንዘቡ የሚከፋፈል ሲሆን በአዋቂ አትሌቶች የሁለቱም ፆታዎች የውድድር መደቦች በግል  ውጤት ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ለ1ኛ 30ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 15ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 7ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 5ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 3ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡ በቡድን ውጤት ለሚያሸንፉ አገራት ደግሞ ለ1ኛ 20ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 16ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ4ኛ 10ሺ ዶላር፣ ለ5ኛ 8ሺ ዶላር እንዲሁም ለ6ኛ ደረጃ 4ሺ ዶላር የሚታሰብ ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች ድብልቅ የዱላ ቅብብል ውድድር ለ1ኛ 12ሺ ዶላር፣ ለ2ኛ 8ሺ ዶላር፣ ለ3ኛ 6ሺ ዶላር፣ እንዲሁም ለ4ኛ 4ሺ ዶላር እንደሚሸለም ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ  ባለፉት 42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች
ባለፉት 42 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ላይ ኢትዮጵያ በአዋቂዎች ረጅም ርቀት ውድድር በሁለቱም ፆታዎች በግልና በቡድን 34 የወርቅ ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ በአዋቂዎች ረጅም ርቀት በወንዶች 10 የወርቅ፤ 6 የብርና 8 የነሐስ ሜዳልያዎች በግል እንዲሁም 8 የወርቅ፤13 የብርና 7 የነሐስ ሜዳልያዎችን በቡድን የኢትዮጵያ አትሌቶች ተጎናፅፈዋል፡፡  በአዋቂዎች ረጅም ርቀት በሴቶች ደግሞ 6 የወርቅ፤ 7 የብርና 9 የነሐስ ሜዳልያዎች በግል እንዲሁም 10 የወርቅ፤12 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን በቡድን አስመዝግበዋል፡፡
በሻምፒዮናው የኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪክ በአዋቂዎች ምድብ የአጭርና ረጅም ርቀት ውድድሮች ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አትሌት  ቀነኒሣ በቀለ ነው። ቀነኒሣ በአጭር ርቀት 4 ኪ.ሜ እና በረጅም ርቀት 12 ኪ.ሜ ውድድሮች በ5 ሻምፒዮናዎች በተከታታይ በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ሲሆን በ2008 እ.ኤ.አ ላይ በረጅም ርቀት 6ኛውን የወርቅ ሜዳልያ በማግኘቱ ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ታሪክ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ያስመዘገበ አትሌት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው በአዋቂዎች ምድብ ውጤታማ ከሆኑ የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች መጠቀስ ያለባቸው ደራርቱ ቱሉ፤ ጌጤ ዋሚ፤ ጥሩነሽ ዲባባ፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ ዋናዎቹ ናቸው፡፡  አትሌት ደራርቱ ቱሉ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት ያሸነፈች ሲሆን፣ ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ በአዋቂዎች ምድብ በረጅም ርቀት ለ3 ጊዜያት እንዲሁም በአጭር ርቀት 1 ጊዜ ማሸነፍ ከኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ትልቁን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1981 እ.ኤ.አ ላይ በአዋቂዎች ምድብ በወንዶች የ12 ኪ.ሜ ውድድር ሲሆን መሃመድ ከድር ባገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ አትሌት መሐመድ ከድር ከዓመት በኋላ በ1982 እኤአ በተመሳሳይ ረጅም ርቀት አሸንፎ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል፡፡ በአዋቂ ወንዶች የ12 ኪሎሜትር ውድድር ኢትዮጵያ ከሰበሰበቻቸው 10 የወርቅ ሜዳልያዎች ስድስቱን ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ከ2002-2008 እ.ኤ.አ በተካሄዱት የዓለም ሻምፒዮናዎች ነው። ሌሎቹን 4 የወርቅ ሜዳልያዎች ደግሞ መሃመድ ከድር (በ1982 እ.ኤ.አ)፣ በቀለ ደበሌ (በ1983 እ.ኤ.አ)፣ ገብረእግዚአብሔር ገ/ማርያም (በ2009 እ.ኤ.አ) እንዲሁም ኢማና መርጋ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ አስመዝግበዋል፡፡
በአዋቂ ሴቶች የ8 ኪ.ሜ የረጅም ርቀት ውድድር ደግሞ በኢትዮጵያዊ አትሌት የመጀመሪያ የሜዳልያ የተገኘው በ1991 እ.ኤ.አ ደራርቱ ቱሉ በወሰደችው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በ1995 እ.ኤ.አ ላይ አሁንም ደራርቱ ቱሉ የተጐናፀፈች ሲሆን ሌሎች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ደግሞ በ1975 እና በ2000 እ.ኤ.አ አግኝታለች፡፡ በአዋቂ ሴቶች ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 9 የወርቅ ሜዳልያዎች 3 ከጥሩነሽ ዲባባ (በ2005፣በ2006፣ በ2008 እ.ኤ.አ) 2 በጌጤ ዋሚ (በ1996፣ በ1999 እ.ኤ.አ) እንዲሁም በወርቅነሽ ኪዳኔ (2003 እ.ኤ.አ) ተገኝተዋል፡፡
በርካታ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሜዳሊያዎችን በግል እና ከቡድን ጋር በማግኘት በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ በአጠቃላይ 27 ሜዳሊያዎችን በመውሰድ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ21 ሜዳሊያዎች መሪነቱ ላይ ተቀምጣለች። በግልና በቡድን የወርቅ ሜዳሊያዎች ድምር የአለም አገር አቋራጭን የተቆጣጠሩትም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው። በወንዶች በግል ያገኛቸውን 12 ወርቅ ሜዳሊያዎች እና በቡድን ያገኛቸውን አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ጨምሮ በ16 ወርቅ ሜዳሊያዎች ቀነኒሳ በቀለ መሪነቱን ሲይዝ፣ በሴቶችም በግሏ አምስት፣ በቡድን ዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ በ14 ወርቅ ሜዳሊያዎች በሴቶቹ ምድብ  አንደኛነቱን ይዛለች። በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪካቸው ቢያንስ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሰባት የኢትዮጵያ አትሌቶች ክብረወሰኑ አላቸው። እነሱም ሀይሉ መኮንን፣ ጌጤ ዋሚ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማሪያም፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰለች መልካሙ ናቸው።

የዓለም አገር አቋራጭ አዘጋጅነት ለኢትዮጵያ?
የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች በአንጋፋነቱ እና በፈታኝነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡  ከ1973 እኤአ ጀምሮ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው ለ38 ጊዜያት በየዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ከ2011 እ.ኤ.አ ወዲህ ግን በየሁለት ዓመቱ እንዲደረግ የተወሰነው፤ በተለይ ባለፉት 30 አመታት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በየውድድር መደቡ እስከ 10 ያለውን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በመቆጣጠር ያሳዩት የበላይነት  ባስከተለው ጫና ሲሆን በየሁለት ዓመቱ መካሄድ ከጀመረ የዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በተሳትፎ ታሪኳ  ታላላቅ ውጤቶችን አስመዝግባለች። በኦሎምፒኮችና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ታላላቅ ስኬት ያገኙ አትሌቶች የተገኙት ከፈታኙ የአገር አቋራጭ ሩጫ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ከ2 ዓመት በፊት የሻምፒዮናውን መስተንግዶ የምስራቅ አፍሪካዋ አገር ኡጋንዳ አግኝታ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ ለኢትዮጵያ ጥሩ መነቃቃት መፍጠር ነበረበት።  ከ2 ዓመት በፊት   ሻምፒዮናው አፍሪካ ውስጥ በኡጋንዳ፤ ካምፓላ ሲካሄድ አህጉሪቱ ለ5ኛ ጊዜ መስተንግዶውን ያገኘችብት ነበር፡፡ ሞሮኮ ለሁለት ጊዜያት በ1975 እና በ1998 እኤአ፤ ደቡብ አፍሪካ በ1996 እኤአ እንዲሁም ኬንያ በ2007 እኤአ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን እንዳዘጋጁ ይታወቃል። ከአውሮፓ እንግሊዝ፤ ፖላንድ፤ ፈረንሳይ፤ ስፔን፤ ፖርቱጋልና ጣልያን ከአንድ ጊዜ በላይ ውድድሩን ያስተናገዱ ከተሞች ሲሆኑ፤ አሜሪካም ከአንድ ግዜ በላይ አዘጋጅ ነበረች፡፡ ከኤስያ ጃፓን፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ጆርዳን ሁሉ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን አስተናግደዋል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ውድድሩን የማዘጋጀት እቅድ ሊኖራት ያስፈልጋል፡፡  በዚህ አቅጣጫ ትኩረት አድርጎ መስራት ደግሞ የፌደሬሽኑ ሃላፊነት ነው፡፡ ከኡጋንዳዋ ካምፓላ ከተማ በኋላ ዘንድሮ 43ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  የዴንማርኳ አሩውስ ከተማ ስታስተናግድ፤  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቢያንስ   በ2021 እ.ኤ.አ ላይ 44ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ወይንም በ2023 እኤአ 45ኛውን የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ለማስተናገድ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

Read 16788 times