Sunday, 03 March 2019 00:00

የደም ማነስ በእርግዝና ወቅት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)


አንዲት ሴት ስታረግዝ የደም ማነስ ሊይዛት ይችላል፡፡
ያረገዘችው ሴት የደም ማነስ ከያዛት በደምዋ ውስጥ በቂ እና ጤናማ የሆነ ቀይ የደም ሴል አይኖራትም፡፡
እርጉዝዋ ሴት የደም ማነስ ካለባት ቀይ የደም ሴል ለሰውነትና ለተረገዘው ልጅ ንጹህ አየር (OXYGEN)  ማድረስ ይሳነዋል፡፡
በእርግዝና ወቅት ሰውነት የተረገዘውን ልጅ ለማሳደግ ሲል ቀደም ሲል ከነበረው የደም መጠን የበለጠ ደም ያመርታል፡፡  

በኢትዮጵያ በውጭው አቆጣጠር በ2016/ በተደረገው የEDHS ሪፖርት  እድሜያቸው ከ15-49 አመት የሆኑ ሴቶች 24% የደም ማነስ እንደነበራቸው የጤና ባለሙያዎች ያደረጉት የዳሰሳ ጥናት ያሳያል። ይህ መረጃ እንደሚያስነብበውም በኢትዮጵያ የደም ማነስ በተጠቀሰው የእድሜ ክልልና ጾታ ከ2011/ መረጃ በ7% ጨምሮ ታይቶአል፡፡ በእርግጥ ከመስተዳድር መስተዳድር የሚታዩ ልዩነቶች አሉ። ለምሳሌም በሶማሌ 60% በአዲስ አበባ 16% የተመዘገበ ሲሆን ይኸውም በኢትዮጵያ ከፍተኛውና ዝቅተኛው ቁጥሮች ናቸው፡፡
አንዲት ሴት በምታረግዝበት ወቅት ሰውነትዋ የተረገዘውን ልጅ እድገት ለመደገፍ ሲል ቀድሞ ከነበራት ደም የበለጠ ያመርታል፡፡ ነገር ግን እርጉዝዋ ሴት በቂ አይረን ወይንም ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች ንጥረነገሮችን የምታገኝ ካልሆነ የሚያስፈልገውን ያህል ደም ማምረት ስለማትችል በእርግዝና ጊዜ ሰውነትዋ ሊያመርት የሚገባውን ያህል ተጨማሪ ደም ሊኖራት አይችልም፡፡
በእርግጥ ከቫይታሚንና አይረን እጥረት፤ እንዲሁም ከሌሎች ምክንያቶች የተነሳ መጠነኛ የሆነ እና ብዙም የህክምና ድጋፍ የማያስፈልገው የደም ማነስ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ የሚወ ሰነው በሕክምና ባለሙያዎች ስለሆነ ተተገቢውን ሕክምና ማድረግ እና የምክር አገልግሎታ ቸውን መጠቀም ይረዳል፡፡
የደም ማነስ የመድከም ስሜትን ሊፈጥር ይችላል። ስሜቱ ከባድ ቢሆንም ግን ብዙዎች የህክምና እርዳታን ስለማይጠይቁ ውሎ አድሮ ሌሎች ከባድ የሆኑ የጤና እውክታዎችን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተለይም እርግዝናውን ወደተለያየ ችግር የመግፋትና አልፎ ተርፎም ካለጊዜው እንዲወለድ የማድረግ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል፡፡  በእርግዝና ጊዜ የደም ማነስ መኖር ያለመኖሩን ለማወቅ ምክንያቶቹን ፤ ምልክቶቹንና የህክምናው እርዳታ ምንድነው የሚለውን አስቀድሞ ማወቅ ይረዳል፡፡
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የደም ማነስ ሶስት አይነት ነው፡፡ በሳይንሳዊ ቃሉም፡-
የአይረን እጥረት የደም ማነስ፤
የፎሌት እጥረት የደም ማነስ፤
የቫይታሚን ቢ12 እጥረት የደም ማነስ ተብሎ ይለያል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ለምን የደም ማነስ ይከሰታል?
የአይረን እጥረት የደም ማነስ፤
የአይረን እጥረት የደም ማነስ የሚከሰተው ሰውነት በቂ አይረን ካላገኘ እና በቂ የሆነ ሄሞግ ሎቢን ማምረት ሲያቅተው ነው፡፡ ይህ ማለትም በቀይ የደም ሴል ውስጥ ፕሮቲን አለመኖር ሲሆን ይህም ኦክስጂንን ከሳንባዎች ወደ ተቀረው የሰውነት ክፍል የሚያዳርስ ነው፡፡ በእርግዝና ጊዜ የአይረን እጥረት በጣም የተለመደ እና በብዙዎች ላይ የሚያጋጥም ነው፡፡
የፎሌት እጥረት የደም ማነስ፤
ፎሌት ማለት በተፈጥሮ በተለያዩ ምግቦች ውስጥ ማለትም አረንጉዋዴ ቅጠል ውስጥ የሚገኝ ቫይታሚን A እና B ሲሆን ይህም ሰውነት ጤናማ ቀይ የደም ሴሎችን ጨምሮ አዳዲስ ሴሎች እንዲፈጠሩ የሚያስችል ነው፡፡ በእርግዝና ጊዜ ሴቶች ፎሌትን ከተለመደው በላይ በተጨማሪ ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ባልታሰበ ሁኔታ በምግባቸው ውስጥ የሚፈለጉት ቅጠሎች ካልተካተቱ የፎሌት ንጥረ ነገር እጥረት ይኖራል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰውነት በቂ ቀይ የደም ሴል ስለማይኖረው ኦክስጂንን ለሰውነት ማዳረስ አይችልም፡፡ የፎሌት እጥረት ሲያጋጥም በወሊድ ላይ የተለያዩ ጉድለቶችን እንዲከሰት ያደርጋል ፡፡ ለምሳሌም ከክብደት በታች መወለድ የመሳሰሉትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህንን ለመደገፍ ሲባልም ፎሊክ አሲድ የተሰኘው ንጥረ ነገር በድጋፍ መልክ ላረገዘችው ሴት ይሰጣል፡፡
የቫይታሚን ቢ12 እጥረት፤  
ጤናማ ቀይ የደም ሴሎችን ለመፍጠር ሰውነት ቫይታሚን ቢ 12/የተሰኘውን ንጥረነገር ይፈልጋል። እርጉዝ የሆነችው ሴት ይህንን ቫይታሚን የያዙ ምግቦችን በበቂ ሁኔታ ካልተመገበች ጤናማ የሆኑ ቀይ የደም ሴሎችን ለማምረት አትችልም፡፡ ቫይታሚን ቢ 12/ የሚገኙበት ምግቦች እንደ ስጋ ፤ዶሮ፤ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች፤ እንቁላል የመሳሰሉት ሲሆኑ እነዚህን ምግቦች አለመመገብ ቫይታን ቢ12/ን ላለማግኘት ይዳርጋል፡፡ ይህ ካልተሟላ የሚወለደው ልጅ የነርቭ መስመሮች ችግር፤ ካለጊዜው መወለድ የመሳሰሉት ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በመውለድ ጊዜ ወይንም ከወሊድ በሁዋላ እናትየው የደም መፍሰስ አደጋም ሊገጥ ማት ይችላል፡፡
በእርግዝና ጊዜ የደም ማነስ አደጋዎች፤
ሁሉም እርጉዝ ሴቶች የደም ማነስ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በመገመት ከተለምዶው ከፍ ባለ ሁኔታ አይረንና ፎሊክ አሲድ እንዲኖራቸው አስቀድሞ ማሰብና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በእርግዝና ጊዜ የደም ማነስ ችግር የተባባሰ የሚሆነው፤
እርግዝናው መንትያ ከሆነ፤
ከመጀመሪያው እርግዝና በቅርበት በድጋሚ እርግዝና ከተከሰተ፤
የጠዋት ጠዋት ትውኪያ (morning sickness) ብዙና የማያቋርጥ ከሆነ፤
እርግዝናው በታዳጊነት እድሜ ከሆነ ፤
በአይረን የበለጸገ ምግብ የማይመገቡ ከሆነ፤
ከእርግዝናው በፊት የደም ማነስ ታማሚ ከሆኑ፤ ነው፡፡
አንዲት ሴት በእርግዝና ወቅት በደም ማነስ ለመያዝዋ ምልክቶች፤
የገረጣ እና የለሰለሰ ቆዳ ፤ጥፍር፤ከንፈር፤
ድካምና አዝጋሚ መሆን ወይንም አቅም ማጣት፤
የትንፋሽ መቆራረጥ፤
የፈጠነ የልብ ምት፤
አንድ ነገር ላይ ትኩረት የማድረግ ችግር፤
የመሳሰሉት የሚታዩ ከሆነ ያረገዘችው ሴት ሳታወላውል ወደሐኪም ሄዳ ማማከር አለባት። በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች በሌሎች ምክንያቶችም ሊከሰቱ እንደሚችሉ ከወዲሁ ማወቅ ይገባል፡፡ የደም ማነስ ሕመም በጅምሩ ምንም ምክንያቶች ላይታይበት ይችላል፡፡ ማንኛዋም እርጉዝ ሴት የደም ማነስ ቢኖርባትም ባይኖርባትም ከሕክምናው አለም መራቅ አይገባትም፡፡ የህክምና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር መሰረት መመገብ እና መታከም የደም ማነስ ቢኖርም ባይኖርም ለማንኛዋም እርጉዝ ሴት ጠቃሚ ነው፡፡

Read 14222 times