Sunday, 17 March 2019 00:00

በዓለም አትሌቲክስ የኢትዮጵያዊያን ሪከርዶችና ክብረወሰኖች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)


        • ብዛት ከ 24 በላይ ሆኗል፡፡ ከ9 በላይ የዓለም ፤ 8 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ፤ 3 የዓለም ሻምፒዮና 4 የኦሎምፒክ ናቸው፡፡
        • የቀነኒሣ 10ሺና 5ሺ ሜትር ሰዓቶች ያለተቀናቃኝ 15 ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡
        • የጥሩነሽ 5ሺ ሜትር ሰዓት ያለተቀናቃኝ 11 ዓመታት ሲቆይ፤ የአልማዝ 10ሺ ሜትር ሰዓትም ላይደፈር ይችላል፡፡
       • በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ከተመዘገቡት 8 የኢትዮጵያ ናቸው፡፡ በወንዶች ምድብ 3 ፤ በሴቶች ምድብየገንዘቤ አምስት ክብረወሰኖች ፤ ገንዘቤ
            1 የዓለም 5 የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ክብረወሰኖች አሏት፡፡
      • በዓለም አትሌቲክስ በብዙ የውድድር መደቦች በብዛት ሪከርዶችን በማስመዝገብ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን የሚስተካከል የለም፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ረጅሙን የሩጫ ዘመን በ21
አመታት የፈፀመው ኃይሌ ከ27 በላይ ሪከርዶችን ከ2 ማይል እስከ ማራቶን ባሉ ርቀቶች አስመዝግቧል፡፡
     • በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ የኢትዮጵያን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በሴቶች 5ሺ ሜትር 14 ደቂቃ ከ11.15 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ የያዘችው የዓለም ሪከርድ
ማንም ሳይሰብረው 11 ዓመታት አልፈዋል፡፡
      • በመካከለኛ ርቀት በኢትዮጵያ አሌቲክስ የምንግዜም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በትራክና የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮች 7 የዓለም ሪከርዶችን
ይዛለች፡፡ በ1500ሜና በ2ሺ ሜትር ትራክ ላይ እንዲሁም በቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች በ1500 ሜትር፣ በ1 ማይል እንዲሁም በ2 ማይል ሩጫ በ3ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር
ያስመዘገበቻቸው ክብረወሰኖቿ ናቸው፡፡
    • አትሌት አልማዝ አያና በ2016 እ.ኤ.አ በሪዩ ዲጄኔሮ በተካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በ10ሺ ሜትር ያስመዘገበችው 29 ደቂቃ ከ17.45 ሰኮንዶች የዓለም ሪከርድና የኦሎምፒክ
ክብረወሰን በረጅም ርቀት ከፍተኛ ብቃት መለኪያ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
   • በረጅም ርቀትና በ አገር አ ቋራጭ ውድድሮች የ ምንግዜም ም ርጥ አትሌት የ ሆነው ቀ ነኒሳ በ ቀለ በ 5ሺ በ 12 ደቂቃ ከ 37.35 ሰኮንዶች እና በ 10ሺ ሜትር 2 6 ደቂቃ ከ 17.53 ሰኮንዶች
ያስመዘገባቸው ሁለት የዓለም ሪከርዶች ሳይደፈሩ 15 ዓመታት አልፏቸዋል፡፡ ቀነኒሳ በተመሳሳይ ርቀቶች የዓለም ሻምፒዮናና የኦሎምፒክ ክብረወሰኖችን እንደተቆጣጠረ ይታወቃል፡፡


         በዓለም  አትሌቲክስ በረጅምና መካከለኛ ርቀቶች ላይ በትራክ እና በቤት ውስጥ ውድድሮች፤ በጎዳና ላይና በሌሎች ሩጫዎች በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተያዙ የዓለም፤  የዓለም ሻምፒዮናና የኦሎምፒክ  ሪከርዶች እንዲሁም ክብረወሰኖች ብዛት ከ24 በላይ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት  በመካከለኛ ርቀት በሁለቱም ፆታዎች ለረጅም ዓመታት ሳይሻሻሉ የቆዩትን እንዲሁም ከረጅም ርቀት በሴቶች 10ሺ ሜትር  ከ20 ዓመታት በላይ ያልተደፈረውን የዓለም ሪከርዶች የኢትዮጵያ አትሌቶች መቆጣጠራቸው ዓለምን አስደንቋል፡፡ ይህ የስፖርት አድማስ ትንታኔ የኢትዮጵያ አትሌቶች ባለፉት 20 አመታት ከማራቶን ባሻገር በረጅምና በመካከለኛ ርቀት እንዲሁም በሌሎች ሩጫዎች የዓለም ሪከርዶች እና ክብረወሰኖች ሂደት ላይ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚዳስስ ነው፡፡
ባለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የውድድር መደቦች የተመዘገቡት የዓለም ሪኮርዶች እና  ሌሎች ክብረወሰኖች የሚሻሻሉበት እድል እየተመናመነ መምጣቱን የተለያዩ ጥናቶች ማመልከታቸው ያስገርማል፡፡ በተለይ በረጅም ርቀት 10ሺ ሜትርና 5ሺ ሜትር ውድድሮች በሁለቱም ጾታዎች  ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቧቸው የዓለም ሪከርዶች እንዲሁም ሌሎቹ የዓለም ሻምፒዮናና የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች የሚሰበሩባቸው ሁኔታዎች በተለያዩ ምክንያቶች አጠያያቂ ሆነዋል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የሚጠቀሰው ምክንያት በ10ሺ ሜትር በዓለም ዙርያ የሚካሄዱ ውድድሮች መመናመናቸው ነው።
የ10ሺ ሜትር ውድድሮች በሁለቱም ፆታዎች በየአገሩ ሚኒማ ለማሟላት ከሚደረጉ ማጣርያዎች ባሻገር በየሁለት እና በየአራት ዓመቱ በሚደረጉ የዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ የተወሰኑ ሆነዋል፡፡  በ5ሺ ሜትርም ተመሳሳይ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ሲሆን በቅርቡ አይኤኤኤኤፍ የውድድር መደቡን ከዳይመንድ ሊግ መርሃግብሮች  መሰረዙም በርቀቱ የሚኖረውን የሪከርድ ሂደት የሚያጓትተው ነው፡፡ በ10ሺ እና 5ሺ ሜትር የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ያላቸው የውጤት የበላይነት በረጅም ርቀት ህልውና ላይ እንቅፋት ሆኖ መታየቱ አወዛጋቢ ነው፡፡
የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ከደም አይነታቸው፤ ከአኗኗራቸው፤  በውድድሩ ያሏቸው ጀግኖች እና ታሪኮች ተወራርሶ በረጅም ርቀት ፍፁም የበላይነት መያዛቸው  ተምሳሌት ሆኖ  ከሌላው ዓለም ክፍል በሚፈጠር ትጋት ተፎካካሪ ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ የዓለም አትሌቲክስ የረጅም ርቀት ሩጫዎችን ከመገዳደር ይልቅ ከውድድር መድረክ እያጠፋ የሄደበት አቅጣጫ የስፖርቱን እድገት ያደናቅፈዋል፡፡ በአጠቃላይ በትራክ የረጅም ርቀት ውድድሮች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የፈጠሩት የበላይነት ከሌላው ዓለም የሚፎካከረው መጥፋቱ በተለያየ የውድድር መደብ ያስመዘገቧቸውን የዓለም ሪከርድ ሰዓቶች ከራሳቸው በቀር በቅርብ ዓመታት ሌሎች ማሻሻላቸውን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ ይህም ብዙዎቹ የዓለም ሪከርዶችና የተለያዩ ክብረወሰኖች በኢትዮጵያውያኑ ይዞታ ስር ለረጅም ጊዜ እንደሚቆዩ የሚያመለክት ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ በመካከለኛ ርቀት እና በቤት ውስጥ አትሌቲክስ በቅርብ ዓመታት የተመዘገቡት የዓለም ሪከርዶች እና ሌሎች ፈጣን ሰዓቶችንም ለማሻሻል ከኢትዮጵያዊ ወይንም ከኬንያዊ ሯጮች በቀር ላይታሰብ ይችላል፡፡ በተያያዘ የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ በተለይ በረጅም ርቀት ያላቸው የበላይነት የተዳከመው በማራቶን ልዕልቷ ነው፡፡ የዓለም የማራቶን ሪከርድ በተለይ በወንዶች ምድብ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከራቀ ከ10 ዓመታት በላይ ሲሆነው በሴቶች ምድብ በዚሁ የዓለም ሪከርድ ተቀናቃኝነት ያለው እድል ብዙም ግምት ያልተሰጠው ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም የማራቶን ሪከርድ በወንዶች የነበራቸው ጉልህ አስተዋፅኦ እና በሴቶች ያላቸው የመስበር እድል የተዳካመ ቢመስልም በዓለም ትልልቅ ማራቶኖች የቦታዎቹን ሪከርድ በማስመዝገብ ከኬንያውን የሚፎካከሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች በመሆናቸው ነው፡፡
ከ9 በላይ የዓለም ሪኮርዶች በኢትዮጵያውያን
ባለፉት 20 አመታት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1500 ሜትር እስከ ማራቶን፤ ከ2 እስከ 10 ማይል፤ በተለያዩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እንዲሁም ከ2ሺ  እስከ 5ሺ ሜትር በሚደረጉ የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች በፍፁም የበላይነት ሲያሸንፉ፤ በርካታ የዓለም ሪከርዶችና ሌሎች የውጤት ክብረወሰኖችን በማስመዝገብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር (አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ) በአሁኑ ወቅት በአትሌቲክስ ስፖርቶች 53 የዓለም ሪከርዶች የተመዘገቡ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቶች ከ9 በላይ የዓለም ሪከርዶችን አስመዝግበዋል፡፡
በትራክ ውድድሮች    በወንዶች ምድብ አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ከመዘገባቸው የአትሌቲክስ የዓለም ሪከርዶች መካከል አራቱ በኢትዮጵያውያን ስም ሲሆን ቀነኒሳ በቀለ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር፤ እንዲሁም ኃይሌ ገብረስላሴ በልዩ ሁኔታ  በ1 ሰዓት ሩጫ እና በ20ሺ ኪሜትር ውድድር ያስመዘግቧቸው ናቸው፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ከመዘገባቸው የአትሌቲክስ የዓለም ሪከርዶች መካከል አምስት ሪከርዶች በኢትዮጵያውያን ስም ሲሆን  በ5ሺ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ ፤ በ10ሺ ሜትር አልማዝ አያና ፤ በ1500 ሜትር ገንዘቤ ዲባባ በ1 ሰዓት ሩጫ ድሬ ቱኔ እንዲሁም በግማሽ ማራቶን ነፃነት ጉደታ ያስመዘገቧቸው ናቸው።  
በዓለም የቤት  ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች በወንዶች ምድብ 3 የዓለም ሪከርዶች በኢትዮጵያውያን የተያዙ ሲሆን ቀነኒሳ በቀለ በ5ሺ ሜትር ፤ ሳሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትርና ዮሚፍ ቀጀልቻ በማይል ሩጫ ናቸው፡፡ በሴቶች ምድብ ያሉ 5 የዓለም ሪከርዶችን ደግሞ  ገንዘቤ ዲባባ የያዘች ሲሆን በ1500 ሜትር ፤በማይል ሩጫ፤ በ2ማይል ሩጫ፤ በ3ሺ ሜትርና በ5ሺ ሜትር ያስመዘገበችው ናቸው፡፡
በዓለም ሻምፒዮና፤ በኦሎምፒክ፤ በዳይመንድ ሊግ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከፍተኛ ተወዳጅነት ባለው የ5ሺ ሜትር የትራክ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች  የዓለም ሪከርዶች በኢትዮጵያውያን የተያዙ ናቸው፡፡  በወንዶች 5ሺ ሜትር  ከ1884 እኤአ ጀምሮ 37 የዓለም ሪከርዶች የተመዘገቡ ሲሆን የሪከርድ ሰዓቶቹን በማሻሻል ሂደት ላይ 5 ኢትዮጵያን አትሌቶች አስተዋፅኦ ነበራቸው። ኃይሌ ገብረስላሴ ከ1994 እስከ 1998 እኤአ ድረስ ለአራት ጊዜያት የ5ሺ ሜትር ሪከርዶችን በተደጋጋሚ በማሻሻል ከፍተኛውን ድርሻ መወጣቱ ይታወሳል፡፡  በ2004 እኤአ ላይ በሆላንድ ሄንግሎ በተካሄደ ውድድር ግን አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ12 ደቂቃ ከ37.35 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ሪከርድ ግን ላለፉት 14 ዓመታት ሳይሰበር ቆይቷል፡፡ ራንኒንግ ዎርልድ በሰራው ጥናታዊ ዘገባ በሰው ልጅ ብቃት በ5ሺ ሜትር ከ14 ዓመታት በኋላ 12 ደቂቃ ከ09.39 እንዲሁም ከ26 ዓመታት በኋላ ደግሞ 11 ደቂቃ ከ56.19  ሰኮንዶች ሪከርዶች ሊመዘገቡ የሚችል ሲሆን በ5ሺ ሜትር በወንዶች ምድብ ሊገባ የሚቻለው የመጨረሻው ፈጣን ሰዓት 11 ደቂቃ ከ11.61 ሰከንዶች  ነው።
በሴቶች 5ሺ ሜትር ከ1922 እኤእ ጀምሮ 27 ጊዜ ሪከርዶች ሲመዘገቡ ከ2004 እኤአ ጀምሮ የተመዘገቡ አራት ክብረወሰኖች በትውልድ ኢትዮጵያዊ በሆኑ አትሌቶች የተሳኩ ናቸው፡፡ በ2004 እኤአ የርቀቱን ክብረወሰን 14 ደቂቃ ከ24.68 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ አስመዝግባ የነበረችው በትውልድ ኢትዮጵያዊ ብትሆንም በዜግነት ለቱርክ የምትሮጠው ኢልቫን አብይ ለገሰ ነበረች፡፡ የኢልቫን አብይ ለገሰን ሪከርድ በ2006 እና በ2007 እኤአ አከታትላ ለመስበር የበቃችው ደግሞ መሰረት ደፋር ናት፡፡ ከእሷ በኋላ ላለፉት 11 ዓመታት ሳይሰበር የቆየውን ሪከርድ በ2007 እኤአ በኖርዌይ ኦስሎ በተካሄደ ውድድር 14 ደቂቃ ከ11.15 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ የያዘችው ጥሩነሽ ዲባባ  ናት፡፡ ራንኒንግ ዎርልድ በሰራው ጥናታዊ ዘገባ በሰው ልጅ ብቃት በ5ሺ ሜትር በሴቶች ሊመዘገብ የሚችለው ሪከርድ  ከ14 ዓመታት በኋላ 13 ደቂቃ ከ41.56 ሰከንዶች ከ26 ዓመታት በኋላ ደግሞ 13 ደቂቃ ከ37.25 ሰኮንዶች ሊሆን የሚችል ሲሆን 12 ደቂቃ ከ33.36 ሰከንዶች የመጨረሻው የሪከርድ ወሰን ነው፡፡
በዓለም ሻምፒዮና፤ በኦሎምፒክና  ከፍተኛ ተወዳጅነት ቢኖረውም በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች በጠፋው 10ሺ ሜትር የትራክ ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ሁለቱም የዓለም ሪከርዶች የኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
በወንዶች  ከ1847 እኤአ ጀምሮ 47 ሪከርዶች ሲመዘገቡ የኢትዮጵያ ሁለት አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ እና ኃይሌ ገብረስላሴ ለአምስት ጊዜያት  የሪከርድ ሰዓቶቹን አሻሽለዋል፡፡  በ2005 እኤአ ላይ ቤልጅዬም ብራሰልስ ላይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ያስመዘገበው 26 ደቂቃ ከ17.53 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በርቀቱ ላለፉት 14 አመታት ተይዞ የቆየውን ሪከርድ  አስመዝግቧል፡፡ በራንኒንግ ዎርልድ ጥናታዊ ዘገባ በሰው ልጅ ብቃት በ10ሺ ሜትር ሊመዘገብ የሚችለው ሪከርድ  ከ14 ዓመታት በኋላ 25 ደቂቃ ከ32.27 ሰኮንዶች ከ26 ዓመታት በኋላ ደግሞ 25 ደቂቃ ከ04.36 ሰከንዶች ሲሆን 23 ደቂቃ ከ36.89 ሰከንዶች የመጨረሻው የሪከርድ ወሰን ነው፡፡ አልማዝ አያና በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪኮርድ ያስመዘገበችው በ2016 እ.ኤ.አ ላይ የብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ ያዘጋጀችው 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ነበር፡፡ ይህ የዓለም ሪኮርድ በኢትዮጵያዊ አትሌት ሊመዘዝ የበቃው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በ29 ደቂቃ ከ17.45 ሰኮንዶች ነው።
በጎዳና ላይ ሩጫዎች ላይ
ሌሎች የኢትዮጵያውያን የዓለም ክብረወሰኖች
በዓለም አትሌቲክስ በብዙ የውድድር መደቦች በብዛት ሪከርዶችን በማስመዝገብ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን የሚስተካከል የለም፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ረጅሙን የሩጫ ዘመን በ21 አመታት የፈፀመው ኃይሌ ከ27 በላይ ሪከርዶችን ከ2 ማይል እስከ ማራቶን ባሉ ርቀቶች አስመዝግቧል፡፡ ከእነዚህ የዓለም ሪከርዶቹ መካከልም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ያገለገለበትን ሁለት ዓመታትን ጨምሮ ሩጫውን ባቆመበት 46ኛ ዓመቱ   በተለይ 3 በላይ የአለም ሪከርዶችን በስሙ እንደተቆጣጠረ ነው።
የመጀመርያው በ20ሺ ሜትር የትራክ ውድድር በ2007 እእእ በቼክ ኦስትራቫ 56 ደቂቃ ከ25.98 ሰከንዶች በማስመዝገብ የያዘው  ሲሆን ሌላው ደግሞ በ10 ማይል የጎዳና ላይ ሩጫ  በ2005 እኤአ በቲበርግ ሆላንድ ውስጥ 44 ደቂቃ ከ23 ሰከንዶች የጨረሰበት ናቸው። በ2007 እኤአ ላይ በቼክ ኦስትራቫ በ1 ሰዓት ውስጥ 21285 ሜትር ርቀት በመሸፈን ሪከርዱ ተመዝግቦለታል። በ8ኪ.ሜ የጐዳና ላይ ሩጫ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ በ2011 እ.ኤ.አ ላይ ደሪባ መርጋ 21.51 በሆኑ ደቂቃዎች ያስመዘገበው ክብረወሰንም አለ፡፡
በሴቶች ምድብ በጎዳና ላይ ሩጫ የሚጠቀሰው ትልቁ የኢትዮጵያዊ ክብረወሰን ነፃነት  ጉደታ በግማሽ ማራቶን በ2018 እኤአ ያስመዘገበችው 1 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ሰከንዶች የሆነ ጊዜ ነው፡፡ በሌላ  በኩል በቼክ ኦስትራቫ በ1 ሰዓት ሩጫ በድሬ ቱኔ የተሸፈነው 18517 ሜትር ርቀት የዓለም ክብረወሰን ሲሆን፤ በማራቶን ሪሌይ -ገነት ገ/ጊዮርጊስ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ አየለች ወርቁ፣ ጌጤነሽ ዋሚ፣ ጌጤነሽ ኡርጌና ሉቺያ ይስሃቅ በዴንማርክ ኮፐንሃገን ተወዳድረው በ2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ04 ሰኮንዶች ያስመዘገቡት ነው፡፡
8ቱ  ሪከርዶች በዓለም የቤት ውስጥ  አትሌቲክስ
በዓለም የቤት ውስጥ  የአትሌቲክስ ውድድሮች በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተመዘገቡት የዓለም ሪከርዶች ብዛታቸው በወንዶች 3 በሴቶች ደግሞ አምስት ደርሷል፡፡ በወንዶች በዓለም የቤት ውስጥ  የአትሌቲክስ የ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ በ2004 እኤአ በእንግሊዝ በርሚንግሃም 12 ደቂቃ ከ49.60 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ በዚሁ  የ5ሺ ሜትር ሪከርድ መሻሻል ሂደት ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ ለሶስት ጊዜ ሰከንዶችን በመሸፈን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በተመሳሳይ በሴቶች የ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ብርሃኔ አደሬ በ2004 እኤአ፤ ጥሩነሽ ዲባባ በ2005ና በ2007 እኤአ  እንዲሁም መሰረት ደፋር በ2009 እኤአ ጀምሮ ካስመዘገቧቸው 4 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሪከርዶች በኋላ አሁን ተመዝግቦ ያለውን ሪከርድ ያስመዘገበችው በ2015 እኤአ ላይ በስዊድን ስቶክሆልም ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ18.86 ሰኮንዶች የጨረሰችው ገንዘቤ ዲባባ  ናት፡፡
 በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮች ሌሎች ሪከርዶች የተመዘገቡት በመካከለኛ ርቀቶች ነው፡፡ ሁለት አዳዲስ ሪከርዶችን በወንዶች ምድብ በቅርቡ ያስመዘገቡት ወጣቶቹ አትሌቶች ሳሙኤል እና ዮሚፍ ናቸው፡፡ ሳሙኤል ተፈራ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ የ1500 ሪከርድን ያስመዘገበው ርቀቱን በ3 ደቂቃ 31.04 ሰኮንዶች በመሸፈን ሲሆን ዮሚፍ ቀጀልቻ ደግሞ በ1 ማይል ሩጫ ርቀቱን በ3 ደቂቃ 47.01 ሰኮንዶች በመሸፈን ነው፡፡ በዓለም የቤት ውስጥ  አትሌቲክስ ሌሎች 4 ክብረወሰኖችን ያስመዘገበችው  ገንዘቤ ዲባባ ስትሆን በማይል በ2016 እኤአ በስዊድን ስቶክሆል 4 ደቂቃ ከ14.31 ሰኮንዶች፤ በ2000 5 ደቂቃ 23.75 ሰኮንዶች በስፔን ሳባዴል በ2018 እኤአ ፤ የ3ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን 8 ደቂቃ ከ16.60 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ከማስመዝገቧም በላይ በካርሉስርህ ጀርመን በተካሄደ የ1500 ሜትር ውድድር ደግሞ ርቀቱን በ3 ደቂቃ ከ55.17 ሰከንዶች የሆነ የሪከርድ ጊዜ አስመዝግባ ነው፡፡
3 የዓለም ሻምፒዮና እና 4 የኦሎምፒክ ሪከርዶች በኢትዮጵያውያን
በዓለም አትሌቲክስ  ሻምፒዮና ላይ በወንዶች ምድብ   ኬንያውያን በ800፤ በ3ሺ መሰናክል፤ በ5ሺ ሜትር እና በማራቶን ያሉ ሪከርዶችን በመቆጣጠር ከኢትዮጵያውያን ይልቃሉ፡፡ በወንዶች ምድብ  በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ  ሪከርድ ይዞ የሚገኝ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን በ2009 እኤአ በርሊን ላይ ርቀቱን በ26 ደቂቃ ከ46.31 ሰኮንዶች 10ሺ ሜትርን በመሸፈን ያስመዘገበው ጊዜ ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ   በሴቶች ምድብ ከተመዘገቡ ሪከርዶች የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለት ውድድሮች ሲጠቀሱ አንዲትም ኬንያዊ አትሌት የለችበትም፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ5ሺ ሜትር ሴቶች 14 ደቂቃ ከ38.59 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜን  ሄልሲንኪ ላይ በ2005 እኤአ  እንዲሁም በ2003 እኤአ ፓሪስ ላይ ብርሃኔ አደሬ በ10ሺ ሜትር 30 ደቂቃ ከ04.18 ሰኮንዶች በሪከርድ እንደተመዘገበላቸው ነው፡፡
በኦሎምፒክ መድረክ በወንዶች  በ5ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር ሁለት ክብረወሰኖችን የያዘው  ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ሁለቱንም የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች እኤአ በ2008 በቤጂንግ በተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ሲያስመዘገባቸው በ5 ሺ ሜትር 12 ደቂቃ ከ57.82 ሰኮንዶች እንዲሁም በ10ሺ ሜትር 27 ደቂቃ ከ04.7 ሰኮንዶች የሰፈሩ ናቸው፡፡ ኬንያውያን በ800፤ በ1500፤ በ3ሺ መሰናክልና በማራቶን የተያዙ የኦሎምፒክ ሪከርዶችን በመቆናጠጥ የተሻለ ውክልና አላቸው። በኦሎምፒክ መድረክ በሴቶች ምድብ በተመዘገቡ ሪከርዶች ኢትዮጵያ በሁለት አትሌቶች ስትጠቀስ ኬንያ ግን አንድም አላስመዘገበችም። በኢትዮጵያውያን የተያዙት ሁለት የረጅም ርቀት የኦሎምፒክ ሪከርዶች በ2016 እእአ ላይ በሪዩዲጄኔሮ ኦሎምፒክ አትሌት አልማዝ አያና በ10ሺ ሜትር  29 ደቂቃ ከ17.45 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችውና በ2012 እኤአ ላይ በለንደን በተካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ ቲኪ ገላና በማራቶን ስታሸንፍ ርቀቱን የሸፈነችበት 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ07 ሰኮንዶች ናቸው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች ሪከርዶች እና መጨረሻቸው
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ዙርያ በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ጥናቶች የሚያመለክቱት ከ100 ሜትር እስከ ማራቶን ርቀቶች በየጊዜው የሚመዘገቡ የተለያዩ የሰዓት ሪከርዶችን የሚያሳኩት አትሌቶች ከተወሰኑ አገራት የሚገኙ ናቸው፡፡ በተለይ በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫዎች የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶችን  የውጤት የበላይነትና የሪከርድ ባለቤትነትን ላለፉት 20 አመታት የሚቀናቀን ጠፍቷል፡፡ በአጭር ርቀት ውድድሮች ደግሞ የጃማይካ እና የአሜሪካ አትሌቶችን ስኬት የሚስተካከል አልተገኘም።  ከላይ ከተጠቀሱት አራት  አገራት የሚወጡ አትሌቶች በአትሌቲክስ ውድድሮች ያስመዘገቧቸው ሪኮርዶችን የማሻሻሉ እድል በየዓመቱ በ0.5 በመቶ መወሰኑን ስፖርትሳይንቲስትስ የተባለ ድረገፅ በሰራው ትንታኔ አመልክቷል፡፡  የላቀ ብቃት፤ የላቀ ፍጥነት እና የላቀ ጥንካሬ በሚለው የኦሎምፒክ መርህ  መሰረት የእነዚህ 4 አገራት ምርጥ አትሌቶች ጉዛቸውን ቀጥለዋል። ሆኖም ግን በአትሌቲክስ ስፖርት በሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ብቃት ሊሳካ የሚችለውን የሪከርድ አቅም 99 በመቶ አሟጥጠውታል የሚል ድምዳሜን የስፖርትሳይንቲስት ባለሙያዎች በጥናታቸው አረጋግጠዋል፡፡
በስፖርቱ አለም ከሚከናወኑ 147 አይነት የስፖርት  ውድድሮች የሚመዘገቡ የተለያዩ ሪከርዶችና ክብረወሰኖች በሰው ልጅ ብቃት የሚደርሱበት መጨረሻ በ2027 እኤአ  እንደሚደረስ አይኤንኤስኢፒ የተባለ እና በፓሪስ ተቀማጭ የሆነ የስፖርት ኢንስቲትዩት በሰራው ጥናት አረጋግጧል።  በአሁኑ ወቅት በስፖርቱ አለም በተለይ በአትሌቲክስ ውድድሮች ሪከርዶችን ለማስመዝገብ እጅግ ወሳኝ ከሆነው ተፈጥሯዊ ክህሎት ባሻገር፤ ለፍጥነት የሚመደቡ አሯሯጮች፤ በቴክኖሎጂ የታገዙ የመሮጫ ጫማዎች፤ ዘመናዊ ህክምናዎች እና መድሃኒቶች፤ እጅግዘመናዊ የስልጠና፤ የአመጋገብ እና የስነልቦና ዝግጅቶች እንዲሁም በስኬት  የሚገኝ ገቢ አስፈላጊ ይሆናሉ፡፡
በዘመናችን በህክምና ረገድ ያሉ አገልግሎቶች እና መድሃኒቶች አትሌቶች ለረጅም ጊዜ እየተወዳደሩ በመቆየት ካላቸው ልምድ ሪከርዶችን የመስበር እድላቸውን ከማስፋቱም በላይ፤ ከጉዳቶች ሙሉ ለሙሉ ለመዳንና ለማገገም በሚኖራቸው እገዛ ስፖርተኞች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ጂን ቴራፒ አይነት ዘመናዊ ህክምናዎች ስፖርተኞች በጡንቻዎቻቸው አላግባብ ጉልበት የሚያፈሱበትን ሁኔታ እና ድክመታቸውን በመፈወስ ብቃታቸውን እንደሚያግዝ ታኖበት በስፋት የተሰራበት ነው፡፡ በአጠቃላይ የአትሌቶች ብቃት እያደገ ሲቀጥል፤ የቴክኖሎጂ እና የሳይንስ ድጋፍ እየመጠቀ ሲሄድ በርካታ የአትሌቲክስ ሪከርዶች እየተሻሻሉ መሄዳቸው አይቀርም ግን መጨረሻዎች የተቃረቡ ይመስላሉ። በተለይ በሩጫ ስፖርት በዓለም አትሌቲክስ ላይ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ  የወርቅ ሜዳልያዎችን ከማግኘት በላቀ ሁኔታ እንደከፍተኛ ስኬት የሚቆጠረው ሪከርዶችን ማስመዝገብ ነው፡፡ ለምን ቢባል  የየትኛውንም የአትሌቲክስ ውድድር ሪከርድ ማስመዝገብ በውድድር አይነቱ ያለተቀናቃኝ የበላይነት መያዝ መቻሉን የሚያረጋግጥ ስኬት በመሆኑ ነው፡፡
ሪከርዶች የሩጫ ውድድሮችን የፉክክር ደረጃ ከማሳደጋቸውም በላይ ለተመልካቾች የማይረሳ ልዩ ስሜት በመፍጠርና የስፖርቱን ተወዳጅነት በመጨመር አስተዋፅኦ አላቸው፡፡  ሪከርድ የሚያስመዘገቡ አትሌቶች በተለያዩ የውድድር የቦነስ ሽልማቶች ይጠቀማሉ፡፡ የትጥቅ እና የመሮጫ ጫማዎችን በሚያቀርቡላቸው ስፖንሰሮች ተጨማሪ ክፍያ እና የገቢ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚካሄዱ ውድድሮች በቀጥታ ተጋባዥ የሚሆኑበትንም እድል ያገኛሉ፡፡

Read 9799 times