Saturday, 26 May 2012 13:07

መራሄ ትውልድ ስለሺ ደምሴን

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(3 votes)

መራሄ ትውልድ (የትውልድ መሪ)፤ ሃሳበ ትጉህ፤ በአውሮጳና በአሜሪካ  በኦፊሴል ያለተሾመ የአገሩ የኢትዮጵያ የባህል አምባሣደር ነው ስለሺ ደምሤ፡፡ በሙዚቃ ጥበብ የተካነ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ባህልና ማንነት የተቀረፀ የታነፀ፤ ለማንጐራጐር ብቻ ሣይሆን ለሌሎች የታላቅ ሰብዕና መታያ ባህሪያት የተሰጠ የጥዑም ልሣን ባለቤት …ሥልጡንና ጠንካራ፤ ብርቱ ጥብቅ ሰው ነው ስለሺ ደምሴ፡፡ የጥንት አባቶቹ እና ወላጆቹን በጐና ጠቃሚ ያማሩ እሴቶችን ብቻ ሳይሆን የማይረሣ የማይረሳሳ፤ የሚያከብር የሚያበለጽግ፤ ስለመጪው ብቁ ኢትዮጵያዊ ትውልድ አካላዊ አእምሮአዊና መንፈሳዊ ጥንካሬና ሥልጣኔ (ምልዓት) በማሠላሠል የሚተጋ፤ የማይተኛ የማያንቀላፋ ባለራዕይ ትውልድ ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀው…ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሠብዕና ነው ስለሺ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሪ ጄኔራሎች አንዱ የሆነው ደራሲና ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ፤ ለኢትዮጵያዊው ገጣሚ ዮፍታሔ ንጉሴ “ተወርዋሪው ኮከብ” የሚል ግጥም ጽፎአል፡፡ ግጥሙ  ዮሐንስ አድማሱ ካለፈ ካረፈ በኋላ “እስከ ተጠየቁ” በሚል የግጥም መድብል ታትሞአል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ዲፓርትመንት ምሁር “ ተመራማሪና  መምህር፤ ሊቀ ጽሑፍና ገጣሚ የሆነው ዶክተር ፈቃደ አዘዘ “ተወርዋሪው ኮከብ” ነው ያለው በአንድ ጥበባዊ የሊቃውንት ጉባኤ ላይ፤ ስለሺ ደምሴን፡፡ “ተወርዋሪው ኮከብ” በአጭሩ ሲቀነጨብ ሲቆነጠር እንዲህ ይላል:-

በራሱ ነበልባል

በራሱ ነዲድ

ተቃጥሎ የጠፋ

ተወርዋሪው  ኮከብ

በምናውቀው ሰማይ

ነበረ በይፋ

በተለምዶ መስቀል አደባባይ እያልን እምንጠራው አደባባይ ጋ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አለ፡፡ ከቤተክርስቲያኑ ግቢ አጠገብ ዓመቱን ሙሉ በለምለም ሣር ጢም ግጥም ያለና አልፎ አልፎ ዛፎች የተተከሉበት የፀዳ አፀድ አለ፡፡ በዚያ የፀዳ አፀድ በሚገኝበት ሥፍራ ባለፍኩ ባገደምኩ ቁጥር የተቀለበና በእንክብካቤ የተያዘ ሠንጋ ፈረስ አያለሁ፡፡ ይሄ ሠንጋ ፈረስ የማነው ብዬ ብጠይቅ፤ የስለሺ ደምሴ ነው…አሉኝ፡፡ ብዙዎች በሚያውቁት መጠሪያ ሥሙ ደግሞ የጋሼ አበራ ሞላ ነው…ብለውኛል ወዳጆች፡፡ “ጋሼ አበራ ሞላ” ከስለሺ ደምሴ ውብ ዜማዎች መሀከል የአንደኛው መነሻ የሆነ፤ ከጥበብና ከጉብል ድብን ያለ ፍቅር የያዘው አስገራሚ ጠቢብ ሰብዕና ነው፡፡ “ጋሼ አበራ ሞላ ጋሼ አበራ ሞላ አበደ ይሉሃል ጉዳይህ ሳይሞላ” የዜማው አንድ ሰበዝ ሲሆን፤ በግሌ በብዙ ምክንያቶች ስለሺ ደምሴን ጋሼ አበራ ሞላ ብዬ አልጠራውም፡፡

ስለሺ ደምሴ አሜሪካን አገር ራዲዮ ጣቢያ ላለው ስመ ጥሩው አሜሪካዊ ዘፋኝ ስቲቪ ወንደር በስጦታ ያበረከተለት ራሱ በእጁ የሠራው የኢትዮጵያን ባህላዊ ዝነኛ የሙዚቃ መሣሪያ የሆነውን ክራር ነው፡፡

ስለሺ ስቲቪ ወንደር ራዲዮ ጣቢያ ይገኝና ስለ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ባህልና ማንነት ለውሱን ደቂቃዎች ያንጐራጉራል፤ የፈቀደለት እንደ ብዙዎች አፍሪካን አሜሪካን ሁሉ የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ የሆነው አሜካዊው ዓለምአቀፍ አቀንቃኝ ስቲቭ ወንደር ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ውበትና እውነት፤ ስለ ጥበብና ኪነት ክራሩን የማነጋገር ያህል እያጫወተ ይጫወታል፡፡ የስለሺ ደምሴ ዜማዎች ሥረ መሠረት ከኢትዮጵያ በቀር የትም ሌላ ቦታ የሚገኙ አይመስለኝም፡፡

ምክንያቱስ? ቢሉ በአብዛኛው ዜማዎቹ ከኢትዮጵያውያን አባቶችና ወላጆች ባህላዊ ሥረ መሰረት የተመዘዙ ውብና ህያው ማህበራዊ እሴቶች፤ ለሺህ ዘመናት የዘለቁ የህዝቡ አንጡራ ሀብቶች ናቸው፡፡

ስለ ዓባይ ወንዛችን በስለሺ ደምሴ መጠን አግንኖ አሳምሮ የተጫወተ (ያዜመ) ሌላ ዘፋኝ ማንንም አላቅም፡፡ በዓለም ረጅም የሆነው አባይ ወንዛችን ዋነኛ መነሻ ከጣና ሀይቅ ማዶ ያለ የኢትዮáያ የምድር ማህፀን ነው፡፡ ስለዚህ ነው “የአገሬ ገበሬ ዓባይ በጣና ላይ ሄደ ተንጐማሎ አንተም ውሃ እኔም ውሃ” ብሎ ያለው፡፡ አያችሁት ጐበዝ ይሄን ነገር መውደድ ዓባይ በጣና ላይ ይፈልጋል መንገድ…

በወጣት መዘምራን ታጅቦ፣ ስለሺ ደምሴ ክራሩን አንስቶ ዓባይ ተፀነሰ …ይለናል፤

ዓባይ ተፀነሰ ከሰሜን ተራራ

አልወለድ ብሎ በአሣር በመከራ

እናቱ ደጀን አባቱ ጣና

የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና፤

የዓባይ ወንዝ ዳር ዳሩ ጥጥ እያበቀለ

እናቱም በቀለች ልጇ ቢያበቅል

ከጣና ከናቱ እንደ ምሥራቅ ጮራ

ተፍለቅልቆ በራ

ተፍለቅልቆ በራ፤

ኧረ ዓባይ

እንዴት እሆናለሁ እኔ አንተን ሳላይ፤

ጐንደር ግንባሩ ነው

ወሎ ትከሻው፤

ተከዜ እጁ ነው

ዘር መጨበጫው፤

ሸበሌ እግሩ ነው

መረማመጃው፤

አዋሽ እትብቱ

የልጅ እንብርቱ፤

ወገቡ ዓባይ ነው

መነቃቂያው፤

አራት እጥፍ ጥምጥም የጠቀለለው

ቢዞር ቢፈታው ከቶ እማያልቀው

ደጀን ተነስቶ ካይሮ እሚደርሰው

ሱዳን በረሃን የሚጫወተው

ሎሬሄ መንደር ቁርስ እሚጐርሰው

ካይሮ ገብቶ የተንጣለለው፤

ዓባይ

….

በ811 ዓ.ም ልክ የዛሬ 193 ዓመት ዓፄ ቴዎድሮስ (አባ ታጠቅ ካሣ) … ጐንደር ውስጥ ሻርጌ እተሰኘ አካባቢ ሲወለድ፤ በዚያው ዓመት ወሎ ውስጥ የተወለዱት ሼህ ሁሴን ጅብሪል ዓባይ ወንዛችን በስምንተኛው የኢትዮጵያ መሪ እንደሚገደብ በአፈቃል ትንቢታቸው ግልፅ አድርገው ነበር፡፡ በዛሬው ዘመን አንድ የሼህ ሁሴን ጅብሪልን ትንቢቶች በመጽሐፍ እንዲታተሙ አድርገዋል፡፡

ስለሺ ደምሴ ከባህር ማዶ ወደ አገሩ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ከነደፋቸው በጐ መርሀ ግብሮች - Clean & Green Addis (አዲስ አበባን ንፁህና አረንጓዴ) ማድረግ የሚለው ይወሳል፡፡ የመርሀ ግብሩ ዓላማ በወጣቶች ተሳትፎ በመታገዝ፤ አዲስ አበባንና ሌሎች የኢትዮጵያውያን ከተሞች ንፁህ ማድረግና ማሳመር፤ በዛፎችና በአበቦች ማስዋብ ነው፤ እንዲሁም በከተሞች ውስጥ የሚገኙትን ወንዞችና ሌሎች ተፈጥሮዎች ማጽዳትና ማሳመር፤ መንከባከብና ማበልፀግ ነው፡፡

በአሥር ሺህ የሚሠሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ይዞ ለዚህ መርሃ ግብር ክንዋኔ የተንቀሳቀሰው ስለሺ ደምሤ፤ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ከፍ ከፍ ባሉ የኢትዮጵያ ከተሞች ተሳክቶለታል፡፡ ይህን መርሃ ግብር ለመከወን በመሰናዳት ላይ እያለ ስንወያይ ወደፊት በቆሻሻ ብዛት የምትጠፋ ከተማ ብትኖር አዲስ አበባ ናት አለኝ፡፡ አዲስ አበባን ንፁህና አረንጓዴ የማድረግ Clean & Green Addis ፕሮጀክት እንዲህ ተጀመረና፤ ራዕይና ሥፍራውን ወደ ሌሎችም ጠቃሚ ግብሮችና ሥፍራዎች (ኢትዮጵያዊ ከተሞች) አሠፋ አሥፋፋ፡፡ በዚህ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች፤ በዚያውም በሙዚቃ እውቀት በግጥም ጥበብ ልብና አእምሮአቸውን እንዲያሳድጉ አደረገ፡፡

በዚህ ውስጥ ትውልድን የማረቅ (Trained የማድረግ) የማነጽና የማጐልበት ሥራም አለ፡፡

የስለሺ ዘፈኖች ኢትዮጵያዊ ልጅነታችንን በማሳደግ ውስጥም አሉ፡፡ ለምሣሌ መሰቦ ወርቄ…ሊወሳ ይችላል፡፡

መሠበ ወርቄ ተሽከረከረች

ዓባይን ዞራ በደም ተነከረች

የጐበዝ ልቡ ተራራ ነው

ተራራ ነው

አህያ ሞቶ ጅብ ሲያለቅስ

እቴሜቴ የሎሚ ሽታ ያ ሰውዬ ምናለሽ ማታ…የሚለው ከስለሺ ደምሤ ዘፈኖች አንዱ ነው፡፡ “ተስፋዬ…” የሚል በጽኑዕ መንፈስ የተኳለ ይዘት ያለው ዘፈን አለው፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ለህዝብና ለአፍቃሪዎቹ ይፋ የሚሆን የሙዚቃ አልበም ማሰናዳቱን ሰምቻለሁ፡፡

ስለሺ ደምሤ እጅግ በብዙው በልዩ አድናቆትና ክብር ከማያቸው ጥቂት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን መሀከል አንዱ ነው፡፡ ይሄ ጽሑፍ ለስለሺ ደምሤ ታላቅ ሰብዕና ክብርና አድናቆት መግለጽ ቢችል እነሆ፡፡

ሠላምዎ ይብዛ በፍቅር!

Soli- Deo.Gloria!

 

 

Read 4436 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 13:14