Saturday, 30 March 2019 13:09

ከዋልያዎቹ አንዱ ሞገስ ታደሰ ድጋፍ ይጠይቃል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

   ስም ፡ ወ/ሮ ሠርክዓለም አለባቸው ቦጋለ
              በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ፡ 1000247375418


          የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ሞገስ ታደሰ የገጠመው ህመም በይፋ ከታወቀ በኋላ ቤቱ ድረስ በአካል ተገኝተው የሚጠይቁትና የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጡት መበራከታቸውን ገለፀ፡፡ ሰሞኑን የአጥንትና ሌሎች ምርመራዎችን ማድረጉን ለስፖርት አድማስ የገለፀው ሞገስ የህክምና ውጤቱን ለሃኪሞች አቅርቦ እነሱ ያለበትን ሁኔታ ገምግመው ህክምናውን የት ማግኘት እንዳለበት ፤ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድበትና ምን ያህል ብር እንደሚያስፈልገው ውሳኔ ይሰጣሉ ብሏል፡፡ ህክምናውን የሚያገኝበትን አገር ለመወሰን እየተሰራ መሆኑን የገለፀው ሞገስ፤ በህንድ፤ ታይላንድ፤ ደቡብ አፍሪካ እና በተለያዩ አውሮፓ አገራት ያሉ የህክምና ተቋማትን ለማግኘት እየተሞከረ ነው፡፡
ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጎልተው  ከወጡ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው    ሞገስ ታደሰ ፤ በክለብ ደረጃ በቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣቶች ቡድን ጅማሮውን ካደረገ በኋላ በሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዲያ ተጫውቷል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነትም በሴካፋ፤ በቻን ውድድር እና በአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በተለይ ደግሞ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ውጤታማ የዋልያዎች ስብስብ ቡድን ውስጥም መካተት ችሎ ነበር።
ሞገስ ታደሰ ካለፈው የውድድር ዘመን መጨረሻ  አንስቶ በገጠመው ህመም  በመኖርያ ቤቱ፤ ከቤተሰቡና የቅርብ ጓደኞቹ አስቸጋሪ ግዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ በአዳማ ከተማ የባጃጅ አደጋ ከደረሰበት በኋላ በግራ እጁ ላይ የቀዶ ጥገናን አድርጓል፡፡  ከዚህ አደጋው ካገገመ በኋላ በኤሌክትሪክ ሲጫወት የነበረ ሲሆን ባለፈው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ወደ ወልዲያ ክለብ ተዛውሮ ህመሙን በመታገል ሲጫወት ቆይቷል። ይሁንና ህመሙ እየተባባሰ በመሄዱ ላለፉት አስር ወራት በእጆቹ እና እግሮቹ እክሎች ተፈጥረው ከሜዳ ለመራቅ ግድ ሆኖበታል፡፡  አሁን ደግሞ የነርቭ ሞተሩ በመጎዳቱ ከቤቱ መውጣት  ያቃተው ሲሆን እጁ ላይ የጀመረው በሽታ እንደልብ እንዳይንቀሳቀስ እያደረገው ነው፡፡
ሞገስ ታደሰ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው የሚያስፈልገውን አስቸኳይ ህክምና አጠቃላይ ሂደት ለመከታተልና ድጋፉንም ለማስተባበር 16 ሰዎች ያሉበት ኮሚቴ  የተቋቋመ ሲሆን፤ ከእግር ኳስ ተጨዋቾች አሉላ ግርማና ኤፍሬም ወንደሰን እንዲሁም ጎረቤቶቹ እና በሰፈሩ የሚገኙ ትልልቅ ሰዎች እንደሚገኙበት ተናግሯል፡፡ በገንዘብ አሰባሰብ ችግር እንዳይፈጠር ኮሚቴው እንደሚሰራ እምነቴ ነው ያለው ሞገስ፤ በወላጅ እናቱ ወ/ሮ ሠርክዓለም አለባቸው ቦጋለ ስም የሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ለሚደግፉት ሁሉ መዘጋጀቱን አመልክቷል። ድጋፍ ለመስጠት የሚፈልጉ ሁሉ  ገንዘቡን ሲያስገቡ የተመዘገበበትን ስም እንዲያረጋግጡ እና ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ተጠይቋል።

Read 12144 times