Saturday, 30 March 2019 13:17

የስነተዋልዶ አካላት ሕመም ምክንያቶች

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)


            የስነተዋልዶ አካላት ሲባል በሴቶች በኩል ማህጸንና ከማህጸን ጋር ተያያዥነት ያላቸው አካላት፤እንዲሁም ከማህጸን አጎራባች ሆነው የሚገኙትን አካላት እንደ ሽንት ፊኛ የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡ እነዚህ አካላት በተለያዩ ምክንያቶች ሕመም ይገጥማቸዋል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለዚህ አምድ እንዲገልጹ የተጋበዙት ዶ/ር መብራቱ ጀምበር ይባላሉ፡፡ ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት በአሁኑ ወቅት የሚሰሩት በብራስ የእናቶችና የህጻናት የህክምና ማእከል ነው፡፡
ዶ/ር መብራቱ እንዳሉት በማህጸን ዙሪያ የጤና ችግሮችን ሊያመጡ የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በተለይ ግን በእርግዝና ሰአት ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ እና በሌላም በኩል እርግዝናው እራሱ እንዳይኖር ማድረግ የሚችሉ አንዳንድ እውነታዎች አሉ፡፡ ከዚህም ጋር ተያያዥ በሆነ መንገድ የግብረስጋ ግንኙነትን ፍላጎት ሊያዛቡ የሚችሉ የጤና እውክታዎች እንደሚከተለው ይገለጻሉ፡፡
በኢንፌክሽን ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ ወይንም ኢንፌክሽን ሳይኖርም ከማህጸን ተፈጥሮ ውጪ በሆነ መንገድ ማህጸን ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አንዳንድ ችግሮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ በኢንፌከሽን ወይንም በቁስለት ዙሪያ ያሉትን ስንመለከት የአባላዘር በሽታ በሚባሉት ምክ ንያቶች የማህጸን አካባቢን ሊያቆስሉ የሚችሉ ሕመሞች አሉ፡፡  እነዚህም በተለምዶ በአማር ኛው ቂጥኝ፤ ጨብጥ፤ ውርዴ…ወዘተ በመባል ይታወቁ የነበሩት (Syphilis gonorrhea trichomoniasis fungal elements) ከህመም አምጪዎቹ መካከል የሚጠቆሙ ናቸው፡፡ ፈንገስ የሚባለው ከማህጸን በብልት በኩል አድርጎ የሚፈስ ነጭ ፈሳሽ ይኖረዋል ፤ያሳክካል፤እንዲሁም ደግሞ የሚፈረፈር ፈሳሽ ይኖረዋል፡፡ ይህ ሕመም በጊዜው ሕክምና ካላገኘ መጀመሪያ ነጭ ፈሳሽ ይሆንና እየዋለ እያደረ ደግሞ ፈሳሹ ወደአረንጉዋዴነት ይለወጣል፡፡ እንዲሁም ጠረኑም እየተበላሽ ይመጣል፡፡ ሌላው ጎኖሪያ የሚባለው ደግሞ እንደመግል የመሰለ ፈሳሽ የሚኖረው ሕመም ነው፡፡ ከእነዚህ ሕመሞች መካከል ውርዴ የተሰኘው ቀደም ባሉት ዘመናት እንደ ሕመም ሳይሆን እንደጥሩ ነገር የሚቆጠርና ውርዴ አውጥቻለሁ በማለት ታማሚው የሚገል ጽበት አጋጣሚ የነበረ መሆኔን ብዙዎች አይረሱትም፡፡ ግን ድሮ እንደሚገለጸው ሳይሆን ውርዴ መጥፎ ከሚባሉት የአባላዘር በሽታዎች አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ጤናን ከማወክ ባሻገር እርግዝና እንዳይኖርም ተጽእኖ ያደርጋሉ፡፡
Tuberculosis ሌላው የማህጸን Genital TV በመባል የሚታወቅ አስከፊ ሕመም ነው፡፡ ይህ ሕመም በማህጸን ላይ ቁስለትን ከማምጣት ባሻገር እርግዝና እንዳይኖርም ያደርጋል፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት ነገሮች መምጫ መንገዳቸው ከታወቀ ለመከላከል ይቻላል። ሕክምናውም በቀላሉ ሊደረግ የሚችል ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ከተለመደው አይነት ውጭ ፈሳሽ ሲኖር ወይንም ጠረን ሲቀየር ወይንም በግንኙነት ጊዜ ከማዝናናቱ ውጪ በተቃራኒው ሕመም ካለው ችግር መኖሩን ተረድቶ ወደሕክምናው መሄድ ጥሩ ነው፡፡
ዶ/ር መብራቱ እንዳሉት ከላይ የተገለጹት ከኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ደግሞ በማህጸን ላይ ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ የሚከሰቱ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚያም በማህጸን በዋናው አከል ላይ ወይንም በዘር ማስተላለፊያው ቱቦ ላይ ወይም በዘር ፍሬው ላይ የሚገኙ የተለያዩ የጤና ችግሮች አሉ፡፡
ዋናው ማህጸን ላይ አብዛኛውን ጊዜ ፋይብሮይድ ወይንም ደግሞ ማዮማ የሚባለው ይከሰታል፡፡
ኢንፌክሽኑ በዘር ማስተላለፊያው ቱቦ ላይ እብጠት እንዲኖር ወይንም እንዲዘጋ አለዚያም ውሀ እንዲቋጥርና መግል እንዲይዝ ያደርጋል፡፡
እንቁላሉ ላይ ውሀ የቋጠረ ሲስት የሚባል ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ሲስት ማለት በቀላሉ ወይንም በትንንሹ ውሀ የቋጠረ ከረጢት ወይንም የተለያዩ ከረጢቶች ያሉት አንድ ከረጢት ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ከውሁድ ጋር የተያያዘና በውሁድ መዛባት ምክንያት ሊመጣ የሚችለው Polycystic Ovary የተባለው ችግር ጭምር እርግዝና እንዳይኖር ሊያደርግ  ይችላል፡፡ በእርግጥ ሕክምና ያለው ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ሕክምናው ቢደረግም መዳን ስለሚያቅተው ረዘም ያለ የህክምና እርዳታ እንዲደረግ ያስፈልጋል፡፡  
እንደነዚህ ያሉት ነገሮች ቁስለት ስለሚያስከትሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ሕመም ከመሰማቱ ባሻገር እርግዝና እንዳይኖር እንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡  
የስነተዋልዶ አካላትን ጤና መጉዋደል በሚመለከት የመኖሪያ አካባቢም አንዱ ተጽእኖ ሊያደርስ የሚችል ነገር ነው፡፡ ለምሳሌም በከተሞች አካባቢ ከተለያዩ እንዱስትሪዎች የሚወጡ የተቃጠሉ ጭሶች፤ የመኪና ጭስ፤ የሚቃጠሉ ነገሮች ጭስ፤እንዲሁም ፕላስቲክ መጠቀሚያዎች መብ ዛት፤ የመሳሰሉት ሁሉ ለስነተዋልዶ ጤና መጉዋደል ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ከፕላስቲክ መጠቀሚያ ዎች የሚወጡ ኬሚካሎች ከምግብ ጋርም ይሁን ከመጠጥ ጋር አብረው ወደ ሰውነት ውስጥ ስለሚገቡ የካንሰር አጋላጮች ናቸው ከመባሉም በተጨማሪ እርግዝና ላይ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ናቸው፡፡
ሌላው ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ መንገድ የሚፈጠር ችግር ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ለመኖር ምቹ ናቸው ተብለው የሚለመዱ የተለያዩ  ነገሮች ለበሽታ አጋላጭ እንደሚሆኑ እሙን ነው። ከሰውነት አለልክ መወፈር ወይንም አለልክ መቅጠን ወይንም በተለያዩ ምክንያቶች ለኢንፌክሽን ከመጋለጥ በተጨማሪ የምንወስዳቸው ምግብና መጠጥ አይነቶች ከማህጸን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ባይመስሉም ግን ልጅ ከማርገዝና ከመውለድ ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህም፤-
ሲጋራ ማጤስ
ከልክ በላይ አልኮሆል መጠጣት
ጭንቀት
በቂ የሆነ ምግብ አለመመገብ
ከአግባብ ውጭ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ምክንያት ልጅ ማርገዝ እንዳይቻል ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ይስተዋላሉ፡፡
ኢንዶሜትሪያሲስ የሚባለው የስነተዋልዶ አካል ጤና ችግር ከሚፈጠርባቸው ሁኔታዎች አንዱ ነው፡፡
ዶ/ር መብራቱ አክለው እንዳብራሩት ይህ ኢንዶሜትሪየም የሚባለው የማህጸን ግድግዳ ነው፡፡ ኢንዶሜትሪያል ሴልስ የሚባሉት ደግሞ በተፈጥሮአቸው መኖር ያለባቸው ስፍራ ማህጸን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሴሎች ከተፈጥሮአዊ ቦታዎች ማለትም ከማህጸን ውጭ መኖር ይችላሉ፡፡ ከማህጸን ውጭ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ላይ፤ እንቁላሉ ላይ ፤ አንጀት አካባቢ ፤እንዲሁም ጭንቅላት ድረስ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ሊኖር የሚችል በመሆኑ የወር አበባ በመጣ ቁጥር በተደጋጋሚ በመቁሰል ጠባሳ እየፈጠረ ይሄዳል፡፡ ጠባሳ እየፈጠረ ሲሄድ ደግሞ ቋሚ የሆነ ሕመም ይፈጠራል፡፡ ስለሆነም የግንኙነት ስሜትን ይቀንሳል፡፡ እርግዝናም እንዳይኖር ያደርጋል ብለዋል ዶ/ር መብራቱ ጀምበር ፡፡ ባጠቃላይ ግን ሴቶች ማንኛውንም አይነት ሕመም ሳይንቁ በጊዜ ወደሕክምና መሄድ እንደሚጠበቅባቸውም መክረዋል፡፡

Read 13413 times