Saturday, 13 April 2019 13:21

ምንኛ ታድሏል የሰነፍ አዕምሮ እንኳን መማር ቀርቶ ፊደል ሳያጠና ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋልና … አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ

Written by 
Rate this item
(13 votes)


         ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ገጠር ሀብታም፣ በአንድ ትንሽ ከተማ ይኖር ነበረ፡፡ ይህ ሀብታም ሶስት ልጆች ነበሩት፡፡ አንደኛው መስማት የማይችልና ጆሮው የደነቆረ ልጅ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ መናገር የተሳነው ዲዳ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ማየት የተሳነው ዓይነ ስውር ነው፡፡ አባትየው ተጨንቆ ተጠቦና አውጥቶ አውርዶ፤ ከአንድ ጠቢብ ጋር ሊማከር ወደ ሩቅ ሃገር ሄደ፡፡ ለጠቢቡም፤
“ሶስት ልጆች አሉኝ፡፡ ነገር ግን ሶስቱም አንድ አንድ ችግር አለባቸው፡፡
አንደኛው - አይሰማም፡፡
ሁለተኛው - አይናገርም
ሶስተኛው - አያይም፡፡
ምን ባደርግ ይሻለኝ ይመስልሃል?”
ጠቢቡም እንዲህ ሲል መለሰለት፤
“ለማይሰማው ጽሑፍ አስተምረው፡፡
ለማያየው የዳሰሳ ሰሌዳ (ብሬል) አስተምረው፡፡
ለማይናገረው የምልክት ቋንቋ አስተምረው፡፡”
ሀብታሙ ሰውም ጠቢቡ የመከረውን ለማድረግ የፅሁፍ አስተማሪ፣ የብሬል አስተማሪና ብሬል፣ የምልከት ቋንቋ አዋቂ መቅጠር ነበረበት፡፡ ይህን የሚያስደርግ በቂ ገንዘብ ግን አልነበረውም፡፡ ስለዚህ ሰው ቤት ተቀጠረ፡፡ “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” እንዲሉ፣ ቀጣሪው ሰው እጅግ ክፉ ነበረና ሱሪ ባንገት የሚያስወልቀው ዓይነት ሆነ፡፡
“እንደምን አደርክ?” ይለዋል፡፡
“ይመስገነው፡፡ በጣም ጥሩ እንቅልፍ ነበረኝ፡፡”
“አንተማ ምን ታረግ? የሥራውን ጭንቀት ለእኛ ጥለህ ለጥ ብለህ ትተኛለህ”
“ምን ማድረግ ነበረብኝ ጌታዬ?”
“አለመተኛት፡፡ ከእኔ ጋር መጨነቅ፡፡”
“እሱንማ አልችልም”
“ያ እኮ ነው ችግሩ፡፡ ለልጆችህ ገንዘብ ለማጠራቀም ጊዜ ግን ትችላለህ”
“ያዘዙኝን ሁሉ‘ኮ እየፈፀምኩ ነው ጌታዬ”
“አትተኛ ስልህ ‹እሺ ጌታዬ› ብለህ አለመተኛት ነው፡፡ ትዕዛዝ መፈፀም እንጂ አንድ ቤት ውስጥ ጌታው እንቅልፍ እያጣ፣ ሌላው እንቅልፉን እየለጠጠ የሚያድሩበት ሁኔታ መለወጥ አለበት፡፡”
“እንዴት ሊለወጥ እንደሚችል ያውቃሉ ጌታዬ?”
“አላውቅም”
“እንድነግርዎት ይፈቅዳሉ?”
“አሳምሬ!”
“ማድረግ ያለብዎት አንድ ነገር ብቻ ነው”
“ምን ማድረግ ነው ያለብኝ እሺ? ንገረኝ”
“በእኔ ቦታ እርሶ፣ በእርሶ ቦታ እኔ ሆነን እንድንሰራ ያድርጉ!”
***
“The right man at the right place” የዋዛ አነጋገር አይደለም፡፡ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ ይገባል፤ እንደ ማለት ነው፡፡ ካልሆነ ስራ አይሰራም፡፡ ስነምግባሩም ይበላሻል፡፡ ሙያተኝነትና ስነ ምግባር ከቶም የሚነጣጠሉ አይደሉም፡፡ ምሉዕነት ያ ነው፡፡
“Uneasy lies the head that wears the crown” ይላል ሼክስፒር፡፡ ዘውድ የጫነን አናት ጭንቀት አይለየውም እንደማለት ነው፡፡ ቦታውን መያዝ፣ መሾም - መሸለም ብቻ የቢሮክራሲውን ስራ ውጤታማ አያደርገውም፡፡ ሰው መለዋወጥም ጉልቻ ቢቀያር ወጥ አያጣፍጥምን እንድንረሳ ማድረግ የለበትም፡፡ ዋናው የተለወጡት ሰዎች ማንነት፣ ቀናነት፣ ታታሪነት፣ ፅኑነትና ቆራጥነት ነው፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በፃፈው “እሳት ወይ አበባ” ላይ፤ “እንቅልፍ ነው የሚያስወስድህ” የሚል ግጥም አለው፡-
“.. ትቻቸዋለሁ ይተዉኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ
ዕውነት ይተዉናል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
የተወጋ በቅቶት ቢ‘ኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው
እና በእኔ ይሁንብህ
እንቅልፍ ነው የሚያስወስድህ”
“ታንዛንያ፣ ዳርኤ ሰላም በሌተር ቦምብ ለተገደለው ለአልፍሬድ ሞንድ ላንድ - የፍሬሊሞው ታጋይ)
ዋናው ነገር፤ እኛ በቃን ብለን ብንተኛም ጠላቶቻችን አይተኙልንም ነው፡፡ ያ ማለት ጠላቶቻችን ሁሌም ይፈሩናል፡፡ ስለዚህም መቼም አይተኙልንም፡፡ ጠላት ያለው ሰው የሰላም እንቅልፍ እንደማይኖረው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ መልካም ጎረቤት እንዲኖረን የምናደርገው እኛው ራሳችን ነን፡፡ ዲፕሎማሲን እንደዋዛ ማየት በራስ እንደመቀለድ ነው፡፡ “ሲግል በማንኪያ ሲበርድ በጣት” የተለመደ አካሄድ ቢሆንም አስቦ፣ ቀምሮ፤ ወጪ ገቢውን አስቦ መጓዝ ያባት ነው፡፡ አገርና ህዝብ መቼም አሉ፤ ይኖራሉም፡፡ ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው፡፡ መሪዎች ይለዋወጣሉ፡፡ ቀና መሪዎች ይቆያሉ፡፡ ከፊተኛው የኋለኛው ትምህርት ማግኘቱ ግድ ነው፡፡ አለበለዚያ ውድቀቱን ማፋጠኑ አይቀሬ ነው፡፡ ወቅት ምንጊዜም መሪዎችን መፈታተን አይሰንፍም፡፡ ስለሆነም መሪዎቻችን ወቅትን ማሸነፍ አለባቸው፡፡ ሥልጣን ከእርግብ ላባ ከወርቅ የተሰራ አልጋ አይደለምና ነቅቶ ማየት ብልህነት ነው፡፡ አዋቂ የሚናገረውን ማዳመት የመሪ ኃላፊነት ነው፡፡
“… አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
የሚለው ግጥም የሚያፀኸየው ይሄንኑ ነው፡፡   

Read 11163 times