Saturday, 13 April 2019 13:41

ያረፈደ ጥያቄ

Written by  ከዳግማዊ እንዳለ (ቃል፡ ኪዳን)
Rate this item
(12 votes)


               እኩለ ለሊት ሲሆን ድንገት ከእንቅልፉ ባኖ ነቃ፡፡ ከመንቃቱ በፊት በህልሙ፤ ፊኛዉን በረዶ እንደነከሰ ጥርስ አክብዶት የነበረዉን ሽንት፤ ሲያንፎለፉለዉ እያለመ ሲደሰት ነበር፡፡ ነቅቶ አልጋዉ ላይ እንዳለ ሲያዉቅ ግን ህልሙን አስታዉሶ ደነገጠ፡፡ እየፈራ የለበሰዉን የመኝታ ሱሪ መጋጠሚያና የተኛበትን ፍራሽ በዓይኖቹ መረመረ - በስብሰዉ አልጠቆሩም፡፡ እርግጠኛ ለመሆን በመዳፉ አፍንጫ የተኛበትን ቦታ እየዳበሰ አነፈነፈ - ምንም እርጥበት የለም፡፡ በደንብ እርግጠኛ ለመሆን መዳፉን አንስቶ አሸተተ - እራት ከበላዉ ድርቆሽ-ፍርፍርና ከጎረቤት መጥቶለት ከጠጣዉ ቅራሬ  ዉጪ ሌላ የለም፡፡ በደስታ ተነፈሰ፡፡
በልቡ ፈጣሪዉን እያመሰገነ ተነስቶ አልጋዉ ጠርዝ ላይ ተቀመጠ፡፡ ከዛም ቆንጆ ወጥቶልኛል ያሉትን ፎቶ ደጋግሞ እንደማየት ያለ፤ ያሸነፉበትን የሎተሪ ቁጥር ደጋግሞ ከማዉጫዉ ጋር እንደማመሳከር ያለ፤ ጋዜጣ ላይ ወጣልኝ ያሉትን ወግ ደጋግሞ እንደማንበብ ያለ፤ በተመሳሳይ ሂደት የለሊት ልብሱንና መኝታዉን ደጋግሞ መረመረ፡፡ ከእሱ እምነት መጉደል ዉጪ ሁሉም ነገር ሰላም ነዉ፡፡ እቤት ማስታጠቢያ ላይ እንኳን የማይሸና፣ የወንዶች ወንድ እንዴት አልጋዉ ላይ ሊሸና ይችላል?
ህልሙ ህልም ብቻ ሆኖ በመቅረቱ ተደሰተ፡፡ ያለፈዉ ቅዳሜ ከህልም ዓለም ወደ እዉነታዉ ዓለም ድንገት ተፈናቅሎ በመመለሱ ተከፍቶ ነበር፡፡ ያን እለት በህልሙ የሚስቱ የሚወዳቸዉ አካላቷ፤ ገላዋ ላይ እጥፍ ትልቅ ሆነዉ እያለመ ሲደሰት ነበር፡፡ ግና ድንገት ባኖ ነቃ፡፡ ከዛም ያየዉ ሁሉ ህልም ሆኖ እንዳይቀር እየጸለየ ሚስቱን ዞር ብሎ አጤናት፡፡ ከንፈሮቿ፣ ጡቶቿ፣ ዳሌና መቀመጫዋ መደበኛ መጠናቸዉን እንደያዙ በቅሬታ ሲመለከቱት፤ ተመለከተ፡፡ አብዝቶ አዘነ፡፡
አሁን በመንቃቱ ቢደሰትም ስለ ህይወት አንድ ነገር ግራ ገባዉ፡፡ ‹ሰዉ ከሚያስጨንቅና የሚያስፈራ ቅዠት እንጂ እንዴት ከሚያስደስት ህልም ደንግጦ ይነቃል?› ሲል ጠየቀ፡፡ ‹ያለፈዉ ቅዳሜ የነቃሁት በምመኘዉ ልክ ደስተኛ ሆኜ እንድኖር ስላልተፈጠርኩ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁንስ ምን ተገኘ? በህልሜ ስሸናና እንደዛ ስደሰት እያለሁ፤ እንዴት ድንገት ባንኜ ነቃሁ? የወረዳችን አስተዳደር ከኔዘርላንድስ መንግሥት ጋር በመተባበር፤ እገነባላችኋለዉ ብሎ ንድፉን በሸራ ላይ አሳትሞ የሰቀለዉ፤ መጸዳጃ ቤት ዉስጥ ሳይሆን፤ ሜትር ከሃያ አልጋዬ ላይ እንዳለሁ፤ የትኛዉ ያልተኛ አካሌ ነግሮ ቀሰቀሰኝ?› ሲል ማታ ሲጠጣዉ ያመሸዉን ቅራሪ የመሰለ ሀሳብ ዉስጥ ተዘፈቀ፡፡
ሀሳቡ ዉስጥ እየዋኘ ሳለ በቆዳዉ ቀዳዳዎች የገባዉ ቅራሪ፤ ከመኝታ በፊት አብዝቶ ከጠጣዉ ቅራሪ ጋር ሲገናኝ፤ ፊኛዉን ከበፊቱ የበለጠ ስለወጠረዉ፤ ሽንቱ ‹በክብር አዉጥተህ የማትደፋኝ ከሆነ፤ በራሴ ጊዜ በየአቅጣጫዉ እፈሳለሁ› ብሎ ሲዝትበት ሰማ፡፡ በድንጋጤ ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡ ሲቆም ሲዋኝበት የነበረዉን የሀሳብ ባህርን ለሁለት ከፈለዉ፡፡ ወዲያዉ ባለዉሃ ግድግዳ ማዕዶት ፊት ለፊቱ ተዘረጋ፡፡ የሙሴና የፈርኦኑን ንትርክ አስታዉሶ፤ የፊኛዉን ፈቃድ ሊፈጽም፤ ነጠላ ጫማ ተጫምቶ በማዕዶቱ ላይ ወደ በሩ አመራ፡፡ በሩ ጋር ሚስቱ፤ ለድንገተኛ ሽንት መቀበያ ብላ ያዘጋጀችዉ፤ ዉስጡ የእርሱን ጥርስ የመሰለዉ ማስታጠቢያ፤ ቡሀቃ የመሰለዉ አፉን እያቁለጨለጨ፤ አንስቶ የኑሮ ግዳጁን እንዲፈጽም እንዲረዳዉ ተለማመጠዉ፡፡ አዘነለት፡፡ ግና ሚስቱ አይታዉ፤ ‹ፈሩ፣ ፈሩ ማጀት ሸኑ› ብላ ወንድነቱን ከጥያቄ ዉስጥ እንዳታስገባበት ሰጋና፤ በሩን ከፍቶ፣ ሦስት ጊዜ አማትቦ ወደደጅ ወጣ፡፡
ሰፈሩ ጸጥ ብሏል፡፡ ጨረቃዋ፤ የነገሰዉን ቅዝቃዜ በእልህ ለማሸነፍ ሞክራ፤ ጉልበቷን ጨርሳ፤ ጭል ጭል ትላለች፡፡ ደጃፉ ላይ እንደቆመ ዛሬ የትኛዉ ጎረቤቱ አጥር ላይ መሽናት እንዳለበት ሲያማርጥ (እነሱ ግቢ የላቸዉም)፤ የሟቹ መሰንቆ ተጫዋች እዝራ ለጅ የሆነዉ ሳልሳዊ፤ የአባቱን መሰንቆን አንግቶ፤ ዋናዉን መንገድ ይዞ ሲሄድ ተመለከተዉ፡፡ ያቺ ጨቅጫቃ እናቱ አማራዉ ይሆናል፣ በዚህ በሌሊት የወጣዉ ሲል አሰበና አዘነለት፡፡
ልጁ መሰንቆዉን እንዳነገተ፤ ሰፈሩ ዉስጥ በብዙኃኑ የሚፈራዉንና የሚከበረዉን አዋቂን ቤት አልፎ ከመሄዱ፤ አዋቂዉ በር ላይ በአሥር ሣንቲም ገመድ የተንጠለጠለችዉ እስስት በድን፤ በነፋስ ኃይል ይንዠዋዠዉ ጀመር፡፡ ቀጥሎ ደጃፉ ጋር ከበቀለዉ ዓይነቱ ከማይታወቅ ትልቅ ዛፍ ላይ ካረፈ ግዙፍ ወፍ ዓይኖች ብሌን ዉስጥ እሳት የሚመስል ጨረር ወጥቶ፤ የልጁን አቅጣጫ ይከተል ጀመር፡፡
ሰዉዬዉ በሚያየዉ ነገር ግራ እንደተጋባ አካባቢዉን ሲቃኝ፤ ከአዋቂዉ ቤት ትይዩ፤ ትንሽ ከፍ ብሎ ካለዉ የፖሊስ አዛዥ ቤት፤ የአዛዡ ሚስት በሯን ከፍታ ወጣችና እደጇ ላይ ሽንቷን ሸንታ፤ የአዋቂዉን ቤት ተሳልማ ተመልሳ ገባች፡፡ ሰዉዬዉ ሽንቷ የፈሰሰበት ሣር ሲቃጠልና ሲጨስ ሲመለከት፤ የሴትዬዋ ሽንት አሲድ ነዉ ተብሎ የሚወራዉ ወሬ እዉነት እንደሆነ አመነ፡፡  
ባለ ማሲንቆዉ ልጅ የሴትዬዋን ቤት አልፎ እንደሄደ፤ ደንገት ሣሩ ላይ የሚጨሰዉ የሴትዬዋ ሽንት፤ ወደላይ ከተግተለተለ በኋላ ወደሚጠቀለሉ ሦስት ትላልቅ ነፋሳት ተቀየረና ወፉ ከሚረጨዉ ጨረር ጋር በአንድነት የልጁን ዱካ መከተል ጀመረ፡፡
ሰዉዬዉ በድንጋጤ ሽንቱ ጠፋ (ሰዉ ሲደነግጥ ሽንቱ ያመልጠዋል እንጂ ይጠፋበታል እንዴ?)፡፡ ድንገት አንድ የሚያስገመግም ድምጽ ‹‹ወደቤት ግባ›› ሲል ትዕዛዝ ሰጠዉ፡፡ በድንጋጤ ተሳስረዉ የነበሩት እግሮቹ ተላቀዉ እንዲገባ በመንቀጥቀጥ ነገሩት፡፡ እግሮቹን እያንኮሻኮሸ በፍጥነት እቤቱ ገብቶ በሩን ቀረቀረ፡፡
በሩን በጀርባዉ እንደተደገፈ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ ያየዉ ነገር ህልም ይሁን እዉን ማወቅ አልቻለም፡፡ ሚስቱን ቀስቅሶ ሊያወራት ወደደ፡፡ በሩን ከፍቶም እንደገና አካባቢዉን ለማየትም ዳዳ፡፡
‹‹አርፈህ ተቀመጥ፡፡ ለምን በማያገባህ ትገባለህ?›› አለዉ፤ የቅድሙ ድምጽ ጆሮዉ ሥር መጥቶ፡፡ ድምጹ ብዙ ጊዜ ሲያወሩ የማይሰሙት የአዋቂዉ ደምጽን መሰለዉ፡፡ ጀርባዉን ለበሩ መስጠቱ ስላስፈራዉ ቀጥታ ወደ መኝታዉ ሄደ፡፡
ሚስቱ አልጋዉ ላይ በእሱ በኩል ያለዉ አካሏ ተራቁቶ ተኝታለች፡፡ አጠገቧ ባይኖርም ጀርባዋን ሰጥታዉ ነዉ የተኛችዉ፡፡ ሁልጊዜም ለሽንት ከነቃ በኋላ እንደሚያደርገዉ፣ ፊት ለፊቷ ቆሞ፤ እጁን አጣምሮ ቁልቁል አፈጠጠባት፡፡ ጠይም ሰልካካ ፊቷ፤ ፊቷ ላይ የተበተነዉ የተተኮሰዉ ረጅም ጸጉሯ፤ በገዛላት የብር ሀብል ያጌጠዉ፤ ጠረኑን የሚወደዉ አንገቷ፤ በአልጋ ልብስ ተሸፍነዉ የማይታዩት፤ ግን በእርግጠኝነት ከሁለት አንዳቸዉ፤ ከዉስጥ ልብሷ ሾልከዉ የወጡት ጡቶቿ (ያልወለድኩት ጡት አስጣይ እንዳይመጣብኝ ብዬ እንጂ መሀን ስለሆኑ አይደለም ይላል ለእራሱ፡፡)፤ እንደ አገሩ መልከአ ምድር ከፍ ዝቅ ያለዉ አካሏ፤ ጸሐይ መዉጫ የመሰለዉ ወገቧ……ጭኗ ጋር የተሸበሸበዉ የለሊት ልብሷ፤ እሱን አልፎ የወጣዉ ታፋዋ፤ የሚያምሩት እግሮቿ…….ለደቂቃዎች አተኩሮ ቢያያትም ሌላ ጊዜ ለሊት ላይ ነቅቶ ሲያያት እንደሚሰማዉ ዓይነት፤ የእድለኝነት ስሜት ሊሰማዉ አልቻለም፡፡
ከደጅ ከገባ በኋላ የተለየ ስሜት እየተሰማዉ እንደሆነና ሁሉን ነገር አምኖ ተቀብሎ፣ ደስተኛ ሆኖ ይኖር የነበረዉን ልቡን የሚሞግተዉ አንዳች፤ ተጻራሪ መንፈስ ከአካሉ እንደገባ ተሰማዉ፡፡ ድንገት፤
‹‹ግን ታምናታለህ?›› አለዉ ዉስጡ፡፡ ዉስጡ ከመቼዉ ሁለት ቦታ እንደተከፈለ ሲያስብ ደነገጠ፡፡ ዉስጡ ቀጠለ…
‹‹አብራችሁ ብዙ ዓመታትን ቆይታችኋል፡፡ ግን አንድ ቀን እንኳን ‹ከእኔ ዉጪ ሌላ ሰዉ ታያለች ወይ? በኔ ላይ ሄዳ ታዉቃለች ወይ?› ብለህ ጠይቀህ አታዉቅም፡፡ ይዘሀት ስትመጣ ‹ያዩት ሴቶች ሁሉ ይወዱት የነበረዉን፤ መልከ መልካሙ መሰንቆ ተጫዋቹ እዝራ ከሞተ ቆየ፤ ከእንግዲህ በማን ልስጋ?› አልክ፡፡ ልጁ እሱን ሆኖ እንደሚያድግ እንኳን አላሰብክም ነበር፡፡ ተመልከተዉ እስኪ! ቁጭ አባቱን አኮ ነዉ የሚመስለዉ፡፡››
የእዝራ ልጅን አስታወሰ፡፡ ቁጭ አባቱን ነዉ የሚመስለዉ፡፡ እንደዉም በተሻለ ዘመን ተፈጥሮ የተሻለ ወጣት ሆኗል፡፡ ግን ‹እሱ ከእናቱ ጭቅጭቅ ወጥቶ የሰፈሩን ሴት የሚያማግጥበት ሰዓት ከየት ያመጣል?› ሲል እራሱን አረጋጋ፡፡
‹‹ቆይ ለእኔ ታማኝ ናት ወይ ብለህ እራስህን ጠይቀህ የማታዉቀዉ ስለምታምናት ነዉ ወይስ ለእሷ ግድ ስለሌለህ? ሰዉ እንዴት በፍቅረኝነትና በትዳር ስድስት ዓመታትን አብሮ ኖሮ፤ ፍቅረኛዬ ወይ ሚስቴ ለእኔ ታማኝ ናት ወይ ብሎ እራሱን አይጠይቅም?››
‹‹ስለማምናት ነዉ፡፡ አምናታለሁ፡፡ ደግሞ አብረን በቆየንባቸዉ ጊዜያት እንድጠራጠራት የሚያደርግ ምንም ነገር አድርጋ አታዉቅም፡፡ እና ለምንድን ነዉ የምጠራጠራት?›› ሌላኛዉ ዉስጡ መለሰ፡፡
‹‹እዝራ ስለሞተ ሌላ በእሱ ልትጠረጥራት የምትችልበት ወንድ ሰፈር ዉስጥ የለም ማለት ነዉ?››
‹‹እሱም ባይሞት አልጠረጥራትም!››
‹‹ቆይ እንደዉም አንተ እሷን ከማግኘትህ በፊት፤ አዝራም ሳይሞት በፊት የሚተዋወቁ ቢሆኑስ እሺ? ሙዚቀኛን የማያዉቅ ማንም የለም፡፡ እንደዉም ልጁ የእሷ ቢሆንስ? እዝራን አስወልዳዉ የከዳቸዉ ቢሆንስ?››
‹‹ምንድነዉ የምታወራዉ? ሴት ስታረግዝ ወንዱ ይከዳታል እንጂ አስረግዛ ትከዳለች እንዴ? ደግሞ ሳልሳዊን እናቱ ስትወልደዉ እኔ እዛዉ ነበርኩ፡፡››
‹‹እሺ…እሺ! ለካ ሴት ናት! አገለባበጥኩት፡፡››
‹‹ምንድን ነዉ ነገር እንደዚህ መፍተል? ተወኝ በቃ! ሽንቴን ልሽናና ልተኛበት፡፡››
ማስታጠቢያዉን አንስቶ ዓይኖቹን ከድኖ ሽንቱን መሽናት ጀመረ፡፡ ሽንቱ የእሱ ጥርስን የሚመስለዉን የማስታጠቢያዉን ግድግዳ እየመታ ወፍራም ኃይል ያለዉ ድምጽ ማዉጣት  ጀመረ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የማስታጠቢያዉ ሙሉ አፍ በሽንቱ ሲሸፈን፤ የሽንቱ ድምጽ ቀጠነ፡፡ ሰዉዬዉ ዓይኖቹን ከድኖ የሚሰማዉ የሽንቱ ድምጽ፤ የአዋቂዉ ሰዉዬ በራፍ ላይ በገመድ ተንጠልጥላ የተሰቀለችዉን እስስት ምስል አእምሮ ዉስጥ ፈጠረበት፡፡
‹‹ተመራመር፡፡ አረጋግጥ፡፡ በጭፍን ፍቅር አትደሰት፡፡ ዉጪ ያየኸዉን እስክትረሳ ድረስ በራስህ ጉዳይ ተጨነቅ፡፡›› የሚል ቃል በእስስቷ ድምጽ የጆሮዉ ታምቡር ላይ ነጠረ፡፡
ደንግጦ ዓይኖቹን ከፈተ፡፡ ወዲያዉ እያንፎለፎለዉ የነበረዉ ሽንት አበቃ፡፡ ሽንቱን ጨርሶ ይሁን አይሁን እርግጠኛ ሊሆን አልቻለም፡፡ ማስታጠቢያዉን መሬት አስቀምጦ፤ ሱሪዉን ከፍ አደረገ፡፡  ወደ መኝታዉ ሊሄድ ሲል ግን ሽንት መክፈያዉን አለማራገፉ ትዝ አለዉና፤ ከከተተበት አዉጥቶ አራገፈ፡፡
ሲያራግፍ፤ ሙርጡ ዉስጥ እረግተዉ በረዶ ሊሠሩ የነበሩ ሰባት የሽንት ጠብታዎች ተስፈናጥረዉ በየአቅጣጫዉ ተወረወሩ፡፡ አራቱ ጠብታዎች በአራቱ የቤቱ ማዕዘኖች እግር ላይ አረፉ፡፡ አንደኛዉ የሚስቱ ግንባር ላይ ሄዶ ተቀመጠ፡፡ ሌላኛዉ እንዳወላወሉት መላእክት አየር ላይ ቀረ፡፡ የቀረዉ አንዱ ኢላማዉን መትቶ፤ ማስታጠቢያዉ ዉስጥ ከዘመዶቹ ተቀላቀለ፡፡
በአራቱ ጥጋቶች ያረፉት አራቱ የሽንት ጠብታዎች ቤቱ ዉስጥ ያለዉን የመሬት ስበት አጠፉት፡፡ ሚስትየዉ፣ የተኛችበት አልጋና የሽንት ማስታጠቢያ ብቻ ሲረጉ፤ ሰዉዬዉና ቤቱ ዉስጥ ያሉት ዕቃዎች ሁሉ አየር ላይ ተንሳፈፉ፡፡ ሚስትዬዉን ግንባሯ ላይ ያረፈዉ የሽንት ጠብታ ከነአልጋዋ ባለችበት አጸናት፡፡ ማስታጠቢያዉንም እንደዛዉ፡፡
አየር ላይ የቀረዉ ጠብታ፤ አንደርቢ የሰዉ ጣራ እንደሚወግረዉ፤ በአልቦ የመሬት ስበት አየር ላይ የሚንሳፈፉትን የቤት ዕቃዎች በፍጥነት እየጠለዘ ወደ ቦታቸዉ ይመልስ ጀመር፡፡ ማስታጠቢያዉ ላይ ያረፈዉ ጠብታ፤ ዘመድ አዝማዶቹን አሳምኖና ኃይል አሰባስቦ አየር ላይ የሚዋልለዉን ሰዉዬ፣ በነጠላ ጫማዉ ሶል እየገፋዉ ወደ ሚስቱ መኝታ ወስዶ፤ እንደ ጥላሞትዋ ከላይዋ አቆመዉ፡፡
ግንባርዋ ላይ ያለዉ ጠብታ ሰዉዬዉ መቅረቡን ሲመለከት፤ በፍጥነት በጆሮዋና በግንባርዋ መሀከል ባለዉ ክፍተት ላይ ወደ አእምሮዋ የሚያስገባ መሹለኪያ አበጀ፡፡ ከዛ ሰባቱም ጠብታዎች ተበባብረዉ ሰዉዬዉን ወደ ሚስቱ አእምሮ ወረወሩት፡፡ ወደ ዉስጥ መምዘግዘግ ሲጀምር፤ የሰባቱ ጠብታዎች የተባበረ ድምጽ ተከተለዉ፡፡
‹‹ትወድሀለች ወይስ ትወድልሀለች? ምንህን ነዉ የእኔ የምትለዉ? ምኗ ነዉ ያንተ? በለሊት ተነስተህ በሰዉ ጉዳይ ጥልቅ ከምትል እስኪ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ፈልግ! ››
‹‹እኔ በማንም ጉዳይ ጥልቅ አላልኩም፡፡ በአጋጠሚ ነዉ የተነሳሁት›› እየተምዘገዘገ መለሰ፡፡
‹‹ምንም ሆነ ምንም የማይገባህ ቦታ ተገኝተሀል፡፡ በል እራስህን አስጨንቅ፡፡ ደስታህን እጣዉ!›› ብለዉ የተከፈተዉን ሲዘጉበት በጨለማ ተዋጠ፡፡
ለደቂቃዎች ከተምዘገዘገ በኋላ ደፍ ብሎ ሴቶች ዉሃ በእንስራ የሚቀዱበት፤ ከብቶች አፋቸዉን ተክለዉ የሚጠጡበት አንዲት ወንዝ ዳር ላይ ወደቀ፡፡ ከወደቀበት ቀና ብሎ ዙርያ ገባዉን ሲመለከት ቢጫ-አረንጓዴ የሣር ምንጣፍ የለበሰ፤ ምንጣፉ ላይ የሚላፉ፤ ምንጣፉን በጥርሳቸዉ የሚነጩ ነጭ፣ ጥቁር፣ ነጭ በጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸዉ ከብቶች፤ ምንጣፉ ላይ ወደቅ፣ ወደቅ ያሉ ቢጫ አበቦች፤ የተዋበ መልከአ ምድር ታየዉ፡፡ ይሄንን ሲያይ ፈገግ አለ፡፡ ወድያዉ ሚስቱ ለምን ሁሌም በእንቅልፍ ልቧ ፈገግ እንደምትል ተገለጠለት፡፡ ድንገት ከወንዙ በላይ፤ ዳገቱ ላይ፤ ጥርሱን አስጥቶ ቁልቁል ሚስቱን የሚያያትን ልጅ አግር አረኛ ተመለከተ፡፡ የሚስቱ ፈገግታ ለእረኛዉ አንጂ ለተፈጥሮዉ ዉበት እንዳልሆነ ተረዳ፡፡
እረኛዉ ከትንሽነቱ በስተቀር ሁለመናዉ ቁርጥ እሱን ነዉ የሚመስለዉ፡፡ ‹ምን ማለት ነዉ?› ሲል አሰበ፡፡ እሱ እረኝነትን በዘፈን ወይ በቴሌቭዢን ድራማ ላይ ነዉ የሚያዉቀዉ፡፡ በአእምሮዋ እረኛ አደርጋ እየሣለች እያሾፈችኝ ይሆን ሲል ተበሳጨ፡፡
ድንገት አካባቢዉ በደመና ደበዘዘ፡፡ ከዛም ካፊያ ጀመረ፡፡ እጸዋቱ አንገታቸዉን ደፉ፡፡ ወንዙ ዉስጥ ሥራ ፈተዉ ወሬ ይሰልቁ የነበሩ የዉሃ ጠብታዎች መባተል ጀመሩ፡፡ ወንዙ ነፍስ ዘራ፡፡ እየተገለባበጠ፤ ያገኘዉን እያገላበጠ እያጓራ ያልፍ ጀመር፡፡ ዳርና ዳር ያሉ፤ ቶሎ እንዳይገናኙ አዉቀዉ ተከዙ፡፡ ባለዋሽንቱ ይህንን አዉቆ ወንዙን በሙዚቃ አባብሎ ሊለምንላቸዉ ገሳ ለብሶ ብቅ አለ፡፡
እረኛዉ ግን አሁንም ሣቁ ሳይጠፋ እሷን እያያት ይደሰታል፡፡ ‹ዳርና ዳር ሆኖ መተያየት ከሆነ ዕጣ ፈንታቸዉ፤ መሀሉ የማያሳልፍ ቢሆን፣ ባይሆን ለእነሱ ምንተዳቸዉ? እሷ ግን የት ነዉ ያለችዉ? ልጁ ዝናብ እንዲህ ሲቀጠቅጠዉ እያየች እንዴት አስቻላት? ደግሞ ከወንዙ ትንሽ ከፍ እንዲል ብትነግረዉስ ምን ነበረበት? እሱ በቅርበት ሆኖ እሷን ማየቱን እንጂ የወንዙን ሙላት ልብ አላየም፡፡› ሲል አሰበ፡፡  ድንገት ደራሽ መጣና እረኛዉንም ባለዋሽንቱንም ጠራርጎ ወሰዳቸዉ፡፡ የዛኔ እሪታዋን አቀለጠችዉ፡፡
እረኛዉ አስክሬኑ ተፈልጎ ታጣ፡፡ ቤተሰብ በበርኖስ ይለቀስ ብሎ ወሰነ፡፡ ጎረቤቶች እረኛ ስለነበረ በገሳ ካልተለቀሰለት ብለዉ አመጹ፡፡ ጭቅጭቁ ሲበዛ የመንደሩ ዳኛ ‹አገር ጥሎ ጠፍቶ ነዉ እንጂ እንደዉም አልሞተም› ብለዉ ሁሉንም እንዳያለቅሱ አዘዉ ወደመጡበት መለሷቸዉ፡፡ እሷ ግን ማንም ሳያያት ነጠላዋን አዘቅዝቃ፤ ጸጉሯን ተላጭታ፤ ነጭ ማተብ አሥራ ሙሾ ስታወርድ ኖረች፡፡ ተኝታ ፊቷን በሀዘን ክስክስ የምታደርገዉና በሲቃ የምትወራጨዉ ለምን እንደሆነ ተገለጸለት፡፡
‹እረኛዉ ማነዉ? ለምን እኔን መሰለ? በባለፈዉ ህይወቴ ዉሃ የበላዉ እረኛ ነበርኩ? ወይስ?› እረኛዉ ቁጭ ብሎ የነበረበት ጉብታ ላይ ቁጭ ብሎ ማሰብ ጀመረ፡፡ አሻግሮ ሲያይ ሚስቱ በቤቷ መስኮት ተንጠራርታ አሻግራ ስታየዉ ተመለከተ፡፡ ከዛም እንባዋን ጠራርጋ፤ ተመልክታዉ ስታበቃ፤ በምንም አይልም እራሷን ከነቀነቀች በኋላ ፈገግ ስትል አስተዋላት፡፡
ደነገጠ፡፡ ከዛም ያገኘዉን መንገድ ተከትሎ እግሩ እንደመራዉ መራመድ ጀመረ፡፡ አቀበት ወጣ፤ ቁልቁለት ወረደ፤ የወንዝ ዉሃን እየተጎነጨ አቋረጠ፤ በመጨረሻም አምሳለ ሲኦልን በመሰለ ዋሻ አልፎ፤ መዝጊያቸዉ ወደ ጎን ተገልብጦ፤ ከላይ ወደ ታችና ከታች ወደ ላይ የሚከፈትና የሚዘጋ፤ መዝጊያዎቹ መሀል ላይ እንደ ጸጉር መቆንጠጫ ተቆላልፈዉ የሚጋጠሙ፤ ጎን ለጎን በአጭር ርቀት የቆሙ፤ በሮች ጋር ደረሰ፡፡ በየትኛዉ ሾልኮ መዉጣት እንዳለበት ሲያስብ ቆየና፤ ሄዶ እንደ ምንም በራቸዉን ፈልቅቆ፤ አንድ እግሩን በአንደኛዉ፤ ሌላዉን ደግሞ በሌላኛዉ አሾልኮ ወጣ፡፡ ሲወጣ ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡ ዓይኖቹ ሲከፈቱ እራሱን አልጋዉ ላይ የእንግላል ተኝቶ አገኘዉ፡፡ ሚስቱ እንደሌላዉ ጊዜ ስላልናፈቀችዉ እንደነቃ ዞር ብሎ አላያትም፡፡
‹ሚስቴ የወደደችኝ በልጅነቷ ገጠር እያለች ዉሃ የበላዉን ፍቅረኛዋን ስለምመስላት ነዉ?› ሲል አሰበ፡፡ ‹እኔም የልጅነት ፍቅረኛዬን የምትመስል ሴት መንገድ ላይ ሳይ ደስ የሚል ስሜት እንደሚሰማኝ ተሰምቷት ይሆን? እንደዛ ከሆነ ከስርያለሁ፡፡ በነጠፈዉ መሀጸናቸዉ አስገዳጅነት በልጅ ፈንታ አሻንጉሊት፤ በለሊቱ ቅዝቃዜ፤ በፍቅረኛቸዉ ፈንታ ትራስ አቅፈዉ በሚተኙ ሰዎች ክንዶች መሀል ካሉት አሻንጉሊቶችና ጨርቃቸዉ ከወየበዉ ትራሶች በምን እለያለሁ?› እንዲህ፣ እንዲህ እያለ ሲያስብ ለሽንቱ ተነስቶ፤ በራፉ ላይ ምን አይቶ እንደነበረ ጨርሶ እረሳ፡፡

Read 2781 times