Saturday, 20 April 2019 14:12

ቻን 2020

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

 ከኢትዮጵያ ማምለጡ ያስቆጫል፡፡ የስታድዬሞች አለማለቅ፤ የበጀት ችግርና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የቀረቡ ምክንያቶች ናቸው ካሜሮን ምትክ አስተናጋጅ ሆናለች


             ኢትዮጵያ የ2020ውን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ እንደማታስተናግድ የተረጋገጠ ሲሆን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ምትክ መስተንግዶውን ለካሜሮን እንደሰጠ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ የካሜሮን እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በ2020 እኤአ ላይ ቻንን በተሳካ ሁኔታ በማስተናገድ በ2021 የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ በተሟላ ዝግጅት ለማካሄድ መልካም አጋጣሚው እንደተፈጠረለት አስታውቋል:: በ2019 የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ ከመንግስት በቂ ድጋፍ ባለማግኘት እና ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የካሜሮንን መስተንግዶ ካፍ ማንሳቱና ግብፅ ምትክ ሆና እንድታዘጋጀው መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን በኢትዮጵያ ዝግጁነት ላይ ያደረገውን የመጨረሻ ግምገማ ይፋ አላደረገም፡፡
ካፍ የቻን መስተንግዶውን ለካሜሮን ከመስጠቱ በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ  ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት  ‹‹ቻንን ለማስተናገድ የምንፈልግ ቢሆንም ስታድዬሞች ሙሉ ግንባታቸው ተጠናቅቆ እና መስፈርቶቹን አሟልተው ለውድድሩ መድረሳቸውን ስለምንጠራጠር ዝግጁ አይደለንም›› ብለዋል፡፡ ‹‹ውድድሩ በሚካሄድበት አመት የፓርላማ ተወካዮች ምርጫ ስለሚካሄድም መስተንግዶውን አስቸጋሪ ያደርገዋል›› በማለትም ተጨማሪ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ የስፖርት ኮሚሽን ባለስልጣን በግል አስተያየታቸው አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ነባራዊ  ሁኔታ ቻንን ማዘጋጀት አትችልም ብለው ነበር፡፡ የስፖርት ኮሚሽኑ ከፍተኛ ስራ ሃላፊ በወቅቱ ቻን ማዘጋጀት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብለው ሲናገሩ ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ነበራቸው፡፡ በመጀመርያ ያነሱት ምክንያት ለመስተንግዶው ወጭ ይሆናል የተባለው 1.5 ቢሊዮን ብር ወይም (50 ሚ. ዶላር)፤ በአገሪቱ ካለው የተፈናቃዮች ችግር አንጻር ወጭ ማድረጉ ተገቢ ላይሆን ይችላል በሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የሚታየው አለመረጋጋት ሻምፒዮናውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ አያስችልም ብለዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት እና የስፖርት ኮሚሽኑ ባለስልጣን የ2020 ቻን መስተንግዶን ለመተው ያቀረቧቸው ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም፡፡ አቶ ኢሳያስ ጂራ የፌደሬሽኑን የፕሬዝዳንትነት ስልጣን ከ11 ወራት በፊት እንድተረከቡ የሚታወቅ ሲሆን በቆይታቸው አህጉራዊ ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ በበኩላቸው የረባ እንቅስቃሴ አላደረጉም ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከስታድዬሞች ሙሉ ለሙሉ አለመጠናቀቅ ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች በአፋጣኝ የሚያስተካክሉበት በቂ ግዜ ባይኖራቸውም፤ ምናልባትም የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በወልዲያ ስታድዬም የነበረውን የተሟላ የግንባታ አፈፃፀም በማስተዋል በኩባንያው በኩል ስታድዬሞቹን ለሻምፒዮናው ለማድረስ መሞከር ነበረባቸው:: በ2020 የሚደረገው የፓርላማ ምርጫ ከእግር ኳስ ጋር በማያያዝ አግባብ ያልሆነ ስጋት ውስጥ መግባታቸውም የሚያስተች ነው፡፡ በሌላ በኩል የስፖርት ኮሚሽኑ አህጉራዊ ሃላፊነትን ከወቅታዊ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና ሌሎች የፖለቲካ ቀውሶች ጋር ማያያዛቸው ተገቢ ያልሆነ እና የማያሳምን ነው፡፡
ባለፉት 10 ዓመታት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ሆኖባቸው በመላው ኢትዮጵያ የተገነቡት ግዙፍ ስታድየሞች ሙሉ ለሙሉ አለመጠናቀቅ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑንና የስፖርት ኮሚሽኑን ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ስታድዬሞቹ አህጉራዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ የማይችሉ  ከሆነ በሌሎች አገራት እንዳጋጠመው ለየከተሞቻቸው  ነጭ ዝሆን (White Elephant) ሆነው መቀጠላቸው ነው፡፡ በተያያዘ ደግሞ  ኢትዮጵያ ለቻን መስተንግዶው በተሰጣት እድል ሃላፊነቱን ለመወጣት ባለመቻሏ በቀጣይ ለምታቀርባቸው የአዘጋጅነት ጥያቄዎች የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በቂ ትኩረት ላይሰጥ ይችላል፡፡ኢትዮጵያ በ2007 የሴካፋ ውድድርን ከማስተናገዷ በቀር በአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር ካስተናገደች 17 ዓመት አልፏታል፡፡ ከቻን መስተንግዶ መሰረዝ በኋላ የካፍ አህጉራዊ ውድድሮችን የማስተናገዱ እድል እየጠበበ መሄዱ ያሳስባል፡፡
የ2020 የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና /2020 ቶታል አፍሪካ ኔሽን ሻምፒዮንሺፕ በኢትዮጵያ ሊዘጋጅ የነበረው ለ6ኛ ጊዜ ነው፡፡  በ2020 ላይ ከጃንዋሪ - ፌብርዋሪ ወራት ሊካሄድ ለነበረው ሻምፒዮናው በተለያዩ ድረገፆች የኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሠፈረ ቢሆን የሻምፒዮናው ሎጎ አለመታየቱ፣ ጨዋታዎች የሚካሄድባቸው ስታድየሞች በዝርዝር አለመተዋወቃቸው እና ላለፉት 6 ወራት ሻምፒዮናውን አስመልክቶ ምንም እንቅስቃሴዎች አለመታየታቸው አዘጋጅነቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶት ነበር፡፡  16 ብሔራዊ ቡድኖች ለሚሳተፉበት የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ  ማጣርያው በቅርብ ወር  የሚጀመር ሲሆን አዘጋጅነቷን የሰረዘችው ኢትዮጵያ መሳተፏ ያጠያይቃል፡፡ በማጣሪያው ውድድር የሚሰለፉት 47 ብሔራዊ ቡድኖች ሲሆን ጅቡቲና ጋቦን በ2018 ለተካሄደው ማጣሪያ ላይ ባለመካፈላቸው ታግደዋል፡፡

ያላለቁ የስፖርት መሰረተ ልማቶች
ኢትዮጵያ 6ኛውን የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮንሺፕን (ቻን) በ2020 እኤአ ላይ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ከ2 ዓመት በፊት ነበር፡፡ በሞሮኮ የተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) በካዛብላንካው መሃመድ አምስተኛ ስታዲየም ሲፈፀም፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በወቅቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ለነበሩት ጁነዲን ባሻ አርማውን ማስረከቡ ይታወሳል፡፡ አንድ አገር አህጉራዊ ውድድር አስተናግዳለሁ ብሎ ሲነሳ ያሉትን የስፖርት መሰረተልማቶች፤ የመንግስትን ሃላፊነት እና ባለቤትነት ሌሎችንም ዋንኛ መስፈርቶች በተሟላ ሁኔታ እንደሚሳካ በሚያቀርበው ምክረ ሃሳብ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ግን ይህ ዝግጁነት አልነበረም፡፡
የኢትዮጵያ አዘጋጅነት በይፋ ከተገለፀ ከ2 ወራት በኋላም የካፍ ኢንስፔክሽን ቡድን ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ ያለችበትን ደረጃ በመጀመርያ ዙር ገምግሞ ነበር፡፡ የኢንስፔክሽን ቡድኑ ከ2 ዓመት በፊት የፍተሻ ስራውን ሲያከናውን  የስታዲየሞች ጥራት እና ለውድድሩ በጊዜው የመድረስ ዕድላቸውን የፈተሸ ሲሆን በወቅቱ በተለያዩ ክልሎች የተገነቡት ስታዲየሞች ሙሉ ለሙሉ ያልተጠናቀቁ መሆናቸው የግምገማውን  ትኩረት የወሰደ ነበር፡፡በባህርዳር፣ ሃዋሳ እና መቀሌ ያሉት ስታዲየሞች ባይጠናቀቁም ጨዋታዎችን በፕሪሚዬርሊግ እንዲሁም የባህርዳር እና ሃዋሳ ስታዲየሞች የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ መቻላቸው የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ያዘናጋው ይመስላል፡፡ ከስታዲየሞቹ ባሻገር የትራንስፖርት፣ የሆቴል አቅርቦትም ለአህጉራዊ ውድድር ዋና መስፈርቶች ሆነው ስለሚፈተሹም በዚህ በኩል ያሉት ሁኔታዎች የሚያበረታቱ አለመሆናቸው የመጀመርያውን ግምገማን የሚያከሩ ነበሩ፡፡
የካፍ ኢንስፔክሽን ቡድን የመጨረሻውን ግምገማ ከወራት በፊት ሲያደርግ በከፍተኛ ባለሙያዎች ሲሆን የሀዋሳ፣ መቐለ፣ ባህርዳር እና የአደይ አበባ ስታዲየሞችን በመዟዟር ጎብኝተዋቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ መሟላት ከሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ዋንኛው የስታድየም ቅድመ ሁኔታዎች በመሆናቸው በዚያ ረገድ በቂ ዝግጅት አለመኖሩም በወቅቱ አሳስበዋል፡፡ በየስታድዬሞቹ ደረጃውን የጠበቀ የመጫወቻ ሳር፣ የተጠባባቂ ተጫዋቾች እና የቡድን አመራሮች መቀመጫ፣ ፓውዛ፣ በስታድየሙ የተለያዩ ክፍሎች የሚገጠሙ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች፣ በቂ የመልበሻ ክፍል፣ የሚዲያዎች እና የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል፣ በቂ መፀዳጃ ክፍሎች፣ በአንድ ከተማ እስከ አራት የልምምድ ሜዳ እና የመሳሰሉትን በማሟላት መስራት አልተቻለም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችም የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ፤ የስፖርት ኮሚሽኑ እና የመንግስት የቤት ስራዎች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

በቀድሞ ፌደሬሽን የታሰበው በአዲሱ የማይቀጥልበት…
የእግር ኳስ ፌደሬሽን አስተዳደር በቀጣይ እና ዘላቂ እቅዶች ለመስራት አለመቻሉም በቻን መስተንግዶ መሰረዝ ማስተዋል ተችሏል:: አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የፌደሬሽን አስተዳደር ዓመት ሊሞላው ቢሆንም አስቀድሞ የነበረው ፌደሬሽን በፈጠራቸው እድሎች ላይ ለመስራት ከጅምሩ አለመነሳሳቱ ሌላው ችግር ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የረጅም ጊዜ ታሪክ ለማስተዋል እንደሚቻለው በቀድሞ ፌደሬሽን የታሰቡ እና የተያዙ እቅዶች በአዲሱ እንደማይቀጠልበት ነው፡፡ አስቀድመው የነበሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በስልጣን ዘመናቸው አህጉራዊ ውድድሮችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ፅኑ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ አቶ ጁነዲን በ2019 እና በ2021 እኤአ የሚካሄዱትን 32ኛው እና 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫዎችን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ጥያቄ አቅርበው ባይሳካላቸውም፤
በ2020 እ.ኤ.አ ላይ የአፍሪካ አገራት ሻምፒየንሺፕን (ቻን) ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ አስችለዋል፡፡ በወቅቱም ይህን መስተንግዶ ማሳካታቸውን አስመልክቶ አቶ ጁነዲን ሲናገሩ ‹‹የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በስፖርት መሰረተልማት የደረስንባቸውን ደረጃዎች ከግምት ውስጥ አስገብቷል፡፡ ስለዚህም ቻንን በማስተናገድ  የተሰጠንን ዕድል በመጠቀምና  ስኬታማ በመሆን የአገሪቱን እግር ኳስ ለማነቃቃት እና ገፅታ ለመገንባት እንፈልጋለን::›› ብለው ነበር፡፡
አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው ፌደሬሽን ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቀድሞውን አይነት የአህጉራዊ ውድድር መስተንግዶ እንደ እቅድ ሊሰራበት መቻሉ ያጠያይቃል፡፡ የቻን መስተንግዶ ከመሰረዙ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ደግሞ በቀድሞው ፌደሬሽን አማካኝነት በ2025 እ.ኤ.አ ላይ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ የቀረበው ጥያቄ እና የተደረጉ ጥረቶች የፈጠሩት አበረታች ተስፋዎች እንዳይበላሹ ነው፡፡ ካፍ በአህጉራዊ ውድድሮች መስተንግዶ ለምስራቅ አፍሪካ ብዙም ትኩረት የለውም፡፡ ይህን በመገንዘብ የቀድሞው ፌደሬሽን አህጉራዊውን ተቋም በዚህ አቅጣጫ እንዲያስብ በርካታ የማግባባት ስራዎችን ተሰርተዋል፡፡  ይህን ተከትሎም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በ2025 እ.አ.አ የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያስተናግዱ የመጨረሻ እጩ ካረጋቸው 3 አገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗም ተገልፆ ነበር፡፡

አዘጋጅ ለመሆን የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ሁኔታዎች
 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫና ለቻን ውድድር አዘጋጅነት ብቁ የሚላቸው አገራት በሆቴል እና መስተንግዶ፤ ቢየያንስ አራት አለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ ስታድዬሞች ከእነ ልምምድ ስፍራቸው፤ በቂ የአየር እና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት፤ አስተማማኝ ደህንነት እና ፀጥታን ማሟላት መቻላቸውን በዋና መስፈርቶቹ ይመለከታል:: ኢትዮጵያ አህጉራዊ ውድድርን ለማስተናገድ የምትችልብት ደረጃ ለመድረስ ከሌሎች አገራት ብዙ ልትማር ያስፈልጋል፡፡ ለማንኛውም አህጉራዊ ውድድር በሚደረግ ዝግጅት በእግር ኳሱ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን የአዘጋጅ ኮሚቴ የቦርድ አባላት በማሰባሰብ ውድድሩ ከመዘጋጀቱ ቢያንስ ለ3 እና 4 ዓመት በፊት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ብሄራዊ የአዘጋጅ ኮሚቴ ሚኒስትሮች፤ ዲኤታዎች፤ ባለሃብቶች፤ ታዋቂ ሰዎች፤ ትልልቅ እና ባለታሪክ ስፖርተኞች እና ሌሎችንም ያካተተ እና እስከ 30 አባላት በቦርድ አባልነት የሚሰሩበት ነው፡፡ ከዚሁ ቦርድ ስር ደግሞ ቢያንስ አምስት የተለያዩ ኮሚቴዎች መመስረት አለባቸው፡፡ ንዑስ ኮሚቴዎቹ የውድድር አካሄድን፤ ፀጥታ እና ደህንነትን፤ የፋይናንስ ጉዳዮችን፤ የማርኬቲንግ እና የንግድ ተግባራትን፤ የሰው ሃይል ምደባን፤ የሆቴል እና የትራንስፖርት አቅርቦትን እንዲሁም የሚዲያ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነትን ያንቀሳቅሳሉ:: ከመንግስት የበጀት ድጋፍ፤ ከካፍ የገንዘብ አስተዋፅኦ፤ ከስፖንሰርሺፕ እና ከተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ገቢ ይሰባሰባል፡፡ የውድድር ማካሄጃ፤ የአስተዳደር ስራዎች፤ የጉዞ እና የሆቴል አገልግሎት እና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን በሚኖሩት ወጭዎች ላይ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ባለድርሻ አካላትን መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡   በሁሉም አዘጋጅ ከተሞች የውድድሩ ብሄራዊ ኮሚቴ አብሮ የሚሰራበት ምክር ቤት፤ ከአምስት በላይ ከብሄራዊ ኮሚቴው ጋር ተፈራርመው የሚሰሩ የመንግስት ተቋማት፤ ለ16 ብሄራዊ ቡድኖች በአዘጋጅ ከተሞች ሙሉ የስልጠና ሜዳ እና ከስታድዬም ከ5 እስከ ሰላሳ ደቂቃ ጉዞ ያላቸው የማረፊያ ሆቴሎች፤ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟሉ ቢያንስ አምስት ስታድዬሞች፤ ከ200 በላይ ከብሄራዊ ኮሚቴው ጋር የሚሰሩ ሰራተኞች፤ ከ2500 በላይ ውድድሩን የሚያስተናግዱ በጎፍቃደኞች፤ የውድድሩ ኦፊሴላዊ ድረገፅ፤ ውድድሩን የሚገልፅ መርህ፤ የውድድሩ መለያ የሆነ ምልክት እና ሎጎ፤ በከፍተኛ ደረጃ ውድድሩን የሚያስተዋውቁ ባነሮች፤ ቢልቦርዶች እና ፖስተሮችም አንድ አዘጋጅ አገር አህጉራዊ ውድድርን በተሳካ መንገድ ለማስተናገድ የሚያከናውናቸው ስራዎች ናቸው፡፡ ማንኛውንም አህጉራዊ ውድድር በማስተናገድ ለሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በቂ ተመክሮ እና አቅም ይገነባል፡፡ የስፖርቱን አስተዳደር ሁለገብ አቅም ያሳድጋል፡፡ አለም አቀፍ ትኩረት ይገኝበታል፡፡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ምክንያት ይሆናል፡፡ የስፖርት እድገትን ለማቀላጠፍ ያግዛል፡፡

Read 6335 times