Saturday, 20 April 2019 14:14

ቅፅል ስም ፍለጋ

Written by  አንለይ ጥላሁን
Rate this item
(10 votes)

ቦታው  አዲስ አበባ ነው፡፡ ሰፈሩ ደግሞ ጨርቆስ፡፡ ከሰማይ ላይ የሚወረወር ንስር የመሰለው የሰፈሩ አቀማመጥ በእጅጉ  ቀልብ ይገዛል፡፡ ግራ ቀኝ የተወጠሩት ክንፎቹ የተበጣጠሰ፣ የነተበ እራፊ ለብሰዋል:: የዘመንን መልክ ከማሳየታቸው ባሻገር ታመዋል፤ ያቃስታሉ፡፡
ከነዚህ በአንደኛዋ እራፊ ተጠልያለሁ:: ዝናብም፣ ውሽንፍርም፣ ቁርም፣ ረሃብም… የማስታገስ አቅም እንደሌላት አምናለሁ፡፡ ግና ተጠልያለሁ፡፡ ሽንቁሯን መርጫለሁ፡፡
ሽንቁሯ … በሁለት ሜትር ከፍታ … የቆርቆሮ ጣራዋ ፈጓል፡፡ ግድግዳዎቿ በጭቃ የተለደሱ፣ ንቃቃቶች ዳግም የሞገጉባት፣ የእንሽላሊትና የበረሮዎች መርመስመሻ ጠለል  ናት፡፡
በዚች አነስተኛ ክፍል ውስጥ የእድሜ ሚዛን የማይገባቸው የጊዜ እቁብተኞች ተሰባስበዋል፡፡ አንድም ሊበሉ፤አንድም ሊያስበሉ፡፡
በርከት ያሉ በመሆናቸው ኑሯቸውን የሚያሳብቁ፤ ጮኸው የሚናገሩ ወንበሮች ላይ ተጣብቀዋል፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ የተለያዩ ሀሳቦች ይሰነዘራሉ፡፡ ሁሉም ትዕዛዞች ናቸው:: ግን አንዳቸውም ተነስተው ሲተገብሯቸው አይታዩም፡፡ ቧልት ይደገሳል፡፡
በዚህ መሃል አለባበሱ ከቁመናው፣ ፈገግታው ከባህሪው፣ምግባሩ ከልቡ ጋር የሰመረ መልከመልካም  ብቅ አለ፡፡ ናላዋ የዞረ ይመስል ጥቂት ተንገዳግዳ ቀጥ ያለችው ደሳሳ ዳሳችን ቀልብ እየገዛች፣ እየሰከነች ፍፁም ፀጥታ ውስጥ ተዘፈቀች፡፡
“የዛሬ ውጤታችሁ መልካም አይደለም!” አሉ እኒህ መልከመልካም፡፡
ጥቂት የድምፅ መርመስመስ ከተሰማ በኋላ …
“ይሄ ይጣልና የበቀደሙ ይያዝ!” አለ አንድ ወጣት፤ ግንባሩን ቋጠር ፈታ እያደረገ፡፡ ሰለሞን ነው፡፡
“ለመሆኑ ትናንት ተጥሎ ዛሬ የሚባል ነገር አለ እንዴ?  ዛሬስ ተጥሎ ነገ ይኖር  ይሆን? አትሳሳቱ፤ ሁለቱም ህልውናችሁ ነው፡፡ የእናንተ መልክ፡፡ ትናንትን አቅርቦ የሚያሳይ፤ ነገን የቋጠረ፡፡” አሉ ፤ንግግሩ ኮርኩሯቸው፡፡
በድጋሚ ደሳሳ ጎጇችን  መንገዳገድ ጀመረች:: ድምፆች ተርመሰመሱባት፡፡
“አንዴ…አንዴ… ፀጥታ… ማናጆ በመሆን  ህልውና የለም፡፡ ቱቦ ውስጥ እንደሚጎርፍ  ቅራቅንቦ …ምርጫም የለ…መንጎድ ብቻ…ቅኝታችሁን አስተካክሉ፡፡” አሉና አንገታቸውን ደፉ፡፡
ቤቷን ግራ ቀኝ ተመለከቱ፡፡ ጣራዋን አስተዋሉ፡፡ የቆሙበትን መሬት መረመሩና… ፊታቸውን ቅርጭም አንደበታቸውን ግጥም አድርገው ተመሙ… ”ዳግም ህልውና ይኖር  ይሆን?” ብለው ጠየቁ፡፡ ከንፈራቸው በጥቂቱ ተንቀሳቀሰ…ጮክ በማለት  “እናንተ ጎረምሶች፤ እውነት መዳፋችሁ ውስጥ መሆኑን  አታውቁምን? የሰው ባህሪስ ስለ መሆኑ ትጠይቃላችሁን? የጠባይንና የባህሪን አንድነትና ሁለትነትስ ተረድታችኋልን...?”  በአርምሞ ተመለከቱ፡፡ የጉልምስና ፀዳል ሲያበራ በፊታቸው ላይ ይታያል፡፡
የተሸከመችው እንስራ ከውስጧ እሳት ጋር ተዳብሎ እንደሚያናውጣት ኮረዳ የምትናውዘው ጎጇችን ስታቃስት ይሰማኛል፡፡
በረከት ፈገግ አለ…
“እናም ሬድዮናችን ከማሰራጫ ጣቢያው በሚስጢር የተላኩትን ድምፆች እንደሚተረጉምልን ሁሉ ታላቁ ሀይልም እውነትንና ህይወትን በውስጣችንና በዙሪያችን አስቀምጦልናል፡፡ ወሳኙ ነገር የሬድዮኗን ሚና መጫወቱ ነው፡፡ እልፍ አእላፉ ይህን አያደርግም፡፡ ግና ይህን ለማድረግ ጠባይን ማረቅ ያስፈልጋል፡፡ ባህሪ ለሰው ልጆች የተሰጠ ፀጋ ነው፡፡ ጠባይ ደግሞ በልምምድ የሚገኝ ነው፡፡ አውሬነት፣ እንስሳዊነት፣ሰዋዊነትና መላዕክትነት  ጠባዮች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ይበልጡ ባውሬነት፣ በርከት ያለው ደግሞ በእንስሳዊነት ጠባይ ተደብቋል፡፡ እጅግ ጥቂቱ ሰዋዊነት ስር ተጠልሏል፡፡ አንድ ሁለቱ አማልክት (መልዐክ) ሆነዋል፡፡ ሁሉም ግን የስራ ውጤቶች  ናቸው:: ‘ሰውን ሰው ያደረገው ሥራው ነው‘ እንዳሉት ብልህ አያቶቻችን… የስራችን ውጤት፣ የጥረታችን ልኬት ሚዛኑ ይሄው ነው፡፡ የውስጠኛው እንደሆነው ሁሉ የውጨኛውም ይሆናል፤ የላይኛው እንደሆነው ሁሉ የታችኛው ይሆናል… ነውና ነገሩ፡፡
በሉ ይበቃል … እኔም ልሂድ እናንተም  ሂዱ…  በማለት ተሰናብተው ወጡ፡፡
አሁን ጥቂት የነፍስ ጥያቄ የተቀሰቀሰ ይመስላል፡፡ ቤቱ በአርምሞ ተወጥሯል፡፡ ሁሉም ማስታወሻቸውን ዘጉ… ስለ መምህራቸው አሰላሰሉ…ለየብቻ አወሩ… በመንፈስ ህብረት ለመፍጠር ዳከሩ… በስጋም ለመጣመር በነጎዱበት ነጎዱ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው:- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3027 times