Saturday, 27 April 2019 10:04

“እናትና አባቴን በጊዜ ቀብሬ መንግሥት እጦራለሁ አንጀቴን አሥሬ”

Written by 
Rate this item
(11 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ መንደር በየዕለቱ የሚፈጠር አንድ ችግር ነበር፡፡ የችግሩ መንስዔ በየማታው እየሰከረ የሚመጣ አንድ ወንደላጤ መኖሩ ነበር፡፡
የሚፈጥረው ዋንኛው ችግር፣ ልክ እሱ ሲመጣ የመንደሩ ውሾች መጮህ መጀመራቸው ሲሆን“በእኔ ላይ፣ በእኔ ላይ ነው የምትጮሁት? ማን መሰልኳችሁ? ሁሌ ስመጣ ቅንጣቢ ስጋ የምሰጣችሁ እኮ ነኝ? በዓመት በዓልማ ማነው አስቦ ስጋ ይዞላችሁ የሚመጣው? ልክ እንደ ዛሬው ማለቴ ነው!?”
ውሾች መጮሃቸውን አላቋረጡም፡
ያ ሰካራምም እንደ ወትሮው ድንጋይ ይለቃቅምና መወርወር ይጀምራል፡፡ ይስታቸዋል - በስካር ዐይኑና በስካር እጁ በመሆኑ፡፡ በአካባቢው ያለውን የብረትም፣ የቆርቆሮም በር ያናጋዋል፡፡
የብረትና የቆርቆሮውን በር፣ እንዲሁም ውሾቹን ያልፍና መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ሌላ ብረት በር ፊት ለፊት ይደርሳል፡፡ ሌሎች ውሾችም ብቅ ብቅ ይሉና ይጮሁበታል፡፡
“ኧረ በፋሲካ ምድር አታሳብዱኝ?” ይልና ድንጋዩን ሰብስቦ መወርወሩን ይቀጥላል፡፡ ይስታል፡፡ የሌሎቹን በር ይመታል፡፡ እንዲህ እንዲያ እየሆነ ለወራት ሰፈር ሲበጠብጥ ይከርማል፡፡ የሰፈሩ ሰው በዚህ ሰው ጉዳይ ላይ መመካከር ጀመረ፡፡
“እንደው የዚህን ሰካራም ነገር ምን ብናደርግ ይሻላል?”
አንዱ።-
“በራችን የተሰበረብን ሰዎች እንሰብሰብ”
ሁለተኛው፤
“ምን ልንሆን?!”
ሦስተኛው፤
“እንመካከርና፣ መፍትሄ እንድናመጣ ነዋ?!”
አራተኛ፤
“ይሄ በጣም መልካም ሀሳብ ነው! የሰፈሩ ሰው ይንቀሳቀስ፡፡ ይምከርና መላ ያብጅ እንጂ እስከመቼ አንድ ሰው ተሸክመን እንዘልቃለን? ላንዴም ለሁሌም ዘላቂ ዘዴ እንዘይድ!”
ሁሉም በሀሳቡ ተስማሙ፡፡
አንድ እሁድ ማለዳ የመንደሩ አዛውንቶች እንዲያገኙት ቀጠሮ ተያዘ፡፡
ተገኘላቸው፡፡
የፋሲካ እለት ጠዋት፡፡
እንዲህ አሉ፤ የአዛውንቶቹ ተወካይ፡-
“አየህ፤ አንተ የመንደራችን ህዝብ ውድ ወንድም ነህ፤ ስለዚህ ቀረብ ብለን ልናይህ ነው አመጣጣችን”
እሱም፤
“ስለምን ጉዳይ ልታማክሩኝ አሰባችሁ?”
ሽማግሌዎቹ፡-
“ወንድማችን፣ መቼም መጠጥ ጎጂ መሆኑን ማንም አያጣውም፡፡ አንተም ጎጂነቱን አትስተውም!”
እሱም፤
“እንዴታ! እንዴት እስተዋለሁ?”
ሽማግሌዎቹ፤
“አየህ አምሽተህ ስትመጣ ከውሾች ጋር ትጣላለህ፤ ድንጋይ ትወረውራለህ፡፡ የሰው በር ትመታለህ፡፡ ይሄ ሁሉ የመነጨው አምሽተህ በመምጣትህ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ወንድማችን ሆይ፤ እባክህ አታምሽ!”
እሱም፤
“ውይ አባቶቼ፤እንዲያው በከንቱ አደከምኳችሁ! አሁንማ ማምሸት ትቼ! አሁንማ ተመስገን ነው፡፡ እያነጋሁ ነው የምገባው!”
***
ኢትዮጵያ ትንሳኤ ያስፈልጋታል፡፡ የዲሞክራሲ መስዋዕትነቷ አብቅቶ የተባ ትንሳኤ ያሻታል፡፡ የወገናዊነት በደሏ ይሻር ዘንድ ትንሳኤ ያስፈልጋታል፡፡ የፍትህ እጦት መከራዋ ይወገድ ዘንድ ትንሳኤን ትሻለች፡፡ በዕድሜዋ ያልገጠማትን ዓይነት የመፈናቀል አደጋዋ ለአንዴም ለሁሌም ይታገድ ዘንድ “ኢትዮጵያ ታበፅዕ እደዊሃ ሀበ እግዚአብሔር” መባሉ ዛሬም መኖር አለበት (ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች እንደማለት ነው) ፍትህ ርትህ ያልተጓደለባት ለአንዱ እናት፣ ለአንዱ እንጀራ እናት እንዳትሆን፣ ልጆቿ እንዲታገሉላት ትፀልያለች::  የትምህርት ሥርዓቷ ደክሞ ከሚያንቀላፋበት ቀና ብሎ ወደ ጥንቱ ጠንካራ ንቃቱ ይመለስ ዘንድ አማልክቱን ትማለዳለች፡፡ የህዝብ ጤነኝነት የአገር ጤና ነውና የጤናም ትንሳኤ ያሻታል፡፡ ከለማበት የተጋባበት እንዲሉ፣ የጎረቤት አገሮች በሽታ እንዳይተላለፍባትና ድንበሯ ይከበር ዘንድ ህዝቧ አንድነቱን እንዲጠብቅ፣ የውስጥ ጥንካሬው በይዘትም በቅርፅም እንዲታነፅ አራሽ፣ ቀዳሽ፣ ተኳሽ ልጆቿ እንዲበረቱ አምላኳን ትማጠናለች::  የዘንድሮው ትንሳኤ የተጀመረው ለውጥ የሚጠናከርበት ይሆን ዘንድ የህዝቦቿ ልቦና በቅንነትና በፍቅር እንዲከፈት ፀሎቷን ማሰማት አለባት፡፡ ከሚያወሩ አፎች ይልቅ የሚሰሩ እጆች መድህኖቿ መሆናቸውን ልጆቿ ማወቅ አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ በመታገል እንጂ በዕድል እንደማትለማ መገንዘብ ግዷ ነው፡፡
ዛሬም ከገሞራው ጋር፤
“… ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር”
…ማለት አለባት፡፡
መሪዎች የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ አለባቸው፡፡ ፖለቲካዊ ቅሬታውንና ኢኮኖሚያዊ ብሶቱን ከልብ ማዳመጥ ዋና ነገራቸው ነው፡፡ ህዝብም ጉዳዩን ሁሉ ለመሪዎች ጥሎ እጆቹን አጣጥፎ መቀመጥ የለበትም፡፡ አገር “ቀኗ ሲደርስ ትቀናለች” የምትባል የምኞት አስኳል አይደለችም፡፡ “መንገዶች ሁሉ ወደ ልማት ያመራሉ” ብሎ መመኘት በሥራ ካልታገዘ ምኞት ብቻ ነው፡፡ ዱሮ ስለ ትግል ሲወራ፤ “ጉዟችን ረዥም፣ ትግላችን መራራ ነው” ይባል ነበር፡፡ ይሄንን ሲሰብክ የቆየ ካድሬ ቀን ጎድሎበት ታሰረ፡፡ መፈክሩንፈተሸውና፤
“ይሄ አግባብ አይደለም፡፡ ‹መራራ ከሆነ አጠር ይበል፣ ረዥም ከሆነ ደግሞ ጣፈጥ ይበል እንጂ መራራም ረዥምም ማድረግ በጭራሽ በጎ አካሄድ አይደለም!” አለ አሉ፡፡
ጊዜ የማይለውጠው ነገር የለም፡፡ ለጊዜ ጊዜ መስጠት ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ ምናልባት ከደራሲ ከበደ ሚካኤል ጋር፤
“ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰለሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት ራሱ እሚሞት ምን ጊዜ እንደሆን”
…ማለትም ያባት ነው፡፡
የዛሬውን ትንሳኤ የመንፈስ እርገት እንዲሆን ከፈለግን፣ ከልባችን እንነሳ፡፡ ከዚህ ቀደም፤
“እናትና አባቴን በጊዜ ቀብሬ
መንግሥት እጦራለሁ አንጀቴን አስሬ”
…እንል የነበረውን ቀይረን፤ ለውጡን እንዴት እናግዝ? የሚለውን አቅጣጫ ማሰብ አንድ መላ ነው፡፡ በዚህ መላ ትንሳኤውን ትንሳኤ እናደርገው ይሆናል፡፡
መልካም የትንሳኤ በዓል!!

Read 12997 times