Saturday, 27 April 2019 10:12

የፋሲካው ፍየል

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(8 votes)

 አባታችን ቀብራራ ነው፡፡ አንቀባርሮ ነው ያሣደገን፡፡… ግን ደሞ ነጭናጫ ነው፡፡ አንዳንዴ ወፈፍ ያደርገውና ያልሆነ ነገር ያመጣል፡፡… ዐውደ ዓመት ግን ሁሌ እንዳሥደሠተን ነው:: ልብስ የሚገዛልን መርጦና አሥመርጦ ነው:: በግ ይሁን ፍየል፤… ዶሮ ይሁን ቅርጫ አይኑን አያሽም!... በጓደኞቻችን ፊት ሁሌ እንደኮራን ነው፡፡
ገንዘብ አይሠሥትም፡፡ ግን መርህ የሚል ጣጣ አለው፤ የሀገር ሀብትና ክብር የሚለው ዲስኩር አያጣም!... ቡና ነጋዴ ስለሆነም ኪሣራ አይፈራም። የቡና ገበያ ከፍና ዝቅ ስለሚል፤ ሣይለምደው አይቀርም፡፡ አንዴ ደግሞ ቆዳና ሌጦ መነገድም ጀምሮ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ይልካል፡፡… ጠንቃቃ ነው። ሌጦ እንዳይቀደድ፣ ቆዳም እንዳይበላሽ ሰዎችን ያሥተምራል፡፡
በትምህርት ብዙ አልገፋም፤… ግን ጥሩ ያሥባል። ለነገሩ እኔስ ገና አሥረኛ ክፍል አይደለሁ… አለታ ወንዶ ደግሞ አገሬውም ጥሩ ነው፡፡.. ተማሪን ያበረታታል፡፡
ለፋሲካ በዐል እኛ ቤት የተለየ ክብር አለው።
የአባቴ ዘመዶች ቤተክህነት አካባቢ ስለ ነበሩ ያሳደሩበት በጎ ተፅዕኖ ይመሥለኛል፡፡
‹‹የነፃነታችን ቀን!›› የሚል የጠለቀ ስሜት አለው::. ሕማማቱንም ይታመማል… ጠልቆ ያሥባል::… ጎልጎታ አናት ላይ የወጣ ይመሥል፤ ላቡ ችፍ ይላል፡፡ ጌቴሰማኔ የተንበረከከ ያህል ያምጣል።
በመንፈንሳዊው ብቻ አይደለም፤ለሥጋዊውም በዐል ድምቀት በግ ይሸምታል፡፡
በአንደኛው ፋሲካ ግን የፍየል ሙክት ነበር የገዛው፡፡ ታዲያ እኔና ታናሽ ወንድሜ አጥናፉ ፍየሉ መገዛቱን ባንጠላም፤ ቀደም ብሎ መገዛቱን ግን አልወደድነውም፡፡ ለእርሱ ሳር ማጨድ፤ ውሃ ማጠጣትና መጠበቅ፤ ከሚበላው ሥጋ ጋር ሲሠላ ትርፉ ያን ያህል ጮቤ አያሥረግጥም፡፡ በዚያ ላይ ፍየሉ ሾልኮ ጎረቤታችን ያሉት ሽማግሌ ጓሮ ከገባ፤ በቆመጥ ወገቡን ይቆምጡታል፤ በጦር ይሠቀሥቁታል፤ ቀልድ አያውቁም፡፡ ይህ ለኔና ለአጥናፉ ራስ ምታት ነው፡፡ የበዐል ስሜታችንን ሁሉ ይረብሸዋል፡፡
አባቴ ምንቸገረው! እርሱ ሥራ ውሎ፤ ጂንና ቢራውን ጠጥቶ ሲመጣ፣ ፍየሉ ካልተመዘነ ሊል ይችላል፤ ፀጉሩ ቆመ፤ ጢሙ አደገ፤ ጥፍሩ ተንሻፈፈ፤ እያለ ከመገምገም አይመለሥም፣ኧረ ሙቅ ሻወር ይምጣም አለማለቱ እሱ ሆኖ ነው፡፡
ወንድሜ አጥናፉ ተናድዶ፤‹‹..ምነው እንደነ ዘሪሁን ቤት ቅርጫ በገባን!›› አለ፡፡ ምን ያህል እንደመረረው ያወቅሁት በዚያ ነው፡፡ ሌላ ጊዜም ዘሪሁንን ያበሸቀዋል፤ ‹‹ሙዚቃ አልባው የእነዘሪሁን ቤት!›› እያለ ያሾፍበታል። የበግ ፍየል ድምጽ የለም!›› ለማለት ነው። አንዳንዴ ደሞ ‹‹አባትህ ሬሳ መጎተት ይወድዳሉ።” ይለው ነበር:: እኛ ነን ያሥተውነው:: አሁን ግን የፍየሉ ነገር አበሳጨው፣ በተለይ ትናንት ማምሻ፣ የጎረቤታችን ሽማግሌ ፍየሉን በጦር ከወጉት በኋላ ሁላችንም ተናድደናል::… በርግጥ ፈተናውም ቀላል አይደለም፡፡
በዚያ ላይ በግ ቢሆን ኖሮ ምንም አልነበረም። ፍየል ግን ዝም አይልም፡፡ ገና ጫፉ ሳይነካ ነው አገር ይያዝ የሚለው፡፡ ደግነቱ ትናንት አባቴ በጣም አምሽቶ ነበር የገባው፡፡ “ሰርግ ነበረብኝ” ሲል እናቴ፤ “በሁዳዴ የምን ሰርግ አለ! ደ‘ሞ” ብላ ስቃበታለች። ተሣስቶ ነው፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ሲቀመቅም ነበር ያመሸው፡፡
እኔና አጥናፉ ግን መላ አላጣንም፡፡ ፍየሉ እየበጠበጠ ሲያስቸግር ትንሽ ካቲካላ ቢጤ ለቀቅንበትና አሰከርነው፡፡
ከዚያ በኋላ፣ አፉን በጨርቅ ጥፍር አድርገን አሳደርነው፡፡ የአባቴ ነገር አንዳንዴ አይታወቅም:: ባይደክመው ኖሮ የፍየሉን አፍ ካለሸተትኩ ሊል ይችላል፡፡ አንዴ እንዲያውም ራሱ የጠጣው ኡዞ ሸትቶት፣ “በጉን ኡዞ ያጠጣው ማን ነው?” ብሎ፣ እናቴ ሆድዋ እስኪቆስል ስቃበታለች፡፡ ትናንት ግን ቢያየው ካቲካላ ማን አጠጣው? ይለን ነበር፡፡ ለነገሩ ዘዴ አናጣም፤ “አተላ ጠጥቶ ነው” እንለው ነበር፡፡
አሁን ስጋታችን እስከ ፋሲካ ድረስ ነው፡፡ በጦር መወጋቱን ካየ፣ከሰውየው ጋር ሊጣላ ይችላል። እኛንም “ለምን አትጠብቁም ነበር›› ብሎ መከራ ያሳየናል። አልፎ አልፎ ደግሞ እንደ መንግስትም ያደርገዋል:: የሀገር ሀብት … ልማት … እያለ ይፈላሰፋል፡፡
ወንድሜ እንዲያውም፤
“…ይህ ሰው ማዘጋጃ ቤት ሰርቷል እንዴ?” ይላል:: እንሳሳቃለን፡፡ አባቱ አላሳደጉትም፣ ነጋዴ አጎቱ ቤት ነው ያደገው፡፡ እርሳቸውም እዚሁ አለታ ወንዶ የታወቁ ቡና ነጋዴ ነበሩ፡፡
ከአጥናፉ ጋር ተቀምጠን በሁለት ነገር መከርን፡፡ አንዱ አባታችን ፍየሉ መወጋቱን እንዳያይ መከላከል ሲሆን፣ ሁለተኛው ቆዳው የሚገፈፍ ቀን፣ አባዬ ቆዳውን የማያገኝበት ዕቅድ መንደፍ ነበር፡፡ ግን እንዴት እናድርግ?
አጥናፉ አንድ ዘዴ ዘየደ፡፡ ማምሻ ማምሻ የፍየሉ ድምፅ እንዳይሰማ፣ መዝሙር መክፈት! … አባዬ ደግሞ የበገና ድምፅ ከሰማ አይችልም፤ ልቡ ወደ ፈጣሪ ያመልጥበታል፡፡ ቅዝዝ ይላል:: ወደ ክርስቶስ ይሄዳል ! ይህቺን ዘዴ አሰብን፡፡
ሌላው ፍየሉ የሚገፈፍ ቀን፣ ቀድመን የተመሳሳይ ፍየል ቆዳ ገዝተን አባታችንን ለማታለል አሰብን።
ያዕቆብ አብረሃምን እንዳደረገው ማድረግ አለብን። በተለይ አጥናፉ ቅዱስ መጽሐፍ ስለሚያነብብ ዘዴ አያጣም፤ ተሳሳቅን፡፡ ከዚያ ለእማዬም ነገርናት፣ ሳቀችና ተቀበለችን፡፡
ምን ያህል እንደሚሳካልን የምናውቀው ግን ከአባዬ ጋር ፊት ለፊት በጉዳዩ ላይ ተጋጥመን ስናልፍ ብቻ ነው፡፡ … ሆሣዕናም አልፏል፡፡
ህማማት ... ነው። አምስት ቀን ሲቀረው አባዬ ድንገት አንድ ትልቅ ዳለቻ ሙክት እያስጎተተ መጣ፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን ጎረቤቱ ሁሉ ተደነቀ፡፡ በቀደም የፍየል ሙክት፣ ዛሬ ደግሞ የበግ ሙክት! … ምን ሊያደርግለት ነው? የሁላችንም ጥያቄ ነበር፡፡
እቤት ገብቶ ሰራተኛው ፍየሉን ይዞ እንዲሄድ አዘዘው፡፡
“የት ነው አባዬ? .. የት ሊወስደው ነው?” አለ አጥናፉ፡፡
“ፋሲካ የክርስቶስ በዓል ነው! … ክርስቶስ ደግሞ የታረደው በግ፤ ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ የተነገረለት ነው፡፡” ሲል አጥናፉ አንገቱን ነቀነቀ፤እኔ ምኑንም አላውቀው፡፡
“እሺ ፍየሉስ የት ሊሄድ ነው?”
“አይ ሥጦታ ሊሰጥ ነው፡፡”
“ለማን?”
“ለቀበሌው ሊቀመንበር! … ሰሞኑን …. ለሚደረገው ችግረኞችን የመርዳት መዋጮ፣ ሰጥቼዋለሁ!”
“ግሩም … ግሩም … አባዬ!” ብለን አደናነቅነው፡፡
አባዬም ፊቱ ብርሃን ለበሰ፣ አንዳች ፌሽታ ገፁ ላይ ፈነጠዘ፡፡ እናቴ ግን እንደፈራች ነገረችን፡፡ .. የተወጋው ቦታ እንዳይታይ!
… ፋሲካ … ደረሰ፡፡ ጧት በጉ ታርዶ ሁሉም ነገር አበቃ፡፡ እኛም ከዕዳ ተገላገልን ብለን ተረጋጋን፡፡ … ቡና ተፈልቶ፣ ቄጠማ ተጎዝጉዞ፣ ፈንድሻ ፈንድቶ … ከብበን ሳለ በር ተንኳኳ፡፡
በሩ ሲከፈት ደነገጥን፡፡
“ጋሼ ግባ! … ግባ!”
የቀበሌው ሊቀመንበር፣ ፍየል የሸጠላቸው አቶ ፋላስ ናቸው፡፡
“ጋሽ ደስታ፤ይህን ካንተ አልጠብቅም! … የቆሰለ ፍየል፣ ለቆሰለ ሕዝብ!”
አባቴ ተስፈንጥሮ ተነሳ፡፡
“ለምንድነው?”
“ፍየሉ ቁሥላም ነው!”
“አይደረግም!” አለ አባቴ፡፡
የጎረቤታችን ሽማግሌ መጡ፡፡ …
“ይቅርታ! … የወጋሁት እኔ ነኝ! … ተሳስቻለሁ:: … ለአረዊያን የሚሰጥ ነው አሉ!....”
እርሳቸው ሌላ በግ ይዘው መጡ!
አባቴ ወደ እኛ ዞሮ ተቆጣ፡፡
“ፍየል ማገድ ያቅታችኋል?!”
“ፍየል ማገድ ከባድ ነው” አለች እናቴ፡፡
የጎረቤታችን በግና የአባቴ ፍየል ተቀየጡ፡፡ ሁለቱም ለአረጋዊያን ተሰጡ፡፡

Read 2679 times