Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 02 June 2012 09:11

የትኛውም ሰበብ ከስኬት አያደናቅፍም!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ህይወትዋ እንደ ቦሊውድ ፊልሞች ሴራ (plot)  ነው  - በርካታ መሰናክሎችን ተጋፍጦ በደስታ በሚቋጭ ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን፡፡ በህንድ ማህበረሰብ ዘንድ በንቀት ከሚታየው ዳሊት ከተሰኘው የህብረተሰብ ክፍል የወጣችው ካልፓና ሳሮጅ፤ ያልደረሰባት መከራና ስቃይ የለም፡፡ በቤተሰብዋ” በማህበረሰብዋና በትምህርት ቤት ሳይቀር ብዙ ግፍና በደል ቀምሳለች፡፡ ሲመራት ህይወትዋን ለማጥፋት ሞክራ ነበር - አልተሳካላትም እንጂ፡፡ በህንድ እንደ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል ከሚቆጠረው ዳሊት የተወለዱ ህንዳውያን ለዘመናት አድልዎና መድልዎ ሲደርስባቸው እንደኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ካልፓናም የዚህ የበደል ፅዋ ገፈት ቀማሽ እንደነበረች ለቢቢሲ ተናግራለች፡፡ “የአንዳንድ ጓደኞቼ ወላጆች እቤታቸው እንድገባ አይፈቅዱልኝም ነበር፤ በትምህርት ቤት ውስጥ በሚደረጉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ አልችልም፤ ምክንያቱም ከዳሊት የተወለድኩ ስለሆንኩኝ”  ያለችው ካልፓና ፤ ይሄም ክፉኛ ያበሳጫት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ “ቢያንስ የሰው ልጅ አይደለሁም እንዴ እያልኩ ክፉኛ እረበሽ ነበር” ብላለች፡፡

አባትዋ እንድትማር ቢፈልጉም በአብዛኛው ቤተሰቦችዋ ግፊት የ12 ዓመት ታዳጊ ሳለች ባል እንድታገባ የተገደደችው ካልፓና፤ በባልዋ አገር ሙምባይ የጠበቃት የተጎሳቆለ የመከራ ህይወት ነበር “የባለቤቴ ታላቅ ወንድምና ሚስቱ ክፉኛ ያሰቃዩኝ ነበር፡፡ በትልቅ በትንሹ ፀጉሬን እየጎተቱ ይደበድቡኛል፡፡ በአካላዊ ጥቃትና በስድብ ስሜቴ እንክትክቱ ወጥቶ ነበር” ትላለች፡፡ በህንድ ባህል ትዳር ጥሎ መውጣት መጥፎ ስም ቢያሰጥም ካልፓና ግን እድሜ ለአባቴ ትላለች፡፡ አባትዋ ሊጠይቁዋት ሙምባይ ጎራ ባሉ ጊዜ ያዩትን ማመን አቃታቸው፡፡ ልጃቸው ከስታና ቡትቶ ለብሳ ሲያገኙዋት በድንጋጤ ፈዝዘው ቀሩ፡፡ አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሳይሉ ልጃቸውን አንጠልጥለው ወደ ቀዬአቸው፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ትዳርዋን ጥላ በመምጣትዋ ብዙ ቢያስወሩባትም” ካልፓና የመንደርተኛውን ወሬና ሃሜት ችላ ብላ ስራ ፍለጋ ላይ አተኮረች፡፡ የልብስ ስፌት በመማርም ስራ አፈላልጋ ተቀጠረችና በገቢ ራስዋን ቻለች፡፡ ሆኖም የማህበረሰቡ ጫና በረታ እንጂ አልቀነሰላትም፡፡ ይሄኔ ነው በህይወትዋ ላይ ለመፍረድ የወሰነችው፡፡

“አንድ ቀን ህይወቴን ለማጥፋት ወሰንኩ ፤ ከዚያም ሶስት ጠርሙስ የምስጥ ማጥፊያ መርዝ ጠጣሁኝ” ብላለች- ካልፓና ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ፡፡ ትረፊ ሲላት ግን አክስትዋ ደረሱላት፡፡ ክፍልዋ ሲገቡ በአፍዋ ምራቅ ደፍቃና ራስዋን ስታ መሬት ላይ እየተንፈራፈረች ነበር፡፡ እቺ ክስተት የህይወትዋ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነች የምትናገረው ካልፓና፤ ህይወቴን መኖርና አንድ ትልቅ ነገር ሰርቼ መሞት እንዳለብኝ ወሰንኩ ትላለች፡፡

በ16 ዓመትዋ አጎትዋ ወደነበሩበት ሙምባይ ተመልሳ በልብስ ሰፊነት ስራ የጀመረችው ካልፓና፤ የወር ደሞዝዋ ከአንድ ዶላር ያነሰ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በዚህ ተስፋ ቆርጣ ግን አልተቀመጠችም፤ ይልቁንም የኢንዱስትሪ የልብስ ስፌት ማሽን ላይ መስራት ተምራ ገቢያዋን አሳደገች፡፡ ገቢዋ በቂ እንዳልነበር የተገነዘበችው ከህመምዋ ልትድን ትችል የነበረች እህትዋን በመታከሚያ ገንዘብ እጦት በሞት ከተነጠቀች በሁዋላ ነው፡፡

“በጣም አዝኜ ነበር፤ ገንዘብ  በህይወት ውስጥ ትልቅ ትርጉም እንዳለውና የበለጠ ገንዘብ መስራት እንዳለብኝ የተገነዘብኩት ይሄኔ ነው” ትላለች - ካልፓና፡፡ እናም በቆራጥ የስራ ፈጣሪነት መንፈስ ተሞልታ መትጋት ጀመረች፡፡ ወዲያው ከመንግስት ብድር ወሰደች - የፈርኒቸር ቢዝነስ ለመጀመርና የልብስ ስፌት ስራዋን  ለማስፋፋት፡፡ በቀን ለ16 ሰዓት ትሰራ እንደነበር የምታስታውሰው ካልፓና፤ ዛሬም ድረስ ከዚህ ልማድ መላቀቅ እንዳልቻለች ትናገራለች፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ሁለተኛ ጋብቻዋን በፈርኒቸር ቢዝነስ ላይ ከተሰማራ ሰው ጋር መመስረቱዋንና ሁለት ልጆችም ማፍራታቸውን ለቢቢሲ ገልፃለች፡፡ በስራዋ መልካም ስምና ዝና ማትረፍ የቻለችው ካልፓና፤ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቆ የነበረውን Kamani Tubes የተባለ የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ተረክባ እንድትመራ ተጠየቀች፡፡ አላቅማማችም፡፡ ያቄውን ተቀብላ ወደ ስራው ገባች፡፡ “ሰራተኞቹ የችሎታቸውን ያህል እንዲጠቀሙ እፈልግ ነበር፡፡

ኩባንያውን ከውድቀት ማዳን ነበረብኝ፡፡ ቤተሰባቸውን የመመገብ ሃላፊነት ከተጣለባቸው የኩባንያው ሰራተኞች ጋር የምጋራቸው ታሪክ አለኝ” ብላለች፡፡ በእርግጥም ካልፓና ተሳክቶላታል፡፡ የማታ ማታ ኩባንያውን ከኪሳራ ማዳን ብቻ ሳይሆን ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያንቀሳቅስ ትርፋማ የንግድ ድርጅት ልታደርገው በቅታለች፡፡

“በጣም በትንሽዬ መንደር ውስጥ በማደጌ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሙምባይ ስመጣ ወዴት እንደምሄድ እንኩዋን አላውቅም ነበር፡፡ ዛሬ በከተማው ከሚገኙ ጎዳናዎች ሁለቱ በኩባንያዬ ስም ተሰይመዋል” ብላለች - ህይወትዋ የቱን ያህል እንደተለወጠ በአጭሩ ስትገልፅ፡፡

ዛሬ ኩባንያው  Kamani Tubes በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የመጡ ባለሙያዎች የሚሰሩበት እንደሆነም የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆነችው ራስዋ ካልፓና ትናገራለች፡፡

እንደ ራታን ታታ እና ሙኬሽ አምባኒ ከመሳሰሉት ዝነኛ የቢዝነስ ሰዎች ጋር ትውውቅ የመሰረተችው ካልፓና ፤ በ2006 (እኤአ) በስራ ፈጣሪነት ላሳየችው ቁርጠኝነት እጅግ ከፍተኛ ክብር ያለው ሽልማት ተሸልማለች፡፡ ስኬትና ዝና ግን የትውልድ ቀዬዋን አላስረሳትም፤ ዘወትር ከመጎብኘትዋም ባሻገር እርዳታ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ የበጎ አድራጎት ስራ እያከናወነች ትገኛለች፡፡

ከዳሊት ቤተሰብ የወጣችና እንስት መሆንዋ ብቻ ታሪኩዋን እጅግ አስደናቂ ቢያደርገውም በህንድ እንደሱዋ ካለው ቤተሰባዊ መሰረት ወጥተው የዋና ስራ አስፈፃሚነት ደረጃ ላይ የደረሱ እንስቶች ቁጥር እጅግ ኢምንት መሆኑ የካልፓናን ታሪክ የበለጠ አስደማሚ ያደርገዋል፡፡

“ልብህንና ነፍስህን ለስራህ ከሰጠህና ተስፋ ካልቆረጠክ ስኬት ልትቀዳጅ ትችላለህ”  የምትለው ካልፓና፤ በህይወትዋ የገጠሙዋትን ፈተናዎች ሁሉ ያሸነፈችው በዚህ የህይወትዋ መመርያዋ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

ይሄ መመርያ ዛሬም በ52ኛ ዓመት ዕድሜዋ ላይ ለምትገኘው ካልፓና ሳሎጅ ይሰራል፡፡ እቺን የስኬት ተምሳሌት የትኛውም ፈተና አላሸነፋትም - አድልዎና መድልዎ፤ ግፍና በደል፤ ስቃይና እንግልት ወዘተ--- ቢፈራረቁባትም አንዳቸውም ግን ከምትፈልገው ስኬት አላገዱዋትም፡፡ ለዚህ ነው የትኛውም ሰበብ ከስኬት አያደናቅፍም የምንለው፡፡ ጎበዝ ስኬት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው!

 

 

Read 3670 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 09:18