Saturday, 27 April 2019 10:39

ጥሪት የሚያሟጥጠው የኩላሊት ህመም

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

 • መንግስትና ባለሃብቶች ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠይቋል
  • ባንኮች ለህመምተኞች እገዛ ለማድረግ ተስማምተዋል
                
              አቶ መሐመድ ሀሰን የ60 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት በኩላሊት ህመም እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ይናገራሉ:: የአራት ልጆች አባትና ባለትዳር የሆኑት አዛውንቱ፤ በሳምንት ሶስት ቀን የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) ለማድረግ 4ሺህ 500 ብር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በወር 18 ሺ ብር ማለት ነው:: ይሄ ደግሞ እንኳንስ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደሳቸው በህመም ላይ ለቆየ ሰው ቀርቶ ለማንም ቢሆን  ከፍተኛ ወጪ ነው፡፡ “ሌላ ንብረቴን ሁሉ ሸጬ ጨርሻለሁ፤ አሁን የቀረኝ የመኖሪያ ቤቴ ነው” የሚሉት አቶ መሐመድ፤ መኖሪያ ቤታቸውን ሸጠው ገንዘቡን ለህክምና በማዋል ህይወታቸውን ለማቆየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ “እስከ ዛሬ ህይወቴ የቆየው በወንድሞቼ እርዳታ ነው፤ አሁን ግን ቤተሰቤን በትኜ መኖሪያ ቤቴን ለመሸጥ በዝግጅት ላይ ነኝ።” ብለዋል፤ በሃዘንና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሞልተው፡፡
አቶ መሐመድን ያገኘኋቸው በቶም የኩላሊት እጥበት ማዕከል ውስጥ ነው፤ ባለፈው ሳምንት ከ17ቱ የግልና የመንግስት ባንኮች ንግድ ባንክን ጨምሮ ከ13 ባንኮች የተወከሉ ሃላፊዎች የኩላሊት ህመምተኞችን በጎበኙበት ወቅት:: “መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠቱ ህዝቡ እያለቀ ነው” ሲሉ ለጎብኝዎቹ በምሬት የተናገሩት አዛውንቱ፤ መንግስት ችላ ቢል እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡
የደሴ ነዋሪና የዩኒቨርሲቲ መምህርት የሆኑት ወ/ሮ ገነት፣ በቶም የኩላሊት እጥበት ማዕከል የተገኙት ሴት ልጃቸውን ለማሳከም ነው፡፡ ልጃቸው የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደነበረች ገልጸው፤ በደሴ የእጥበት ማዕከል ባለመኖሩ ሥራቸውን እንዲያቋርጡና 400 ኪ.ሜ ተጉዘው አዲስ አበባ እንዲመጡ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡ የታማሚዋ ታላቅ የሆነችው የጤና መኮንን ልጃቸውም ስራዋን አቋርጣ ታናናሾቿን የማሳደግና ቤተሰቡን የመምራት ኃላፊነት እንደተጫነባት የገለፁት እናት፤ መንግስትና ባለሀብቶች በእጅጉ እየተስፋፋ ለመጣው የኩላሊት ህመም መፍትሄ እንዲያበጁለት ጠይቀዋል፡፡ ታማሚዎችን ለመጎብኘት የተገኙትን የባንክ ሃላፊዎችም፤ “እባካችሁ በልመና የሰው ፊት ከማየት ታደጉን” ብለዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ወልደማሪያም በደሴ ከተማ የትልቅ ሬስቶራንት ባለቤት ነበሩ፡፡ አሁን ግን በኩላሊት ህመም የተነሳ ቤት ንብረታቸውን ሸጠው፣ በአዲስ አበባ አንዲት ክፍል ቤት በመከራየት በሽታቸውን ያስታምማሉ፡፡ ላለፉት ሶስት አመታት በዚህ ህመም እየተሰቃዩ እንደሚገኙ የተናገሩት አዛውንቱ፤ በደህና ጊዜ ያፈሯቸው መልካም ጓደኞቻቸው እያዋጡ በሚልኩላቸው ገንዘብ በሳምንት ሶስት ቀን የኩላሊት እጥበት ሲያደርጉ እንደቆዩ ጠቁመው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አቅም እያጠራቸው በመምጣቱ፣ እጥበቱን በሳምንት ሁለት ጊዜ ብቻ ለማድረግ መገደዳቸውን አስረድተዋል:: የኩላሊት ህመምተኛ ከመሆኔ በፊት ሙሉ ጤነኛ ነበርኩ የሚሉት አዛውንቱ፤ ህመሙ ለደም ማነስ፣ ለአይን ሞራ ግርዶሽና ለሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች እንደዳረጋቸው ይገልጻሉ፡፡
“ግዴለም በረከቱን በልጆቻችሁ ታገኛላችሁና ፈጣሪ እስከፈቀደ ድረስ ሳንቸገር እንድንኖር እርዱን” ብለዋል፤ አዛውንቱ በእንባ እየታጠቡ፡፡ “ቶም የኩላሊት እጥበት ማዕከል የገንዘብ ቅናሽ እያደረገ፣ ሞራል እየሰጠና አይዟችሁ እያለ፣ ከጐናችን ባይሆን ኖሮ እስካሁን በተስፋ መቁረጥ አልቀን ነበር፣ ፈጣሪ ባለቤቱን ይባርክው” ሲሉ መርቀዋል፤ አቶ ተስፋዬ፡፡  
የቶም የኩላሊት እጥበት ማዕከል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቶማስ፣ ታማሚዎችን ክፍያ በመቀነስና በማበረታታት ለማገዝ ቢሞክሩም ችግሩ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ “ህመምተኞች አገልግሎቱን ለማግኘት ከአፋር፣ ከኢሊባቡር፣ ከሶማሌ ክልልና ከየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ ይመጣሉ፤ ቤት ንብረታቸውን ሸጠው አቅማቸው እስከቻለ ድረስ ይታገላሉ፤ በየክልሉ ቢያንስ በዋና ዋና ከተሞች የእጥበት ማዕከላት ቢከፈቱ ታማሚዎች ቤተሰቦቻቸው በቅርብ እየረዷቸው መታከም ይችላሉ፡፡” ብለዋል፤ አቶ ቶማስ:: “ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ስራቸውን አቋርጠው ልጃቸውን ለማስታመም እዚህ የመጡት ወ/ሮ ገነት ‹ህክምናውን ለምን ደሴ አትከፍትልንም› እያሉኝ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ “እስቲ የደሴ ከተማ ከንቲባ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጠኝነት ያሳይና እኔ ህክምናውን እዚያ መክፈት ያቅተኝ” ብለዋል፡፡
ከዘጠኝ አመት በፊት ሥራውን ስጀምር የታማሚው ቁጥር አነስተኛ ነበር ያሉት አቶ ቶማስ፤ አሁን ግን ታማሚው ስፍር ቁጥር እንደሌለው ጠቁመው፣ ችግሩ ተስፋፍቶ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ “ያ ከመሆኑ በፊት ከመንግስት ጋር ተቀራርበን የምንመካከርበት ሰፊ መድረክ ቢመቻች፣ ትውልዱን ለመታደግ እንችላለን” የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የሚናገሩት በዘውዲቱ ሆስፒታል የተከፈተው የኩላሊት ህሙማን እጥበት በጐ አድራጐት ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል 20 በመቶ የነበረው ተላላፊ ያልሆነ በሽታ መጠን አሁን ወደ 54 በመቶ ማደጉን ጠቁመው፣ የህመሙን ስርጭት ለመግታትም ሆነ ታማሚዎችን ለመታደግ፣ የመንግስትን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡   
እሳቸው በሚመሩት ማዕከል የእጥበት አገልግሎት ለማግኘት ተመዝግበው ከነበሩ 676 ታማሚዎች መካከል መርዳት የተቻለው 413ቱን ብቻ እንደሆነ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ ታማሚዎችን በስፋትም ሆነ በዘላቂነት ለማገዝ በማቀድ ባንኮች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉበትን ፕሮጀክት ቀርጸው ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ባለፈው ሐሙስ፣ 13 የመንግስትና የግል ባንኮች ተወካዮች፣ በቶም የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተገኝተው፣ ህሙማኑ ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡ በወር እነዚህ 17 ባንኮች በድምሩ 100ሺህ ሰራተኞች እንዳሏቸውና እያንዳንዱ ሰራተኛ በወር 20 ብር እንኳን ቢለግስ በወር 2 ሚ. ብር እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዚህም ገንዘብ በየመንገዱ ለሚለምኑት ታማሚዎች ነፃ የእጥበት አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡  
በአሁኑ ወቅት መንግስት ለኩላሊት ህመም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ በአዲስ አበባ በዘውዲቱ፣ በምኒሊክና በጳውሎስ ሆስፒታሎች የእጥበት አገልግሎት በስፋት እየተሰጠ እንደሆነና በ12 የጤና ኮሌጅ ባለባቸው የክልል ከተሞችም አገልግሎቱ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የኩላሊት ህሙማን እጥበት በጐ አድራጐት ማዕከል፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ትልቅ አገር አቀፍ የኩላሊት ህመም ጥናት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑንና ቅድመ መከላከል ላይ አትኩሮ ለመስራት መታቀዱን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ባንኮች ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ከተመረጡ 40 ድርጅቶች ድጋፍ ለማግኘት ደብዳቤ ማስገባታቸውን ገልፀዋል:: የኩላሊት ታማሚዎች ወደ ህክምና ሲሄዱና ሲመለሱ ቢያንስ በኪሎ ሜትር ከአምስት ብር በላይ እንዳይከፍሉም ከ“ፒክ ፒክ” ታክሲ ጋር ውይይት ጀምረናል ብለዋል፡፡  
ቶም የኩላሊት እጥበት ማዕከል፣ ለህሙማን እገዛ በማድረግ ረገድ ሊመሰገን የሚገባውና በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ለአንድ ጊዜ እጥበት 1ሺህ 500 ብር ይከፈል የነበረውን በ980 ብር በማጠብ፣ ገንዘብ የሌላቸውን በመርዳት፣ በሞራል በማገዝና በማማከር አገራዊ ግዴታውን እየተወጣ ነው በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ ማዕከሉ ባሉት 35 የእጥበት ማሽኖች በቀን 105 ታማሚዎችን በማጠብ፣ የዲያሊስስ ማሽኖችን በማስመጣትና ለመንግስት ሳይቀር በማቅረብ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል፡፡
60 በመቶው የኩላሊት ህመም በስኳርና በደም ግፊት፣ 40 በመቶው ደግሞ በኢንፌክሽን እንደሚከሰት ጥናቶችን በመጥቀስ የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፤ ችግሩ ከመንግስትና ከበጐ አድራጐት ማህበራት አቅም በላይ በመሆኑ ባለሃብቶችን ጨምሮ ሁሉም አካል ችግሩን ለመፍታት በጋራ መረባረብ እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

Read 4845 times