Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 02 June 2012 09:16

ብርሐን እና ጥላ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በጣም ለረጅም ዘመን … ማስታወስ እስከሚችልበት ጊዜ … ሁሌ ለመሞት ሲዘጋጅ … ለመሞት ሲጓጓ ነው የቆየው፡፡ የሚያውቀውን እየጠላ ለማያውቀው ሲጐመጅ ራሱን አጥብቆ ጠይቆ አያውቅም፡፡ “ለምን … ለምንድነው ለመሞት የምትፈልገው?” ልጅ እያለ መሞት የሚፈልገው የሂሳብ አስተማሪ በእየቀኑ ስለሚገርፉት … ከሳቸው ዱላ ለመትረፍ ያለው ብቸኛ አማራጭ መሞት ብቻ ይመስለው ስለነበር ነው፡፡  ሁለተኛ ክፍል በነበረበት ወቅት እሁድ ማታ ሙሉ የልብስ ሳሙና በልቶ ለመሞት ሞክሮ ነበር፡፡ እሱም አልሞተም፤ ሰኞም በጠዋት እንደሌላው የትምህርት ቀን በሰአቱየመጀመሪያው  ፔሬድ ተደወለ፡፡ የሂሳብ አስተማሪውም “ዳንኤል በቀለ ና ውጣ! አንተ ድንጋይ!” ብለው  ሁለተኛው ፔሬድ ላይ ገረፉት፡፡ ሳሙናውን በውሀ እያወረደ ለመብላት የፈጀበትን ጊዜ የቤት ስራውን በመስራት ቢተካ ኖሮ፣ ከመገረፍ ይተርፍ እንደነበረ ያኔም ሆነ አሁን አልተከሰተለትም፡፡

ለመሞት መመኘት እንጂ ምኞቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከዚያ በኋላ ሞክሮ አያውቅም፡፡ … የማይችልበትን ነገር መሞከር ተወ፡፡ በእሱ ፈንታ የሁለተኛ ክፍል ሂሳብአስተማሪው ሞቱ፡፡ እሱ መኖር ቀጠለ፡፡ ሲያገኝ ደግሞ ደሞዙ ስለማይበቃው መሞትን እንደሚመኝ አወቀ፡፡ በእውቀቱ ላይ እውቀት ቀጠለበት፡፡ በምኞት ላይ ምኞት፡፡ በውድቅት ላይ ውድቀት፡፡ ፍቅረኛ ከማግኘቱ በፊት ገንዘብ አግኝቶ ነበር፡፡ ገንዘብ ሲያገኝ መሞት የሚፈልግበትን አዲስ ምክንያት አብሮ አገኘ፡፡ መሞት የሚፈልገው ለፍቅረኛ የታደለ ባለመሆኑ ምክንያት ሆነ፡፡ ሆኖ ቆይቶ … ስለነበር መጠጥ እና ሌላ ትርፍ ሱሶችን አሳድጎ ሞቱን ለማፋጠን … በዜሮ ማርሽ ተንደረደረ፡፡ ፍቅረኛ ሲያገኝ ያሳደጋቸውን ሱሶች ማጣት አቃተው፡፡ ሞቱን ተመኘ፡፡ እየተመኘ ፍቅረኛው ለአቅመ ሚስት ሳትበቃ ፍቅሩ በመሀላቸው ሞተ፡፡ እንዲኖር የሚፈልገው ነገር ሞቶ፣ ለመሞት የሚፈልገው እሱ መኖር ቀጠለ፡፡ …መሞት የሚፈልግበትን ምክንያት በአዲስ መልክ ረቀቅ አድርጐ አወቀ፡፡ መሞት የሚፈልገው ከኢትዮጵያ ሀገር መውጣት ስላልቻለ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አስከሬን ሳጥን ውስጥ ሚስማር ተመትቶ እንደመኖር ነው፤ አለ - ምክንያቱን ሲያጠናክር፡፡ ከኢትዮጵያ ለመውጣት ሞክሮ ግን አያውቅም፡፡ ለመኖር ሞክሮ አያውቅም፡፡ መሞትንም ከሳሙናው በኋላ መሞከር እርም ብሎ ትቶታል፡፡ የማያውቅበትን ነገር መሞከር ይፈራል፡፡ ሞክረው የሚሳካላቸውን ግን ያስቀኑታል፡፡ … ለመኖር ሞክረው የተሳካላቸውን በአፉ እያደነቀ በልቡ ግን ያጣጥላል፡፡ ለመሞት ሞክረው የሚሳካላቸውን በአፍ እያወገዘ በልቡ ይቀናባቸዋል፡፡ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ሳይሞክር ከመሞቻ ምክንያቱ ጋር የተክሊል ጋብቻ ፈፀመ፡፡ ወደ አሜሪካ ሄደው መኖር አቅቷቸው ግራ ተጋብተው የሚመለሱትን ታዘበ፡፡ ከመሞቻ ምክንያት ጋር የፈፀመውን ጋብቻ ወዲያው አፈረሰ፡፡ ወዲያው ሌላ ወጣት ምክንያት አገባ፡፡ የመሞቻ ምክንያት፡፡ ያገባት አዲሷ ምክንያቱ … ከዚህ በፊት ከነበሩት ምክንያቶች ሁሉ የተዋበች … ሀቀኛ፣ አመዛዛኝ፣ እመቤት የሆነች ምክንያት ነበረች፡፡ እቺን እፁብ ድንቅ የሆነች ምክንያት ሀይማኖቱ አደረጋት፡፡…

በአጠራቀመው ገንዘብ እና ቁሳዊ የሀብት ኮተት ምክንያት ደስታውን እንዳጣ ተገነዘበ፡፡ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአለም ሞት ምክንያት ገንዘብ እንደሆነ አወቀ፡፡ ደስታ ከሰው ልጆች የራቀው ለአለም በገንዘብ ፍቅር ምክንያት ነው አለ ለራሱ፡፡ “ሰው መኖር ያለበት ያለ ገንዘብ ነው” አለችው አዲሷ እውቀቱ እና እውነቱ፡፡ ያለ ገንዘብ በማይኖርበት አለም ውስጥ ለመኖር መሞከር መሞት እንደሆነ ግልፅ ነበር፡ እቺ አዲሷ እውቀቱ እውን እስክትሆን መሞት መፈለጉን እድሜ ልኩን መፈለግ እንደማያቆም አመነበት፡፡ ይህችን ምክንያቱን ካገኘ በኋላ ነው የዳንኤል ህይወት እንደ አዲስ የጀመረው …
ግን በቆይታ እቺኛዋንም እምነቱን ሻራት፡፡ ገንዘብ በሰው የታነፀ ሀውልት ነው፤ ሰው ራሱ ላነፀው ሀውልት ራሱ ተንበርክኮ በመስገዱ … ሀውልቱ ሀጢአተኛ ሊሆን አይችልም፤ ማለት ጀመረ፡፡ ጅማሮው ላይ ቀጠለበት … ገንዘብ የሰይጣን ምንጭ ነው ማለት … ሰው ደግሞ ምንጩ የፈለቀበት ተራራ ነው ከማለት አልተናነሰም …፡፡ ሰው ማለት ደግሞ እሱ ራሱ ዳንኤል ነው፡፡ እና ዳንኤልን መሰል በጥላ ውስጥ የተዋጡ ብርሀን ናፋቂዎች፡፡ ብርሀን እና ጥላን በትክክለኛ ማንነቱ ለማወቅ መፈለጉን ቀጠለ፡፡ ፍለጋውን እንዳያቋርጥ
የሚያደርገው ትልቁ የስበት ሀይል ሞት ነበር፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ አብሮት እንደ እስትንፋሱ የማይለየው የመሞት ፍላጐት፡፡ ሞትን ለመፈለግ በስለት ጠርዝ እና በእሾክ አለቶች ላይ መኖር ጀመረ፡፡ ሞትን በፈለገው ቁጥር የህይወት ፍጥነቱ እየጨመረ … ራሱን በስለት እና በጠርሙስ ስብርባሪ ነፀብራቅ ውስጥ እያየ …ባላሰበው ጥርጊያ ወደ ዋናው ጐዳና ሲያመራ ራሱን አገኘ፡፡ አዲስ እና የመጨረሻ የመሞት ፍላጐቱን የሚገልፅ የማያወላዳ ምክንያት ከፊቱ ተጋረጠ፡፡ እሱ መሞት የሚፈልግበትን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ ባይፈልጉም የሚሞቱበትን ምክንያት አወቀው፡፡ … ብርሀኑን የሚጋርደው ጨለማ …ሀጢአት እና ሰይጣን ሰውን ከመሆን ወደ አለመሆን የሚቀይሩበት ጥበባቸው ተገለጠለት፡፡ ይህ ጥበብም የመሬት ስበት ተብሎ በተለምዶ የሚጠራው ነው፡፡  ሰውን ከመንሳፈፍ የሚያግደው … ለመንቀሳቀስ እንዲችል ምግብ እንደ ቀረጥ የሚያስበላው …ልሽሽ ቢል የማያመልጠው … ለስበቱ የሚገባውን ግብር ባይከፍል የሚጥለው … በስበቱ ህግ ለመኖር ሲል የመሬት ግዞተኛም ሆኖ … መሬት ለመግዛት እና ለሎችን ጭሰኛ ለማድረግ የሚያፈራግጠው …
ከሰው በላይ የሆነው … ከትዝታው እድሜ በፊት በአባት በአያቶቹ በጥንት ጀማሪዎቹ ዘመን ለተሰራ ሀጢአት ክፍያ የተሰጠው መቀመጫ እንደሆነ ገባው፡፡ የመሬት ስበት!!  ይህ ሲገባው ይህንን የመሬት ስበት ሀይል ለመቃወም … ሀይማኖተኛ ሆነ … “የክንፍ” ሀይማኖት አራማጅ ሆነ፡፡ የመሬት ስበት በአካሉ ላይ ብቻ የሚሰራ ስለሆነ ስበቱን ለመቀነስ ኪሎውን ቀነሰ፡፡ ብዙ ቁሳቁስ እና ሀብት መሰብሰብ ከመሬት ስበቱ ጋር ያለውን ሀይል መጨመር መሆኑ ሲገባው … ኮተቱን አስወገደ፡፡ ስስ ልብስ መልበስ … በባዶ እግሩ መሄድ ጀመረ፡፡ ወፎችን አይቶ ቀና … የወፍ አጥኚ ሆነ … ነዳጅ የማያስፈልገውን ክንፍ ግን በጥናቱ ሁሉ ፈልጐ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ወፎችም ቢሆኑ እንደሰው እስረኛ ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ከመሬት ከፍ ብለው ቢበሩም እንደ ተኮነኑ መልእክት ርቀው አይሄዱም፡፡ ተላቅቀው አይላቀቁም፡፡ እውነተኛ ክንፍ በሀሳብ ወይንም ምናብ እንጂ በአካል እና በእውን እንደማይገኝ አረጋገጠ፡፡ ግን
ጉልበቱ አልንበረከክ አለው፡፡ አካሉን ሰበረ … ስጋውን በአጥንቱ አስበላ … አስጋጠ…፡፡ የመሬት ስበት ቀነሰለት እንጂ አልለቀቀውም፡፡ የመሞት ፍላጐቱ እየመነመነ መጣ፡፡ በቆይታ ጭራሽ ጠፋ፡፡ ሞቶ መሬት መግባት አይፈልግም፡፡ ባሰረው ጥላ ከርስ ውስጥ … አፈር ተምሶለት መሬት መቀበር፡፡ የሲኦል ትርጉም ነው፡፡ ፀሎቱ ብቻ ከመሬት ስበት ያመልጣል፡፡ አብዝቶ መፀለይ ጀመረ፡፡ የግዞት ዘመኑን ለማስቀነስ ሳይሆን…አካሉ በተገዛበት ሃይል ውስጥ በአጥንትም ይሁን ሌላ መልክ ተውጦ እንዳይቀር፡፡ …ብዙ ብዙ ፀሎት … ተኮሰ፤ ወደ ብርሃን አቅጣጫ…ብርሃን ወዳለበት፤ ከመሬት ስበት ተቃራኒ ወደሆነ አንፃር ሁሉ፡፡ …የፀሎቱ መልስ የመጣው በጣም ዘግይቶ ነበር፡፡ የፀሎቱ መልስ ክንፍ አልነበረም፡፡ የምድርንም ስበት የሚያመልጥበት የእሳት ሰረገላም አልተሰጠውም፡፡ ገላው ብቻ ግን ከቡቱቶው ስር እንደ ዝሆን ጥርስ መንጣት ጀመረ፡፡ እንደ ሻማ ለሰለሰ፡፡ ቀኑን ማስታወስ ይከብዳል፡፡ ቀኖች በሙሉ እንደተቀቀለ መኮሮኒ አንድ ላይ ተጠባብቀዋል፡፡ ጊዜው ግን ጥላ ጨለማ መስሎ የነገሰበት ነው፡፡ ፀሐይ እንኳን ሳይጥቃ ለመግባትያስቸገራት ጥላ በየአቅጣጫው ወድቋል፡፡ ጥላው የቀንድ አምሳል አለው፡፡ በብዛት ችምችም ሲል ደግሞ የጥርስ…የክራንቻ፡፡ ሁሉም ገንዘብን በመውደድ ከመሬት ስበቱ ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማይፈታ ሰንሰለት አቆላለፈዋል፡፡ በጣም የተቆላለፈ ሁሉ በግንባሩ ላይ ብቅ ያለ አንድ ቀንድ አውጥቷል፡፡ ገንዘብ ካልተገኘ ቀንዱ አድጐ ጭንቅላታቸውን ለሁለት ፈርክሶ ሊገድላቸው ይችላል፡፡ መጠጥ እና ምርቃና በቀንዶቹ ግጭት መሀል እንደ ማለስለሻ ጠብ ያደርጋሉ፡፡ የመሬት ስበቱን ሃይል ለቅጽበት የቀየረላቸው የሚመስል የቀን ቅዠት በጥቁር ክንፍ ያሳያቸዋል፡፡ በነፃ የሚገኝ ነገር የለም፡፡ ጫማ ጠቦአቸው ሀገር የሰፋቸው፤ የመሬት ስበት ጠብቆባቸው አቅጣጫው እንደጠፋበት ነፍሳት አንድ ቦታ መላልሶ ያሽከረክራቸዋል፡፡ አንድ ሰው ብቻ እዚህ ውስጥ የለበትም፡፡ አንድ ሰው ብቻ በከተማው ውስጥ ቀንድ አላበቀለም፡፡ ጤነኛ ጠፍጣፋ ግንባር አለው፡፡ ***
“ማነው ይሄ ሰውዬ?” ብሎ ጠየቀ፤ የቤቱ አባወራ ወደ ሚስቱ ግራ በመጋባቱ ቀርቦ፡፡
“እኔ ስሙን አላውቀውም “ሰው” እያሉ ነው የሚጠሩት”
“የምን ሰው?...የእግዜር?”
ሰራተኛዋ ቀስ ብላ በሩን ከፍታ ወደ አራተኛው ውሽማዋ ቤት ልትሾልክ ስትል ቀንዷ በሩ ላይ የቆመው ሰው ደረት ላይ ተሰክቶ ነበር፡፡ “ውይ በስማም” ብላ መለስ አለች፡፡ በሽተኛ ስለሚመስላት በምሽት ስታየው በሩጫ የምትሸሸው ያ ረጅሙ ሰውዬ ነው የተገተረው፡፡ በሩን በድንጋጤ ዘግታ ወደ ማድቤት ሮጠች፡፡ አባወራው ሰውዬ በር ላይ የቆመ ሰው አለ ሲባሉ፤ ጋቢያቸውን በጭንቅላታቸው ላይ አልብሰው ወጡ፡፡ ቀንዳቸው ጋቢውን እንደ ድንኳን ወጥሮታል፡፡
“አቤት” አሉ በሩን ከፍተው፡፡ ቆጣ ማለት አልቻሉም፡፡ ውጭ የቆመው ሰውዬ ፊት እንደ ብርሃን በከባዱ ተሰምሯል፡ “ምን የማግዛችሁ ስራ አለ” ብሎ ጠየቀ፡፡ ጥያቄው፤ ከሆነ ከጠያቂው ቁመት በላይ ከራቀ ከፍታ እንጂ…ከአፉ የወጣ አይመስልም፡፡ “ስራ…አለ ወይ ነው ያልከው?” አሉ አባወራው፡፡ ቀንዳቸው ከስር ከመሰረቱ…ከበቀለበቱ …አመማቸው፡፡ አሳከካቸው፡፡ ነዘራቸው፡፡ እንደተበላሸ የመንጋጋ ጥርስ፡፡ “ቦዩ ተደፍኗል…መጠረግ አለበት፡፡ እኔ ደግሞ ህመም ነበረብኝ አሁን ግን በጣም እየጠናብኝ ነው ልታክመኝ ትችላለህ?...ወንዱ ልጄ ራሱን ለመግደል ገመድ የሚቋጥርበት ዛፍ መቆረጥ አለበት፤ ባለቤቴ እኔ እንድሞት ከጠንቋይ ያመጣችውን መድሀኒት የቀባችበትን ወይ የቀበረችበትን ቦታ ታሳየኛለህ?...ቤቱ እንዲሸጥ ትፈልጋለች ተይ ትልልኛለህ?..ሴት ልጆቼ ኮሌጅ ሳይጨርሱ ሁለት ሁለት ልጅ ወልደው ከክልል ልከውልኛል …ማሳደጊያ መንገድ ትጠቁመኛለህ?...መሞት አልፈልግም
ታድነኛለህ?”አባወራው በቁመት በጣም አጭር ነው፡፡ ቀንዱ ነው ትክክለኛ የአዋቂ ቁመት ያለው፡፡ “ሰው” ከላይ የለበሰውን ስስ መጐናፀፊያ ሰበሰበ፡፡ ወደ ስራው ገባ፡፡ አካፋ እና ዶማ ይዞ ቦዩ ውስጥ ገብቶ መጥረግ ጀመረ፡፡ ቦዩ ውስጥ የተንጣለለው ደም ውስጥ የሞቱ ህፃናት ፀጉር፣ ጥርስ እንደ ሀሞት
አረፋ ብቅ ብለው እልም ይላሉ፡፡ በሀይል መስራት ጀመረ፡፡ እውነቱ ብቅ እስኪል መቆፈር ቀጠለ፡፡ በአካፋ እና ዶማ እንደ ሰይፍ የተከማቸውን ስቃይ እና መከራ በማውጣት ገፋበት፡፡ እውነት እንደ አለት ሲመታ ያ ሁሉ ደም፣ ማውረጃ እንዳገኘ እንባ ፈሰሰ፡፡ ፈሶ ተንቆርቁሮ ተሰወረ፡፡ አባወራው ወደ ቤታቸው ገብተው ቀንዳቸውን ከመሬቱ ጋር እያሹ ነው፡፡ ያቃስታሉ፡፡ እንባቸው እንደ ላብ አጥምቋቸዋል፡፡ በቁም ሳጥኖቻቸው ውስጥ የከመሩት ብር እንደ ውሻ ሬሳ ሽታው ከሩቅ ይተናነቃል፡፡ባለቤታቸውን ከሚቀረናው ብር ላይ ሊያባርሩዋት አልቻሉም፡፡ አሁን ግን ቀንድ መለካካት ጀምረዋል፡፡ ሚስት ባልን በልጣቸዋለች፡፡ **
እያሳከካቸው ብቻ ሳይሆን እያሳመማቸው ነው፡፡ እየተንከባለሉ መጮህ ጀመሩ፡፡ ሚስታቸውን ከገንዘብ ላይ የማራቂያ ፋታ አጡ፡፡ ህመማቸው ከአቅማቸው በላይ ሆነ፡፡ ስቃያቸው በረታ፡፡ በጭንቅላታቸው ላይ እየበቀለ ያለው ቀንድ በመሐፀን ውስጥ እንደሚበቅል ጽንስ…በሀይለኛ ምጥ ሊወለድ ይመስላል፡፡ እንደ ገፊ ልጅ ወላጁን ገድሎ የሚሞቅ በቆልት ነው፤ ቀንድ፡፡ ሠራተኛው ቦዩን የሚያፀዳበትን አካፋ ጥሎ የሰውየውን የሚሰቀጥጥ ጩኸት ወደሚያስተጋባበት የውስጥ ክፍል አመራ፡፡ የአባወራውን ቀንድ እግሩን ጭኖ ፀለየበት፡፡ እንደ አንቴና ማጠር ጀመረ፡፡ ድንገት፡፡ ሰውዬው አጋንንት እንደወጣለት እብድ ራሳቸውን ስተው ተዘረሩ፡፡ የሰውዬው ባለቤት ራሷን ብዙ አድርጋ ቁምሳጥኑ ውስጥ የሞተውን ብር እያፈሰች ነው፡፡ ብዙ ከመሆኗ የተነሳ…መስኮት ከፍቶ ማስወጣት አልተቻለም፡፡ ወይዘሮዋ አንበጣ ሆናለች፡፡ መቶ - መቶ ብሩን በልታ የምትጨርስበት፡፡ የአባወርየውም ቀንድ እግሩን ጭኖ ሲፀልይ ከቆየበት ሲያነሳ ቀንዱ መልሶ መብቀል ይጀምራል፡፡ አረም የሆነ ቀንድ ነው፡፡
***
“ሰው” የመስሪያ እቃዎቹን አስቀመጠ፡፡ ከቁሻሻ ክር የተፈጠረ ልብስን አጥቦ ማጽዳት አይቻልም፡፡ መብራቱ…ሻማው ከተለኮሰ እንደማይጠፋ ያውቃል፡፡ በዚህ ቁሻሻ ጋን ውስጥ መብራቱን ለኮሰው…መብራቱ ራሱ እሱ ላይ ነው የተለኮሰው፡፡ መሞት ይፈልግ የነበረባቸው ዘመኖች ትዝ አሉት፡፡ አሁን ግን ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች ሲል ሊሞት ነው፡፡
እየተበሳጨ እየተማረረ ከመሞት…አምልጧል፡፡ አሁን ሞት እና ትንሳኤ አንድ ሆነዋል፡፡ ፈገግታው ከጧፉ ጋር ፊቱ ላይ ቀለጠ፡፡ ከፊቱ አልፎ ልቡ ላይ ፈሰሰ፡፡
ልቡን አሟሟው፡፡
ጉልበቱ ላይ ደረሰ፡፡
ተንበረከከ፡፡

 

 

 

Read 3164 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 09:33