Monday, 06 May 2019 12:49

መስቀለኛ መንገድ

Written by  ከዳግማዊ፡ እንዳለ (ቃል ኪዳን)
Rate this item
(16 votes)


            በእኩለ ለሊት የአባቴን መሰንቆ ከተሰቀለበት ግድግዳ አወረድኩ፡፡ የሟች አባቴን መሰንቆ እንዳነሳ ያስገደደኝ ነገር፣ በዋናነት ለእናቴ ያለኝ ጥላቻ ቢሆንም፤ ዛሬ ጎረቤታችንና የአባቴ አሳዳጊ የነበሩት እትዬ ወለቱ ያሳዩኝ የአባቴ ፎቶ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በፎቶው ላይ አባቴ ከለበሰው የአገር ባህል ልብስና ካጎፈረው ፂሙ በስተቀር በመልክና በቁመናዉ ቁርጥ እኔኑ ነው የሚመስለው፡፡ የመሰንቆ መጫወትና ማንጎራጎር ጥበቡን ከተማርኩ ደግሞ እሱኑ ሆንኩ ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እኔና እሱን ለምትጠላው እናቴ፣ ትልቅ የሚያናድድ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡
አባቴ፤ እናቴ እኔን ነፍሰጡር እያለች ነው የሞተው:: እናት ተብዬዋ የአባቴን ሞት ተከትላ፤ ከአራስ ቤት ሳትወጣ፤ ያገተው ጡቷ ሳይነጥፍ፤ አክምባሎ ሰባሪ የሚሆን ሌላ ባል አገባች:: ነብስ እያወቅሁ፤ መልኬ የአባቴን እየመሰለ ሲመጣ የወለደችኝ እናቴ፤ በእንጀራ አባቴ ላይ ተፈናጣ፣ የእንጀራ እናቴ እየሆነች መጣች:: ከእናቴ መውለድ ያልቻለው የእንጀራ አባቴ ደግሞ በተቃራኒው፣ የልጅ ፍቅሩን ሊያስታግስ ደጌ እየሆነ መጣ፡፡ እንደውም አንዳንዴ በእናት ተብዬዋ ምክንያት፤ አባቴን በመምሰሌ ብቻ ያልበላሁትን ዕዳ እየከፈልኩ እንደሆነ እንደሚያምን በሀዘኔታ ከሚያዩኝ ብሩህ ዓይኖቹ ላይ ለእኔ ብሎ የጻፈውን የሀዘን እንጉርጉሮ አነባለሁ፡፡
‹‹አወይ ይሄ መልክህ፤ ያመጣብህ ጣጣ
እባትህን መስለህ፤ እናትህን አስቆጣህ
ስህተትህን አርም፤ በል ሂድ ሆዷ ግባ
እራሷ ላይ አፍጥጣ፤ ራሷን አʻርጋህ ወልዳ
ድንጋይ ልቧ ይባባ››
መሰንቆውን ስጠራርገው እላዩ ላይ ሰፍሮ የነበረው አቧራ በቀላሉ ድራሹ ጠፋ፡፡ የእናቴም ነገርም፣ ነገ ዕጣ ፈንታው እንደዚህ ነው:: ሲነጋ ታላቅ መሰንቆ ተጫዋች እሆናለሁ፡፡ ለመንደሬ ሰው የዛሬውን ንጋት የሚያበሥሩት፣ ጠሀይና ዝናብ ያወየባቸው የመንደሬ ወፎች ሳይሆኑ የእኔ መሰንቆ ነው፡፡ የነገ ጀምበር ስትሠርቅ፣ መሰንቆን የሚያስለቅስና የሚያሥቅ፣ ሲያሻው የሚያስቃስት መሰንቆ ተጫዋች እሆናለሁ:: መሰንቆን አናግራታለሁ፡፡ ስለ አባቴ እጠይቃታለሁ:: ነብስ ሳላውቅ፣ እናቴ ስለ አባቴ ያወራቻቸውን መጥፎ ነገሮች ሁሉ እንድትነግረኝ አደርጋለሁ፡፡ ከመሰንቆ ጋር አፍ ለአፍ ገጥመን እናወራለን፡፡ እኔና መሰንቆው አፍ ለአፍ ገጥመን ስናወራ ደግሞ እናቴ አብዳ ጨርቋን ትጥላለች - እሱን ነው የምፈልገው እኔ! ከፈለገች ጠና የሚወይልበት ታክሲ ጎማ ሥር ተወርውራ ትግባ፡፡
እትዬ ወለቱ ዛሬ በሀሳቤ እንድቆርጥ አጋጣሚ ፈጠሩልኝ፡፡ ቀን ላይ ለዓይኖቻቸው መደባበሻ የሚጠቀሙበትን፣ ከአጥራችን ላይ ቆርጬ ያመጣሁላቸውን የወለሞ ቅጠል ተቀብለውኝ ሲያበቁ ትክ ብለዉ ተመለከቱኝና፤
‹‹አንተ አባትህን አከልክ አይደል? ቁርጥ እሱኑ እኮ ነው የምትመስለው›› አሉኝ፤ እራሳቸውን በግርምት እየነቀነቁ፡፡
‹‹አባቴ እኔን ይመስል ነበር?›› ስል ጠየቅኋቸው:: ቤታቸው ይዘውኝ ገብተው፣ አንድ ፎቶ ከአልበም ውስጥ አውጥተው ሰጡኝ::
ፎቶው ላይ ለደቂቃዎች ተመስጬ ከቆየሁ በኋላ፤ ተገርሜ እትዬ ወለቱን ቀና ብዬ ባያቸው፣ ከዓይኖቻቸው የሚፈሰውን እንባ በወለሞው ቅጠል ሲያደራርቁ አገኘኋቸው፡፡ ሴትየዋ ያለ ድምጽ እያለቀሱ ነበር፡፡ ወይ ደግሞ ጆሮዬን ደፍኜ የአባቴ የቁም ፎቶ ላይ ተመስጬ ነበር፡፡
‹‹እግዜሩ እኔን አሮጊቷን አስቀምጦ ገና ህይወትን እንኳን ያላዩትን ልጆቼን ወሰዳቸው!›› ተንሰቀሰቁ፡፡ ሴትየዋ ሁሌ ጸሐይ ሞቀው ከገቡ በኋላ ልጃቸውንና ያሳደጉት አባቴን እያሰቡ ያለቅሳሉ፡፡ ምናልባት ጸሀይቱን የሚሞቁት፤ ለአንድ ቀን የጠጡትን ውሃና በየቤቱ እየዞሩ ያንቃረሩትን ቡና፤ ከሰውነታቸው እያተነነች፤ የዓይኖቻቸው ቆቦች ውስጥ ደመና እንድትሠራላቸው ይሆናል፡፡
መሰንቆዬን አንግቼ ከቤት ወጥቼ ደጃፉ ላይ ቆሜ፣ በጨረቃ ብርሃን ሰፈሩን ለመቃኘት ሞከርኩ:: ሰፈሩ በጥልቅ እንቅልፍ ሰጥሟል:: እናቴ ብቻ ናት በዚህ እኩለ ለሊት አባቴ በሰላም አርፎ እንዳይተኛ ስሙን እያነሳች የምትጥለው፡፡ ከቤታችን ደጃፍ የምትመነጨው ቀጭን መንገድ፣ ዋናው መንገድ ፊት አንሳ ላለመታየት፣ እየሰፋች ትሄድና ከዋናው መንገድ ጋር ትቀላቀላለች፡፡ ዋናው መንገድ መጨረሻው አይታይም፡፡ በግራና በቀኙ ተንጋደው የተደረደሩት፣ የበለዙ ቤቶች፣ መንገዱን የሰነፍ ሰው ጥርስ አስመስለውታል፡፡ የሰፈራችን አዋቂ ቤት ብቻ ከጎኑ የወለቀ የመንጋጋ ጥርስ እንዳለ ሁሉ ገንጠል ብሎ ለብቻው ቆሟል፡፡ አዋቂው ሰውዬ በሠፈሩ ሰው እንዲህ የሚፈራውና የሚከበረው፣ ከጥንቆላ ሥራው በተጨማሪ ቤቱን ገንጠል አድርጎ በመቀለሱ ይመስለኛል፡፡
መንገድ ጀምሬ አዋቂው ቤት ጋ ስደርስ፣ በሩ ላይ በገመድ የተንጠለጠለችውን እስስት ለማየት ሞከርኩ፡፡ ጨለማው አላሳይ አለኝ፡፡ ይህቺ እስስት አንድ ዓይኗን ወደ ፊት፤ ሌላኛውን ወደ ኋላ አድርጋ ማየት መቻልዋ በእዚህ ጠንቋይ እጅ፤ በገመድ ተንጠልጥላ ከመሞት አላዳናትም፡፡ የጠንቋዩ ደጃፍ ላይ ከበቀለ የሰይጣን ዛፍ ላይ ጠፍጣፋ ፊት ያለውና የዋና መነጽር የለበሰ ይመስል ትላልቅ፣ ክብ ዓይኖች ያሉት አንድ ጉጉት ይታያል፡፡ ሰውየው ለመያዝ የሚያስቸግሩ እንስሳትን እንዴት እንደሚይዝ ሳስበው እገረማለሁ፡፡
ጉጉቱ እኔን ሲያይ ክብ ዓይኖቹ የደኅንነት ካሜራ ይመስል የእኔን እንቅስቃሴ ተከትለዉ መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ አዋቂዉን ስለማልፈራዉ ጉጉቱ የፈለገዉን ነገር ቢነግረዉ ግድ የለኝም:: ነገር ግን ጉጉቱ የት ለመሄድ እንደወጣሁ ሳያውቅ እንዳልቀረ ልቤ ነግሮኛል፡፡
ከአዋቂው  ቤት ትይዩ፤ ትንሽ ከፍ ብሎ፤ ካለች አንዲት ቤት፤ አንዲት ሴት ወጥታ ገላምጣኝ ስታበቃ ቀሚሷን ወደ ላይ ሰብስባ ለሽንት ቁጭ አለች፡፡ በሰፈራችን ያለው የፖሊስ አዛዥ ሚስት፣ የጠንቋዩ ቁጥር አንድ ደንበኛ ናት፡፡ ሴትየዋ ገና ቀሚሷን ገልባ ከመቀመጧ እንደ መኪና ማጠቢያ ውሃ የሚገፋ ኃይል ያለው ሽንት ማፍሰስ ጀመረች፡፡ ስትጨርስ ልብሷን አስተካክላ፣ የአዋቂውን ቤት ተሳልማና አንዳች ነገር አነብንባ ወደ ቤቷ ገባች፡፡ ጉጉቱ መልዕክቷን እንደሚያደርስላት እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሴትየዋ ሽንቷን የሸናችበት ቦታ ስደርስ፤ ቅጠሎችና ሣሮች ደርቀው ተመለከትኩ:: አዋቂው ምን እንደሚያጠጣት እንጃ፣ የሰፈራችንን አትክልቶችና ዛፎች፤ ከመጥረቢያና መጋዝ ባልተናነሰ ሁኔታ በሽንቷ ጨፍጭፋለች:: በእሷ ሽንት ምክንያት አስም ያልያዘው የሰፈራችን ሰው የለም፡፡ የሚገርመኝ ሴትየዋ ባሏ የፖሊስ አዛዥ ሆኖ ለምን አዋቂው ዘንድ እንደምትሄድ ነው፡፡ ከእሷ ጋር የተጣላ አለቀለት፡፡ እኔ ግን አልፈራትም፡፡
የእሷን ቤት አለፍ እንዳልኩ፤ እላይ ሰፈር ካለው ትልቁ ግቢ፤ ትልቁ ሰውዬ ወጡና በራቸው ላይ ቆመው የአዋቂውን ቤት ተሳለሙ:: ሰውየዉ እራቁታቸውን ነበሩ፡፡ ወዲያው ዋናውን መንገድ ይዘው እሩጫ ጀመሩ፡፡ ለሊት ተነስተው እራቁታቸውን የሚሮጡትን ሰዎች፣ የሰፈር ጎረምሶች አትሌቶቹ እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡
እውነት ይሁን ቀልድ ባላውቅም፣ ስለ እኚህ ሰውዬ የሚነገር አንድ ታሪክ አለ፡፡ አንድ ጠዋት ጠና የተባለው የሰፈራችን አንጋፋ የታክሲ ረዳት፣ ለሊት ለሥራ ሲወጣ ሰውየው በራቸው ላይ አመድ ነስንሰው ሲንከባለሉ አገኛቸው፡፡ ጠና ይሄንን ሲያይ ጠጋ ብሎ ‹‹ጋሼ ለምንድነው?›› ብሎ ሲጠይቃቸው መንከባለላቸውን ሳያቆሙ፤ ‹‹ለእስካንያ ነው! ለእስካንያ ነው!›› ይሉታል፡፡ ጠናም ቀበል አድርጎ፤ ‹‹እስኪ ለላዳ ትንሽ ጠጋ ይበሉልኝ!››
መሰንቆዬን እንዳነገትኩ፣ ደጋኑን በእጄ ጨብጬ እሯጩን ሰውዬ ከዓይኖቼ እስኪሰወሩ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ሰውየው ሲሮጡ እግሮቻቸዉ የፈረስ ኮቴ ዓይነት ድምጽ ነው የሚያወጡት፡፡
ድንገት ሰው አዲስ ነገር ባገኘ ቁጥር ዓይኖቹ የሚቀሉት(ሰዉዬዉ አይጠጣም ግን ሁልጊዜ ዓይኖቹ ቀይ ናቸዉ)፤ ልብስ ሰፊ ሰዉዬ፤ የሀሰን ቆቁን ሱቅ ሲተሻሽ አገኘሁት፡፡ ድንገት ሀሰን ቆቁ (ምንም ስለማይሸወድ ነዉ እንደዛ የሚጠራዉ) የሱቁን መስኮቶች ከፍቶ፤ ‹‹ቡዳ ቤት ሰላቢ ገባ አሉ! ጥፋ ከዚህ›› ብሎ ጮኸበት፡፡ ሰዉዬዉ፤ ትልቁ ሰዉዬ የሚጋልቡበትን አቅጣጫ ይዞ በሩጫ ተፈተለከ፡፡
ይሄን ሁሉ አልፌ ያሰብኩት መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሼ ቆምኩ፡፡ ጊታር እንኳን መጫወት የማይችሉ የነበሩ ታዋቂ ሙዚቀኞች፤ ጊታራቸዉን ይዘዉ በለሊት መስቀለኛ መንገድ ላይ ሲቆሙ፤ ሰይጣን መጥቶ ጊታር መጫወትና ማንጎራጎር እንዳስቻላቸዉ ሰምቻለሁ፡፡ ምናልባት እነዚህ ሰዎች ጊታር መጫወት መቻልን የፈለጉት እናታቸዉ ወይ ሌላ ሊያናድዱት የሚፈልጉት ሰዉ ቢኖር ነዉ:: ካልሆነማ ያልተሰጣቸዉን ተሰጥኦ ለማግኘት ሲሉ እንደዚህ አይሞክሩም ነበር፡፡
መስቀለኛዉ መንገድ ላይ ትንሽ እንደቆምኩ፤ ታላቅ ድምጽ ያላቸዉ እንደ‹ቶርኔዶ› የሚጠቀለሉ ሦስት ነፋሶች ከኋላዬ መጥተዉ አጠገቤ ደርሰዉ ቆሙ፡፡ የሚጠቀለል ነፋስ ሰይጣን ተሸክሞ እንደሚዞርና ሰባት ምላጮች ወደ ነፋሱ ቢወረወር፤ ሰይጣኑን እንደሚቆርጠዉና ደሙን እንደሚያፈሰዉ ልጅ እያለሁ ሰምቻለሁ:: ድንገት ከሦስቱ ነፋሶች ሦስት ሰይጣኖች ዱብ ዱብ እያሉ ወረዱ፡፡ ከዚያም በሚሰቀጥጥ ድምጽ፤ ‹‹የተራራዉ ይሻልሀል እሱን ምረጥ!......አይደለም የወንዙን ምረጥ!......የበረሃዉ ነዉ የሚሻልህ እሱን ምረጥ!›› እያሉ ተንጫጩ:: ከዚያም እርስ በእርስ ትንሽ ከተጨቃጨቁ በኋላ ‹በቃ እራሱ ይምረጥ› ብለዉ፤ ወደኔ መጥተዉ ፊት ለፊቴ ቆሙ፡፡
ሰይጣኖቹ የሰዉ አካል ያላቸዉ ሲሆን ግንባራቸዉ ግራና ቀኝ ላይ ትንንሽ ቀይ ቀንዶች ይታያሉ፡፡ ከኋላቸዉ ዉን፣ ዉን የሚል፤ ነገር የሚፈልግ የሚመስል፤ ጫፉ ላይ ቀስት ያለበት ጭራ አላቸዉ፡፡ አትኩሬ ስመለከታቸዉ፣ አንደኛዉ ሰይጣን መልኩ የእናቴን ይመስላል፡፡ ሌላኛዉ የክርቶስ ሰምራ ምስል ላይ፤ ክርስቶስ ሰምራ ቀንዱን ይዛ ከእግዚሀር ልታስታርቀዉ የምትሞክረዉን ሰይጣን ይመስላል፡፡ ክርስቶስ ሰምራ የጨበጠችዉ ቀንዱ ለምልሞ፤ እላዩ ላይ አደይ አበባ በቅሎበታል፡፡ ሌላኛዉ እንግዳ ነዉ፡፡ እንግዳዉ ሰይጣን፤ ‹‹ከባህር፣ ከተራራና ከበረሃዉ ሰይጣን የቱ ይሻልሀል? እራስህ ምረጥ›› አለኝ፡፡ ምላሽ ሳልሰጥ ለደቂቃዎች ዝም አልኩኝ፡፡ አልፈራኋቸዉም፡፡ እሳት በሚተፉት ዓይኖቻቸዉ የእነሱን እንድመርጥ ለማባበል ሞከሩ:: ችግሩ የትኛዉ የባህር፣ የትኛዉ የተራራ፣ የትኛዉ ደግሞ የበረሃ እንደሆነ ላዉቅ አልቻልኩም፡፡ ማንኛዉም ቢሆን እኔ የምፈልገዉ፤ እንዳባቴ ጎበዝ መሰንቆ ተጫዋች የሚያደርገኝን ነዉ፡፡ ይሄ እንዴት አይገባቸዉም:: እናቴን የሚመስለዉ፤
‹‹ሣልሳዊ ገብቶሀል አይደል ያልነዉ?›› ድምጹ የሚያስፈራ ቢሆንም፣ አነጋገሩ ግን ከእናቴ ይልቅ የለሰለሰ ነዉ፡፡ ያሉት ቢገባኝም አንድ ያልገባኝ ነገር ግን እንግዳዉ የተናገረዉን፤ በአንድነት እንደተናገሩት ሁሉ ‹ገብቶሀል ያልነዉ?› ማለቱ ነዉ፡፡
‹‹እኔ የምፈልገዉ እንዳባቴ ጎበዝ ማሲንቆ ተጫዋች የሚያደርገኝን ነዉ›› አልኳቸዉ፤ ቆፍጠን ብዬ፡፡
‹‹እናትህን ልታናድዳት?›› አለኝ እናቴን የሚመስለዉ ሰይጣን ፈገግ ብሎ፡፡ ሰይጣን ፈገግ ይላል እንዴ? ደግሞ እነዚህን ሁሉ ሹል ጥርሶች ከየት አመጣቸዉ? ጥርሶቹ እንደዚህ ከሆኑ፣ ሁሌ እንደተኮሳተረ ቢኖር ይሻለዋል፡፡
‹‹እናቴን ላናድዳት እንደምፈልግ እንዴት አወቅህ? ደግሞ እናቴን ነዉ የምትመስለዉ›› አልኩት፡፡
ሦስቱም በሣቅ ወደቁ፡፡
‹‹እንዴት አወቅህ? ማን መሰለህ ወደዚህ ጎትቶ ያመጣህ? ሁሉን ነገር እናዉቃለን፡፡ ደግሞ እናትህን የምመስለዉ ቤተኛችሁ ስለሆንኩ ነዉ::››
‹‹ታድያ ካወቅህ ለምን መሰንቆ መጫወቱን አታስተምሩኝም? እናንተ ካልቻላችሁ ሮበርት ሊሮይ ጆንሰንን ጊታር መጫወት ያስተማረዉ ጋር ዉሰዱኝ::››
‹‹ታድያ ለምን ሚሲሲፕ አትሄድም››
እንግዳዉ አንድ ሺህ የሚበልጡ ሹል ጥርሶቹን እያንቀጫቀጨ ሣቀ፡፡
‹‹ካልቻላችሁ አንችልም አትሉም እንዴ? ሙድ ትይዛላችሁ እንዴ?›› ተቆጣኋቸው፡፡
‹‹ባንዴ ዝም ብሎ ማስለመድ አለ እንዴ?›› እናቴን የሚመስለዉ ተናገረ፡፡ እናቴን ስለሚመስል ብቻ ጉዳዩን እሱ መያዝ ፈልጓል መሰለኝ፡፡
‹‹እንጃ!›› አልኩት፡፡
‹‹ቆይ መሰንቆ መጫወት ከቻልኩ በኋላ እናቴ እንዳባቴ ታስገድለኝ ይሆናል ብለህ አልፈራህም?››
‹‹አባቴን እናቴ ናት እንዴ ያስገደለችዉ?››
‹‹እንደዛ ነገር›› አለኝና የክርስቶስ ሰምራ ሰይጣን፤ ሦስቱም ተያይዘዉ ተሳሳቁ፡፡
እናቴን የሚመስለዉ ቀጠለ፤ ‹‹እናትህ ባባትህ ትቀና ነበር፡፡ በዚህ ጋ መልኩ፤ በዛ ላይ ደግሞ ሙዚቀኝነቱ ተደማምሮ ሴቶች ሁሉ ይከንፉለት ነበር፡፡ እናትህ ቅናቱን አልቻለችም፡፡ በዛ ላይ እኔም እየሄድኩ በይ፣ በይ እላታለሁ፡፡ ከዛ አንዱ ጥላ ወጊ ጋ ሄዳ፤ መሰንቆዉን እንዲወጋላት ተስማማች፡፡ ይህን ያደረገችዉ ሙዚቃዉን መጫወት እንዲያቆም ነበር:: ነገር ግን ጥላ ወጊዉ መሰንቆዉን ከወጋ በኋላ አባትህ መሰንቆ መጫወት ስላልቻለ፣ በድብርትና በጭንቀት ወዲያዉኑ ታሞ ሞተ፡፡›› ተያይዘዉ ተሣሣቁ፡፡ በሣቃቸዉ ኃያልነት ቦታዉ መብረቅ የወደቀበት ያህል በነጎድጓድ ታረሰ፡፡
ሰይጣኖቹን አንድ በአንድ እያነሳሁ ባፈርጣቸዉ በወደድኩ፡፡ ግን እትዬ ወለቱ እንደነገሩኝ ሰዉዬ፤ ሰይጣኖቹን አንስቼ ካፈረጥኩኝ በኋላ፣ አካሌ ልፍስፍስ እንዲሆን አልፈልግም፡፡ ልፍስፍስ ከሆንኩ መሰንቆ መጫወት አልችልም፡፡ እናቴ እንደዛ ከሆንኩ፣ አባቴ ልፍስፍስ የሆነ ያህል ደስ ይላታል፡፡
‹‹አሁን እንዴት ነው መሰንቆ መጫወት የምችለው?›› አልኳቸው፡፡
እናቴን የሚመስለው ወደኔ ቀረብ ብሎ፤ ‹‹ልጅ ይኸውልህ መሰንቆ መጫወቱን ከመማርህ በፊት፤ የምትፈጽማቸው ሥርዓቶች አሉ፡፡››
‹‹የምን ሥርዓቶች?››
‹‹ይሄ ጊዜአችንን ሊገድል ነው፡፡ ለምን አጠናግረነው ወደ ሥራችን አንሄድም›› አለ እንግዳው ሰይጣን፡፡
‹‹ቆይ! ቆይ! ይሄም ሥራ እኮ ነው፡፡ ሌሎች ወደኛ እንዲመጡ ከማድረግ  ወደኛ የመጣን ማስተናገዱ አይቀድምም!›› አለ እናቴን የሚመስለው፡፡
የክርስቶስ ሰምራው ሰይጣን ብዙም አያወራም፡፡
‹‹አንተማ ከቤታቸው በላሁ ብለህ ማገዝህ ነው::›› እንግዳው ተነጫነጨ
‹‹ለእሱ አይደለም!›› አለ እናቴን የሚመስለው ሰይጣን፡፡
ከዚያም ወደ እኔ ዞሮ፤ ‹‹በነገራችን ላይ እናትህ ለምንድን ነው መሶቡን ባዶ የምታሳድረው? በፊት፣ በፊት እኔና ቤተሰቦቼ፣ ገብተን ሰውን እያስመሰልን፤ በሰው ሥርዓት የምንጫወትበት ቁራሽ እንጀራ ትተውልን ነበር፡፡ አሁን ግን መሶባችሁ በአብዛኛው ባዶ ነው፡፡ ምን መሆኗ ነው ግን?››
‹‹ኑሮው ነዋ! አሁን እንኳን ቁራሽ እንጀራ ልትተው ቀርቶ በቅርቡ የመሶቡን አክርማና ሰበዝ መብላት መጀመራችን አይቀርም፡፡ አሁን አመጣጤ ለእሱ ሳይሆን ለመሰንቆው ነው፡፡ እሺ ስለ ሥርዓቱ ንገረኝ? ሥርዓቱ ምንድነው?››
‹‹መጀመርያ ‹ሚሳብ› ያስፈልግሀል!›› አለ እናቴን የሚመስለው፡፡
‹‹ሚሳብ ምንድነው?››
‹‹ወይኔ ይሄ ልጅ! ለምን ግን አናጠናግረውም!›› እንግዳው ተናደደ፡፡
የክርስቶስ ሰምራ ሰይጣን ቀርቦ፤ ‹‹ሚሳብ አስፈላጊውን ምስ አቅርቦ መንፈሱን ጠርቶ፤ ከመንፈሱ ጋር የሚያዋርስህ ደብተራ ነው፡፡ እሱ የሚልህን ከፈጸምክ በኋላ፣ ፈጣሪህን ክደህ፣ ከጩሌ ጣትህ ደም አፍስሰህ፣  ከመንፈሱ ጋር የደም ቃል ኪዳን ትገባለህ፡፡ ስትሞት ነብስህን እኛ ነን የምንወስዳት፡፡››
‹‹ነፍሴ ምን ያደርግላችኋል?›› ተያይዘው መሬት ላይ እየተንፈራፈሩ ሣቁ፡፡
እነ  ጆንስን ጊታር መጫወት ለመቻላቸው፤ በምላሹ ነብሳቸውን ሸጠዋል ሲባልም ሰምቻለሁ:: እኔ ግን አላመንኩም ነበር፡፡ ቆይ ሰይጣን የሰው ነብስ ምን ያደርግለታል? ምን ሊሠራበት? እግዚሀሩን ለማናደድ ቢል እንኳን የትኛው እግዚሀር? የሌለ ነገርን ማናደድ ይቻላል እንዴ? ምናልባት ሰይጣኑ እንዲያው በብላሽ አለማመድኳችሁ ላለማለት ይሆናል እንደዛ ያስወራው፡፡
‹‹እውነቴን እኮ ነው! እኔ ከሞት በኋላ ባለ ህይወት አላምንም፡፡ ባይገርማችሁ በፈጣሪ መኖር እንኳን አላምንም፡፡ ታድያ መኖሩን እንኳን የማላምነውን ፈጣሪ እንዴት ልክድ እችላለሁ? ከቻላችሁ ለምን ዝም ብላችሁ መሰንቆውን መጫወት አታስተምሩኝም?››
‹‹እኛ እኮ ሰይጣኖች ነን፡፡ ሙዚቃ አስተማሪዎች አይደለንም፡፡ ለምን ሙዚቃ ትምህርት ቤት አትገባም?›› እንግዳው ሣቁን አቋርጦ አፈጠጠብኝ፡፡
‹‹እኔ እንደ ሮበርት ጆንሰን በአንድ ቀን አስደናቂ የሙዚቃ ችሎታ እንዲኖረኝ ነው የምፈልገው::›› አልኳቸው፡፡ የክርስቶስ ሰምራው ሰይጣን፣ የጓደኞቹን/ወንድሞቹም ሊሆኑ ይችላሉ/ ትኩረት በእጆቹ ለማግኘት እየሞከረ፤ ‹‹ጋይስ ጋይስ ቆይ ፈጣሪ አለመኖሩን ከካደ ከዚህ በላይ ምን እንፈልጋለን? ለምን አናስለምደውም?››
‹‹ኖ ኖ የእግዜር ነገር አይታወቅም፡፡ በኋላ አንድ ነብሱን ማዳኛ ምክንያት አያጣም፡፡ ዕድላችንን ለማስፋት የግድ የደም ቃል ኪዳን ያስፈልጋል፡፡›› እንግዳው ፈርጠም ብሎ ተናገረ:: የቀሩት ሰይጣኖች በሀሳቡ ተስማሙ፡፡
‹‹የእውነት ግን እግዚሀር አለ እንዴ?›› በመገረም ጠየቅኋቸው፡፡ ተያይዘው ተሣሣቁ፡፡ ነገሩ የሚያሥቅ ሆኖ ሳይሆን ፈጣሪን ለማናደድ ብለው እንደሚሥቁ ገብቶኛል፡፡
ግን ፈጣሪ ካለ እንዴት አባቴን ወስዶ እናት የተባለች እሳት ላይ ጣደኝ? ወይስ ለምን እናቴን ወይ ሌላ ሰው እንድመስል አድርጎ አልፈጠረኝም? እውነት እግዜሩ ካለ እንዴት ዕድሜ ጠግበው ወደ ላይ ወደ ላይ የሚላቸውን እትዬ ወለቱን አስቀምጦ፤ እንደ ዓይኖቻቸው የሚሳሱላቸውን ሁለቱ ልጆቻቸውን በጊዜ ወሰደባቸው? የእንጀራ አባቴንስ ለምን እናቴ ላይ ጣለው? እነዚህ ሰይጣኖችንስ ቢሆን ግብር እንደማይከፍሉ የሜዳ ላይ ነጋዴዎች፤ ገበያውን ሲሻሙት እያየ እንዴት ዝም አላቸው? ቆይ ፈጣሪ ምንድነው የሚሰራው? ምን አስቦ ነው ግን?
‹‹ለምን ይሄን ልጅ አጠናግረነው አንሄድም? ዝም ብሎ ነው ጊዜያችንን የሚገድለው?›› አለ እንግዳው ሰይጣን፡፡
‹‹ተረጋጋ! ገና ዘላለም አይደል እንዴ የምንኖረው!›› እናቴን የሚመስለው ሊያረጋጋው እጁን ያዘው፡፡
‹‹ወይ በቃ እንሂድ! እኔ ማሳት እፈልጋለሁ:: የለፋሁበት ነው ደስ የሚለኝ፡፡›› እንግዳው ሰይጣን ተረጋግቶ መለሰ፡፡
‹‹አዎ እንሂድ! ለእሱ እናቱ አለችለት! ኢፍ ዩ ኖው ዋር አይሚን!›› የክርስቶስ ሰምራ ሰይጣን ሁለቱን ጠቀሳቸው፡፡ ሲጣቀስ መብረቅ ወደቀ፡፡
እናቴን የሚመስለው ወደ እኔ ዞር ብሎ፤ ‹‹እሺ ልጅ በቃ ፈጣሪን ክደህ፣ የደም ቃል ኪዳኑን አድርግና ከአባትህ በላይ ጎበዝ የመሰንቆ ተጫዋች እናደርግሀለን፡፡ የዚያኔ እናትህን ጨርቋን አስጥለህ ማሳበድ ትችላለህ፡፡ እሱን ነው የምትፈልገው አይደል?››
‹‹ቆይ ግን መሰንቆ ነው ማሲንቆ ነው የሚባለው ግን?›› አለ የክርስቶስ ሰምራው ሰይጣን፡፡
‹‹የማላምነውን ፈጣሪ ምን ብዬ ነው የምክደው?››
‹‹አንተ ካላመንክበት መካዱ ለምን ከበደህ?››
‹‹እውነቱን ልንገራችሁ፤ እውነት ፈጣሪ ካለማ ከሁሉም ነገር በፊት እሱን ልጠይቀው የምፈልጋቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ፡፡ ቆይ የት እንደማገኘው ትነግሩኛላችሁ? አንተኛው ቆይ፤ ክርስቶስ ሰምራ ከእግዜሩ ጋር ልታስታርቅህ የት ነው ይዛህ የሄደችው? ቦታውን ታስታውሰዋለህ?››
‹‹ይሄ ልጅን እናጠናግረው›› የክርስቶስ ሰምራው ሰይጣን ተቆጣ፡፡
‹‹አዎ!›› አለ እንግዳው፡፡
‹‹ካለማ እግዚአብሔርን እፈልገዋለሁ!›› አልኩኝ::
ይሄን ከማለቴ ሦስቱም ሰይጣኖች እንደ መብረቅ ብልጭ ብለው ጨለሙ፡፡ ግራ ተጋብቼ ትንሽ ከጠበቅኋቸው በኋላ፣ ፊቴን አዙሬ መንገድ ስጀምር፣ ከርቀት የሚያስተጋባ አንድ ድምጽ፤
‹‹ነገ እናንተን ለማስመሰልና በሰው ሥርዓት ለመጫወት፣ ቤተሰቦቼን ይዤ እቤታችሁ እመጣለሁ:: እናትህን ቁራሽ እንጀራ መሶቡ ውስጥ ማስቀረቷን እንዳትረሳ ንገራት፡፡ አለበለዚያ ባዶ ያድርግሽ ብዬ ነው የምረግማት::›› አለኝ፡፡ እናቴን የሚመስለው ሰይጣን ድምጽ እንደሆነ ገባኝ፡፡
ሌላ ድምጽ በእልህ፤ ‹‹መጀመርያውኑ እናጠናግረው እያልኳችሁ አልነበረ!›› ሲል ተሰማኝ፡፡
እንግዳው ሰይጣን ለምን እንደጠመደኝ አላውቅም፡፡ ማንን እንደሚመስል ማስታወስ ስላቃተኝ  ይሆን?
‹‹እንዳትረሳ ለእናትህ ንገራት›› አለኝ እናቴን የሚመስለው ሰይጣን በታላቅ ድምጽ፡፡
ጮክ ብዬ፤ ‹እሺ› ልለው አሰብኩና፣ ባልነግረውም እንደሚያውቀዉ ስለገባኝ ተውኩት፡፡ ሌላ ሀሳብ ገባኝ፡፡ ለእናቴ ይሄን ባልነግራት፤ እንደውም መሶቡ ውስጥ የተረፈ ካለ አውጥቼ ብጥለው፣ እናቴን ማስረገም እችላለሁ ማለት ነው ስል አሰብኩ፡፡ ግን ደግሞ ሰይጣኑ አሳዘነኝ፡፡ ቤተሰቦቹን ሰብስቦ መጥቶ አዝኖ ለምን ይመለስ? እንደውም እናቴ ባታስተርፍለት እንኳን እኔ የራሴን እራት መሶብ ውስጥ አኖርለታለሁ፡፡
ቆይ ግን ይሄ ሰይጣንና ቤተሰቡ፣ ከእኛ ቤተሰብ ምናችንን ነዉ የሚያስመስሉት? እሱ እናቴን ነዉ የሚመስለው፡፡ ስለዚህ እናቴን ሆኖ አንድ የሚያሰቃየው ልጅ ሳይኖረው አይቀርም:: ክርስቶስ ሰምራ ያኛውን ሰይጣን ሳይሆን የዚህን ሰይጣን ልጅ ነበር እግዚአብሔር ጋ ይዛ መሄድ የነበረባት:: ልጅየው በእርግጠኝነት እንደኔ እግዚሀሩን የሚጠይቀው ብዙ ጥያቄዎች ይኖሩታል፡፡ አሁን እግዚሀሩ የት እንደሚገኝ የሚያሳየኝ  ሰው መፈለግ ሳይኖርብኝ አይቀርም - ላናግረው እፈልጋለሁ፡፡

Read 3671 times