Saturday, 02 June 2012 09:35

የአሜሪካ የስፔሊንግ ቢ ተወዳዳሪ ኢትዮጵያዊቷ ታዳጊ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የአርቲስት ሙላቱ “ተተኪ” የተባለው ሳሙኤል ኮንሰርት ያቀርባል

ኢትዮጵያዊቷ ታዳጊ ናጃት አልከድር፤ በአሜሪካ የመለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች መካከል በሚደረገው የእንግሊዝኛ ስፔሊንግ ውድድር መሳተፍ የጀመረችው አምና ሲሆን በምትኖርበት በኖርዝ ካሮሊና በተደረገው ክልላዊ ውድድር አሸንፋ ነበር፡፡ የ13 ዓመቷ ናጃት NACHTMUSIK የሚለውን ቃል ስፔሊንግ ተጠይቃ በትክክል የመለሰች ሲሆን ትርጉሙም የጀርመናውያን የምሽት የሙዚቃ ሥራ ማለት ነው፡፡ በዘንድሮው የስፔሊንግ ውድድር የተካፈለችው ናጃት፤ SUGGESTIBLE  የሚለውን ቃል ስፔሊንግ በትክክል በመመለስ በዋሺንግተን ለሚደረገው ብሄራዊ የስፔሊንግ ውድድር  አልፋ ነበር፡፡ በአሸናፊነቷም ከተለያዩ ባንኮችና ኩባንያዎች እስከ 100 ዶላር የሚደርሱ የገንዘብ ስጦታዎች እንደተበረከተላት ለማወቅ ተችሎዋል፡፡ በተለይ አባቷ ወደ ብሄራዊ የስፔሊንግ  ውድድር ከገባች እንደሚገዙላት ቃል የገቡላት ሞባይል ስልክ ናጃትን ተግታ የስፔሊንግ ጥናቱዋን እንድታጠና እንዳነቃቃት ትናገራለች፡፡

የመጀመርያው ዙር የስፔሊንግ ውድድር በአሜሪካ 50 ግዛቶች የተካሄደ ሲሆን 278 ተወዳዳሪዎች ተካፍለውበታል፡፡ ከተወዳዳሪዎቹ 24 በመቶ ያህል አማካይ ዕድሜያቸው 13 ነው ተብሏል፡፡ ከአሜሪካውያን ውጭ የተለያዩ አገራት ዜጐች በተሳተፉበት ውድድር፤ ኢትዮጵያ (በታዳጊዋ)፣ ካናዳ፤ ጃማይካ፤ ጋና እና አውሮፓውያን እንደተወከሉ ታውቋል፡፡

“ጥሩ ጭንቅላት አላት፡፡ ፈጣሪ አድሎታል እኮራባታለሁ” ብለዋል - አባቷ አቶ አሚኒ አለሙ፡፡  የናጃት ቤተሰቦች አሜሪካ በስደት የገቡት ከ17 ዓመት በፊት ሲሆን ወላጆቿ እንኳን እንግሊዝኛ ይቅርና አረብኛም አይችሉም፤ የሚናገሩት አማርኛ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ገና በሁለት ዓመቷ አሜሪካ የገባችው ናጃት፤ በእንግሊዘኛ ነው አፏን የፈታችው፡፡ አማርኛ ትሰማለች እንጂ ብዙ አትናገርም፡፡ ገና በ3 ዓመቷ እንግሊዘኛን ማንበብና መፃፍ የጀመረችው ናጃት፤ ለሰሞኑ ወድድር  በቀን እስከ 3 ሰዓት የእንግሊዝኛ ስፔሊንጎችን በመሸምደድ ስትዘጋጅ ቆይታለች፡፡

የህፃናት ሃኪም የመሆን ህልም ያላት ናጃት፤ የኮርያ ፊልሞች፤ ድራማዎችና ሙዚቃዎችን ትወዳለች፡፡ ከምግብ ላዛኛ የምትወደው ታዳጊዋ፤ ስካትዴሪዬን የተባለውን ጌም በመጫወትም ትዝናናለች፡፡ እንግሊዘኛ ንባብ እና ታናሾቿንና ወላጆቿን በማስተማር ጊዜዋን እንደምታሳልፍም ተናግራለች፡፡ ባለፈው ሐሙስ ለንባብ የበቃው ዊንስተን ሳሌም ጆርናል፤ ነጃት አልከድር ረቡእ እለት በተሳተፈችበት 85ኛው የስክሪፕስ ስፔሊንግ ቢ ውድድር ለግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ አለመቻሏን ጠቁሟል፡፡ ታዳጊዋ ማለፍ ያልቻለችው በቃል በቀረበላት የስፔሊንግ ጥያቄ ሳይሆን በኮምፒውተር በተጠየቀችው የቃላት ፐዝል (የጎደለውን ፊደል ሙላ) እንደሆነ ጆርናሉ አመልክቷል፡፡ ነጃት በመጀመርያ ዙር የሁለት ቃላት ስፔሊንግ በቃል ተጠይቃ ሁለቱንም በትክክል መልሳ ነበር፡፡ fenestrated እና schadenfreude  የሚሉትን ቃላቶች፡፡

በኮምፒውተር በቀረበው የስፔሊንግ ፈተና 277 ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ለግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ 23 ነጥቦች ማስመዝገብ ይጠበቅባት ነበረ፡፡ ናጃት ግን 17 ነጥቦችን ብቻ በማግኘቷ ለግማሽ ፍፃሜ ሳታልፍ ቀርታለች - የ7ኛ ክፍል ተማሪዋ ናጃት፡፡

በሌላ በኩል የአርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ተተኪ እንደሚሆን የተገመተው ኢትዮጵያዊው ፒያኒስት ሳሙኤል ይርጋ፤ በቀጣዩ አንድ ወር በአውስትራሊያ ሦስት ከተሞች በሚደረጉ ዓለም አቀፍ የጃዝ ፌስቲቫሎች ኮንሰርቶች ላይ እንደሚሳተፍ ተገለፀ፡፡ በፒያኖ ተጨዋችነቱ የተደነቀው ሳሙኤል ይርጋ፤ ከወር በፊት አስራ አንድ የኢትዮጵያ ክላሲካል ዜማዎችን “ጉዞ” በሚል የአልበም መጠርያ በአውስትራሊያና በኒውዝላንድ ለገበያ አቅርቧል፡፡ ይሄ የመጀመርያ አልበሙ ኒውዎርልድ ሪከርድስ በተባለ አሳታሚ በቅርቡ በመላው አለም ለገበያ ይቀርባል፡፡

አልበሙ “የባቲ ቆይታ”፤ “አቤት አቤት”፤ “ትዊስቲ”፤ “ፊርማና ወረቀት” የተሰኙ ዜማዎችን ያካተተ ሲሆን ለጥላሁን ገሰሰ መታሰቢያነት የተሰራ “ዳንስ ዊዝ ሌጀንድ” የተባለ ዜማም  እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡

በአውስትራሊያ የሚሟሸው የፒያኒስት ሳሙኤል ኮንሰርት በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ እና በሌሎች የአውሮፓ አገራት ይቀጥላል ተብሏል፡፡ የ25 አመቱ ሳሙኤል ይርጋ በመጀመርያ አልበሙ ስኬት እንደሚቀዳጅ ግምታቸውን የሰነዘሩ የአውስትራሊያ ሚዲያዎች፤ የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ አባት የሚባለውን አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ሊተካ እንደሚችል ተንብየዋል፡፡

ሙዚቃ ለመማር በ16 አመቱ በያሬድ ሙዚቃ ቤት የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና ከ2500 ተወዳዳሪዎች ጋር የወሰደው ሳሙኤል፤ 3ኛ ወጥቶ የመማር እድል እንዳገኘ ያስታውሳል፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መማር ሲጀምር ግን “የእጆችህ ጣቶች ትንንሽ ናቸው” በሚል ከፒያኖ ይልቅ ክላርኔት እንዲማር ተመደበ፡፡ ለሶስት ሳምንት ት/ቤቱ ዲያሬክተር ጋር ተመላልሶም ከክላርኔት ክፍል ወደ ፒያኖ ክፍል ተቀየረ፡፡ ለሦስት አመት በቀን የ12 ሰዓት ከባድ ልምምድ እያደረገ በፒያኖ አጨዋወት የተካነው አርቲስቱ፤ ከፒያኖ በተጨማሪ ክራር፤ ባለአምስት ስትሪንግ በገና እና ማሲንቆንም በመማር በከፍተኛ ብቃት ለመመረቅ ችሎዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በኬንያ ተካሂዶ በነበረው የምስራቅ አፍሪካ የሙዚቃ አዋርድ ላይ በዳኝነት የሰራው ሳሙኤል፤ የአራት ወራት ኮንሰርቱን ሲያጠናቅቅ በአፍሪካም ሥራዎቹን በስፋት የማቅረብ ዕቅድ አለው፡፡ ከአፍሪካ ትላልቅ ሙዚቀኞች ጋር አብሮ በመስራት እውቀቱን ማዳበር እንደሚፈልግም ይናገራል፡፡

ለሙያው መጐልበት የሙዚቃ ትምህርት የተከታተለበት ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ታላቅ ባለውለታው እንደሆነ የሚያስታውሰው ሳሙኤል፤ ይሄን ውለታ ለመመለስም በመጀመርያ አልበሙ ላይ የት/ቤቱን አስተማሪዎች እንዳሳተፈ ገልጿል፡፡ ቤተሰቡ በተለይ አባቱ ኢንጂነር እንዲሆን ይወተውቱት እንደነበር የሚናገረው ፒያኒስቱ፤ አያያዙን ካዩ በኋላ ግን “የተፈጠረው ለሙዚቃ ነው” በሚል መደገፍ መጀመራቸውን ይናገራል፡፡ “ጉዞ” የተሰኘው የአርቲስቱ የመጀመሪያ አልበም ዋጋ በኢትዮጵያ ብር ሲሰላ ወደ 272 ብር ገደማ ሲሆን ዋጋው ለኢትዮጵያውያን የማይቀመስ እንደሚሆን የተረዳው ሳሙኤል፤ በአገር ቤትም ትላልቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ለማቅረብ አቅዷል፡፡

 

 

Read 2075 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 09:49