Monday, 13 May 2019 00:00

የረመዳን ሶላት

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(1 Vote)

ረሺድ ኢብኒ ዛይድ በኢየሩሳሌም ሰሜናዊ ምስራቅ በምትገኝ መንደር ውስጥ ሶስት ክፍል ያለው የግንብ ቤት የተከራየው ለመላው ነበር፡፡ በ”ኢየሩሳሌም ትሪቡን” ላይ ዋና አምደኛ ሲሆን አብዛኛዎቹ ፅሑፎቹ ፖለቲካና ሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ፡፡ የብዙ ሃይማኖቶች መቀመጫና ማዕከል  በሆነችው ኢየሩሳሌም ውስጥ ስለ ሃይማኖትና ፖለቲካ መፃፍ፣ ለአንድ ሙስሊም አምደኛ፣ በጣም አደገኛ ስራ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በብዙ ጠላቶች የግድያ ሙከራ ቢደረግበትም፣ እንደ አጋጣሚ ይሁን ወይም እሱ እንደሚለው አላህ ጠብቆት፣ብዙ  የግድያ  ሙከራዎችን አምልጧል፡፡
በሮመዳን ዋዜማ የደረሰው ደብዳቤ ግን የመጨረሻ ህልፈቱ በነጋታው እንደሚሆን የሚጠቁም ሲሆን መሞቱ እንደማይቀር ያረጋገጠው ለግድያው ኃላፊነቱን የሚወስደውን ድርጅት አርማ ፖስታው ላይ ከተመለከተ በኋላ ነው፡፡ “T.R.F” በመላው ዓለም መረቡን የዘረጋ “የሰይጣን አምላኪ” ድርጅት ነው ደብዳቤውን የላከለት፡፡ ከሳምንት በፊት ባወጣው መጣጥፍ፣ ድርጅቱ በየቀኑ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ህፃን ልጅ እያረደ ለሰይጣን እንደሚገብር አጋልጦ ነበርና፣ አያ ረሺድ፣ “በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ” ውርጅብኙን እንደሚቀበል ሁሉም ሰው ማውራቱ አልቀረም፡፡ እሱም ይህን ያውቅ ነበርና፣ ኒውዮርክ ሲቲ ላለው ሀብታም ወዳጁ፣ ከኢየሩሳሌም ለመውጣት ይረዳው ዘንድ አንድ ሚሊየን ዶላር እንዲልክለት ስልኩንና ኢሜይሉን ሰጥቶ፣ በምላሹ ገንዘቡ በመጀመርያው የሮመዳን ቀን፣ በዌስተርን ዩኒየን እንደሚገባ ቃል ተገብቶለታል፡፡ የሚጠብቀው የሚስጢር ቁጥሩን ወዳጁ፣ ስልክ ደውሎ እስኪነግረው ድረስ ብቻ ነው፡፡
እቅዱ የጎህ ሶላት ከሰገደ በኋላ ገንዘቡን ከባንክ  አውጥቶ ወደ ሃይፋ መብረር ነው፡፡ ከዚያም በመርከብ ተሳፍሮ ወደ እንግሊዝ፣ ከእንግሊዝ ደግሞ ወደ ኒውዮርክ መሻገር፡፡ “በሮመዳን ሰይጣን ይታሰራል” የሚለውን የነቢይን ሃዲስ ሙሉ ለሙሉ ቢያምንበትም፣ “አላህን አምኜ ግመሌን ትቼ መስጊድ ልስገድ ወይስ ግመሌን አስሬ ገብቼ ልስገድ?” ብሎ ለጠየቃቸው በደዊ (ባላገር)፣ ነብዩ የመለሱትን የበለጠ ያምንበታል፡፡ “አላህንም እመን ግመልህንም እሰር” ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ አላህንም አምኖ ከግድያውም ለማምለጥ ማድረግ ያለበትን ጥንቃቄ ሁሉ አደረገ፡፡  
የአይን መነፅር የማይለየው ረሺድ፤ ካኪ ሱሪውንና ካኪ ኮፍያውን ከጥቁር ጃኬቱና ፊቱን ከሚሸፍን ስካርፍ ጋር ካደረገ በኋላ በማንቆርቆሪያ ውሃ እየቀዳ ውዲ ማድረግ ጀመረ፡፡ ውዲውን አድርጎ ከጨረሰ በኋላ ከመስጂድ አል አቅሳ ጋር የተገኘውን ቻናል ከፈተና አዛን መጠባበቅ ያዘ፡፡ እንግዲህ ፆም የሚገባበት ቀን ነው፡፡ ከአዛን በፊት በነብዩ ሱና መሰረት፣ እህል ውሃ ነገር (አዛን እስኪባል ድረስ) መቀማመስ ግድ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ጥቂት ቴምሮችና የተቆራረጡ ፍራፍሬዎችን ከውሃ ጋር አዘጋጅቷል፡፡ ፍራፍሬዎቹን ሲመለከት ከአገሩ እስራኤል መለየቱን አሰበና አይኖቹ እንባ አቀረሩ፡፡ እልም ባለ በረሃ ውስጥ የኤደን ገነት፣ የፍራፍሬ ጥጋብ ለህዝብዋ የፈጠረች ብቸኛ ግን ኃይለኛ አገሩ እስራኤል!
ፍራፍሬውን ቀማምሶ ውሃ ከጠጣ በኋላ ሙአዚኑ አላህ ወአክበር አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ምግብ መቅመስ አይቻልም። አሰጋጁ (ኢማም) ማሰገድ ጀመረ፡፡ ልክ ስግደቱን እንደ ጀመረ፣ ስልኩ ጠራ፡፡ ልቡ መምታት ጀመረ፡፡ ስልኩን አለማንሳት አንድ ሚሊዮን ዶላር ማጣት ብቻ ሳይሆን ህይወቱን ማጣት ጭምር ነው፡፡ ሶላቱን ማቋረጥ ደግሞ እስከዛሬ የኖረበትን እውነቱንና የአላህ ፍራቻና ፍቅር ማጣት ነው፡፡ ሁለቱም ህይወት ማጣት ነበር፡፡ ገንዘቡን አግኝቶ አላህን ማጣት ወይም አላህን ይዞ ገንዘቡንም ህይወቱንም ማጣት አጣብቂኝ ፈተና ሆነበት፡፡ ሶላቱን ላለማቋረጥ ወሰነ፡፡ ስልኩ ለአስር ጊዜ ያህል ጮሆ ቆመ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ይጠራ ይሆናል ብሎ ገምቷል፡፡ ኢማሙ የሚቀራው ቁርአን በጣም ረጅሙን ኮይል ነው፡፡ ስልኩ እንደገና መጥራት ጀመረ፡፡ አሁን አቋርጦ ለማንሳት ተወሰወሰ፡፡ ነገር ግን የቁርአኑ መልዕክት፤ በእምነታቸው ለፀኑ ባርያዎች አላህ ስለአዘጋጀው ጀነት የሚገልጽ ነበር፡፡ “አቋርጬ  እንደገና መስገድ እችላለሁ” ብሎ ቢያስብም፣ ቁርአኑ ስለ መናፍቆች ወይም አድርባይ አማኞች የሚጠቅሰው ክፍል ላይ ደርሶ ነበርና ጥርሱን ነክሶ ሶላቱን ቀጠለ፡፡ አሁንም ስልኩ ዘጠኝ ጊዜ ጠርቶ ቆመ፡፡
 ሶላቱ መገባደጃ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ስልኩ ጠራ፡፡ ረሺድ ግን አሁን ለመሞት ወሰነ፡፡ ቁርአኑ፤ አላህ ለመፍት የአላህ ባርያዎች ከጭንቅ አውጥቶ ምድራዊውንም ሰማያዊውንም አለም፣ ያሻቸውንና የምኞታቸውን እንደሚሰጥ የሚያበስር ነበር፡፡ ስለቱ ተገባደደ፡፡ ረሺድ እስከ ጠዋቱ አስራ ሁለት ሰአት ተኩል ድረስ ስልኩ ላይ አፍጥጦ መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ዳግመኛ አልተደወለም፡፡ ጫማውን ተጫምቶ ቤቱን ለቆ ወጣ፡፡ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ፡፡ ከቤቱ ራቅ ብሎ በሚገኝ ጭር ያለ አውራ ጎዳና ላይ መኪናውን አቆመና፣ ላፕቶፑን ከፍቶ ኢሜይሉን ማየት ጀመረ፡፡ ወዳጁ ሮበርት መልዕክት ልኮለታል፡፡ “ለማንኛውም ኢሜይልህን እንደምትከፍት ስለማውቅ የሚስጥር ቁጥሩ 90444947 ነው፡፡” ይላል፡፡ ልቡ በደስታ ጮቤ እየረገጠ፣ ወደ ባንኩ በፍጥነት  መንዳት ጀመረ፡፡
ዋናው የ”T.R.F” ድርጅት ፕሬዚዳንት፣ ይሄን በማያገባው የሚገባ ሾካካ ጋዜጠኛ መሞት አለመሞት ለማረጋገጥ ሬሳውን እሱ እራሱ ለማየት ወስኗል፤ምናልባት ካልሞተም የድምፅ ማፈኛ በተገጠመለት ሽጉጥ ሊገላግለው ተዘጋጅቷል፡፡ በሩ ከተቆለፈ በሚል ማንኛውንም ቁልፍ መስበር የሚችል ዘመናዊ መሳርያ ታጥቋል፡፡ የሱ ሰዎች “ስለ አገዳደሉ አትጨነቅ፣ እኛ እንሰራዋለን” ቢሉትም፣ ጠንቃቃው የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ግን ማንንም አምኖ ፈዞ የሚቀመጥ ሰው አልነበረም፡፡ ጊዜውም ለፈዛዞች ቦታ የለውም፡፡ የጦርነት ጊዜ ነውና፡፡ በሩን ገፋ ሲያደርገው እንዳጋጣሚ ክፍት ነበር፡፡ ወደ ውስጥ ዘልቆ ገባና በአይኑ ቤቱን ቃኘ፤ ማንም ሰው የለም፡፡ ዞር ሲል ግን ድንገት ስልኩ ጠራ፡፡ እንዴት ሊያመልጥ ቻለ ሲል አሰበና ምናልባት ውሽማው ወይም አንዱ ጓደኛው ሊሆን ይችላል በሚል ግምት፣ ጥቂት ፍንጭ ቢገኝ ብሎ ስልኩን አነሳው፡፡ ከእጀታው ጋር የተገጠመው ቦንብ፣ በሶስት ሰከንድ ውስጥ የሚፈነዳ ሲሆን እሱ ያየው አንድ ሰከንድ ብቻ ሲቀረው ነበር፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጠጠና “ገደል ግባ!” ብሎ አምባረቀ፤ጩኸቱን ተከትሎ ቤቱ በፍንዳታ ተናወጠ፡፡ የፈንጂው ኃይል አንድ ትልቅ ሆስፒል ዶግ አመድ ማድረግ የሚችል ነበር፡፡
 በቀጣዩ ቀን የወጣው “ኢየሩሳሌም ትሪቡን”፣ ረሺድ ኢብን ዘይድ የተባለው እውቅ አምደኛ እንደተገደለና በእሳት የተለበለበ ሬሳው እንደተገኘ፣ ከእሳቱ ኃይለኝነት የተነሳ የሟችን ማንነት መለየት ባይቻልም ከዚህ በፊት የደረሱትን የግድያ ማስጠንቀቂያዎችና ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች በመጥቀስ መሞቱን የዘገበ ሲሆን እሱ ይፅፍበት በነበረው አምድ ላይ ከሱ ጋር ተመጣጣኝ እውቀትና የአፃፃፍ ስልት ያለው ሮበርት የተሰኘ አምደኛ ፅሑፍ  አውጥቶ ነበር፡፡


Read 2334 times