Print this page
Monday, 20 May 2019 10:48

የግቢው ወግ...

Written by  ስ.አ
Rate this item
(3 votes)


            እንደለመደው ጽሁፉን ለጋዜጣ ለመላክ በዚያች አራቷም ጎኗ እኩል በሆነ ካሬ ጠረጴዛው ላይ እየፃፈ ደረስኩኝ፡፡ ሰአቱ ከረፋዱ አምስት ከሩብ ሆኗል፤ ከአልጋው ወርዶ ምንም ስራ እንዳልሰራ ሁኔታው ነግሮኛል.....ከቁምጣ ያልተናነሰ ፓንቱን እንዳደረገ፣ ጃፖኒ ለብሶ ደህና ልምጭ የማታክለውን ክንዱን ገላልጦ፣ በሩ  በጠባቡ ገርበብ ብሎ፣ በሩ ስር በፖፖ ያስቀመጠውን ሽንት እንኳን ሳይደፋው፣ ካልሲው እዚህም እዚያም ቄጠማ ላይ እንደሚበተን ፈንዲሻ ተበትኖ፣ አልጋው ላይ ያለው ብርድልብስና አንሶላ ወዲያና ወዲህ ምስቅልቅል ብሎ፣ ያልታጠበ ብረትድስትና ጭልፋ ተጠራቅሞ..... ነበር የደረስኩት::
“ምን ሆነህ ነው በናትህ ምሳ ሰአት እየደረሰ እኮ ነው...... እስካሁን ከአልጋህ አልወረድክም እንዴ?” አልኩት፡፡
“ምነው አልጋ ወራሽ! ምሳ ሰአት የደረሰስ እንደሁ ምን ላርገው ታዲያ.....ግዴታ ከአልጋ መወረድ አለበት ለምሳ ሰአት?” አለኝ.....በባህሪው ብዙም ቀጥተኛ መላሽ አይደለም፤ ይልቁንስ ጥያቄን በጥያቄ በመመለስ መፈላሰፍ  ይወዳል፡፡
“ኣኣይ እኩለ ቀን ሆኗል ብዬ ነው..... በዚያ ላይ ምናለበት ከተነሳህ አይቀር ሽንትህን ደፍተህ፣ ካልሲህን ሰብሰብ አርገህ፣ ትንሽ ቤቷን ፏ ነገር ብታደርጋት፤ ላንተም ለአይንህ ደስ ብሎህ ቀለል እያለህ ትፅፋለህ፤ ምናልባትም ደግሞ እንግዳም ድንገት ቢመጣ አያስደነግጥህም” አልኩት፡፡
ካቀረቀረበት ጠረጴዛ ቀና ብሎ በግርምት አስተያየት እያየኝ፤.
“ጆዬ?” አለኝ
“አቤት” አልኩ
“ዝም ብትል የምቀየምህ መስሎህ ነው የምትለፈልፈው?”
“ኸረ አይደለም፤እንዲያ ብታደርግ ላንተ የተሻለ ይሆንልሃል ብዬ ነው” አልኩት፡፡
“ሆሆ እንደ ነቢይም ያናግርህ ጀመር!....ቆይ ነሲቡ ለራሱ የተሻለውን ነገር አያውቅም ያለህ ማነው?”
ቀጠለ ጓደኛዬ ነሲቡ፤ “ጆዬ ይልቁንስ ቅድም ምን ነበር ያልከኝ? ካልሲህን ምናምን አነሳስተህ ቤቱን ፏ አድርገህ ነበር ያልከኝ? እስቲ ባወራ አፍህ እጅህንም አሰራውና አንዳፍታ እንዳልከኝ አድርጋት፤ እኔ ይቺን የጀመርኳትን ጽሁፍ ልጨርስ ጎሽ!” አለኝ፡፡
በገዛ እጄ ቀበጣጥሬ ስራ ታዝዤ አረፍኩ፡፡ አዬ እድሌ መቼስ ምን ይደረግ፤ በጣም ስለምወደውና ስለሚያሳዝነኝ እሺ ብዬ ቤቱን ማጽዳት ጀመርኩኝ:: ሽንቱንና ካልሲውን ዘወር ብዬ ሳይ ግን ጠረኑ ከአፍንጫዬ ስርን አልፎ ሁለመናዬን ስለረበሸኝ ዝግንን አለኝና፤ “እነዚህን አሲዲክ ንብረቶችህን ግን ራስህ አስወግድ!” አልኩት፤ፍርጥም ብዬ፡፡
“ውይ አንተ ልጅ ግን ታካብዳለህ” አለና እየተነጫነጨ ተነስቶ፣ አሮጌ ሱሪውን ከአልጋው ትራስጌ በኩል ከተቀመጠ አሮጌ ኩርቱ ፌስታል ውስጥ ስቦ አጠለቀና ነጠላ ጫማ አድርጎ ፣ አይኑን በመዳፉ ዳጥ ዳጥ አድርጎ፣ ፖፖውን ይዞ ሽንት ቤት ሊደፋ ወጣ፡፡ እኔ ደግሞ ሽንቱን ደፍቶ እስኪመጣ፣ ካልሲዎቹን በእግሬ ገፋ ገፋ አድርጌ፣ አልጋ ስር እንዲደበቁ አደረግሁ፡፡
አልጋው ስር የሆነ የተጠመጠመ ቀጫጭን ክር መሳይ የኤሌክትሪክ ሽቦ አገኘሁ...ምንድን ነው ብዬ ሳይ በአልጋው እራስጌ በኩል ዘልቆ ከአልጋው አጠገብ ከሚገኘው የቲቪ ስታንድ መሰል የመፅሐፍት መደርደሪያ አናት ላይ ከተቀመጠ ጣውላ መሰል ሬዲዮ ጋር ይገናኛል፡፡ አይ ነሲቡ የሚገርም ሰው ነው.....ሃሳብ እንደሚቀጣጥለው ሁሉ ሽቦ መቀጣጠልም ይወዳል፡፡ ሽቦውን ቀጣጥሎ ሬዲዮ መስማት እንደሚፈልገው ሁሉ ሃሳቡንም ቀጣጥሎ በወረቀት ላይ በማስፈር፣ እንደምን ያለ ድምፅና መልዕክት እንዳላቸው መስማት ይፈልጋል....ድምፅ አልባ ሃሳብ፣ ድምፅ አልባ ቀለም፣ ድምጽ አልባ ህይወት አይወድም.... “በዝምታ ውስጥ ያለ አንዳች ጥልቅ ንግግርና ድምፅ ቢኖርም ቅሉ፣ በጩኸት ካልተናገርክ በቀር በማይሰማህ ህዝብ ውስጥ እየኖርክ ዝምታ ምርጫህ ሊሆን አይችልም” የሚላት አባባል አለችው፡፡
ያችን በብዙ ቅጥልጥል ሽቦ አማካኝነት የምትሰራ ሬዲዮ ከፈትኳት.....የምትገርም ናት፤ እንደዚያ በቅጥልጥል ክር መሳይ ሽቦ ተያይዛም፣ አቧራ ጠግባ ተጎሳቁላም እንደ ብዙዎቹ ሬዲዮ እሽሽሽሽ ሳትል ጣቢያዋ መሥራት ይጀምራል...ደግሞ የድምፅ ጥራቷና ጩኸቷም ግሩም ነው፡፡ አንዱን የኤፍኤም ጣቢያ  ከመክፈቴ......
....“በአሉ እንዴት ነው አባት?” እያለ ከሚያፋጥጥ ጋዜጠኛ ላይ ደረስኩ፡፡
“ምን እንዴት አለው፣ ይኸው እያየኸውም አይደል ጋዜጠኛ!” አሉት፤ ሰውዬው.....
ጋዜጠኛውም፤ .“አይ ማለቴ ምን አዘጋጃችሁ.. .እንዴት ልታሳልፉት አሰባችሁ ለማለት ፈልጌ ነው” አላቸው፡፡
“እህ እንደዛ ለማለት ፈልገህ ነው!” አሉ...ሰውዬው፤ በቀልድና በሽሙጥ የተካኑ ሳይሆኑም አይቀር፡፡.
“ለመሆኑ የኔ ልጅ....ም....ምን ያደርግልሃል የኔ በአል አከባባር? እንዴትስ አድርጌ ባከብረው ላንተ ምን ይጠቅምሃል?” በማለት መልሰው ጠየቁት......
አሁን ጋዜጠኛው በሰውዬው ንግግር ኮስተር ማለትን መርጧል “...እንደሱ ሳይሆን አባት ... እንደዚህ በአል ሲመጣ ህብረተሰቡ እንዴት እንደሚያከብር፣ የበአሉ ድባብ ምን እንደሚመስል እየዞርን በመጠየቅና በሬዲዮ በማስተላለፍ ስሜቱን ለሁሉም ለማጋራት  ነው” አላቸው፡፡
ሰውዬው....“እውነት? አሃሃሃይ” በማለት በምፀት ሳቁበትና....“አይ የኔ ልጅ እ...ሁነኛ ስራ እየሰራህ ነው በለኛ! እንደው ጉድ እኮ ነው ... እየዞርን ህብረተሰቡን እየጠየቅን ስትል፣ በግና ዶሮ ይዘህ ህብረተሰቡን የጠየከው አትመስልም እስቲ....ወገኞች!....ወገኛ ሁላ ተሰብስባችሁ ...ቸገረኝ ብልህ ሽራፊ እማትሞላልኝ ሁላ የበአሉን ስሜት ምንትስ ትላለህ...የህብረተሰቡ ስሜት እኮ ለናንተ ዜና እንጂ ለኛ መልስ ይዞ አይመጣም... ስለዚህ የኔ ልጅ አመትባሌን በገዛ ስሜቴ፣ ሳልናገር ነው እማጣጥመው፤ የማካፍልህ ስሜትም ሆነ ድባብ የለኝም...”
ጋዜጠኛው.....“ይኸው ነው በቃ”
ሰውዬው.....“አዎ ይኸው ነው” አሉት፡፡
ጋዜጠኛው አይታክተውም፤ “ደህና ዋሉ እማማ?” ብሎ ሌላ ኢንተርቪው ሊቀጥል ሲል፣ እኔ ቀድሜ ሬዲዮኑን ዘጋሁ፡፡
ሬዲዮው ውስጥ በሰማሁት አዝናኝ ገጠመኝ ምክንያት ያቋረጥኩትን ሥራ ቀጠልኩ፤ ነገር ግን ግቢ ውስጥ የሆነ የጭቅጭቅ ድምፅ ስለሰማሁ አሁንም በድጋሚ ለማቋረጥ ተገደድኩ.....ዝምታ የሚጠላ፣ ድምፅ ብቻ የሚወድ ጓደኛዬ  ቤት ውስጥ ስለሆንኩ ነው መሰለኝ እያንዳንዷ ድምፅ ታነቃኛለች፡፡
ብቅ ብዬ ሳይ ጓደኛዬ ነሲቡና የቤት አከራዩ አቶ ሽመክት ናቸው የሚነታረኩት....
“ምንድን ነው ችግር አለ እንዴ?” ብዬ ጠየቅኋት... እንደኔ ለወሬ የወጣች የምትመስል ቆንጆ እንስት ጎረቤት፡፡ .
“ኖኖ ኢት ኢዝ ኖት ችግር--- ኢት ኢዝ ኤ ግሬት ዲያሎግ......የነሱ ገራሚ ንግግር እኮ ትምህርት ነው ወንድም፤ ተጣልተው አይደለም ሁሌ ይለካከፋሉ.....ነሲቡ ጓደኛህ ከሆነ እድለኛ ነህ፤ ምርጥ ፈላስፋ ነው...ምሁር ነው.....አባባ ደግሞ ስነ-ቃል ሰንጣቂ ናቸው፤ ተገናኙልሃ ወንድሜ...ይኸው ይባጠሱታል፤ የኛ ግቢ ቲያትረኞች!” አለችኝ፡፡
 ስታወራ አትደነቃቀፍም፤ ጠይም መልኳ ያምራል፤ አንባቢ ወይ አዋቂ ነገር ለመሆኗ ጓደኛዬን የተረዳችበት መንገድ ነግሮኛል....እንግሊዝኛ መቀላቀል ባታበዛ ደግሞ ንግግሯ እንደ መልኳ ውብ ነው.... በፍጥነት እንደ መናገሯ በፍጥነት ሰው የምትግባባም ትመስላለች.....
“ኦ! እና ሁሌ ቲያትሩን በነፃ ትኮመኩማላችኋ!?” አልኳት፤ ከወገቧ በታች ያለው ሰውነቷ ላይ አፍጥጬ፡፡  
“ምነው በነፃ መሆኑ አሳሰበህ?” ጠየቀችኝ....
“ቢያሳስበኝ አይገርምም እኮ እህት--.ይህን ያህል ከተመሰጣችሁበትና ከተማራችሁበት ብትከፍሏቸው ምናለበት--”.አልኩ፤ ቀልዴን እንደሆነ እንድታውቅልኝ ፊቴን ፈታ በማድረግ....
“ያ! ለነገሩ ልክ ነህ፤ ለስንቱ ገለባ ቲያትርና ፊልም ነኝ ባይስ ስንበዘበዝ ኖረን የለ እንዴ!” አለች.....
ጓደኛዬ ነሲቡ ግቢ ውስጥ ከአስር በላይ የሚከራዩ ቤቶች አሉ .... በእርግጥ አንዳንዶቹ በደፈናው ቤት ከማለት ይልቅ የምን ቤት? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የዶሮ ቤት ናቸውን? የውሻ ቤት ናቸውን? የከሰል ማስቀመጫ ናቸውን? ወይንስ የምን? እንዲህም ሆኖ ግን ሽማግሌው ይሉኝታ የላቸውም....... በውድ ገንዘብ ነው የሚያከራዩት..... ነሲቡ ታዲያ የሽማግሌን ባህሪ ቢያውቅም እንዳይነጫነጩ ማድረግ ግን አልቻለም.... ሆነ ብሎ ይጎነትላቸዋል.....ዝምታ ስለማይወድ፣ ሃሳባቸውና ጫጫታቸው ይመቸዋል.....እሳቸውም የዋዛ አይደሉም፤ በሾርኔ ይነግሩታል፡፡ ጨዋታ አዋቂም ናቸው፤ ሲጫወት ይገባቸዋል፤ በቤት ኪራይ ከመጣ ግን ቀልድ አያውቁም፡፡ ዛሬ በረፋድ ሽንቱን በፖፖ ታቅፎ ወደ ሽንት ቤት ሊደፋ ሲንደረደር፣ ሰርክ ፀሐይ ከሚሞቁበት ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ያዩታል....“እ......አጅሬው እስካሁን ሽንትህን አልደፋህም?” ይሉታል....
“ምን እኮ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ የምታክል ሽንት ቤት እየማሱ....በወር አንዴ ለምንሸናው ሽንት ቤታችን ሞላብን የሚለን ሲበዛ ምን እናድርግ!” አላቸው
“አከራዩም እኮ ተቸገረ ብሩን ሳይጠቀምበት እንዲህ እንዳንተ ሽንቱን ብቻ የሚያስታቅፍ ተከራይ እየተንጋጋበት!” ሲሉ መለሱ፡፡
ነሲቡ ዝም አለ፡፡
“እኔ እምልህ ወሲቡ--- ማነህ ማለቴ ነሲቡ.....” ብለው ጠሩት.....
“ስም ቢስቱ አይገርመኝም፤ እድሜዎ ነው!!” አላቸው፡፡
“እድሜ ጠጋ ነው....በዛ ላይ እንዲህ ሃብታም ሆነህ ምድረ ምሁር ነኝ ባይን ሁሉ እየገላመጥክ፣ እያከራየህ ቁጭ ብለህ ስትበላ.....ብትስትም አይገርምም!!” ብለው ገቡለት...
ምድረ ተከራይ ቤቱ ውስጥ ሆኖ የሁለቱን ወግ መጀመር ከሰማ የምን ቴሌቪዥን መክፈት...የምን ድራማ ማየት.... ፓ ገባላቸው፣ ፓፓፓ ገቡለት እየተባባሉ እነሱን ማድመጥ ነው፡፡
“ያቺ ማነች ስሟ በቀደም እየጎተትክ ያመጣሃት--- የማናት አጎዛ በል?” አሉት
“የቷ ደግሞ?” አለ
“አዬ ጉድ አንተም ጠፉብህ....ለነገሩ ምን ታደርግ ከሱቅ ገዝተህ የምታመጣቸው ነው የሚመስለው! ወጣ ብለህ እየጎተትክ መምጣት ሆኗል ስራህ! እንደው እኔም በእድሜዬ ስንቱን አተራምሻለሁ.....ሽመክት ያላበራየው አልነበረም፤ እንደው ያንተው ግን ይባስ ልጄ! እረ በፈጣሪ.......”
“ማንኛዋን ነው ይልቅ አጎዛ ናት ያሉት?” አላቸው፤ ወደቀደመ ነገራቸው ሊመልሳቸው፡፡ .
“ያቺ ናታ በቀደም አጎንብሼ ከምደግምበት ድንገት አባባ ብላ ቀልቤን የገፈፈችው....እንዴ ቀልብ መግፈፍ አንሶላ እንደ መጋፈፍ ቀላል ነገር መሰላት እንዴ! ምን ያለችው ቀልበ-ቢስ ናት” አሉት......
“እርሶስ ቢሆኑ ዳዊት ከሚያነቡበት አቋርጠው መደንገጥዎ ምን ይሉታል! እውን አባባ በማለትዋ ነው የደነገጡት ወይስ በሌላ ነገሯ!” ብሎ በነገር ጠቅ አደረጋቸው......
“እኔ ሽመክት ነኝ አንተ በዚያች ከረፈፍ የምደነግጥ!?” አሉ፤ በተደፈርኩ ባይነት ስሜት፡፡
“ኤዲያ ደግሞ ሽመክት ብሎ ስም እራሱ ምን ይሉታል” ብሎ ደገማቸው...
“ማ ስማ እኔ ይህን ስም ያገኘሁት--- ዠግና የዠግና ልጅ ስለሆንኩ...ታሪካዊ አደራ አባቴ ሲያኖርብኝ ነው አየህ....ካልክስ ስሜን ሆኜ የኖርኩ የምር ዠግና ነኝ....ስም እንዲህ እንዳንተ ዘመን ሳይረክስ በፊት በዘፈቀደ የሚሰጥና የሚወጣ አይደለም” አሉት፤ በንዴት ግለው....
“እኔ እንግዲህ በስምዎ ውስጥ መመከትን እንጂ ማሸነፍን አላየሁበትም፤ በእርግጥ መመከት ለማሸነፍ የመጀመሪያው ደረጃ ሊሆን ይችላል.....በህይወት ውስጥ ጠቃሚው ነገር የመጨረሻው ውጤት በመሆኑ ግን ሲመክቱ እንጂ ከመከቱ በኋላ ስለመዘረርዎ ወይ ስለማሸነፍዎ የሚጠቅስ ሃሳብ አላገኘሁበትም---”
“አይ የዘንድሮ ደራሲ ድንቄም ደራሲ....አይ ምሁር....አዬ ጉድ፤ አዬ አለመታደል፤ስሙን ተሸክማችሁታል አንጀቴዋ አይይይ.....የህይወቴ እንቅስቃሴ በሙሉ በስሜ ላይ ተፅፎ እንዲታይ ነው የምትሻ?” ብለውት ተነስተው ወደ ቤታቸው ገቡ........
አይ የዘንድሮ ደራሲ.....ስሙን ተሸክማችሁታል የሚለው ነገር ደጋግሞ እያቃጨለበት፣ አንገቱን ደፍቶ እያሰላሰለ ወደ እኔ መጣ........“ሄይ አንተ ደግሞ እስካሁን ይቺን እቃ አጥበህ አልጨረስክም እንዴ!” ብሎ አንባረቀብኝ......
“ከዚህ በላይ አልችልም፤ አቅም የለኝም....” አልኩት
“ያደለው ለጓደኛው ሌላ ያደርጋል....አንተ የቆሸሸ ለማጠብ ተለመንክ እኮ.....” አለኝ
“ሰውዬው ልክ ልክህን ሲነግሩህ እኔ ላይ ትጮሃለህ እንዴ?!”
“ዝምታህን የሚያዜምልህ ለኔ ምርጥ ዘፋኝ ነው ብሏል አሉ፤ ካህሊል ጂብራን......ዝምታህን የሚናገርልህ ጥልቅ ተመልካች ከሌለህ ገና ሲነኩህ ትጮሃለህ፤ አሊያም ደግሞ ድምፅ ካለህ እንደ ሸጋው ጥላሁን ገሰሰ......
ጩኸቴን ብትሰሙ
ይኸው አቤት አቤት እላለሁ
 በደል ደርሶብኝ እጮሃለሁ ችያለሁ
ትላለህ........
ዳይ ወደ ትክክለኛው ጩኸት!...”

Read 2402 times