Saturday, 02 June 2012 10:19

ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሴቶችና የቤተሰብ እቅድ ዘዴ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

በአፍሪካ የኤችአይቪ ቫይረስን ታሪክ ስንመለከት ከ30/አመት በፊት ስርጭቱ አለ የሚባል ያልነበረ ሲሆን እንደውጭው አቆጣጠር ከ1980/ ዎቹ በኋላ ግን የስርጭት አድማሱ ቀስ በቀስ ተለውጦ እጅግ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ከፍ ባለ ደረጃ ተመዝግቦአል፡፡ በ2000/እንደ ውጭው አቆጣጠር ከሰሃራ በች ባሉ የአፍሪካ አገራት ወደ 25/ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩና በእነዚሁ አገራት በ2009/በቫይረሱ ምክንያት የሚደርሰው የሞት መጠን ወደ 1.3/ ሚሊዮን እንደደረሰ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቫይረሱ መኖሩ ከተረጋገጠ ጀምሮ ወደ 14.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ከሁለት አንዳቸውን ወይንም ሁለቱንም ወላጆቻቸውን በቫይረሱ ምክንያት አጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ ይበልጡኑ የሚተላለፈው በወሲባዊ ግንኙነት ሲሆን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች እንዳገኘነው ከሆነ በተለይም  ሴቶች ከወንዶቹ ይልቅ በቫይረሱ ይያዛሉ...

በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው በተለይም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሴቶች የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴ አጠቃቀምን በሚመለከት ሊወስዱዋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች አሉ... ወይንስ...? የሚል ነው፡፡ ለዚህ ማብራሪያውን የሰጡን ዶ/ር ነጋ  ተስፋው በ  ሆሻቅሽስሸቄ ጄፓይጎ ኢትዮጵያ የእናቶችና የህጻናት ጤና ቡድን መሪ ናቸው፡፡

----------////----------

ኢሶግ /የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ወይንም ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ የሚባሉት ዘዴዎች

ምንድናቸው?

ዶ/ር የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴ የሚባሉት  ጥንዶች በጋራም ሆነ በተናጠል ስንት ልጆች እና መቼ መውለድ እንዳለባቸው ለመወሰን የሚያስችሉዋቸው  ዘዴዎች ናቸው፡፡ መድሀኒቶቹ በውስጣቸው ሆርሞን ወይንም ንጥረ ነገር ያለባቸው... ማለትም በየቀኑ በእንክብል መልክ የሚወሰዱ ፣ በመርፌ መልክ የተዘጋጀና ለሶስት ወር የሚሰጥ... እንዲሁም በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጥ... ከሶስት እስከ አምስት አመት የሚያገለግል... በመባል የሚከፈሉ የመከላከያ አይነቶች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሆርሞን የሌላቸው... በማህጸን ውስጥ የሚቀመጥ ሉፕ እስከ 12 አመት ድረስ የሚያገለግል ...እንዲሁም መውለድ በቅቶናል ብለው ለወሰኑ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ቋሚ የሆነ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ አገልግሎት ይሰጣል ፡፡ ከዚህ ውጭ ለአጭር ጊዜ የሚያገለግሉ ተፈጥሮአዊ መከላከ ያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጡት በማጥባት ወይንም ቀን በመቁጠር የሚጠቀሙበት የመከላከያ ዘዴዎች በጥንቃቄ አገልግሎት ላይ ሊውሉ የሚችሉ ናቸው፡፡የሴት ወይንም የወንድ ኮንዶምን መጠቀምም ከመከላከያዎቹ የሚመደብ ነው፡፡

ኢሶግ/ እነዚህ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች ለሁሉም ሰው በተመሳሳይ ሁኔታ ይሰጣሉ... ወይንስ እንደተጠቃሚው የጤናና ሌሎች ሁኔዎች የሚለያዩበት መንገድ ይኖራል?

ዶ/ር በእርግጥ መከላከያዎቹ በባህሪያቸው አንዱ ከአንዱ ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ መከላከያውን ለምን ያህል ጊዜ መውሰድ እንደፈለጉ ወይንም አንዱን የመከላከያ አይነት መውሰድ የማይችሉበት ሁኔታ ካለ እና ፍላጎታቸውን በሚመለከት ምንጊዜም ከሕክምና ባለሙያ ጋር መምከር ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን የቤተሰብብ ዕቅድ ዘዴውን መጠቀም አይቻልም የሚያሰኝ አካሄድ የለም፡፡ እነዚህ የተለያዩ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች ደንበኞች ከጤና ባለሙያ ጋር በመመካከር ሊወስዱዋቸው የሚገባቸው ናቸው፡፡ለምሳሌ አንዳንድ ሴቶች የተለያዩ የጤና ችግሮች ሊኖሩባቸውና ሆርሞን ያለባቸውን መድሀኒቶች አንዳይ ወስዱ ሊመከር ይችላል፡፡ ስለዚህ ለጤና ጎጂ ያልሆነና የተሻለ የሚባለውን አማራጭ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡

ኢሶግ/ ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ሴቶች የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴን ሊጠቀሙ የሚችሉት በምን መንገድ ነው?

ዶ/ር ኤችአይቪ በደማቸው ያላቸው ሴቶች ሁሉንም ...ማለትም ሆርሞን ያለባቸውን ፣በማህ ጸን የሚቀመጠውን ሉፕ፣ በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጠውን ፣ኮንዶም ወይንም ቋሚ የመከላከያ ዘዴዎች እንዲሁም ጡት በማጥባት የመሳሰሉትን ሁሉ መጠቀም ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች  የአባላዘር በሽታዎችን ...ኤችአይቪን ጨምሮ ከአንዱ ወደ አንዱ መተላለፍን የማይከላከሉ ስለሆነ ኤችአይቪ በደማቸው ያሉ ደንበኞች ሁልጊዜ እና በአግባቡ ከሚወስዱት መከላከያ በተጨማሪ ኮንዶምን እንዲጠ ቀሙ ይመከራል፡፡

ኢሶግ/ ኤችአይቪ በደማቸው ያለም ሆኑ ሌሎች መከላከያ ዘዴውን ከመጠቀማቸው በፊት ሊያተኩሩበት የሚገባ ነጥብ አለ?

ዶ/ር የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች አስቀድሞውኑ ልብ ሊሉዋቸው ከሚገቡ መካከል የሚከተሉት ይገኙበል፡፡

1/ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴው አስተማማኝት፣

2/ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴው ለጤና ተስማሚነቱ፣

3/ ለረጅም ወይንም ለአጭር እንዲሁም ለቋሚ አገልግሎት የሚሰጡትን መለየት፣

4/ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን የጎንዮሽ ጉዳቶች ማገናዘብ፣

5/ ልጅ ከማጥባት ጋር ሊወሰድ እንደሚችል መለየት፣

6/ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴው የአባላዘር በሽታዎችን ኤችአይቪን ጨምሮ መተላለፍን ይከላከላል ወይንስ አይከላከልም የሚለውን ለይቶ ማወቅ...የሚሉት በቅድሚያ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገባቸው ናቸው፡፡

ኢሶግ/ ሆርሞን ያለባቸውን የመከላከያ ዘዴዎች ኤችአይቪ በደማቸው ያለ ሴቶች ያለምንም ስጋት ሊወስዱዋቸው ይችላሉን?

ዶ/ር ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ደንበኞች ሆርሞን ያለባቸውን መከላከያዎች መውሰድ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በተለይ ፀረ ኤችአይቪ መድሀኒት የሚወስዱ ከሆነ በደም ውስጥ ያለውን ሆርሞን የመቀነስ ባህርይ ሊኖረው ስለሚችል በተወሰነ ደረጃ የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴውን አስተማማኝነት ሊቀንሰው ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡ ስለዚህም ከሚወስዱት የሆርሞን የእርግዝና መከላከያ ዘዴ በተጨማሪ ኮንዶም በአግባቡ እንዲጠቀሙ ይመከ ራል፡፡ ኮንዶምንና ሆርሞን ያለባቸውን መከላከያዎች ሁለቱንም አንድ ላይ መጠቀሙ የሚሰጠው ጥቅም አለ፡፡ ይኼውም ኮንዶም የአባላዘር በሽታዎችን ኤችአይቪን ጨምሮ የመከላከል አቅም ስላለው ሁሉንም በጋራ ለመከላከል ስለሚያስችል ነው፡፡

ኢሶግ/ ኮንዶምን መጠቀማቸው አስፈላጊ ከሆነ ሆርሞን ያለበትን የመከላከያ ዘዴ ባይጠቀሙ ምን ጉዳት አለው?

ዶ/ር እርግዝናን ከመከላከል አንጻር እንደ ሆርሞኖቹ  ፣ሉፕ ፣በክንድ ቆዳ ስር ከሚቀመጠውና ቋሚ የመከላከያ ዘዴዎች ጋር ሲነጻጸር ኮንዶም እርግዝናን የመከላከል አስተማማኝነቱ ዝቅተኛ ስለሆነ ከሌሎቹ የርግዝና መከላከያዎች ጋር አብሮ ቢወሰድ ይመከራል፡፡

ኢሶግ/ ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ሴቶች ሉፕ የተባለውን የመከላከያ ዘዴ ያለ ስጋት መጠቀም ይችላሉን?

ዶ/ር ሉፕ ወይንም አይ ዩ ሲዲ የሚባለውን መከላከያ ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ሴቶች መጠቀም ይችላሉ፡፡ በእርግጥ የማንኛውም መከላከያ ዘዴ ምቹነት የሚወሰነው ከሕክምና ባለሙያ ጋር በሚደረግ ምክክር ነው፡፡ ከቫይረሱ ጋር መኖር ብቻ ሳይሆን ኤይድስ ከሚባ ለው ደረጃ ደርሰው መድሀኒቱን እስኪጀምሩ ድረስ ሉፕ እንዳይጠቀሙ ሊደረግ የሚችል ሲሆን ነገር ግን ፀረ ኤችአይቪን መውሰድ ጀምረው ጤንነታቸው ሲስተካከል ሉፕ መጠቀም ይችላሉ

ኢሶግ/ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሴቶች በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሊያደርጉበት የሚገባ ነጥብ ምንድው?

ዶ/ር ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሴቶች ከሌሎች በተለየ ትኩረት ሊያደርጉ የሚገባቸው

1/ ቫይረሱ ወደሌላ ሰው እንዳይተላለፍ ጥንቃቄ ማድረግ፣

2/ በሌላ አይነት የኤችአይቪ ዝርያ እንዳይያዙ ለማድረግ ኮንዶምን

ከቤተሰብ እቅድ ዘዴው በተጨማሪ  መጠቀም ይገባቸዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች በተጨማሪ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ከሆነ ቫይረሱ ወደ ልጃቸው እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሕክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ፀረኤችአይቪ የሚወስዱ ከሆነ እና አንዳንድ መድሀኒቶችን እየወሰዱ እርግዝና ቢከሰት በጽንሱ ላይ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል ከማርገዛቸው በፊት ከሕክምና ባለሙያ ጋር በመመካከር በሚወስዱዋቸው መድሀኒቶች ዙሪያ ማስተንከያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡በአጠቃላይ ግን ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ሴቶች መውሰድ የለባቸውም የሚባል የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴ የለም፡፡

 

 

Read 3876 times Last modified on Saturday, 02 June 2012 10:25