Sunday, 16 June 2019 00:00

የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ

Written by 
Rate this item
(5 votes)


                   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ መምህር ሲያስተምሩ፣ አንድ ተማሪ አስተዋይና ረቂቅ ነበራቸው፡፡ ተማሪው፤ ሊቃውንት በተሰበሰቡበት ጥያቄ እያቀረበ አስቸገራቸው፡፡ በዚህ ተናደዋል፡፡ ስለዚህ ቆይ እሰራለታለሁ ብለዋል፡፡ የተማሪው ቤት ታች ሜዳው ላይ ነው፡። የመምህሩ አፋፉ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ምን እየሰሩ እንደሆን ለእሱ ቁልጭ ብሎ ይታየዋል፡፡
በዚህ ጠዋት መምሩ የወይራ አለንጋ ግቢያቸው ካለው የወይራ ዛፍ ሊመለምሉ ዛፍ ላይ ወጡ፡፡
 ተሜ ከታች ሽቅብ ያስተውላቸዋል፡፡
ከዚያ መምህሩ ተማሪዎቻቸውን ማስተማር ጀመሩ፡፡
በመካከል ግን ያንን ትላንት ሊቃውንቱ ፊት ያስቸገራቸውን ለማግኘት አስበው “ታምሪሃ ወ-እግዚሃር” አሉ … ታምሪሃ ተ ጠብቆ የማይነበበውን አጥብቀው ነው ያነበቡት፡፡
 ያ ተማሪ ግን ሳይመልስላቸው ፀጥ ብሎ ኑሯል፡፡
“ታምሪሃ ወ-እግዚሃር” አሉ፡፡
ተሜ ጭጭ፡፡ በመካያው መምህሩ ተናደዱና፤
“ምን ሆነህ ነው አንተ፤ አትመልሰኝም እንዴ?”
ተሜም፤
“አዬ የኔታ፤ እቺማ ውስጠ ወይራ ናት” አላቸው፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ውስጠ ወይራ የሚለው ሐረግ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ፣ ፋይዳ ያለው ትርጉም አገኘ!
***
ብልህና በሳል ተማሪ ሊኖር ይችላል ብሎ፣ ብልህ መምህር ራሱን ለማየት  መቻል አለበት፡፡
“አዬ ያ አስተማሪ
ያለበት አባዜ
አስተዋይ ተማሪ
    የጠየቀው ጊዜ”  
የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
እርግጥ ነው ተማሪው ሙሉ ክህሎት ያገኝ ዘንድ አስቀድሞ መምህሩ መቃኘት ይኖርበታል፡፡ አልፎ ተርፎም የተማረውን በሥነ ስርዓት ማደስና ማሻሻል ተገቢ ነው፡፡ ማንም ሰው ለማደግ፣ ካለማደግ ነው የሚጀምረው፡፡
ጥንት ትምህርት ከድል በኋላ መፈክር ነበረ፡፡ ያለ ትምህርት አገር የትም እንደማይደርስ ለሚያውቅ ገዢ ኃይለኛ መፈክር ነው፡፡ ትውልድ ወይ ቤተሰብ ውስጥ፣ ወይ ት/ቤት ውስጥ  ወይ Co-curricular activity ውስጥ ነው የሚወለደው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሶስት ዘርፎች አግዝፈን እንያቸው፡፡ ያለ ትውልድ አገር አትገነባም፡፡ እሱም የአንድ ጀምበር ሩጫ እንዳልሆነ አበክረን እናስተውል፡፡
እዚህች ምስኪን አገራችን ላይ አያሌ መሪዎች ነግሰዋል፡፡ ችግሩ አዲሱ ካለፈው ሳይማር፣ በአሮጌው መንገድ መውደቃቸው ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ሒስ የሚሰጥ ትጉ ሰው አልተፈጠረልንም፡፡ መንገዳችን ገና ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ተቃዋሚና ደጋፊ በሌለበት ሁኔታ እንኳን ተግባብተን የመስራት ባህል አለመኖር እንዳገተን አለ፡፡ ሆኖም እንንቃና እንነሳሳ፤ ጥንት ደጋግመን እንደጠቀስነው፡-
“ከማዕበል በፊት የባህር እርጋታ፣
 ከንግግር በፊት የአርምሞ ፀጥታ፣
 ዛሬም ሀገራችን የአንድ አፍታ ዝምታ፤
 ነገ ግን ይተጋል፤ መነሳቱ አይቀርም፤
ተነስቶም ያሸንፋል፤ አንጠራጠርም”
በሀገራችን ብዙ ቃል የተገቡልን ጉዳዮች አሉ፡፡ ብዙ ጠብቀን ጠብቀን ግን ሳይከሰቱ ሲቀሩ የሀገራችን ተረት ፊታችን ድቅን ይላል፡፡ የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ!

Read 7524 times