Sunday, 16 June 2019 00:00

ባለ ስድስት ጣቱ ቱጃር

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(9 votes)

 ሊን ዋንግ፤ ሻንጋይ ውስጥ በሚገኘው አራት ፎቅ ያለው፣ አባቱ፤ ለሱና ለተወዳጅዋ ሚስቱ በሰጠው ባለ አራት መኝታ ክፍል የምድር ቤት ውስጥ፣ ሳሎን ሶፋው ላይ ተቀምጦ፣ በእጁ የያዘውን፣ አንዱ ሲሲ፤ አንድ ፈረስ የመግደል አቅም ያለውን አደገኛ መርዝ፤ የመስተዋት ብልቃጥ ይዞ “ላድርግ አላድርግ” በሚል ውስጣዊ  እሰጥ አገባ፣ አዕምሮው ተወጥሯል፡፡
ይህን መርዝ፣ አንድ ሊትር ውድ የፈረንሳይ ወይን ጠጅ፣ ቡሽን በስቶ ቢያዋህድ፣ ከተወሰኑ ወራት በኋላ አምስት መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እጁ ይገባል:: ይህንን ካላደረገ ግን የምድርን ስብ ምጥጥ አድርጐ የበላው የሰማንያ አመት ሽማግሌ አባቱ፤ የልጅ ልጁ ለምትሆነው፣ በሞግዚት መልክ ለወሸማት ኮረዳ ሃብቱን ያወርሳል፡፡
አሁን በወር አስር ሺህ ዶላር እየተከፈለው የሚሰራው ምስኪኑ ሊን ዋንግ፤ አባቱ ሲሞት የሃያ አመትዋ የአባቱ ውሽማ ሚስ ኮትኒ፤ እንደ አሮጌ ቁና ከቤት አውጥታ ትወረውረዋለች፡፡ ይሄ ደግሞ ሁሉም ሰው የሚያወራው ነገር ነው:: የአርባ አመትዋ ተወዳጅ ሚስቱ ናንሲ፤ በሎጋ ቁመትዋ በእጥፍ የምትበልጠውና የሃያ አመት ታናሹ ስትሆን፤ በመላው ሻንጋይ በውበትዋ ተወዳዳሪ የሌላት በመሆንዋ፣ የአገር  ሃብታም የሚረባረብባት ብትሆንም ቅሉ በትዕግስት አብራው እየኖረች ነው:: እሱ አሮጌ ቁና የሆነ ጊዜ ግን ጥላው መሄዷ አይቀርም፡፡
የ80 ዓመቱ ሽማግሌ አባቱ ሞት  አስፈላጊነቱ በዚህ ብቻ አይደለም፡፡ እሱ ከአብራኩ የወለደው ልጁ እያለ፣  የሀብቱን ሰነድና ማስረጃ በሙሉ ለዚህች መተተኛ ውሽማው አስረክቧል፡፡
አልጋ ላይ ከመውጣትዋ በፊት ተንበርክካ የምትፀልየው ሚስቱ ናንሲ፤ ጥሩ የፈጣሪ ባርያ ለመሆንዋ ጥርጥር የለውም፡፡ ከፀሎቱ በኋላ ጥቂት ወይን ጠጅ ጐንጨት አድርገው፣ ፍቅር ሲሰሩ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል መዋጥዋን አትረሳም:: ላብ በላብ ሆና፣ ቁና ቁና እየተነፈሰች፣ በጀርባዋ ተዘርግታ አይንዋን እንደከደነች፣ ፀጉሩን ትዳስስና፤ “መቼ ነው እኔም እንደሰው ልጅ ወልጄ የምስመው” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
“ክኒኑን መዋጥ ስታቆሚ!” ይላታል ፍርጥም ብሎ፡፡  
ከአልጋው ላይ አውሬ ሆና ትነሳና፤ “ዝጋ - በገዛ ቤቱ አሽከር ሆኖ፣ አስር ሺህ ዶላር ጠብቆ የሚበላ አባት ያለው ልጅ አልፈልግም!” ወደ መታጠብያ ቤት እየተውረገረገች፡፡
ይህ ነገር የእለት ተእለት ክስተት ሲሆን፤ ሚስቱ ናንሲ ከማረጥዋ በፊት እሱን በእድሜ እኩያ በሆነ ሸበላ ሃብታም እንደምትለውጠው፣ ሊን ዋንግ አሳምሮ ያውቃል፡፡ አባቱ ሲሞት አስር ሺው ይቋረጥና ከቤት ይባረራል፡፡ ይህ ሁሉ አይቀሬ ውርደትና ውድቀት፣ በወይን ጠጅ ጠርሙስ መስተዋት ውስጥ እንደ ፊልም ይታየው ነበር፡፡ ኮትኒ ከአባቱ ጋር እንደምትዳራ አገር ያውቃል፡፡  እሱም እራሱ አንድ ጊዜ በድንገት የአባቱን ክፍል ከፍቶ ሲገባ፣ ከአባቱ ደረት ላይ በርግጋ ስትነሳ ተመልክቷል፡፡ የአባቱ ነጭ ፒጃማ አንገት ግርጌ ላይም ቀይ የከንፈር ቀለም ሰራተኛዋ እንዳገኘች አውርታለች፡፡ ስለዚህ በሰማንያ አመቱ፣ ከሃያ አመት ኮረዳ ጋር የሚተኛ ቅምጥል ውሻ ቢሞት ባይሞት ፈጣሪ ምን ያገባዋል?! እሱ ግን በስድሳ አመቱ ከአርባ አመት ሚስቱ ጋር መኖር አይችልም፡፡ ይህንን ሲያስብ ደሙ ፈላና በንዴት ብልቃጡን ሰበረው፡፡ ሁለት ሲሲ ያህል ወሰደለትና የጠርሙሱን ቡሽ ወግቶ፣ ከወይኑ ጋር አዋሃደው፡፡ ሽማግሌው አሁን ከአፈር ጋር ይዋሃዳል፡፡
ጠርሙሱን በመሃረብ ወለወለና የሹራብ የእጅ ጓንቱን አጥልቆ ወደ ፎቅ ወጣ፡፡ ሽማግሌው በራሱ ገንዘብ እንደዚህ አይነት ውድ ወይን ይጠጣል ማለት ዘበት ነው፡፡ በሰው ገንዘብ ሲጋት ነው የሚያድረው:: ዋናው በር ጋ ሲደርስ የመጥሪያውን ደወል ተጫነ:: በሩ ሲከፈት ሚስ ኮትኒ በሩን ገርበብ አድርጋ ከፈተችና፤ “ምን ነበር? እሱ እንደሆነ እረፍት እያደረገ ነው” አለችው፡፡
“ወራዳ! አሁን አንቺ እንደ ሚስት ቅድመ አያትሽ የሚሆነውን ሰው፣ አንተ ብለሽ ስትጠሪ አታፍሪም” አለ በልቡ፡፡
“ግድ የለም፡፡ ይህንን ስጦታ ለመስጠት ነው:: ለሱ ለአባቴና ለተከበርሽው ውብ ወጣት እመቤት ካለኝ ክብር የተነሳ እኔው እራሴው ነኝ ቤጂንግ ድረስ ሄጄ ይህንን መጠጥ ያመጣሁት፡፡ ዛሬ ሰማንያ አመቱ መሙላቱም አይደል! ረጅም እድሜ ይስጠውና፤ ልደቱን በዚህ ውድ ወይን ቢያከብር፤ እኔም ምርቃት አላጣም ብዬ ነው” አለ፤ ጥርሱን ነክሶ ፈገግ ለማለት እየሞከረ፡፡
“አሃ!  ነው” አለች ጠርሙሱን እያየች፡፡
“አ…ይገርምሻል ይህ መጠጥ ከተጠመቀ አርባ አመታት አልፎታል፡፡ ቤጂንግ የሚኖር አንድ የድሮ ወዳጄ ዘንድ ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ ቅድመ አያቱ አስር ጠርሙስ የሚሆን ተጠምቆ እንዲቀመጥ አድርገው ነበር፡፡ ዘጠኙ በውድ ዋጋ ሲሸጡ፣ እኔ ደግሞ ያው ለአባቴ ይህንን ጠርሙስ እንደምንም ብዬ አስቀረሁት”
“አምጪው!” ሲል ሽማግሌው አባቱ፤ ከውስጡ ድምፁ ይሰማዋል፡፡ ጠርሙሱን ተቀበለችና በሩን ዘጋች፡፡
ሊንግ ዋንግ ስራውን አጠናቀቀ፡፡ ጠዋት ኡኡታ ተሰማ፡፡ ነገሩ በፍጥነት ነበር የተከናወነው:: ኮትኒ እና ሰራተኛዋ እሪታቸውን ሲያስነኩት፣ ሊንግ ወደ አባቱ መኝታ ክፍል ገባና ጠርሙሱን መፈለግ ጀመረ:: ኮሞዲኖው ላይ ተቀምጧል፡፡ ጓንቱን አጠለቀና አንስቶ ሊወጣ ሲል ኮትኒ ዞራ ስታየው፣ አይን ለአይን ተገጣጠሙ፡፡ ጓንቱን ያስተዋለችው ያኔ ነው:: አሻራዋ ጠርሙሱ ላይ አለ፡፡ ወይኑ እንደተመረዘ አሁን ገባት::
ያን ቀን ለሊት ከቀብር መልስ፣ ከፀሎት በኋላ፣ ሚስቱ ወደ አልጋ ስትመጣ ክኒኑን አልዋጠችም:: ከ12 ወር በኋላ እንዳረገዘች ነገረችው፡፡ ስለ ፍርድ ቤት ነገር ሲነሳ “ምን ያስቸኩላል? አባታችን ከሞተ አመት ሳይሞላው ንብረት ፍለጋ ፍርድ ቤት ብንቆም አገር ምን ይላል?” ትለዋለች፡፡
እንግዲህ አንድ አመት ለመጠበቅ ሲስማሙ የሰማችው ኮትኒ፤ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላታል:: አሻራዋ ያለበትን ጠርሙስ ፈልጋ በማግኘት ማስረጃ ለማጥፋት ጊዜ ታገኛለች፡፡ ይህን ማድረግ ከቻለች ሽማግሌው ሳይሞት ሃብቱን ለሷ ተናዞ የፈረመበት ሰነድ በእጅዋ አለ፡፡ ሰነዱ ግን ጠርሙሱ ላይ ያለው አሻራ ካልጠፋ ዋጋ የለውም:: እንዲያውም ገዳይ መሆንዋን ያረጋግጣል እንጂ:: ሊንግ ዋንግ በበኩሉ፤ ጠርሙሱን ደብቆ ስላስቀመጠው ኮትኒን በጭካኔ በአንድ ጊዜ ለማበረር አልወሰነም፡፡ እባብ ለእባብ ካብ ለካብ ጨዋታ ሆነና፣ አንድ አመት ሳይሞላ ናንሲ ምጥ ያዛት፡፡ ያን ቀን ሊንግ ቤት አልነበረም፡፡ ምጥዋ ሲጠና ኮትኒ መኪናዋ ላይ ጭናት ወደ ሆስፒታል መንዳት ጀመረች፡፡ ሆስፒታል የደረሰችው በምጡ ከደከመች በኋላ ነበር፡፡ ህፃኑን ለማዋለድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጐ፣ እንደ ምንም ተወለደ፡፡  የእሷ ህይወት ግን አለፈ፡፡
ኮትኒ እየተርበተበተች ለሊንግ ደወለችና አረዳችው፡፡ ሊንግ ሙሉ ህይወቱና ተስፋው የነበረችው ናንሲ መሞትዋን ሊያምን አልቻለም:: እንደ እብድ አውራ ጐዳናው ላይ ሲነዳ ያላየው የጭነት መኪና የጫነው የፌሮ ብረት ጋር በመስተዋቱ ተጋጨና ነገሩ አሳዛኝ ሆነ፡፡ ሹሉ ብረት ደረቱ ላይ ተቀርቅሮ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ህይወቱ አለፈች፡፡
ኮትኒ ህፃኑን ይዛ ወደ ቤት ልትሄድ ስትል፣ በፖሊስ ተከለከለችና ከሆስፒታሉ ነርስ ለአንድዋ  ተሰጠ፡፡
ናንሲ አርግዛ በነበረችበት ሰአት ኮትኒ ከሊንግ ጋር ተደራድራ ያጣችው ነገር ስለነበር ተስፋዋ ህፃኑ ላይ ብቻ ነው ያለው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- አንድ ቀን ማታ ሊንግ መኝታ ክፍልዋ ድረስ መጣና “ሃብቱ አይገባሽምና ሰነዱን ስጪኝ” አላት፡፡
“አሻራዬን ያረፈበትን ጠርሙስ ከሰጠኸኝ”  
“ከዚያስ?” ጠየቀ ሊንግ
“ያው በፍርድ ቤት ይወሰናል”
“ተስፋ የለሽም፤ የስጋ ዘመድ ልጅም ህጋዊ ሚስትም ስላልሆንሽ አሁንም አይገባሽም”
“እሱን ለኔ ተወው፡፡ ገዳይም ስላልሆንኩ መወንጀል አይገባኝም፡፡
አምጥቶ ሰጣት፡፡ እሷም ሰነዱን ሰጠችው፡፡
ሰነዱን በእጁ ይዞ ሌላ የተፃፈ ሰነድ ሰጣት፡፡
“ምንድነው?”
“ፈርሚ!” በኋላ ጠበቃዬ ጋ ይቀመጣል፡፡ በዚህ ሰነድ መውረስ አትችይም፡፡”
“እኮ ምንድነው?”
“ምንም ሃብት ለመጠየቅ የሚያስችል ሌላ ሰነድ በእጅሽ ቢገኝ፣ የሃሰት መሆኑን ቃል የሰጠሽበት!”
አሰበች፡፡ ምርጫ የላትም፡፡ ጠርሙሱን ለፍርድ ቤት ሰጥቶ፣ እድሜ ልክ ያስቀፈድዳታል:: ፈረመች፡፡
ሽማግሌው የፈረመበትን ሰነድ የእሳት ማንደጃው ላይ ጣለው፡፡ ኮትኒ አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ሲቃጠል ተመለከተች፡፡
እሷም ጠርሙሱን ማንደጃው ላይ ጣለችው፡፡ በእሳት ተንቀለቀለ፡፡
ይህ የሆነው ከአራት ወራት በፊት ነው፡፡
ከሁለት ሳምንታት በኋላ ኮትኒ፤ የህፃኑ ቅድመ አያት ተንከባካቢ በመሆኔም ጭምር ብቸኛ ቤተሰብ ነኝና የሞግዚትነት እድል ይሰጠኝ ብላ አመለከተች፡፡ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን አየና፣ የቅድመ አያትየው የባለ ስድስት ጣቱ ሽማግሌ ሚልዮነኛ ንብረት፣ ምንም ወራሽ ስለሌለው፤ ህፃኑ እንዲወርስ በይኖ፣ ኮትኒ የቅርብ ሰው በመሆንዋ፣ ሃብቱን እንድትጠብቅና እንድታሳግደውም ጭምር ወሰነ፡፡ ኮትኒ ህፃኑን ይዛ ከጋዜጠኛ ፎቶ አንሺዎች ግርግር ተሽሎክልካ፣ ወደ ሊሞዚኑ ገብታ እንደተቀመጠች፣ የህፃኑን እጅ ተመለከተች፡፡ የቀኝ እጁ ስድስት ጣት ነበረው፡፡

Read 2648 times