Tuesday, 02 July 2019 12:00

“እዚችም ሆድ ውስጥ እህል ያድራል?”አለች አሉ ማሽላ ጤፍን አይታ!!

Written by 
Rate this item
(10 votes)

   አንድ አባት ሶስት ልጆች አሏቸው፡፡
አንደኛው የተማረ ነው፡፡
ሁለተኛው ያልተማረ ነው፡፡
ሦስተኛው አንዴ የተማረ የሚመስል፣ አንዴ ደግሞ ያልተማረ የሚመስል አሳሳች ዜጋ ነው፡፡
የሚያስገርመው ነገር፣ የተማረው ልጅ ሁልጊዜ ሲናገር፣  
“ለሀገር መፍትሄ ሊሰጥ የሚችለው የተማረው ክፍል ብቻ ነው! ብትወዱም ባትወዱም ተማሩ። ተመራመሩ፡፡ … አለበለዚያ ዋጋ የላችሁም፡፡” ይላል፡፡
ያልተማረው ደግሞ፤ እንዲህ ይላል፡፡
“የለም! የተማረው መቼም የሀገር መፍትሄ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ምሁር ወጥቶ ወርዶ አንዳች መፍትሔ ሰጥቶ በገላገለን ነበር፡፡ የሚሻለው መሀይሙ ነው፤ ምክንያቱም በንፁህ ልቡናው አገሬን እንዴት ላግዝ እያለ ራሱን ይጠይቃል፡፡ ከተሳካለት ደግ ያረጋል፡፡”
ሦስተኛው፤ የተለየ ሃሳብ ይናገራል፡፡ ለአገር የሚበጀን የተማረም መምሰል፣ ያልተማረም መምሰል የሚችል ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም እንደሁኔታው መጓዝ የሚችለው ሁለቱንም የመምሰል ችሎታ ካለው ብቻ ነው ይላል፡፡
አባት ሶስቱንም አስመጥተው፤
“ልጆቼ፣ ሶስታችሁም ችግራችሁ - አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሶስታችሁም የማክረር ችግር ነው ያለባችሁ፡፡ እባካችሁ ላላ በሉ፡፡ አደብ ግዙ! አሁንም ለሚቀጥለው ዕድሜያችሁ ማክረሩን እንቀንሰው በሉ፡፡ አክርሮ ዳር የደረሰ ማንም የለም፡፡” ሲል መከራቸው፡፡  
***
 የሀገራችን ፖለቲካ ሂደት ከራርነት፣ አስተዋይ ልብ ይጠይቃል፡፡ ነገርን ከማለዘብና ከማላላት ይልቅ ሁሉም ነገር ላይ የዘራፌዋ ባህሪ ማሳየት፣ ኋላ መመለሻው እንዳይቸግረንና አደጋ ላይ እንዳንወድቅ አሳሳቢ ነው፡፡ ይቺ አገራችን ያከማቸቻቸው ህዝቦች የዋዛ አይደሉም፡፡ የረዥም ጊዜ የቅም በቀል ህልውና ያጠራቀምን፣ የረዥም ጊዜ የደምም፣ የጀግንነትም ህልውናና ታሪክ ያለን ኢትዮጵያውያን ነን!
ካሳ ተሰማ፣
“አባረርካቸው በቃ ተመለስ፣
ማንን ይተኳል አንት ብትጨረስ፣
ከባልንጀራው ማታ የተለየ፣
እንደአጥቢያ ኮከብ ሲነጋ ታየ”
ይለናል፡፡
የረዥም ተራራም መንገድ በአንድ እርምጃ እንደሚጀመር አንርሳ፡፡ ሁሉን ነገር ካልታዘልኩ አላምንም ብለን አንዘልቀውም፡፡ ከጥርጣሬ ካልተላቀቅን መንገዳችን አይሰምርም፡፡ አንድም፣
“አገባሽ ያለሽ ላያገባሽ
 ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” የሚለውንም ተረት ተግተን እንገንዘበው፡፡
ብዙ ችግሮች ዛሬም ይፈታተኑናል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ዛሬም እንደወረረን አለ፡፡ ሙስና ዛሬም በሸረሪት ድሩ እንደተበተበን ነው፡፡ የቢሮክራሲው ውስብስብ ገፅታ መያዣ መጨበጫ እንደሌለው መቼም ዐይን ያየው ፀሐይ የሞቀው ነገር ነው፡፡ ተጠገነ ስንለው ተሰብሮ ይገኛል፡፡ ዳነ ስንለው አልጋ ላይ ይውላል፡፡
ህዝብ የቅስም ስብራት ከገጠመው፣ ፖለቲካው አደጋ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ህዝብ በኢኮኖሚው የማገገም ተስፋ አጥቷል ማለት፣ ጉዟችን ቁልቁል ነው ማለት ነው፡፡ ህዝብ በቂም በቀል ከተሞላ፣ በማህበራዊ ምስቅልቅል ከተሞላ ጉዞው እሾሃማ ይሆናል፡፡ መነሻውን እንጂ መድረሻውን የማያውቅ ትውልድ ይፈጠራል፡፡ እንዲህ ያለው ትውልድ በትምህርቱ አይገፋም፡፡ በዕውቀቱ አይጠልቅም፡፡ በብስለቱ አይጠናም፡፡ የቸገነው አይፀድቅለትም፡፡ የኮተኮተው አያድግለትም፡፡
ሌላውና ቀንደኛው ችግራችን የመናናቅ አባዜ ነው፡፡ መከባበር ጥሎን ከጠፋ ውሎ አድሯል፡፡ በቀልና ቅናት የዕለት ጉዳይ ሆኗል፡፡
የእኛ ነገር፤
“ነገር በሆድ ማመቅ
ለትውልድ መርዝ መጥመቅ”
ያለው ዓይነት ነው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡ ተሻሽለን ሳናበቃ ንቀታችን አይጣል ነው፡-
“እዚችም ሆድ ውስጥ እህል ያድራል” አለች አሉ ማሽላ ጤፍን አይታ፤ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡


Read 7843 times