Tuesday, 02 July 2019 11:58

7ኛው “ሆቴል ሾው አፍሪካ” እስከ ነገ ክፍት ሆኖ ይቆያል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 • በሆቴል ኤክስፖው 5 ቢሊዮን ብር ይንቀሳቀሳል ተብሏል
     • ለቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ አስተዋፅኦ ያደረጉ ተሸልመዋል


     7ኛው ዙር የሆቴል ሾው አፍሪካ የሆስፒታሊቲና የቱሪዝም ኤክስፖ ባለፈው ሐሙስ ተከፍቷል፡፡ በኦዚ የሆቴልና ሆስፒታሊቲ አማካሪ ድርጅት በየዓመቱ በሚዘጋጀው በዘንድሮው ኤክስፖ ላይ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት  140 ያህል ኩባንያዎችና ከ500 በላይ ብራንዶች መሳተፋቸውን የሆቴል ኤክስፖው አዘጋጅና የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል አስታውቀዋል፡፡  
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር በሆኑት  ዶ/ር ሂሩት ካሳው ንግግርና ሰሞኑን በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው ላለፈው የአማራ ክልል አመራሮችና የመከላከያ ከፍተኛ የጦር አመራሮች የ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተከፈተው ኤክስፖው፤ እስከ ነገ ምሽት ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ታውቋል፡፡ በዚህ ኤክስፖ ወደ 5 ቢ. ብር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚንቀሳቀስም አቶ ቁምነገር ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የእውቅናና የምስጋና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል:: ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም “African Tourism and Hospitality Personality of the Year” በሚል ዋንጫና የእውቅና የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት ኢትዮጵያንና ትውፊቶቿን በየአካባቢው እያስተዋወቀ የሚገኘው የሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም፣ በምርጥ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ጋዜጠኝነት ዘርፍ ተሸላሚ ሆኗል፡፡  
በኤክስፖው ላይ አስጎብኚዎች፣ የሆቴል እቃ አቅራቢዎች፣ ባለሆቴሎች፣ የትራንስፖርት ድርጅቶች፣የሆቴል የደህንነት መሣሪያዎች አምራቾች፣ “ተርን ኪ” ፕሮጀክቶች (አንድን ሆቴል ከዲዛይኑ እስከ ማጠናቀቂያው ገንብተውና አሳምረው ቁልፍ የሚያስረክቡ ኩባንያዎች) የኮሚዩኒኬሽን ድርጅቶችና ሌሎችም በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዙሪያ  የሚሰሩ ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡
ከአገር ውስጥ ተሳታፊዎች በተጨማሪም ከጣሊያን ቱርክ፣ ቻይና፣ እንግሊዝ፣ሩዋንዳና ሌሎችም አገራት የመጡ ኩባንያዎችና አምራቾች ተሳታፊ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡   
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት ኦዚ የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም አማካሪ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪዝም እንዲያድግና እንዲፋፋ እያከናወነ ያለው እንቅስቃሴ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ኦዚ የሆስፒታሊቲና የቱሪዝም አማካሪ ድርጅት በየዓመቱ ከሚያዘጋጀው “ሆቴል ሾው አፍሪካ” በተጨማሪ ትልልቅ አለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች እዚህ አገር እንዲመጡ በመደራደር፣ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን እስካሁን 28 የሚደርሱ ብራንድ ሆቴሎች እንዲመጡ ድርድር መደረጉን የድርጅቱ ዳይሬክተር  አቶ ቁምነገር አስታውቀዋል፡፡  
ዘርፉ በመንግስት በኩል ያለው ድጋፍ አናሳ መሆኑን የገለፁት አቶ ቁምነገር፤ ለዚህ ማሳያውም ለሆቴሎች ኢንቨስትመንት የባንክ ብድር አቅርቦት መቆሙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎችና ግለሰቦች በሚያደርጉት ጥረት ዘርፉ እያደገ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዘርፍ መሆኑን  አሳስበዋል::   

Read 1882 times