Saturday, 06 July 2019 11:37

ሆድን በጐመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል

Written by 
Rate this item
(8 votes)


              አንዳንድ ትርክቶች እንደፃፍናቸው ሰው አያስተውላቸውም፡፡ ስለዚህ ደግመን ማስታወስ እንገደዳለን፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፤ አባትና ልጅ፤ ጅብ ሊያጠምዱ ወደ አደን ይወጣሉ፡፡
የጅብ አጠማመድ ዓላማና ዒላማቸው፣ ጠመንጃቸው አፈሙዝ ላይ ሙዳ ሥጋ ያስራሉ፡፡ ሙዳ ሥጋውን በገመድ ያስሩና ከቃታው ጋራ ያገናኙታል፡፡ ጅቡ ሥጋውን ሲጐትት ቃታውን ይስበዋል ማለት ነው፡፡ መላው ግልጽና ቀጥታ ነው! በገዛ ስግብግብነቱ ለቃታው ይጋለጣል ማለት ነው!
ይህንኑ መላና አላማ ይዘው ወደ ዱር ገቡ፡፡ ጠመንጃው አፍ ላይ ሙጃውን አስረው የገመዱን ጫፍ ቃታው ላይ ቋጥረው፣ የጅቡ መግቢያ መውጫ ላይ ያስቀምጡታል፡፡ ጅቡ ግን ቃታው ላይ ከታሠረው ሙዳ ይልቅ የጠመንጃውን ሰደፍ ነክሶ ሙሉውን ጠመንጃ ይዞት ሄደ፡፡
ይህንን ጉድ ያየው ልጅ፣ ወደ አባቱ ሲሮጥ መጥቶ፤
“አባዬ …አባዬ…ጉድ ሆነናል…”
“ምነው?” አለ አባት፡፡
“ጅቡ የጠመንጃችንን ሰደፉን ነክሶ ይዞት ሄደ!”
አባትየውም፤
“ልጄ፤ አለቀልን በለኛ! እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው!” አለ!
***
ብዙዎች መንገዶቻችን ከጠመንጃ ተላቀው አያውቁም፡፡ ከተላቀቁም በጭራሽ አለ መዘዝ አይደለም፡፡ ሁልጊዜም ቁጭት፣ ሁልጊዜም ቂም በቀል፣ ሁልጊዜም ደባ፣ ሁልጊዜም ሥር - የሰደደ የተበዳይነት ስሜት፤ ወደ መፍትሔ ከመሄድ ይልቅ ጥያቄያዎችን ማስፋፋትና ማጋጋል እንደ ፖለቲካ ሙያ እንዲታይ መገፋፋት:: አገራችን ወደተሻለ ብርሃን ሳይሆን ወደ ጨለምላማው አቅጣጫ እንዳትሄድ ያሰጋል፡፡ ብልጭ ድርግም የሚለው ሁኔታችን ዛሬም አሳሳቢ ነው፡፡
በዘላቂነት እንደማይበራው መብራታችን፣ በዘላቂነት እንደማይቀጥለው ውሃችን፣ በአስተማማኝነት ፍሬ እንደማይሰጠን ፍትሀችን፣ ለአዲሱ ትውልድ በሙሉ ዕምነት እንደማንለግሰው ተስፋችን ብዙውን ምኞታችንን በሰቀቀን ይዘን መጓዝ ግዴታችን የሆነ ይመስላል፡-
“እኛማ ብለናል
እኛ ተናግረናል
ጥንትም ወርቅ በእሳት
    እኛም በትግላችን
እየተፈተንን
አንጠራጠርም እናቸንፋለን
ድል እናደርጋለን”
ብለን ነበር ዱሮ፤ ዛሬም እንላለን፡፡
“እየነጋ ሲሄድ ድል እናደርጋለን!!”
አብዛኛው ሁኔታችን ዝምታ የዋጠው ነው፡፡ ዝምታችንም ድቅድቅ ጭለማ የወረሰው ነው፡፡ ጠንካራ እልባት ያስፈልገዋል፡፡
ሀ) “ዝም ብንል ብናደባ
       ዘመን፣
        ስንቱን አሸክሞን
የጅልነት እኮ አደለም፣
               እንድንቻቻል ነው ገብቶን”
ፀ.ገ/መ (“ማነው ምንትስ እሳት ወይ አበባ”)
… ያለውን መገንዘቢያችን ሰዓት ነው፡፡ እንንቃ! እንትጋ! እንትባ!
በርትተን ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህንን እንመርምረው፡-
2)  “ዛሬ ለወግ ያደረግሺው
      ወይ ለነገ ይለምድብሻል
      ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው
      ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
      ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ
      ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል!”
እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውን ስንኞች በለሆሳስ ከፈተንናቸው ምናልባት አገራችን ያለችበትን መሠረተ ነገር እንደርስበት ይሆናል፡፡ እስቲ እናጢናቸው፡፡
ለወጣቶቻችን ቦታ እንስጥ፡-
እንደገና ፀጋዬ ገ/መድህንን እንጥቀስ፡-
“ሽማግሌውን ባንቀልባ፣
    ከምንሸከም እንኮኮ
    ጐልማሳውን ከወኔ ጣር፣
    ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ
    ካቃተን ምንድን ነን እኮ!”
… ማለት ፀጋ አይደለም እንዴ?
በጀመርነው ለመደምደም በሎሬቱ የሐምሌት ትርጉም ሁለት ስንኝ
እንሰናኝና እናብቃ፡-
“በምናውቀው ስንሰቃይ፣
    በማናውቀው ስንሰቃይ፣
        የማናውቀውንም ፈርተን
በህሊናችን ማቅማማት፣
    ወያኔያችንንም ተሰልበን
ከአባቶች በወረስነው ጋድ፣
ከቀን ቀን እንሳስባለን…”


Read 8656 times