Saturday, 06 July 2019 12:42

“የማይተማመን ባልንጀራ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

    “--ግን ደግሞ ሁሉም ሙያዎች ላይ በምሳሌነት የምንጠራቸው… አለ አይደል… “እንትና የተባለው የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዘንድ ሂድ፣” “እንትና የተባለውን ፕሮፌሰር ሌክቸር ተከታታል፣” “እንትና የተባለው አርክቴክት ፕላኑን ይስራልህ፣”… ምናምን የምንላቸው ቁጥር ሲያንስብን ትንሽ ማሳሰቡ አይቀርም፡፡ እንደዛ እየመሰለ ነውና! --”        
           

            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሁለቱ የፒ.ኤችዲ. ማእረግ ያላቸው ጓደኛሞች የሆነ ስፍራ ይገናኛሉ፡፡ እናላችሁ… አንደኛው ሌላኛውን… “ዶከተር እንደምን ዋልክ?” ይለዋል:: ያኛውም አጸፋውን ከመመለስ ይልቅ…
“እንደሱ መባባል ቀርቶ!” ይለዋል፡፡
“ማን መባባሉ ነው የቀረው?”
“እኔና አንተ ስንገናኝ ዶክተር መባባል የለብንም::”
“ምንድነው መባባል ያለብን?”
“ሞክሼ….ሞክሼ ነው መባባል ያለብን፡፡”
አሪፍ አይደል! እኔ የምለው… ሀገሪቱ ከአቅሟ በላይ ባለ ማእረግ በዛባት እንዴ! ማወቅ አለብና…አለበለዛ በስንት ልፋት የሆነ የማእረግ ቅጥያ ከስሙ ፊት የተቀጠለለትን ሰው…አለ አይደል… ‘በለመደ አፋችን’ “አቶ እከሌ…” ብለን ለምን ጠላት እናፈራለን፣ ለምንስ ቂም እናተርፋለን! ለምንስ…“ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን በእሱ ቤት መመቅኘቱ ነው፣” እንባላለን!
“አክቲቪስት እከሌ እንዴት ነህ?”  (ያው ‘አክቲቪስት’ የሚለው ከመጠሪያ ስም ፊት የሚገባ የሆነ ማእረግ የሚመስሉ ምልክቶች አይጠፉም ብዬ ነው፡፡)
ስሙኝማ…ብዙ ዶክተር፣ ብዙ ረዳት ፕሮፌሰር፣ ብዙ ፖለቲካ ተንታኝ ምናምን ማግኘታችን አሪፍ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ… ‘የፖለቲካ ተንታኝ’ የሚለው ነገር ‘የማእረግ ስምነት’ ያንሰዋል እንዴ! በየቲቪው ቃለ መጠይቅ ላይ “የፖለቲካ ተንታኙ አቶ እከሌ…” የሚባለው ከመብዛቱ፣ ከ“አቶ” ይበልጥ ጥቅም ላይ የዋለ የማእረግ ስም ሆኖብናላ! እንደ ሀሳብ…የፖለቲካ ተንታኞች ስትገናኙ “ሞክሼ…” እየተባባላችሁ፣ ‘ሞክሼ’ የተባለች የተረሳች ቃልን እየቀባባችሁ አሰማምሩልንማ!)
እናላችሁ…ሀገሪቱ እንዲህ አይነት በእውቀት የመጠቁና ‘በእውቀት መምጠቃቸው’ በአእምሮ ያበሰላቸው ሰዎች በጣም ያስፈልጓታል፡፡ (እነ እንትና እውቀት ሰብስቦ በአእምእሮ መብሰል እንጂ እውቀት ከልክ በላይ ሰብስቦ ‘በአእምሮ ማረር’ ብሎ ነገር የለም፡፡ ወይስ ይኖር ይሆን! ስለ አንዳንድ ሰዎች ስታወሩ እንደዛ ልታስመስሉት ምንም ስለማይቀራችሁ ነው፡፡ ያውም ‘ለእኛዋ ሀገር ፖለቲከኛ! ቂ…ቂ…ቂ…ለጠቅላላ እውቀት ያህል... በቴሌቪዥን ላይ በ‘ፖለቲካ ተንታኝነት’ ወይም በ‘ፖለቲካ አክቲቪስትነት’ ብዙ ጊዜ በመቅረብ ማን ይመራል? ‘ኢትዮጵያ ጎት ታሌንት’ ምናምን የሚባል ነገር ካለ ለመጠቆም እንዲረዳን ለማለት ያህል ነው፡፡)
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ባለሙያዎችን በተመለከተ ችግሩ ምን መሰላችሁ… ከሁሉም ተመሳሳይ ብቃት እንጠብቃለን፡፡ አይሆንማ! ቀሺም መአት ‘ጠሀፊዎች’ ያለነውን ያህል መአት ቀሺም የህክምና ባለሙያ ይኖራላ! መአት ቀሺም ረዳት ፕሮፌሰር፣ ቀሺም የግንባታ ባለሙያ፣ ቀሺም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምናምን ይኖራላ! የህክምና ባለሙያ ሁሉ በሁለት ሦስት መርፌ ካንሰርን እንዲያጠፋ አይነት  እንፈልጋለን፣ ፕሮፌሰር ሁሉ ‘አፍ የሚያስከፍት’ የሚባልና ‘ከዓለም ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ አንደኛ’ የሚያደርገን ምሁራዊ ትንታኔ እንዲሰጥ እንጠብቃለን፡፡  ቢሆን ኖሮ ምንኛ በታደልን ነበር፡፡
ግን ደግሞ ሁሉም ሙያዎች ላይ በምሳሌነት የምንጠራቸው… አለ አይደል… “እንትና የተባለው የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዘንድ ሂድ፣” “እንትና የተባለውን ፕሮፌሰር ሌክቸር ተከታታል፣” “እንትና የተባለው አርክቴክት ፕላኑን ይስራልህ፣”… ምናምን የምንላቸው ቁጥር ሲያንስብን ትንሽ ማሳሰቡ አይቀርም፡፡ እንደዛ እየመሰለ ነውና!
ታዲያላችሁ… ነገርን ነገር ያነሳው የለ…  እንደ ባህል እየመሰለ የመጣው ነገር ሙያና ባለሙያን አጠቃሎ የማናናቅ ነገር ነው፡፡ በትንሹም፣ በትልቁም “እዚህ ሀገር ምን ዶክተር አለና!” እየተባላችሁ እንዴት ነው ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ የሚገፋፋችሁ! “ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ደራሲና አለና!” እየተባላችሁ እንዴት ነው አይደለም መጽሀፉን ማንበብ፣ አንስታችሁ ርዕሱን እንኳን ለማየት ፍላጎቱ የሚኖራችሁ! “ዘንድሮ ምን የኃይማኖት መሪ አለና!” እየተባላችሁ እንዴት ነው በሙሉ ልብ ቤተ እምነታችሁ የምትሄዱት! “ዩኒቨርሲቲ በዛ እንጂ ምን ምሁር አለና!” እየተባላችሁ እንዴት ነው ለምሁራን አመለካከት ጆሯችሁን የምትሰጡት!
እናማ...በዚህ በኩል ችግር አለ…ለፈተናዎቻችን ፍቱን መፍትሄዎች እንዳናገኝ እየጋረደን ያለ ግዙፍ ችግር፡፡ ነገሮች እንዲህ እየተጠቀለሉ በአንድ ሙቀጫ ሲወቀጡ እንዴት ነው ያሉንን የእውነተኛ ባለሙያዎቻችንን እውቀትና ክህሎት መጠቀም የምንችለው! ይቺ ሀገር እኮ… አለ አይደል… በፖለቲካ በሉት፣ በኤኮኖሚ በሉት፣ በማህበራዊ ጉዳዮች በሉት….ክፉኛ ያጠራት እውቀት ነው እኮ! ያሉንን ባለሙያዎች እንደየ እውቀት ደረጃቸው መቀበል ካልቻለን፣ እንዴት ነው ትኩስና ብቁ ባለሙያዎችን ማግኘት የምንችለው! ከእለት እለት እኮ የሚሠሩ ነገሮች፣ የሚነገሩ፣ የሚታዩ ነገሮች ሁሉ እያሳበቁብን ያሉት ብዙ ነገሮች የሚበላሹት በእውቀት ማነስ መሆኑን ነው:: እውቀትም በበኩሏ ጥላን ልትሰደድ ልብሷን “በፌስታል…” እየቋጠረች ነው:: (ቂ…ቂ…ቂ… “ወይ ጦቢያ ሀገሬ!” እንጂ ሌላ ምን ይባላል!)
“ምን ሆነሃል? ሳይህ ደህና አትመስልም፡፡” (ዘንድሮ ‘ሲያዩት ደህና የሚመሰል’ ስንት ሰው አለና ነው!)
“ምን እባክሀ ሆዴን በለው፣ ምኔን በለው ሲጫወትብኝ ነው የከረመው፡፡”
“እና ምን አደርግሀበት!”
“መፍትሄ ይሰጡኛል ብዬ ሆስፒታል ሄጄ ጭራሹኑ በሽታ አይጨምሩብኝ መሰለህ!”
“በስህተት የአእምሮ በሽተኛ መርፌ ወጉህ እንዴ!” (ስሙኝማ… ድሮ እዚህ ካዛንቺስ አካባቢ ‘ሲቀብጡ ይይዛል’ ለሚባለው ‘ያ ነገር’ (ቂ…ቂ…ቂ…) የሚታዘዘው መርፌ ትልቅነቱ የእድር ድንኳን ያቆም ነበር ይባላል፡፡ እናማ..እሱ መርፌ ላይ መተካካት ምናምን ገና አልተካሄደበትም እንዴ!)
“አንተ ምን አለብህ፣ አሹፍ! ለምርመራ ስንትና ስንት ብር አስገፍግፈውኝ ዶክተሩ ምን ቢያዝልኝ ጥሩ ነው… አሞክስሊን፡፡”
“አትለኝም…”
“ስነግርህ፣ እንደ ንፍሮ ብትቀቅለው የቤተሰብ ጉባኤ የሚቀልብ የአሞክስሊን መአት አሸከመኝ ነው የምልህ!”
“ጥፋተኛ እኮ አንተ ነህ፣ መጀመሪያ ነገር እዚህ አገር ምን ዶክተር አለና ነው!”
ይኸዋ! በብዙ ጉዳዮች ነገራችን እንዲህ ሆኗል:: የምር ኮሚክ እኮ ነው…ሀኪሙ ሰባት የኪኒን አይነትና ሦስት የመርፌ አይነት ካዘዘልን በቃ ችግራችንን አውቆልናል ማለት ነው:: አለበለዛ አምስት ቀን ጠዋትና ማታ አንድ፣ አንድ ፍሬ የምንቅማት ኪኒን አስይዞ ከላከን ችግራችንን አላወቀልንም ማለት ነው፡፡ እናላችሁ፣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ህክምና አካባቢ ብዙ ከሙያ ብቃትም፣ ስነምግባር ካለማክበርም፣ ከግብአቶች እጥረትምና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ለልብ ወለድ እንኳን ‘የተጋነኑ’ የሚባሉ ስህተቶች ተፈጸሙ ሲባሉ እንሰማለን:: እውነት ሆኑም አልሆኑም አስተሳሰባችን ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ አለ፡፡ ነገራችን “የማይተማመን ባልንጀራ…” አይነት ሆኖ የት እንደሚደረስ እሱ ይወቀው!
ደግሞላችሁ… አብዛኛው የህክምና ባለሙያ ሥራውን በብቃትና የሙያውን ስነ ምግባር በጠበቀ መልኩ እየሠራ መሆኑን መዘንጋት ትክክል አይሆንም:: የስህተት… ያውም የህክምና ስህተት… ትንሽ የለውም:: ግን ደግሞ… ጠቅልሎ ሁሉንም ባለሙያና ብሎም ሙያው ላይ የሌማት ክዳን መድፋት፣ በዘመኑ ቋንቋ፣ ዋጋ ያስከፍላል:: (‘በዘመኑ ቋንቋ’ የተባለው ቀደም ሲል ‘ዋጋ’ እና ‘መክፈል’ የሚሏቸው ቃላት ጥምረት የሚፈጥሩት ወይ አትክልት ተራ፣ ወይ ጎጃም በረንዳ ወይ ደግሞ (ከልጅ ልጅ ላለመለየት ያህል…) መሸት ሲል ዶሮ ማነቂያ ስለነበረ ነው፡፡)
እናላችሁ… ይቺ  “ምን አለና…” የምትል ነገር ህክምናን በመሳሰሉ ሙያዎች ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር ውስጥ እየገባች ነው፡፡ ግንማ…ፈረንጅ ‘ኤክሴፕሽን’ እንደሚለው…አለ አይደል… “እዚህ ሀገር ምን እዚህ ግባ የሚባል ፖለቲከኛ አለና ነው!” ቢባል ‘በልዩ ሁኔታ’ ልናየው ዝግጁ ነን፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…)
እኔ የምለው…እንግዲህ ሐምሌም መግባቱ ነው፣ ብርዱም “ጭብጦ ባላሳክላችሁ እናንተን አያድርገኝ እያለን ይመስላል፡፡ ‘ሞክሼ’ ጋዜጠኞች…የፎርና ፋይቭ ስታር ሆቴሎች በሮች ወለል ብለው የተከፈቱላችሁ ወዙን በየጉንጫችሁ ያንጠፍጥፍላችሁና የቀረነው የቀድሞውን የጅማ ባርን ሌጌሲ የማናስቀጥልሳ!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2698 times