Saturday, 06 July 2019 14:23

ትዝታን ሽሽት

Written by  መኮንን ማንደፍሮ
Rate this item
(21 votes)

(ክፍል-2)

        ቤርሳቤህ ካወጋችኝ ታሪክ ተነስቼ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በዝምታ እያውጠነጠንኩ ባለበት ሰዓት ነበር የምሽት ክለቡን ታዳሚ ሞቅ ያለ ጭብጨባና ፉጨት ሰምቼ ትኩረቴን ወደ ሙዚቀኞቹ የመለስኩት፡፡ የክለቡ ታዳሚ ደስታውን በፉጨትና በጭብጨባ የገለፀው፣ ራሰ በራውን ጥቁር ዘፋኝ ያጀበው የአገረሰብ የሙዚቃ ቡድን፤ የጥላሁን ገሠሠን እጅግ የታወቀ የአማርኛ ዘፈን መጫወት በመጀመሩ ነበር፡፡  
“አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ አስቲ?” አለች ቤርሳቤህ፣ በመካከላችን ሰፍኖ የነበረውን ዝምታ ሰብራ።
“ምንድን ነው?”
“ለምንወደው ሰው ከፍቅር የላቀ መስጠት የምንችለው ነገር ይኖራል?” ከባድ ፍልስፍና የጠየቀችኝ ይመስል ጥያቄዋን ለመመለስ ዘገየሁ።
“ከፍቅር ሌላ ምን ነገር ይኖራል?” አልኩ በደፈናው። ከወንድ ጋር በፍቅር አብሮ በመኖር ያዳበርኩት ልምድ አልነበረኝም።
“ጥያቄውን ለምን እንደጠየቅሽኝ ግን ግልፅ አልሆነልኝም።”
“ሁለት ወንዶችን አፈቀርኩ፣ ሁለቱም ግን በመክዳት ሸሹኝ።
ያፈቀሩኝ መስለው ሲጠጉኝ ፍቅርን ከመመለስ ውጪ ምንስ ማድረግ እችል ነበር? ወይስ በፍቅር ሕይወት ደስተኛ ለመሆን እድለኝነት ይጠየቃል?” አለችና ጥያቄዎቹን ለራሷ እንደሰነዘረች ሁሉ ተነስታ እቃዋን ሸክፋ፣ ወደ ቤት እንድንሄድ ጠየቀችኝ። ቦርሳዬን አንግቼ ተከተልኳት።
ከቤርሳቤህ ጋር ዳንኤል ወደ ሚጫወትበት የምሽት የሙዚቃ ክለብ ለሁለተኛ ጊዜ የሄድነው ከሳምንት በኋላ ነው፣ በእኔ ጥያቄ መሠረት። የምሽት ክለቡን የሙዚቃ ዝግጅት የከፈተው ዳንኤል ነበር። ሁለት የትዝታ ዘፈኖችን ነበር የተጫወተው፣ ሥራዎቹን አቅርቦ መድረኩን ሲለቅ የምሽት ክለቡን እስከ አፍጢሙ የሞላው ታዳሚ ሞቅ ያለ በጭብጨባና በጩኸት የታጀበ አድናቆቱን ቸረው።
ዳንኤል ከመድረክ ሲወርድ፣ ቤርሳቤህን “እንተዋወቀው--” ብያት ተያይዘን ዞረን ወደ መድረኩ ጀርባ ስንሄድ ወደ ፎቁ እየዘለቀ አገኘነው። የቤርሳቤህን ክንድ ለቅቄ በፍጥነት ወደ እሱ አቅጣጫ ገስግሼ ቀረብኩና ”ዳንኤል!” ብዬ ጠራሁት፤ እርምጃውን ገትቶ ወደ እኛ አቅጣጫ ዞረ።
“ይቅርታ! ሥራህን ወደነው አድናቆታችንን ልንገልፅልህ ፈልገን ነው።“ አልኩ፤ አጠገቡ እንደደረስኩ እጄን ለሰላምታ ዘርግቼ።
“ኦ! አመሰግናለሁ። ዳንኤል እባላለሁ።” አለ፤ የዘረጋሁለትን እጄን እየጨበጠ።
“አስቴር።”
“እሷ ደግም እህቴ ናት።” አልኩ፤ ቤርሳቤህ መጥታ እንደተቀላቀለችን።
“ቤርሳቤህ--” አለች፤ እህቴ ቀኝ እጇን ለሰላምታ እየዘረጋችለት።
“ዳንኤል።” አለ፤ እጇን እየጨበጠ።
“የተጫወትካቸው ሙዚቃዎች እጅግ ደስ ይላሉ።” አልኩ፤ በፈገግታ እያስተዋልኩት።
“አመሰግናለሁ!”
“የማን ሥራዎች ናቸው ግን? ማለቴ ከዚህ በፊት ሰምቻቸው አላውቅም።”
ጥያቄውን ያነሳሁት በብዙዎች ዘንድ በሰፊው የማይታወቁ ዘፋኞች፣ የምሽት ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱት የአንጋፋ ሙዚቀኞችን ሥራ ነው ከሚል የቆየ ልምዴ ተነስቼ ነው።
“የራሴ ሥራዎች ናቸው።” አለ፤ በፈገግታ ተሞልቶ እያፈራረቀ እያየን።
“በጣም ደስ ይላል፣ በርታ።” አልኩ፤ አተኩሬ እየተመለከትኩት። አድናቆቴን መቀበሉን በፈገግታ አጅቦ አንገቱን በመነቅነቅ ገለፀልኝ።
“ከይቅርታ ጋር በዚሁ አጋጣሚ ፈቃደኛ ከሆንክ አድራሻ እንለዋወጥ?” አልኩት፤ እንደ መሽኮርመም ብዬ።
“እሽ፣ ምንም ችግር የለም፣ ሙዚቀኞች ናችሁ?”
“አይ አይደለንም። እሷ መሀንዲስ ነች፤ እኔ ደግሞ የቴአትር ተማሪ ነኝ።”
“ኦ! በጣም ደስ ይላል። ይህ አድራሻዬ ነው።” አለና፤ ከዋሌቱ ውስጥ አውጥቶ ስሙና አድራሻው የታተመበት ትንሽዬ ካርድ ሰጠኝ።
“እናመሰግናለን!”
“ምንም አይደል!” አለና የግል ስልክ ቁጥሬን ስልኩ ላይ መዝግቦ፣ ተሰናብቶን ሄደ።
ከቤርሳቤህ ጋር ዳንኤልን ተዋውቀነው ወደ ክለቡ ስንመለስ፣ የሆነ የተለየ የደስታ ስሜት ከቦኝ ነበር።
ክለቡ ውስጥ ስንገባ አንዲት ጠይም ቀጭን ዘፋኝ መድረክ ላይ የእንግሊዝኛ ዘፈን እየዘፈነች አገኘናት፤ አብዛኛው ታዳሚም አብሯት እየዘፈነ።
ፊት ለፊቴ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ ፓኮ ሲጋር ውስጥ አንድ ሲጋራ አወጣሁና አቀጣጥዬ፣ እያፈራረቅኩ፣ ዘፋኟንና ቤርሳቤህ አብሬው እንድደንስ የጠየቀችኝን ባለ አፍሮ ወጣት መመልከት ጀመርኩ። ባለ አፍሮዉ ወጣት በሶስት ሴቶች ተከቦ እጆቹን በአስረጅነት እያወናጨፈ ያወራል፤ ሴቶቹ በየመሀሉ ረጅም ሳቅ ይስቃሉ፣ ጥርሳቸውን በእጃቸው ጋርደው። የተለየ ቀልድ እያወጋቸው እንደሆነ ገመትኩ።           
ታዳሚው ባሳያት የሞቀ አቀባበል የተደሰተች የምትመስለው ዘፋኝ፤ ሌላ እኔ ራሴ እጅግ የምወደውን የሎሪ ሊበርማንን ዘፈን ቀጠለች።
Strumming my pain with his fingers
Singing my life with my words  
Killing me softly with his song
Killing me softly with his song
Telling my whole life with his words
Killing me softly with his song.
ቤርሳቤህ ጮክ ብላ ከዘፋኟ ጋር አብራ እየዘፈነች ቆየችና፣ የቀኝ እጇን በከንፈሮቿ ስማ ከፍ አድርጋ በማውለብለብ በታላቅ ፈገግታ እኛን እየተመለከተች ለምታዜመው ድምፃዊት ያላትን አድናቆት ገለፀችላት። ድምፃዊቷም ተመሳሳዩን ድርጊት በመድገም፣ አፀፋውን መለሰች።Read 2858 times
More in this category: « ጣዖቷ እስስቱ! »