Saturday, 13 July 2019 11:26

የበላን አብላላው፤ የለበሰን በረደው

Written by 
Rate this item
(17 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት እጅግ እንዳሚዋደዱ የሚነገርላቸው ጓደኛሞች ረዥም መንገድ መሄድ  ይጀምራሉ፡፡
በመንገዳቸው ላይም ዕቅድ ለማውጣት ይመካከራሉ፡፡ የዕቅዶቻቸው አንኳር አንኳር ነጥቦችን እንደሚከተለው ነጠቡ፡-
1ኛ- ቆራጥነት
2ኛ- ጠላት ከመጣ በጋራ ማጥቃትና በጋራ መከላከል
3ኛ- ከወዲሁ መንቂያ ምልክቶችን መሰዋወጥ
4ኛ- በፍጥነት የማምለጫ አቅጣጫ መለየት
5ኛ- ካልተቸገሩ በስተቀር መሣሪያ አለማውጣት
6ኛ- ወደ ጫካ ገብቶ መደበቅ ካስፈለገ፣ በያሉበት ሆኖ የጭስ ምልክት ማሳየት
7ኛ- ጨርሶ ከተጠፋፉ ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ወደ መኖሪያ ቀዬ መመለስና እዚያ መገናኘት የሚሉ ናቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ለጥቂት ሰዓታት እንደተጓዙ፣ ከየት መጣ ሳይባል፣ ጅብ ከተፍ አለና ተፋጠጣቸው፡፡
አንደኛው፤ በደመ- ነብስ ረዥም ዛፍ ላይ ወጥቶ አመለጠ፡፡
ሁለተኛው፤ እዚያው ባለበት ወድቆ የሞት መስሎ ተኛ፡፡
ጅቡም የሞተ መሆኑን እንደማረጋገጥ፣ በጣም ተጠግቶ፣ አሽትቶት መንገዱን ቀጠለ፡፡
አንድ ሰዓት ያህል እንዳለፈ ጅቡም እንደማይመለስ ተረጋገጠ፡፡ ዛፉ ላይ የወጣውም ወረደ፡፡የሞተ የመሰለውም ተነሳ፡፡
ዛፍ ላይ የነበረው እንደ ወረደ ተንደርድሮ መጥቶ፤
“ስማ ስማ፤ ጅቡ ወደ ጆሮህ ተጠግቶ ምን ነበር ያለህ ?” አለና ጠየቀው፡፡
ጓደኝየውም፤
“ምን አለኝ መሰለህ ? ክፉ ጊዜ ሲመጣ የሚሸሽ ጓደኛ አትያዝ!”
*   *   *
የማይታመንን ወዳጅ እንደ ሁነኛ ጓደኛ አድርጎ መያዝ፣ የቁርጡ ቀን ሲመጣ በጉዴ ወጣሁ ያሰኛል፡፡ ከቶውንም ሲጀምሩት ቀላልና ቀና የሚመስል ጓደኝነት፣ ወንዝ ሊያሻግር እንደማይችል ለማየት ዓይንን ማሸት አይጠይቅም፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ  በግለሰብና በግለሰብ መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በቡድንና በቡድን፣ በፓርቲና በፓርቲ፤ በሀገርና በሀገር መካከል ክሱት ነው፡፡ እያደገም ሂያጅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንዳልነው፤ “change is incremental” - ለውጥ አዳጊ ሂደት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አንዳንዱ ለውጥ አይነጥፍም፤አንዳንዱ አይጨነግፍም፤አንዳንዱ ሰው ሳይሰማው ሳያውቀው ከናካቴው አይመክንም ማለት አይደለም፡፡ ለውጥ በድንገቴ ክስተት ሊመጣ ይችላል፡፡ ሥር በሰደደ፣ መሠረት በያዘ መንገድም ውል ሊይዝ ይችላል፡፡ በግርግር ተጀምሮ በለብ ለብ ሂደትም ሊከሰት ይችላል፡፡ እንደ “ለብ ለብ ፍቅር” ማለት ነው፡-
እሳት ያልገባው ልብ
ሚሚዬን ጠየኳት፣
“ሁልጊዜ አረንጓዴ ፣ለምለም ፍቅር አለ
ትወጃለሽ ሚሚ ይሄን የመሰለ
ወይስ ያዝ ለቀቅ ጭልጥ አንዴ መጥቶ
 አፍ ጠራርጎ መሄድ ያገኙትን በልቶ
 ሚሚዬ. እንዲህ አለች ሳስቃ መለሰች
የምን እኝኝ ነው ዕድሜ ልክ ካንድ ሰው
 ቋሚ ፍቅር ይቅር ለብ ለብ እናርገው
ትምርቷ ለብ ለብ
ዕውቀቷ ለብ ለብ
ነገር ዓለሟ ግልብ
እንዴት ይበስል ይሆን እሳት ያልገባው ልብ!
የዛሬው ወጣት እሳት የገባው ልብ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለብ ለቡ ጥብስ ጉዳቱ፣ እኛ በለብ ለብ ያለፍነው ለውጥ፣ ወራሾቻችንን በማይተካ መልክ ዋጋ ማስከፈሉ ነው! ይህን ከልብ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ትምህርት ቤቶቻችን በዚህ ረገድ በአያሌው ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ጤና ጣቢያዎቻችን በቀጥታም ባይሆን ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ማህበረሰቦቻችንም በተቀዳሚ ወላጆች፣ ቀጥሎ ሁሉም ተቋማት ባለዕዳዎች ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ መከራው የሁላችንም ነው፡፡ ማ ተጠይቆ ማን ይቀራል ማለት ያባት ነው፡፡
ሁሉም ነገር እየተመቻቸልን ከከፋን፣ ሁሌ በወርቅ አልጋ በእርግብ ላባ ላይ ካልተኛን ካልን፣ የመጨረሻ የዋህያን ነን ማለት ነው፡፡ የኖህነት አንድ ነገር ነው፤ ጅልነትና ሞኝነት ግን ጎጂም ነው:: ከራስ አልፎ ሌላውን ያሰቃያል፡፡ ከዚህ እንጠንቀቅ!
የተሰጠንን በደስታ መቀበል፤ የተበረከተልንን በፀጋ መያዝና የተሻለ ፀጋ መሻት የወቅታችን ሂደት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ዋናው ሁሉን አቻችሎ  የመጓዝን ክህሎት ማጣጣም ነው:: “አንድ ወደፊት ለመጓዝ አራት ወደ ኋላ” የሚለውን  የጥንት ሊቃውንት ስልት ማሰብም ኋላ ቀርነት አይሆንም፡፡ ሁሉ እየሆነልን፣ እንዳልሆነ ካሰብን ተሳስተናል ፡፡ አበው፡- “የበላን አብላላው፤ የለበሰን በረደው” የሚሉት ለዋዛ እንዳልሆነ መገንዘብ ያለብን ይሄኔ ነው!!

Read 9273 times