Tuesday, 16 July 2019 09:48

እስስቱ!

Written by  ደራሲ - አንቷን ቼኾቭ ትርጉም - አማረ ፈ. ታቦር
Rate this item
(17 votes)

የፖሊስ መምሪያ ሹም ኦቹማዬሎፍ፤ አዲስ ካፖርቱን ለብሶና የተጠቀለለ እቃ ብብቱ ሥር ይዞ፣ የገበያ ቦታውን በማቋረጥ ላይ ነበር። የተወረሱ ፍራፍሬዎችን በእጁ የያዘ ባለ  ቀይ ጠጉር ፖሊስ ከኋላው አስከትሏል። በቦታው ላይ ጸጥታ ነግሷል። ገበያው ውስጥ አንድ ነፍስ እንኳን አይታይም። ተከፍተው የተተዉት የሱቆቹና የመጠጥ ቤቶቹ መስኮቶች፣ በረሃብ በሰፊው ኣ! ብለው የተከፈቱ አፎች ይመስላሉ። አጠገባቸው ለማኝ እንኳን አልነበርም፡፡
ኦቹማዬሎፍ በድንገት አንድ ሰው ሲጮህ ሰማ፤
“ትናከሳለህና፤ አንተ የተረገምክ አውሬ! በዛሬ ጊዜ ውሾች መናከስ አይፈቀድላቸውም። ኧረ በቃ! ወይኔ! ወይኔ!”
የውሻ ጩኸት ተሰማ። ኦቹማዬሎፍ፤ድምጹ ወደመጣበት አቅጣጫ ሲመለከት፣ በሦስት እግሩ እያነከሰ ከጣውላው ቤት ግቢ የሚሮጥ ትንሽ ውሻ አየ። ያልተቆለፈ ነጭ ሸሚዝ የለበሰ ሰው እያሳደደው ነበር። ሰውየው የውሻውን ተረከዝ ለመያዝ ቀርቧል። ድንገት ተደናቀፈ፤ ነገር ግን ሲወድቅ ተንጠራርቶ የውሻውን የኋላ እግር ያዘ። የውሻው ጩኸት እየተደጋገመ ተሰማ። እንቅልፋም ፊቶች በሱቆቹ መስኮት በኩል  ብቅ ብቅ አሉ:: ባጭር ጊዜም ከመሬቱ ውስጥ ወደ ላይ የፈለቀ የሚመስል ሕዝብ ጣውላው ቤት ዙሪያ ተሰበሰበ።
ፖሊሱ፤ “ጠብ ይመስላል ጌታዬ” አለ።
ኦቹማዬሎፍ ዞር ብሎ ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ እየተጣደፈ ተራመደ። የጣውላው ቤት በር አቅራቢያ፣ ያልተቆለፈ ነጭ ሸሚዝ የለበሰ ሰው፣ ቀኝ እጁን ከፍ አድርጎ፤ እየደማ ያለ ጣቱን ለሕዝቡ እያሳየ እንደሆነ ተመለከተ። በሰውየው ግማሽ ሰካራም ፊት ላይ፤ “አንተ ከይሲ፤ ቆይ አሳይሃለሁ!” እንደሚል አይነት አስተያየት ይነበባል። ኦቹማዬሎፍ ሰውየውን አውቆታል። አንጥረኛው ክሩይኪን ነበር። የፊት እግሩ ተዘርግተውና ከራስ ጠጕሩ እስከ እግር ጥፍሩ እየተንቀጠቀጠ፣ ችግሩን የፈጠረው ወንጀለኛ ውሻ፣ በተሰበሰበው ሕዝብ መሀል ተኝቷል:: የሾለ አፍንጫና ጀርባው ላይ ቢጫ ነጥብ ያለው ነጭ ቡችላ ነው። እንባ በቋጠሩት አይኖቹ ውስጥ መከራና ፍርሃት ይነበባል።
ኦቹማዬሎፍ፤ ሕዝቡን በትከሻው እየገፋ ወደ መሃል ገብቶ፤
 “ምንድነው ይሄ ሁሉ ግርግር?” ብሎ ጠየቀ፤ “አንተ እዚህ ምን አመጣህ? እጅህስ ምን ሆነ? ሲጮህ የነበረው ማነው?”
“ጌታዬ፣ እኔ እንደ ምስኪን በግ ዝም ብዬ እየሄድኩ ነበር” አለ ክሩይኪን፤ “ይህ የተረገመ ድንገት ጣቴን የነከሰኝ፣ ማንንም ሰው ሆነ አንዳች ነገር ሳልነካ ነው። ይቅርታ ያርጉልኝ፣ ጌታዬ። እኔ የሥራ ሰው ነኝ፤ ለዕለት ጉርሴ የምሠራውም በየቀኑ ነው፡፡ ምናልባት ለሣምንት ይህንን ጣት ልጠቀም ስለማልችል አንድ ሰው ሊከፍለኝ ይገባል። ጌታዬ፣ ከሚናከሱ ውሾች ጋር አብራችሁ ኑሩ የሚል በሕጉ ውስጥ የለም። እንዲናከሱ ከተፈቀደላቸው ደግሞ፣ በሕይወት መኖር ጥቅም የለውም ማለት ነው።”
“እም’ ም! በጣም ጥሩ” አለ፤ ኦቹማዬሎፍ፤ ኮስተር ብሎ ቅንድቡን ከፍና ዝቅ እያደረገ። “እሺ፤ ይህ ውሻ የማነው? ይሄ  በቀላሉ የምተወው ጉዳይ አይደለም፤ ውሾቻችሁን ፈታችሁ መልቀቅ እንደሌለባችሁ እያንዳንዳችሁን አስተምራችኋለሁ! ኃላፊነታቸውን በማይወጡ ሰዎች ላይ  አንድ ነገር የሚደረግበት ወቅት ነው። የዚህን ውሻ ባለቤት እቀጣዋለሁ። ማንነቴን አሳየዋለሁ! ዬልድሪን፣” አለ ወደ ፖሊሱ ዘወር ብሎ፤ “የማን ውሻ እንደሆነ አረጋግጠህ ሪፖርት አቅርብልኝ፤ በአስቸኳይ ይገደላል። ምናልባትም ያበደ ውሻ ይሆናል። ውሻው የማን ነው?”
“የጄነራሉን ውሻ ይመስላል” አለ፤ ከሕዝቡ መሀል አንድ ሰው።
• [፩] • “የጄነራሉ? እም! ዬልድሪን፤ ካፖርቴን አውልቅልኝ። ዛሬ በጣም ይሞቃል።  ምናልባት ይዘንብ ይሆናል ...” አለ ወደ አንጥረኛው ዞሮ::  በመቀጠልም፤ “ክሩይክን --- አንድ ያልገባኝ ነገር አለ። ይሄ ውሻ እንዴት ሊነክስህ ይችላል? እሱ ወደ ጣትህ ከፍ ብሎ ሊወጣ አይችልም። ውሻው በጣም ትንሽ፣ አንተ ደግሞ ግዙፍ ሰው ነህ። ይኼኔ ጣትህን በምስማር መተኸው ይሆናል፤ ገንዘብ አገኛለሁ ብለህ በማሰብ ውሻው ላይ እያላከክ ነው። እናንተን አውቃችኋለሁ እኮ። አጭበርባሪ ወንበዴ ሁላ!”
“የውሻውን ፊት በሲጋራ ሸንቁሮታል፤ ውሻውም ተናዶ የነከሰው በዚህ ምክንያት ነው፣ ጌታዬ!”
“ውሸት ነው! ሳደርገው አላየህም፣ ታዲያ ለምን ትዋሻለህ? ክቡር ጌታዬ፤ ሁሉን የሚያውቅ ሰው ነው። ማንኛችን እውነት ማንኛችን ውሸት እንደምንናገር ያውቃል። ውሸትን ከተናገርኩ፣ ፍርድ ቤቱ ይፍረድብኝ። ሕጉ በዚህ ዘመን ሁላችንም እኩል ነን ይላል። ፖሊስ ጣቢያ የሚሠራ ወንድም አለኝ። ልንገራችሁ ---’
“’ጭቅጭቃችሁን አቁሙ!”
“አይ፣ ይሄ የጄኔራሉ ውሻ አይደለም፣’ አለ ፖሊሱ በጥልቅ እያሰበ፤ “ጄኔራሉ ይህንን የሚመስል ውሻ የላቸውም። የእሳቸው ውሾች ከዚህ የተለዩ ናቸው።”
“ስለምትለው ነገር እርግጠኛ ነህ?”
“አዎን ጌታዬ፣ በደንብ እርግጠኛ ነኝ።’
• [፪] • “እኔም እራሴ አውቄዋለሁ። የጄነራሉ ውሾች ባለ ልዩ ዘር ናቸው፤ ይህ ውሻ ግን በጭራሽ! ጠጉር የለው፣ አቋም የለው። ለምን ሰዎች እንደዚህ አይነት ውሾች እንደሚኖራቸው አይገባኝም! መስኮብ ወይ ፒተስበርግ ከተሞች ውስጥ እንደዚህ አይነት ውሻ ቢገኝ ምን እንደሚደረግበት ታውቃላችሁ? ማንም ስለ ሕጉ ሳይጨነቅ ውሻው ወዲያውኑ ይታነቃል! ክሩይኪን፣ ተበዳዩ አንተ ነህ፤ መከራም ደርሶብሃል። ይህንን ጉዳይ በቀላሉ የምተወው  አይደለም። ባለቤቱን ልክ ማስገባት አለብኝ!”
“ነገር ግን ምናልባት የጄነራሉ ውሻ ሊሆንም ይችላል፣” ፖሊሱ የሚያስበውን እየተናገረ፤ “በቀደም ዕለት ጄነራሉ ግቢ እንደዚህ አይነት ውሻ አይቻለሁ።”
“በእርግጥ የጄኔራሉ ንብረት ነው፣” የሚል አንድ ድምጽ ከተሰበሰበው ሕዝብ ተሰማ።
• [፫] • “ዬልድሪን፤ ካፖርቴን እንድለብስ እርዳኝ። ይበርዳል። ነፋሱ እየበረታ ነው። ብርዱም አንቀጠቀጠኝ። ውሻውን ወደ ጄኔራሉ ጋ ወስደህ እዛው አጣራ። እኔ አግኝቼ እንደላኩትም ንገራቸው። ውሻው ውጭ እንዳይወጣ እንዲጠብቁትም ንገራቸው። ውድ ውሻ ይሆናል፤ ይሄ አሳማ ሁላ በሲጋራ ከሸነቆረው በቅርቡ ይበላሻል። ውሻ እንክብካቤ የሚፈልግ ፍጥረት ነው። ስማ፣ አንተ ደደብ ሰው፣ እጅህን አውርድ! ይሄ የማይረባ ጣትህን ካሁን በኋላ እንዳታሳየኝ። ጥፋቱ የራስህ ነው!”
“ይኸው የጄኔራሉ ወጥ ቤት መጣ። እሱን እንጠይቀው። እንዴት ነህ፤ ፕሮክኾር፣ አንዴ ወደዚህ ትመጣ! ተመልከት፣ ያ ውሻ የእናንተ ነው እንዴ?”
“የምን ውሻ? ... በዘመናችን እንደዚህ አይነት ውሻ  ጭራሽ ኖሮን አያውቅም!”
• [፬] •”እየዞሩ ጥያቄ በመጠየቅ ጊዜ ማባከን አያስፈልግም፣” አለ ኦቹማዬሎፍ፤ “ርጋጭ ውሻ ነው። ከዚህ በላይ ምንም ማለት አያስፈልግም። እኔ ርጋጭ ውሻ ነው ካልኩ፣ ርጋጭ ውሻ ነው! በቃ ይገደላል!”
“የእኛ ውሻ ነው አይደለም፣” ፕሮክኾር ቀጠለ፤ “ነገር ግን የጄነራሉ ወንድም ንብረት ነው፤ በቅርብ ቀን ከመስኮብ ከተማ መጥተዋል። የእኔ ጌታ እንደዚህ አይነት ውሻ አይወዱም፣ ወንድማቸው ግን ይወዳሉ።”
•  [፭] • “እና ወንድማቸው መጥተዋላ?” ጠየቀ ኦቹማዬሎፍ፤ የደስታ ፈገግታም ፊቱን ሞላው። “ይገርማል! እኔ ግን አላወቅሁም! እንደገና የመጡት ለጉብኝት ነው እንዴ?”
“‘አዎን ጌታዬ፤ ለጉብኝት ነው።”
“ደህና፣ ደህና፣ ደህና። እኔ ጭራሽ አላወቅሁም ... እና የእሳቸው ውሻ ነው አልከኝ? በጣም ጥሩ፤ በጣም ደስ ብሎኛል። ውሰደው! የሚያምር ትንሽ ውሻ። ፈጣን ትንሽ ውሻ፣ የዚህን ሰውዬ ጣት ለቀም አደረገችው! ሃ-ሃ-ሃ። ለምን ትንቀጠቀጣለህ? አንተ ውድ ትንሽዬ ነገር! ግርር ... ግርር ... ያንን ተንኮለኛ ሰውዬ።”
ፕሮክኾር ውሻውን ጠራና ከእሱ ጋር ሄደ። የተሰበሰበው ሕዝብ ክሩይኪን ላይ ሳቀበት።
“አንድ ቀን እይዝሃለሁ!” በማለት ኦቹማዬሎፍ ዛተበት፡፡ ከዚያም እራሱን በካፖርቱ እየጠቀለለ የገበያውን ቦታ ማቋረጡን ቀጠለ።


Read 4114 times