Saturday, 20 July 2019 12:31

እያሽቆለቆለ የመጣው የህክምና ዘርፍ የትምህርት ጥራት? የህክምና ሥርዓት? የሃኪሞች ተግዳሮት?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ዶ/ር ገመቺስ ማሞ በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ባለፈው ሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ምሽት “የኢትዮጵያ ዶክተሮች ቀን”ን፤ ለሁለተኛ ጊዜ፣ በራስ ሆቴል፣ በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች አክብሯል - “አልመው፣ አግኘው፣ ውደደው (Dream it, Find it, Love it”) በሚል መርህ፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የታደመችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በማህበሩ እንቅስቃሴ፣ በአገሪቱ የህክምናው ዘርፍ ችግሮች፣ በሚያዚያ 26ቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የጤና ባለሙያዎች ውይይት፣ በሃኪሞች ተግዳሮቶችና በህክምና ሥርዓቱ ዙሪያ
--- ከዶ/ር ገመቺስ ማሞ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡


      የኢትዮጵያ ህክምና ማህበርን በፕሬዚዳንትነት መምራት የጀመሩት መቼ ነው? ሃላፊነት ከያዙ ጀምሮ ያከናወኗቸውን ጉልህ ሥራዎች ቢጠቅሱልኝ?
በፕሬዚዳንትነት ከተመረጥኩኝ አምስተኛ ዓመቴ ነው:: በሚቀጥለው ዓመት ስልጣን አስረክባለሁ፡፡ በማህበሩ ማገልገል ከጀመርኩኝ ግን ረጅም ዓመት ሆኖኛል፡፡ ከፕሬዚዳንትነቴ በፊት በፀሐፊነት ለሶስት ዓመት፣ ቀጥሎ በዋና ስራ አስፈፃሚ አባልነት ለሁለት ዓመት፤ በድምሩ ለ5 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ በነዚህ የኃላፊነት ጊዜያት፣ በርካታ ስራዎችን ከአጋሮቼ ጋር በመሆን አከናውነናል:: የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር እንደሚታወቀው፣ የ57 ዓመት ዕድሜ ያለው አንጋፋ ማህበር ነው፡፡ በጎ ፈቃደኛ በሆኑ ስራ አስፈፃሚዎች የሚመራ ነው፡፡ በመጀመሪያ በፀሐፊነት በተመረጥኩበት ጊዜ የነበረው ቡድን ትልቅ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በታሪካችን እምርታዊ ለውጥ ያመጣንበት ወቅት ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ሴክሬታሪያት እንዲቋቋም፣ የራሱ የሆነ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር እንዲኖረው፣ የቢሮ ሰራተኞች እንዲቀጠሩ፣ ፕሮጀክቶች እንዲቀረፁ፣ እነዚያ ፕሮጀክቶችን አሸንፎ ተጨማሪ ጥናትና ምርምሮች መስራት እንዲችል የሚሉትን የፈጠርንበትና የሰራንበት ወቅት ነበር፡፡ ያ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡
በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነቴ ወቅት ደግሞ እነዚሁ ነገሮች እንዲቀጥሉና አቅሙ እንዲያድግ ጥረናል:: ፕሬዚዳንት ሆኜ ከተመረጥኩ በኋላ እንደ የትኛውም የሙያ ማህበር፣ የእኛም ማህበር ከፍታና ዝቅታዎች ነበሩት፡፡ ምናልባት እኔ ፕሬዚዳንት ሆኜ ስመረጥ፣ ማህበራችን በአባላት ብዛት በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ነበር፡፡ የአባላቱን ቁጥር ለማስተካከል፣ የአባላት ጉዳይን ግንባር ቀደም ሥራችን በማድረግ፣ ቆርጠን ተነስተን ነበር፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት አምስት አመታት ባደረግነው እንቅስቃሴ ተሳክቶልናል ብለን እናስባለን፡፡
ለምን ነበር የአባላት ቁጥር ያሽቆለቆለው?
ድሮ ሀኪም በተመረቀ ጊዜ ወዲያውኑ የማህበሩ አባል ይሆን ነበር፡፡ ምክንያቱም የሀኪሞችም ቁጥር ትንሽ ነበር፡፡ በደርግ ዘመን፣ የህክምና ማህበሩ “የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች አንድነት ማህበር” በሚባለው ስር ራሱን የቻለ ሆኖ በተደራጀበት ጊዜም፣ በአገሪቱ ከነበሩት ሶስቱም የህክምና ኮሌጆች የሚመረቅ ሀኪም ወዲያውኑ የማህበሩ አባል ይሆንና የአባልነት ክፍያው ከደሞዙ ላይ ይቆረጥ ነበር፡፡ ስለዚህ እስከ 2ሺህ እና 2ሺህ 500 ሀኪሞች በነበሩበት ጊዜ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር አባላት ነበሩ፡፡ ይሄ እስከ መንግስት ለውጥ ድረስ ይዘልቃል፡፡ እንደገና በአዲስ መልክ በሚዋቀርበት ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡
ምን ዓይነት ጥያቄዎች?
የኢትዮጵያ ሀኪሞች የኢኮኖሚ ጥያቄ የዚያን ጊዜ ነው የጀመረው፡፡ የኢኮኖሚው ጥያቄ ትንሽ የበረታበት ሰሞን ስለነበረና ይህን ጥያቄ መንግስት በወቅቱ መመለስ ባለመቻሉ፣ ሀኪሞች ከአገር ይወጡ ነበር፡፡ የሀኪሞች ፍልሰት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑም የተነሳ፣ በአንድ ወቅት አገሪቱ ውስጥ ያለው የሀኪም ቁጥር በጣም አንሶ ነበር፡፡ እንደውም በዚያን ጊዜ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ቁጥር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ጠቅላላ ሀኪሞች ቁጥር ይበልጣል ይባል ነበር፡፡ እዚያ ደረጃ ሲደርስ መንግስት ሁለት ዓይነት እርምጃዎች ወሰደ:: ይኸውም በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀኪም ማስተማሪያ ኮሌጆችን ቁጥር ማብዛትና የሀኪም ቅበላን ቁጥር ማሳደግ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በዚያን ጊዜ ከነበሩት ኮሌጆች (አራት ወይም አምስት ነበሩ መሰለኝ) የሚመረቁትን ሀኪሞች ፈቃድና ዲግሪ መያዝ ነው፡፡ ያንን ፈቃድና ዲግሪ ለማግኘት የሚከፍሉትን ኮስት ሼሪንግ (ወጪ መጋራት) መጠኑን ከፍ በማድረግም እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር አደረሰው:: ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚህ ነገር ውስጥ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ወይ ተሳትፏል አሊያም በሚገባው መጠን አልተቃወመም በማለት የነበሩት ወጣት ሀኪሞች በሙሉ ለእኛ ማህበር መጥፎ አመለካከት እንዲኖራቸው አደረገ:: ሁለተኛው ነገር፤ በዚያው በ80ዎቹ ውስጥ የስፔሻሊቲ ማህበራት በየሙያቸው እየተደራጁ መጡ፡፡ ለምሳሌ የማህፀን፣ የሰርጂካል ስፔሻሊስቶችና ሌሎችም ማህበራት በየራሳቸው ተደራጁ፡፡ በእኛ አገር ደንብ ደግሞ ማህበር ስታቋቁሚ፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ህጋዊ ሰውነቱ እኩል ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም በየሙያቸው ሲደራጁ፣ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበርን አባላት ቁጥር በጣም እያወረደው መጣ ማለት ነው፡፡ ይህንን ለመቀየር ከፍተኛ ሥራ መስራት ነበረብን:: ባደረግነው ጥረትም የአባላትን ቁጥር ወደ 4ሺህ ከፍ ማድረግ ከመቻላችንም በተጨማሪ በዘጠኝ ቦታዎች ላይ ቅርንጫፍ ማህበራትን አቋቁመናል፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ፤ በጅማ፣ አዳማና ሃረር፣ በትግራይ፤ በመቀሌ፣ በአማራ፤ በደሴ፣ ጎንደርና ባህር ዳር፣ በደቡብም እንዲሁ በሀዋሳና በአርባምንጭ ነው ቅርንጫፎቻችን የሚገኙት:: ራሳቸውን የቻሉ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያላቸው ቅርንጫፍ ማህበራት ጽ/ቤቶች ናቸው፡፡
እስቲ ሰኔ 25 ስላከበራችሁት “የዶክተሮች ቀን” ጥቂት ይንገሩኝ ---
በዓለም አቀፍ ደረጃ የዶክተሮች ቀን በየአገሩ ይከበራል፡፡ እኛም እንደ ሀኪሞች፣ የራሳችን ቀን እንዲኖረን አስበን ማክበር ጀምረናል፡፡ ነገር ግን መንግስት በተለይም ጉዳዩ የሚመለከተው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ምን እንደሚል አናውቅም፡፡ እኛ ሰኔ 25ን የሃኪሞች ቀን ብለን ሰይመናል፡፡ ጤና ጥበቃ ሁሉንም ባለሙያ ሰብሰብ አድርጎ “የጤና ባለሙያዎች ቀን” ወይም ሌላ ሊለው ይችላል፤ ነገር ግን ጉዳዩ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሲነሳ የቆየ ነው:: በአጠቃላይ ግን በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች ቀን ያስፈልጋል ብለን ያነሳነው በኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በኩል ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበሩ የጤና ባለሙያዎች ቀናት አሉ:: ለምሳሌ፡- ዓለም አቀፍ የአዋላጆች ቀን፣ ዓለም አቀፍ የነርሶች ቀን ይከበራሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ፣ ቀኑ እንደ ቀን መከበር አለበት ተብሎ በአዋጅ የፀደቀ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ግን የዕውቅና ደብዳቤ አስገብተናል፡፡
ህብረተሰቡ ለሀኪሞች የነበረው በጐ አመለካከትና ክብር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ እርስዎ እንደ ሃኪምነትዎ፣ ለዚህ ምክንያቱ ምን ይመስልዎታል?
አንደኛ ቁጥራችን በዝቷል፤ አገልግሎቱም ሰፍቷል:: ተገልጋዩም እየተማረና እያወቀ መጥቷል:: ምን ያህል አገልግሎት እንደሚጠብቅ ያውቀዋል:: በሌላው አንፃር ስታይው፣ ባለፉት 20 ዓመታት ህብረተሰቡ ለሀኪም ያለው አመለካከት እንዲቀየር ሆኗል፡፡
በምንድነው እንዲቀየር የተደረገው?
ቅድም ያልኩሽ ነገር አለ፡፡ የሀኪም እጥረት የፈጠረው ብዛትን የመምረጥ ሁኔታ አለ፡፡ ይሄ ብዛትን የመምረጥ ሁኔታ፣ ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ ጎድቶታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ አንዱ ነው፡፡ ያኔ ትንሽ ቁጥር ያላቸው ዶክተሮች ነበሩ፤ ፈልገሽ ነው የምታገኚያቸው:: የዶክተሮቹም የትምህርት ሁኔታ ጥሩ ነበር፤ ጥራቱም ላይ ችግር አልነበረም:: በሌላ በኩል፣ አሁን ያለው ጠያቂ ትውልድ ነው፡፡ እኩል የሚማርና የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያገኘው አገልግሎት ላይ የሚያየውን ክፍተት አያልፍም፡፡ የሐኪም የእውቀት ጥራት ማነስ ደግሞ የአገልግሎቱ ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲወርድ ያደርገዋል:: በዛ ላይ የአገልግሎት ግብአቶች አለመሟላት ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ የዚያኑ ያህልም ህብረተሰቡ ይጠይቃል:: ለምንድነው ይሄ አገልግሎት የሚጎድልብኝ? ለምንድነው ያኛው የቀረብኝ? እያለ ይጠይቃል፡፡ በህክምና ሥርዓቱ ላይ ላለው ችግር በሙሉ ተጠያቂ የሚደረገው ደግሞ ሀኪሙ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት ሳያገኝ ሲቀር፣ ችግሩ የሀኪሙ ነው የሚለው ነገር መጣ፡፡ ሀኪሙ ደግሞ በበቂ ሁኔታ ትምህርት እንዳያገኝ መንግስት የያዘው የማጥለቅለቅ ዘመቻና ስትራቴጂ አዳከመው፡፡ ስለዚህ ሀኪሙ በአንድ በኩል፣ በትምህርት በደንብ ያለመታነጽ ችግር አለበት፡፡ በሌላ በኩል፣ የሥርዓቱ ማነቆነትና የአገልግሎት ግብአት አለመሟላት፣ የአገልግሎት ጥራት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድርበታል፡፡ ግን ለሁሉ ነገር ተጠያቂ የሚሆነው ሀኪሙ ስለሆነ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ክብርና አመኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጣ፡፡
ስለዚህ ማህበረሰቡ “እዚህ አገር ምን ህክምና አለ!” ቢል አይፈረድበትም ማለት ነው?
አዎ! እኛ እንደ ማህበርም ስናነሳ የነበረው ግን ነገሩን ለያይተን ማየት እንዳለብን ነው፡፡ ነገሩን ሁሉ ሀኪም ላይ መጫን የለብንም፤ ነገሩን ድፍን አድርገን ካየነው ልክ አይመጣም፡፡ መንግስት እንደ ስትራቴጂ፣ መከላከልን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ላይ ትኩረት በማድረጉ፤ የማከም አገልግሎትን (“ኪዩሬሲቭ ሰርቪስ”ን) ረስቶት ቆይቷል:: እውነት መከላከልን መሰረት ያደረገው ፖሊሲ የሚፈለገውን ውጤት አምጥቷል ወይ? የሚለውም ሌላ ጥናት የሚፈልግ ጥያቄ ነው፡፡
ዋናው ነገር ግን የማከም አገልግሎቱ ሞቷል:: አሁን በየሆስፒታሉ ብትሄጂ፣ ሆስፒታል በሚያሰኛቸው ደረጃ ላይ ናቸው ወይ? አገልግሎታቸውስ ጥራት አለው ወይ? ብትይ፣ ይሄ ራሱ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል:: በህንፃ ደረጃ በእርግጥ ብዙ ተገንብቷል፡፡ በየክፍለ ከተማው 8 ያህል ጤና ጣቢያ ታገኛለሽ፡፡ ግን በነዚህ ጤና ጣቢያዎች የሚሰጠው አገልግሎት ትክክለኛ ነው ወይ? ብቁስ ነው ወይ? በአዲስ አበባ ባሉ ሆስፒታሎች እየዞርሽ አገልግሎቱ ጥራት አለው ወይ? ብለሽ ብትጠይቂ… ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ሀኪሙ በአብዛኛው ያለው የህክምና አገልግሎቱ ላይ ነው:: ማከም ነው ስራው፡፡ ለማከምና ለመመርመር ታካሚን “ጓንት ገዝተህ ና” ብለሽ የምታዢ ከሆነ፤ እውነት ጥራት ያለው ህክምና እየተሰጠ ነው ወይ? የአገልግሎት ጥራት ወርዷል፡፡ ከዚያም ባስ ሲል ከኦፕሬሽን በኋላ “የመስፊያ ክር አምጣ” የምትይ ከሆነ፣ ጥራቱ ወርዷል፤ ይሄ ማሳያው ነው፡፡ ህብረተሰቡ ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂ የሚያደርገው ግን ሀኪሙን ነው፡፡
መንግስት በራሱ ችግር ህብረተሰቡ ለሀኪሞች የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው እያደረገ ነው እያሉኝ ነው?
በትክክል!
ሚያዚያ 26 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት? እንደ ማህበርስ እንዴት ገመገማችሁት? … ብዙ የጤና ባለሙያዎች የተከፉበት መድረክ እንደነበር ይነገራል ---
የሚያዚያ 26ቱን ስብሰባ ምን አመጣው ከሚለው ብንጀምር የተሻለ ነው፡፡ ስብሰባው እውነት እንደተባለው የታቀደ ነው? እኛ እንደ ማህበር፣ የታቀደ ስብሰባ አይደለም ብለን ነው የምናምነው፡፡ ለምን? የታቀደ ስብሰባ ምን ውጤት እንደሚፈለግ፣ ምን ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ሰዎች ተነጋግረውበት ነው የሚደረገው፡፡ ጥሩ ነበር ወይ? ከተባለ፣ አዎ ጥሩ ነበር፡፡ የጤና ባለሙያውን ጠርቶ ማነጋገር በራሱ ጥሩ ነው። ግን ውይይቱ የታቀደ አልነበረም፡፡ ታዲያ ምን አመጣው ውይይቱን? ብለን ወደ ኋላ ብንሄድ፤ የመጀመሪያው የጅማ ኢንተርን ጉዳይ ነው:: ጅማ ላይ በዲዩቲ ላይ የነበሩት ኢንተርኖች በታካሚ ተደበደቡ፡፡ በታካሚ መደብደብን በተመለከተ የጅማው የመጀመሪያ አይደለም፡፡ በየቦታው የሚደረግ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን የጅማ ኢንተርኖች “ለራሳችን ስለምንፈራ ስራ እናቆማለን” አሉ፡፡ የእነሱን አድማ ተከትሎ የአርሲ ኢንተርኖች “እነዚህ ልጆች ያነሱት ጥያቄ ትክክል ነው፤ እኛም እነሱን እንደግፋለን” ብለው ከዶርማቸው ወደ ዳይሬክተሩ ቢሮ ሲሄዱ፣ በኦሮሚያ ፖሊስ ተደበደቡና ነገሩን አጋጋለው፡፡ ከነዚህ በፊት ደግሞ ምን ነበረ መሰለሽ? የግል ሜዲካል ኮሌጆች በተለይ “አያቶች” ትምህርት ጨርሰው ድሮ ይደረግ የነበረውን ምደባ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አልመድብም አለ፡፡ ሰላማዊ ሰልፍም ተደርጓል:: እነሱን ብቻም ሳይሆን ወደ ኢንተርንሽፕ የሚገቡትንም ሀኪሞች፤ በመንግስት የጤና ድርጅቶች አታገለግሉም፤ ገንዘብም አልከፍልም አለ:: እነዚህ ነገሮች ተደራረቡ:: ይህን የተባሉት ወጣት ሀኪሞች ናቸው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው አማካኝነት ግንኙነቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ፈጠሩ፡፡ በዚያው ጊዜ በአማራ ክልል የተመደቡ 25 ሀኪሞችን ክልሉ የምቀጥርበት ገንዘብ የለኝም ብሎ መለሰ:: ይህንን ስናጣራ “የመጀመሪያው አይደለም፤ የሚመደቡ ልጆች በጀት የለም እየተባሉኮ ይመለሳሉ” የሚል ነገር ሰማንና፣ ይህንኑ ጉዳይ ይዘን እንደ ማህበር፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ጋር ስንነጋገር፣ “አይ ወደፊት የሚመረቁት 450 ሀኪሞችንም መመደቢያ ቦታም በጀትም ስለሌለን ስራ ፈልጋችሁ ግቡ  ማለት ጀምረናል” አሉን፡፡ ይቺ ነገር ተሰማች፡፡ ይህን ሲሰሙ ኢንተርንሽፕ ላይ ያሉ ልጆች ተስፋ ቆረጡ፡፡
ድሮ ተመርቀሽ ስራ እንደምታገኚ እርግጠኛ ነሽ። ከሌላውም ሙያ የበለጠ ህክምናን የሚያስመርጠው ይሄ ይመስለኛል፡፡ የስራ ዋስትናው ነበር ሙያውን የሚያስመርጣቸው፡፡ አሁን ስራም ተስፋም ሲጠፋ፣ ልጆቹ የስራ ማቆም አድማ አደረጉ፡፡ ሬዚደንት ሀኪሞችም ይሄን ተቀበሉና “ልጆቹ ትክክል ናቸው፤ ህጋዊ ጥያቄ ነው የጠየቁት፡፡ እነሱ በስራ ላይ ካልሆኑ ስራው ሙሉ ለሙሉ እኛው ላይ ስለሚጫን በስራውም በጥራቱም ላይ ጫና ያሳድራል” በማለት ድጋፍ ሰጡ፡፡
በነገራችን ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዚያን ጊዜ ምላሽ የሰጡባቸው ጥያቄዎች፤ እኛ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን የጨረስናቸው ናቸው:: አራት ወራት ሙሉ ከስብሰባው በፊት ከጤና ጥበቃ ሰዎች ጋር ተነጋግረንበታል፡፡ እኛ ይሄ ስብሰባ  ሲጠራ እንደ ማህበር የምናነሳቸው፣ ትልልቅ የዘርፉ ሀገራዊ ጉዳዮች እንዳሉ፣ ከክቡር ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን ጋር ተነጋግረናል:: እነዚህን ጥያቄዎች ለማቅረብ እድል የምናገኝ ከሆነ እንሳተፍ፣ እድል የማናገኝ ከሆነ ግን እንዲያው ዝም ብሎ በአቦ ሰጡኝ የሚሰጥ ዕድል ላይ መሳተፍ ትክክል አይደለም ብለን ተነጋግረን፣ እድሉ እንዲሰጣችሁ ይደረጋል ተብለን ነው የሄድነው፡፡ እኛ ከስብሰባው በፊት የስፔሻሊቲ ማህበረሰብን፤ አጠቃላይ መሪዎችን ሰብስበን ምን ምን ጥያቄ ማንሳት አለብን ብለን ተነጋግረን፣ የአቋም መግለጫ ይዘን ነው የታደምነው፡፡ እድል ባናገኝ እንኳን ብለን፣ ጥያቄያችንንና የአቋም መግለጫችንን ከስብሰባው አንድ ቀን በፊት በፋክስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ልከን ነበር፡፡ ወደ ስብሰባው የገባነው ማን ምን ይጠይቃል ተባብለን ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አንዳችንም እድል አላገኘንም:: እድል ባገኙት ግለሰቦች የተነሱት ጥያቄዎች ደሞ የሰማሻቸው ናቸው፡፡
ስለዚህ በውይይቱ  የዘርፉ መሰረታዊ ጥያቄዎች አልተነሱም ባይ ነዎት?
አዎ! የዘርፉ ዋናው ጥያቄ ያለው የጤና ሥርዓቱ (ሲስተሙ) ላይ ነው፡፡ ይሄ አልተነሳም፡፡ የጤና ሲስተሙ መታየትና መፈተሽ አለበት፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩሽ፣ ሀኪም እናብዛ ተብሎ የትምህርት ጥራቱ ወርዷል:: አሁን ደግሞ ጎርፍ አድርገነዋል:: በሚቀጥለው ዓመት የሚመረቁት 3ሺህ ሀኪሞች የሚቀጠሩበት ቦታ የለም:: የት እንደሚገቡም አናውቅም፡፡ አሁን ከእሳቸው ውሳኔ በኋላ ለሚመረቁት ሀኪሞች በሙሉ “ስራ ፈልጋችሁ ግቡ” እየተባሉ ዲግሪያቸው እየተሰጣቸው ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከተነጋገርን በኋላ ማለት ነው፡፡ ከእርሳቸው ጋር ስንነጋገር 3800ዎቹን እንቀጥራለን ተብሎ ነበር:: ከጤና ጥበቃም ጋር በነበረን ንግግር፣ ከእንግዲህ ሁሉንም እንቀጥራለን ነው ያሉን፡፡ እስከ ዛሬ ከግል ኮሌጅ የተመረቁት ሀኪሞች ስራ አላገኙም:: ስለዚህ የሚያዚያ 26ቱ ስብሰባ ያልታቀደ፣ መሰረታዊ የጤና ዘርፍ ችግሮች ያልተነሱበትና ዶ/ር ዐቢይም በጤና ባለሙያው ላይ የተዛባ ግምት ያሳደሩበት ይመስለኛል፡፡ በዕለቱ የተነሱት ተቋማዊ ጥያቄዎች ቢሆኑ፣ ለመመለስም ቀላል ይሆን ነበር፡፡ እኛም እንደ ማህበር የምናነሳቸው ጥያቄዎች፣ ከግለሰብ ጥያቄ የተለዩ እንዲሆኑ ነበር የተነጋገርነው፡፡ እኛ ከአንድ ዓመት በፊት ለጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ጥያቄያችንን አቅርበናል፡፡ ጥያቄዎቹን ስንደረድራቸው የግለሰብ ጥያቄዎች መጨረሻ ላይ ነው የሚመጡት፡፡ እንደ አገር በህክምና ትምህርቱ፣ በህክምና አገልግሎቱ፣ በህክምና ሥነ ምግባሩ፣ የግሉን ዘርፍ በተመለከተ፣ የህክምና ኢንሹራንሱን በተመለከተ ምን መደረግ አለበት … የሚሉትን ከደረደርን በኋላ ነው የሀኪሙን የመብት ጥያቄ ያነሳነው? ግን ግብረሃይሉም ላይ ጥያቄ አንስተናል፡፡ ግብረሃይሉን ለመመስረት ጥያቄውን ያነሳው ሀኪሙ ስለሆነ፣ ማህበሩን ያልያዘ ግብረ ኃይል ውጤታማ አይሆንም ብለን ነበር፡፡
በግብረ ኃይሉ ውስጥ የማህበራችሁ ተወካይ አልተካተተም ነበር?
ግብረ ኃይሉ የተመረጠው ከዩኒቨርሲቲዎች ነው:: እኛ ተወካይ የለንም፡፡ መጨረሻ ላይ ለስብሰባ ስንጠራ “እኛ ያልተሳተፍንበት ሀኪሙን ይወክላል ብለን አናምንም” ብለን አቋማችንን አሳወቅን፤ ግን ግብረ ኃይሉ የሰራው ስራ ላይ አስተያየት እንድንሰጥ ወደኛው ነው ያመጡት፡፡ እኛም እንደገና ኮሚቴ አዋቅረን፣ ዶክሜንቶቹን አጥንተን መልሳችንን ሰጥተናል፡፡ ምክንያቱም ይሄ የአገር ጉዳይ ስለሆነ ወደ ኋላ የምንለው አይደለም፡፡  
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ፋክስ ያደረጋችሁት ጥያቄና የአቋም መግለጫስ?
በፍፁም ምላሽ አላገኘም፡፡ ብቻ ባጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሀኪሞች በአንድ አቅጣጫ የታየና የተዛባ መረጃ ደርሷቸዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ለምን? በዚያ ስብሰባ ላይ የሲኒየሩንም የጁኒየሩንም ህሊና የሚነካና የሚያስከፋ ንግግር ተናግረዋል፡፡ ተከፍተናል፡፡
ለምሳሌ?
አሁን ለምሳሌ ሀኪምና ህክምና ኢትዮጵያ ውስጥ የት አለ? የሚል ነገር ተናግረዋል፡፡ ግን እውነት እዚህች አገር ውስጥ ሀኪም አልነበረም ወይ? ህክምናስ አይሰጥም ነበር ወይ? እንላለን:: ማንኛውም ሰው ወይም ተራው ህዝብ ይህን ቢናገር እሺ፣ ግን መራሄ መንግስት ሆነሽ ስትናገሪ፣ አንድም ከዛ በፊት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሀኪሞች የሰጡትን አገልግሎት ገደል እንደ መክተት ነው፡፡ ሁለትም፣ እንደ አገር ራስሽን ጥያቄ ውስጥ መክተትሽ ነው:: ህክምና የለም የምንል ከሆነ፣ መንግስትስ ነበር ወይ የሚል ጥያቄ ይመጣል፡፡ ህክምና የለም ከተባለ ተጠያቂው መንግስትና ሥርዓቱ ነው፡፡ ግለሰቡ አይደለም፡፡ ሲስተም የለም ማለት ነው፡፡ እኛም ስንል የነበረው ሲስተሙ ወድቋል ነው፡፡ ያ በጣም አስከፍቶናል፡፡ ሌላው የጎዳን “የመኪና ሱስ ከሆነ አንድ መኪና ለአምስት ትጠቀማላችሁ” ማለታቸው ነው፡፡ ይሄ ለእኛ ወረደብን፤ እውነት የእኛ ጥያቄ የመኪና ሱስ ነው? ይሄ ሁሉ ሀኪሙን አስከፍቶታል::
እኛ እንደ ማህበርም ጥያቄያችን ከዘር፣ ከሀይማኖት የፀዳና ፖለቲካዊ ይዘትና ሃሳብ የሌለው ነው፡፡ ስራችንም ዘር ቀለምና ሃይማኖት፣ ወንዝና ተራራ ወይም ብሄርን ያማከለ አይደለም፡፡ አገልግሎት የምንሰጠው ለሰው ልጆች በሙሉ ነው:: ሀኪም ዘርና ሃይማኖት፣ ብሔርና ክልል የለውም:: ይሄ የሁልጊዜም መፈክራችን ነው፡፡ ማህበራችን ፖለቲካ ውስጥ የለበትም፡፡ ሙያውን ለሁሉም የሰው ልጅ ያለ አድልኦ የሚሰጡ፣ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር ነው፡፡
የስራ ማቆም አድማ ከማይፈቀድላቸው ውስጥ የህክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ ስራቸው የነፍስ ማዳን ጉዳይ ስለሆነ የስራ ማቆም አድማ እንደማይፈቀድላቸውና ጥያቄያቸውን ስራ እየሰሩ ማቅረብ እንዳለባቸው በአዋጅ የተቀመጠ ነገር አለ፡፡ የሃኪሞቹን የስራ ማቆም አድማ እርስዎ እንደ ሀኪም እንዴት አዩት?
ትክክል ነው! የስራ ማቆም አድማ ከማይፈቀድላቸው መካከል የህክምናው ዘርፍ ይገኝበታል፡፡ ሀኪም ስራ ማቆም አይችልም፤ አዋጁን ይጣረሳል፡፡ የእኛም ማህበር የስራ ማቆም አድማን አይደግፍም፡፡ ማህበራችን የማይደግፈው ግን አዋጁን ስለሚፃረር ብቻ አይደለም፤ የስራ ማቆም አድማ ለሃኪም አግባብ አይደለም፤ ምክንያቱም ከአዋጁ በላይ ህሊናችን ይከለክለናል፡፡ ታካሚዎቻችን በእኛ ስራ ላይ አለመገኘት ህይወታቸው ሲያልፍ፣ ከአለማዊ ዳኝነቱ በላይ የህሊና ዳኝነቱ ከባድ ነው:: ስለዚህ የስራ ማቆም አድማን አንደግፈውም፡፡ እኛ ጥያቄያችንን አገልግሎት ሳናቋርጥ፣ በህጋዊ መንገድ ነው የምናቀርበው በሚለው ላይ ልዩነት አለን፡፡
እስኪ እውነቱን እንነጋገር … ሃኪሞች እንደሚባለው “ድሃ” ናቸው?
  አዎ ድሃ ናቸው!
አንድ ስፔሻሊስት ሀኪም በሚሰራበት የግል ሆስፒታል ውስጥ ለማግኘት ስንትና ስንት ቀጠሮ ተይዞ፤ ሲገኝም ወገብ የሚያጎብጥ ክፍያ ተከፍሎ ነው ይባላል፡፡ ከዚህ አንፃር “ድሃ ናቸው” ሲባል ለብዙዎች አይዋጥላቸውም …
ቆይ የእኔን በምሳሌነት ለምን አልነግርሽም? እኔ ስፔሻሊስት ሆኜ መስራት ከመጀመሬና ገና ለስፔሻላይዜሽን ሬዚደንት ሆኜ መማር ስጀምር፣ የእኔም የባለቤቴም ደሞዝ ስድስት መቶ ከምናምን ነበር፡፡ የሁለታችን ተደምሮ እንግዲህ 1 ሺህ ምናምን ነበር፡፡ አንዲት ልጅ ነበረችን። ደህና ቤት መከራየት ስለማንችል ራቅ ያለ ቦታ ረከስ ባለ ብር ነበር የምንከራየው፡፡ የትራንስፖርት ወጪ አለ፤ ልጃችንን ት/ቤት አስገብተን፣ እኛ ስራ መሄድ ነበረብን፡፡ በዚያች ደሞዝ መኖር ስላቃተን እናምፅ ነበር፤ ማመፅ ስንጀምር ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ መኖሪያ ቤት ተፈቀደልን፡፡ ደሞዛችን 681 ብር ነበር፤ ግን ቢያንስ የቤት ኪራይ ቀነሰልን፡፡ አሁን ደግሞ አንድ ጠቅላላ ሀኪም ተመርቆ የሚያገኘው 4ሺህ ምናምን ብር ነው፡፡ በ4200 ብር ቤት ተከራይቶ፣ ምግብ በልቶ ሸሚዝ ቀይሮ፣ በትራንስፖርት ሄዶ አክም እየተባለ ነው፡፡ ስለዚህ ይሔ ጠቅላላ ሀኪም ሸሚዝ የመቀየር አቅም የለውም፡፡ እያንዳንዳቸውን ብትጠይቂያቸው ይነግሩሻል፡፡ ምናልባት ዲዩቲ ያድራሉ፤ ግን ያ ደግሞ በቀን ስራው ላይ ጫና ይፈጥራል፤ እንቅልፍ ይታገለዋል፤ ይህንን ሁሉ አልፎ ሬዚደንስ የገባ ስፔሻሊስት ተመርቆ ሲወጣ የሚከፈለውና እጁ ላይ የሚደርሰው 9 ሺህ ብር ነው፡፡ ስፔሻሊስት ሆኖ ማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት ምን ማለት መሰለሽ፤ 21 ዓመት ከተማረ በኋላ ነው፡፡ 9ሺህ ብር ማግኘት ሲጀምር ቤተሰብ መስርቷል፣ ልጅ ወልዷል፤ ልጆቹን ማስተማር፣ ባለቤቱን መንከባከብ ይኖርበታል፡፡  ከተመረቀ በኋላ ከጥቁር አንበሳ መኖሪያ ቤቱ መውጣት አለበት፤ ወጥቶ ይከራያል:: የቤት ኪራዩን፣ የትራንስፖርት ወጪውን ማሰብ ነው፡፡ የግል ክሊኒክ ወይም ሆስፒታል መቀጠር አይችልም፤ሁለት ቦታ መቀጠር ስለማይቻል፡፡ ግፋ ቢል ዲዩቲ ቢያድር ነው፤ ያለበለዚያ ታካሚ ህመምተኛ ሊኖረው ይገባል፡፡ ታካሚ እንዲኖረው ደሞ መታወቅ አለበት፤ለመታወቅ ጊዜ ይፈጃል:: ይሄ ሁሉ ፈተና አለበት፡፡ ሀኪም ተፈልጎ አይገኝም የምትይው፣ የብዙ ዓመት ልምድ ያካበተውንና ዕውቅና ያተረፈውን ሀኪም ነው፡፡ በተረፈ ግን ሀኪም በደንብ ደሃ ነው፡፡ እስኪታወቅ ድረስ ያ ልጅ ይጎብጣል፡፡ አዎ፤ሀኪም ደሃ ነው የምለው ለዚያ ነው:: ስለዚህ ማህበረሰቡ፣ መንግስት ሚዲያው፤ሀኪሙን እንዲረዳው እፈልጋለሁ፡፡ ሀኪም፤ የማህበረሰቡ አካል ነውና ልናዝንለትና ልንረዳው ይገባል እላለሁ፡፡Read 1861 times