Saturday, 03 August 2019 13:34

የተማሪዎቹ ታሪክ - በጡዘት ምህዋር

Written by 
Rate this item
(11 votes)


               (በዶ.ር ኤርሲዶ ሌንደቦ የተዘጋጀውና፣ “ኑሮMap” የተሰኘው የለውጥ መፅሐፍ ውስጥ የሰፈረ ትልቅ ታሪክ መዝዘን እንድንመለከት ወደድን፡፡ ከዓመታት በፊት የአገራችንን ችግር የተነበየና መፍትሔውንም ያሳየ ግሩም መጽሐፍ ነው፡፡)
አሳሳቢነቱ የጎላ ትልቅ የአገራችን ችግር፤ ለ”ጡዘት ምህዋር” ሁነኛ ማሳያ ይሆናል - በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከሰት የመቧደን ረብሻና ግጭት (በብሔር ተወላጅነት፤ አልፎ አልፎም በሀይማኖት ተከታይነት)፡፡
ሐጎስና ኤርሲዶ የሚባሉ ሁለት ተማሪዎች ራሳቸው በፈጠሩት አለመግባባት ተጋጩ፤ ተደባደቡ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኤርሲዶ ሐጎስን ጎድቶታል፡፡ ሁለቱ ሲደባደቡ ያገላገለው ተማሪ ባይሳ ነው፡፡ ሐጎስ፤ “ባይሳ ሲገላግል አስመትቶኛል” ብሏል፡፡
የተደባዳቢዎቹንና የገላጋዩን ቃል እንዲቀበል፣ በቅርቡ ከጎጃም የመጣው ፖሊስ ተጫኔ ተመድቧል - በካምፓሱ ፖሊስ፡፡ የተማሪዎች ዲን መሃመድ አሚን፣ ተማሪዎቹን ወደ ክሊኒክ ይዞ ሲሄድ፤ በሶማሌ ክልል የተዋወቃትን ሲስተር ንግስቲን አነጋግሯታል፡፡ ነርሷ፤ ለህክምና የመጡትን ተደባዳቢዎች ተቀብላለች - ሐጎስን ቀድማ በማስተናገድ፡፡
ይህ ተራ የአምባጓሮ ታሪክ፣ በጡዘት ምህዋር በ(escalation) እንዴት እንደሚቀጣጠል ገምቱ።
ሐጎስና ኤርሲዶ፤ “እናፈቅራታለን” በሚሏት አንዲት የሀይስኩል ተማሪ ሰበብ ነው፤ 11 ሰአት ላይ ከካምፓስ ውጪ የተደባደቡት።
በእራት ሰአት ካምፓስ ውስጥ የተወራውስ?
“ሐጎስና ኤርሲዶ ተደባደቡ” መባሉ ቀርቶ፤ “ትግሬና ሀዲያ ተጣሉ” ወይም “ትግራይና ደቡብ ተጋጩ” ተባለ። በብሔር ተወላጅነት መቧደን ለሚፈልጉ ቀሽም ተማሪዎች፤ ሰበብ ይሆናቸዋል - “የትግራይ ልጆች” እና “የሃዲያ የደቡብ ልጆች” በሚል አቧድነው ለመተጋተግ ይመኛሉ!
ገላጋዩ ባይሳ፤ በእግር ኳስ ጨዋታ ከሐጎስ ጋር ቢቀያየምም፤ ዛሬ ግን፣ ገላገለ እንጂ፤ ሆነ ብሎ አላስመታውም፡፡ የተቧደኑ ተማሪዎች ግን ምን ብለው ተረጎሙት? “ያስመታው ኦሮሞ ነው” ተባለና፤ ተቧድኖ መገላመጥና መተነኳኮስ ይጀመራል፡፡ ቀጭኗና ቆንጂየዋ ሲስተር ንግስቲ፤ በአባቷ የትግራይ፤ በእናቷ የሀዲያ ተወላጅ እንደሆነች ማንም አያውቅም፡፡ እሷም አዲስ አበባ ተወልዳ ማደጓንና ነርስ መሆኗን ነው የምታውቀው፡፡ ተደባዳቢዎቹ ወደ ክሊኒክ ሲመጡ፤ የሐጎስ ጉዳት የባሰ እንደሆነ ስታይ፤ ቅድሚያ ሰጥታ አከመችው፡፡ በቡድን ስሜት ሲተረጎምስ? “በትግሬነት አዳልታ ነው” ይባላል፡፡
እንዲህ፤ “ትግሬ”፤ “ደቡብ”፤ “ኦሮሞ” በሚል ጎራ ለይተው የሚተነኳኮሱ ጥቂት ቀሽም ተማሪዎች፤ “እነዚያ’ኮ እንዲህ ሊያደርጉ አስበዋል”፤ “እነዚያ’ኮ እንዲያ አደረጉ” የሚሉ ወሬዎች ታጅበው፣ ፀብ ይጭራሉ:: በአምባጓሮው የክሊኒክ መስታወት የሰበሩ 3 ተማሪዎች ይታሠራሉ - በፖሊስ ተጫኔ:: ሲወራ ግን፤ “በአምባጓሮ መስተዋት ተሰበረ” አልተባለም::
ፖሊሱ አማራ ስለሆነ፣ “የኛን ልጆች አሰረ” ተባለና በዚህ የተናደዱ የቡድን አባላት፤ እየጮሁ ወደ ተማሪ ዲን ይሄዳሉ፡፡ የተማሪ ዲን አቶ መሀመድ፣ ከአንድ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪ ጋር በፈጠረው ግብ ግብ መሬት ይወድቃል፡፡ መነፅሩ ይሠበራል፤ ፊቱ ላይ ይቆስላል፡፡ በሱማሌ ተወላጅነት የተቧደኑ ተማሪዎች፤ “የኛ ሰው የተመታው፣ እኛን ንቃችሁ ነው” በሚል ለፀብ ይነሳሉ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ ጡዘቱ ይቀጥላል...
የጡዘቱ ምክንያቶች ምንድናቸው?
“በትምህርትና በእውቀት በየጊዜው የሚበለፅግ አስደሳች ህይወት መቀዳጀት”፣ ዋና አላማቸው መሆን እንደሚገባው ስለዘነጉ፤ የብሽሽቅና የውድቀት ፉክክር ውስጥ ገብተዋል - ጥቂት ቀሽም ተማሪዎች፡፡
ጡዘቱን የሚያባብስ ሰበብ አግኝተዋል - የመንጋ አስተሳሰብን፡፡
የብሔር፣ የሃይማኖት ቡድን፣ መጠጊያና ዋስትና ሆኗል፡፡ “ከተቧደንክ፤ በቡድን ስም፣ እንደፈለግህ መሆን ትችላለህ!” ተብሏል፡፡
የግለሰብ ሀላፊነት ተረስቷል!
የት/ቤቱ አስተዳደርም፣ እያንዳንዱን ተማሪ እንደየ ስራው ማስተናገድ፣ መምከርና መቅጣት ሲኖርበት፤ በቡድን ያስተናግዳቸዋል፡፡
መፍትሄውስ?
አንድ ተማሪ በሰራው ጥፋት፤ በብሔር ተወላጅነት እየተሰላ፣ ሌላው ተማሪ ባልሰራው ስህተት መቀጣት የለበትም።
የአንድ ተማሪ እውቀትና የፈተና ውጤት፤ በብሔር ተወላጅነት ለሌሎች እንደማይከፋፈል ሁሉ፣ ጥፋት ሲፈፅምም ሃላፊነቱን በብሔር ተወላጅነት ወደ ሌሎች መጫንና መቅጣት የፍትህ ፅንሰ ሃሳብን የሚደመስስ ይሆናል።
እያንዳንዱ ሰው እንደየ ስራው የሚሸለምበትና የሚቀጣበት የፍትህ አስተሳሰብን በመገንባት፣ ኋላቀሩን የመንጋ አስተሳሰብ ስናፈርስ፤ በብሔር የሚቧደኑ ጥቂት ሰዎች የጡዘት ምህዋርን ለማባባስ የሚያገለግል ሰበብ ያጣሉ፡፡
መፍትሄው ይሄ ብቻ አይደለም፡፡
ሰዎች የብሽሽቅና የውድቀት ምህዋር ውስጥ ገብተው የሚተጋተጉትና የሚናቆሩት፤ አላማቸውን ሲዘነጉ ነው፡፡ “በጥረት፣ በየጊዜው የሚበለፅግ አስደሳች ህይወትን መቀዳጀት” ዋነኛ አላማቸው መሆን እንደሚገባው ተገንዝበው፤ የስኬትና የብልፅግና ምህዋር እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል - በቅንብራዊ አስተሳሰብ (ST)፡፡


Read 12497 times