Wednesday, 14 August 2019 09:51

HIV ቫይረስ በጡት ማጥባት ጊዜ ይበልጥ ከእናት ወደ ልጅ ይተላለፋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)


           እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው ጥረት ፀረ ኤችአይቪ የሚወስዱ ቫይረሱ በደማቸው ያለ እርጉዝ እናቶች 69% ነበሩ፡፡ ይህንን መረጃ ያወጣው የአለም ባንክ ሲሆን ዳሰሳው የተካሄደውም የልማት አመላካች ሁኔታዎችን ከመገምገም አንጻር ነበር፡፡
ከ2010-2018 ድረስ ባለው መረጃ በአለም ላይ ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት በ PMTCT ፕሮግራም መሰረት በኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይያዙ ሆነዋል፡፡
ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ የሚተላለፈው በእርግዝና ወቅት በወሊድ ጊዜ እና ጡት በማጥባት ወቅት ነው፡፡ እድሜአቸው ከ0-14 አመት የሚሆናቸው ሕጻናት በአብዛኛው የቫይረሱ ተጎጂ የሚሆኑት ከእናቶቻቸው በሚሰራጨው ቫይረስ ምክንያት ነው፡፡
አንዲት ሴት የኤችአይቪ ቫይረስ በደምዋ ውስጥ እያለ እርጉዝ ከሆነች እና ምንም አይነት የህክምና እርዳታ ካላገኘች ቫይረሱ ወደልጅዋ የመተላለፉ እድል ከ15%-45% ይሆናል፡፡ ነገር ግን በጊዜው ሕክምና አድርጋ ፀረ ኤችአይቪ (ART) መውሰድ ከጀመረች አደጋውን ወደ 5% ዝቅ ያደርገዋል፡፡
ኤችአይቪ ኤይድስን በሚመለከት አለም አቀፉ የመረጃና ትምህርት ድረገጽ www.avert.org እንደሚያስነብበው በአለም አቀፍ ደረጃ ሊተኮርባቸው የሚገቡ ዋና ዋና  ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚያደርገው (PMTCT) ፕሮግራም እድሜያቸው ለስነተዋልዶ የደረሱ እና ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወይንም ለቫይረሱ ይጋለጣሉ ተብለው የሚታሰቡ ሴቶችን ጤንነት በመጠበቅ እና የሚወልዱዋቸውንም ጨቅላዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡
የPMTCT አገልግሎት የኤችአይቪ ቫይረስ ከመጀመሩ በፊት እና በእርግዝናው ወቅት እንዲ ሁም በመውለድ ወይንም ጡት በማጥባት ጊዜ ቫይረሱ የሚተላለፍ መሆኑን ለተገልጋዮቹ እውን በማድረግ መሰራት አለበት፡፡
የPMTCT አገልግሎት ልጆች ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው ሴቶች ገና እንደተወለዱ ማለትም ከአራት እስከ ስድስት ሳምንት ምርመራው ሊደረግላቸው የሚገባ እና ከዚያም በ18/ኛው ወር ወይንም የጡት ማጥባት ወቅት እንዳበቃ ያሉበት ሁኔታ በደንብ መታየትና  ለቫይረሱ ለተጋለጡት ልጆች በተቻለ ፍጥነት ART ሊጀመርላቸው ይገባል፡፡  
በእርግጥ ሴቶችንና ጨቅላዎችን ከወሊድ በሁዋላ በ PMTCT ፕሮግራም በሚያስፈልገው መንገድ መርዳት ከባድ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ብዙ ጨቅላዎች በእርግዝናና ወሊድ ጊዜ ከሚኖረው የቫይረስ መተላለፍ ይልቅ በጡት ማጥባት ጊዜ በሚፈጠረው አጋጣሚ በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው እየሰፋ ይገኛል:: የዚህም ምክንያቱ መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ እና የሚሰጠውን አገልግሎት አንዳንድ ሴቶች ስለማይተገብሩት ነው፡፡
ከ2010-2018 ድረስ ባለው መረጃ በአለም ላይ ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት በ PMTCT ፕሮግራም መሰረት በኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይያዙ ሆነዋል፡፡
ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የተዘረጋው PMTCT የተሰኘው ፕሮግራም ለእናቶች እና ለጨቅላዎቻቸው ሰፋ ያለ አገልግሎትን ይሰጣል፡፡ ለምሳሌም በስነተዋልዶ እድሜ ላይ ያሉ (15-49) ሴቶችን በቫይረሱ እንዳይያዙ ከመከላል ጀምሮ ቫይረሱ በደማቸው ያለ ሴቶች ያልተፈለገ እርግዝናን እንዲከላከሉ እንዲሁም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ቢኖርም እንኩዋን (ART) ፀረ ኤችአይቪን እየወሰዱ በሕይወት ዘመናቸው ጤናማ ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል ይረዳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በእርግዝና ላይ ላሉትም በእርግዝና ወቅት ወይንም በወሊድ እንዲሁም ጡት በማጥባት ቫይረሱ ወደ ልጆቻቸው እንዳይተላለፍ ማድረግ የሚችል ከፍተኛ ፕሮግራም መሆኑን www.avert.org ያስነብባል፡፡
avert እንደሚያስነብው ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የተዘረጋው ፕሮግራም ደህንነታቸው የተጠበቀ ሕጻናትን መውለድ የሚቻልባቸውን መንገዶች የሚያስተምር እና ለጨቅላዎች ትክክለኛው የአመጋገብ ስልት ምን እንደሆነ እንዲሁም ለቫይረሱ የተጋለጡ ጨቅላዎች በጡት ማጥባት ወቅት ሊደረግላቸው የሚገባው ክትትል ምን እንደሆነ ለወላጆች እንዲሁም ለቤተሰብ ያስተምራል፡፡ በተለይም ህጻናቱን ከቫይረሱ ለመከላከል ART ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እና አገልግሎቱን በትክክል መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል::
avert የሚከተሉትን መረጃዎች ለንባብ አቅርቦአል፡፡  
ከ2010-2018 በአለም ላይ ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት በ PMTCT ፕሮግራም በሚደረግላቸው ክትትል ምክንያት በቫይረሱ እንዳይያዙ ማድረግ ተችሎአል፡፡
በ2017 ዓ/ም በአለም ላይ 80% የሚሆኑ እርጉዝ ሴቶች በደማቸው የኤችአይቪ ቫይረስ የነበራቸው ሲሆን የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ወስደዋል፡፡
በአለም ላይ ወደ 740.000 በተዋልዶ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች በ2016 ዓ/ም ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ተገኝቶአል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ወደ 73% የሚሆኑት ሴቶች በ23 ሀገራት የሚገኙ ሲሆን በአብዛኛውም ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ነው፡፡ እነዚህ ሀገራትም በከፍተኛ ደረጃ ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ የሚሰራው ፕሮግራም እንደሚያስፈልጋቸው እና ቅድሚያ እንዲሰጣቸው UNAIDS ይጠቁማል፡፡
በአለማችን በ2017 ዓ/ም ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ማለትም ከ1.8 ሚሊዮን ውስጥ ከግማሽ በላይ ማለትም (52%) የሚሆኑት ፀረ ኤችኤቪ መድሀኒት ይወስዱ የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም ወደ 110.000 የሚሆኑት ህጻናት ተገቢው የህክምና ክትትል ስላል ተደረገላቸው ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ በገጠማቸው ሕመም ምክንያት ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡
avert አክሎም በአለም ላይ በ2017 ዓ/ም በግምት ከ180.000 በአዲስ በቫይረሱ ከተያዙት ህጻናት መካከል ግማሾቹ ቫይረሱ የተላለፈባቸው ከእናቶቻቸው በጡት ማጥባት ወቅት መሆኑ ታውቆአል፡፡ ስለዚህም መረጃው እንደሚጠቁመው በተለያዩ ሀገራት እንደሚታየው ከሆነ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውን ሴቶች በተገቢው መንገድ በተለይም ጡት በማጥባት ወቅት ART እንዲወስዱ ማድረግ እና በተገቢው መንገድ ክትትሉን እንዲያደርጉ ማስቻል አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ቫይረሱን መከላከል ወይንም መቀነስ እና በቫይረሱ የመያዝ እድልን መከላከል በተለይም በእርግዝናና ጡት ማጥባት ወቅት ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት በአንዳንድ አገሮች ጨቅላዎች በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የሚያዙበት ምክንያት በእርግዝና ወይንም በወሊድ ወቅት ሳይሆን ከተወለዱ በሁዋላ በጡት ማጥባት ጊዜ በመሆኑ እናቶች ወይንም መላው ቤተሰብ ልብ ሊለው የሚገባ ነገር ነው፡፡

Read 6309 times