Print this page
Wednesday, 14 August 2019 10:14

ሰበብ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(8 votes)


            ጧት፤ ቡና ጠጥቶ ሊወጣ ሲል፣ የመጨረሻውን ስኒ ቡና ስታቀብለው፤ ‹‹ዋ!  ዛሬም ደግሞ ባዶ እጅህን ናና - ትገባታለህ!...” ያለችው ድምፅ ሲከተለው ነበር የዋለው፡።
እየሳቀ፤ ‹‹ዛሬ እንኳን የምትወጃትን ይዤ ከተፍ ነው፡፡”
‹‹ይ-ታ-ያ-ላ!››
ሽሙጧ ገብቶታል፤ ከያዘች አትለቅም፤ ምክንያት አታውቅም፡። ስራ ቀዝቅዟል፣ ገበያ የለም… ቢሏት አይገባትም፡፡ ወልዶም ቢሆን ያምጣ ነው!
እናትዋም፤ አባትዋን እንዲህ፤ እያስጨነቁ፣ የፈቀዱትን ያስደርጉ እንደነበር ብዙ ቀን አልጋቸው ላይ ነግራዋለች፡፡ ቢሆንም፤ ሀሳቡን ፈልቅቆ መስማት አልቻለም፡፡ ጉያዋ ሆኖ፤ እውነት ማሰብም ሆነ መናገር አይቻልም፡፡ እሷ፤ ጉያዋ ውስጥ እሾክ ይጠወልጋል፣ ብረት ይቀልጣል፤ ወርቅ ይነጥራል፡፡
ድሮ ድሮ - ወርቅ ነኝ ብሎ ያስብ ነበር፡። እንዳልሆነ ያወቀው፡፡ ትዳር ውስጥ ከገባ በኋላ ነው፡፡ የአቻምየለሽ ገላ ምድርን ያስረሳል፣ ገነትን ያስገፋል፡፡ አንዳንዴ ወንድ ሁሉ እንደኔ ይሆን? ብሎ ይጠይቃል::
አንድ ቀን ሠፈራቸው ያለው ከመጽሐፍ የማይላቀቅ ልጅ፤ “የወንድ ልጅ ገነቱም ሲኦሉም? ያው ሴት ናት” ብሎታል፡፡ ድሮም የሪሲያው ደራሲ “ሞቼ - ሞቼ የሬሳ ሳጥን ውስጥ፣ ገብቼ፣ የክዳኑ ምስማር ካልተመታ፣ ስለ ሴት አልናገርም፤ ብሏል ዓለምን ይለዋል፡፡
አንዳንዴ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይደሰታል:: ‹‹አሁን አቻምየለሽ ባትኖር ዓለምን እንዴት አውቃለሁ” የመኖር ጣዕም የት ይገባኛል? … የት አድርሳ እንደምትመልሰኝ እኔስ ትርጉሙን ከየት አመጣለሁ?››… ይላል፡፡ ሲላትም ለብልባ ታቃጥለዋለች፣ እንባውን አውጥቶ እንዲያለቅስ ታደርገዋለች፡፡
ዛሬም፤ ድምጽዋ እየተከተለው ከሄደ በኋላ የሚችለውን ሁሉ ሲጥር ዋለ፡፡ ሥራ የለም፣ ገንዘብ  መበደር ፈልጎ ወደ ጓደኛው ሲደውል፣ ጓደኛው ከከተማ ወጥቷል፡፡ የታባቱ ሄዶ ነው! ይችላል፡፡
ያኔ - ሳይከስር በፊት፣ ያኔ ሱቁ ሙሉ ሳለ፣ ጣጣ አልነበረውም፡፡ ለሁሉም ነገር ብሩን መዥርጦ ያወጣ ነበር፡፡ በኋላ መንግስት በግብሩም - በምኑም እያለ አደቀቀው፡፡ የደርጉ ዘመን ወኔ አልለቅ ብሎት ሲታገል፣ ባዶውን አስቀሩት፡፡ አሁን የቀረው ተስፋውና አዲሷ ሚስቱ ናት፡፡ የድሮዋ ምስኪን እንደዶኮዩ አፈር ቀመሰች፡፡ ይቺን በድህነት ቢያገባትም… ድህነቱን አላወቀችለትም፡፡ ሲብስበት… ያ ኮማንዶነቱ ይመጣበትና ‹‹ቱቦዋን ልዝጋው?›› ይላል፡፡ ቱቦዋን መዝጋት፣ የገነትን በር መዝጋት፣ የፌሽታውን አፀድ መመንጠር ነው!! ከንፈሩን ይነክስና ይተወዋል፡፡
‹‹ስማ ወንድ አጥቼ እንዳይመስልህ፤ አስሩን ነበር የማስከትለው፡፡ ደግሞ ያንተ ጡንቻ ማርኮኝም አይደል፤ ስለምታሳዝነኝ ነው፡፡ ብቻህን ሳይህ አንጀቴ ይንቦጫቦጫል፡፡›› ትለዋለች፡፡
‹‹አዝነሽ ሞተሻል!›› በአፉ አይናገርም፤ በልቡ ነው፡፡
ደሞ - ፌስቡክ ስትወድ!..ለጉድ ነው፡፡ አሁን ፖለቲካው ሲጦዝ ቀዝቀዝ ብላ ይሆናል እንጂ፣ ያኔስ ቡናም አላፈላ ብላ ነበር፡፡ ዕቃ ስታቀብል እንኳ ዐይኗን - ከስልኳ ላይ አትነቅልም፡፡
‹‹በስንቱ ተቃጥሎ - ይቻላል?... ሁለቱ አንድ ይሆናሉ›› የሚሉን፤ እኔና ይህቺን ሴት ነው?
አመሻሽ ላይ ወደ ቤት ገብቶ ሳንጃውን ሲፈትሽ፣ ራሱም ግራ ገብቶታል፡፡
‹‹ይለያል ዘንድሮ የተመስገን ኑሮ!›› እያለ በራሱ ቀለደ፡፡ ቀስ ብሎ ወደ ጓዳ ገባና ሞረደው፡፡
‹‹ምን እያደረግህ ነው?›› ጠየቀችው፡፡
‹‹ዝም ብዬ ነው!››
‹‹ምናልባት ሌላ ነገር አሰኝቶህ ከሆነ?››
‹‹አይ?! ለማታ ቢላዋ እየሳልኩ ነው››
‹‹ድንቄም! ለአንድ ኪሎ ሥጋ ክንድህን ባታዝልስ?...››
‹‹አይ ሙክት አመጣልሻለሁ!”
‹‹የታደሉትማ - ሰንጋም ይጥላሉ!››
‹‹ለድግስ ነዋ!.. አንቺን ደግሜ አላገባሽ?››
‹‹ያንዴውም ቆጭቶኛል ባክህ!››
እየተመላለሱ ከቆዩ በኋላ ወዴት እንደሚሄድም ሳያውቅ ከቤቱ ወጣ፡፡ ስራ ቦታ ገባ ብሎ ወዲያው ውልቅ አለ፡፡ ሱቁ ቢዘጋ፣ ወይ ቢቀር ይሻለው ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ካልሆነ ሥራ የለም፡፡ አንዳንዴ  ከጓደኞቹ ጋ ወጣ ብሎ ድለላ ቢጤ ባይሞክር፣ ትዳሩ ፈርሶ ነበር፡፡ ደግነቱ እዚያች ጦር ሀይሎች አካባቢ ዘው - ዘው ይላል፡፡ ሲለውም በቻይና ኤምባሲ አድርጎ ወይራ ሰፈር፣ ከዚያም ወደ ቤተል ሄዶ ይሸቃቅላል:: ዛሬ ግን ያም የለም፡፡ ጓደኞቹም የሉም:: በዚያ ላይ ሚስቱ ጨቅጭቃዋለች፡፡ “አርግዛ ይሆን እንዴ?›› ብሎም ትንሽ አሰበ እንደመተከዝ ብሎ፡፡
ምንም ሳያገኝ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ሆነ፡፡ ሚስቱ ስትደውል ስልክ አላነሳም፡፡ ቴክስት አደረገች፤ መልስ አልሰጣትም፡፡
‹‹ሰውየው አንተን እየጠበቅሁ መሰለኝ!››
በልቡ “እኔን አዳኝ፤ አንቺ ጌታ ያደረገሽ ፈጣሪ እርሱ ያውቃል!” ብሎ ዝም አላት፡፡ ትንሽ ቆይቶ ስልኩን ዘጋው፡፡ ትንሽ ጂን ቢጤ ቀማምሷል፣ አንዱ ጓደኛው ነው የለቀቀበት፡፡ ጨምር ሲለው መጨመር አልፈለገም፡፡
ድንገት ወደ አንዱ ዞርታ ሄዶ የቆመች መኪና አጠገብ፣ ተጠለለና ቆመ፡፡ ማንም የለም፡፡ ግራና ቀኝ ተገላመጠ፡፡ ወታደርነቱ ትዝ አለውና፤ በሩን ሊፈለቅቅ ከጀለ፡፡ ውስጡ ተሟገተው፡፡ ሳያስበው ‹‹ምናባክ ታደርጋለህ፤ አንተ!›› ሲለው መልስ አልሰጠውም፡፡ በቀኝ እጁ የመኪናውን ቁልፍ እንዳለ ሾለ ነው፡። በግራ እጁ ከሥጋ ቤት ያንጠለጠላትን ፌስታል ይዟል፡፡
‹‹አንተስ ምናባክ ታደርጋለህ!›› አለና ከፍቶ እንደገባ አነቀው፡፡ ግራና ቀኝ ሲያይ ሰው የለም:: ደረቱን ወጋው፤ ከጀርባው በኩል የተቀመጠውን በፌስታል የተጠቀለለ ሥጋ ያዘና አመለጠ፡፡
ሰውየው ሲያቃስት ምንም አልመሰለው፡፡
‹‹በሕግ አምላክ!›› አለና ወደቀ፡፡
ነፍሱን አያውቅም፡፡ ጦር ሀይሎች ደረሰና ታክሲ ተሳፍሮ እብስ አለ፡፡  የተከተለው የለም፡፡
እቤት ሲደርስ ለንቦጭዋን ጥላለች፡፡
እየሳቀ ወስዶ ስጋውን ሰጣት፡፡
‹‹ድንቄም ሥጋ!... ፍርምባና ወርች… ምን ያደርግልኛል!... ፍርምባ ቀን ሙሉ ቢቀቀል የማይበስል ነው፣ ወርችም ለወጥ ካልሆነ፤ ለቁርጥ አይሆን! ለጥብስ አይሆን! ውኃ ይተፋል!...››
ንግግርዋን ከአፏ ሳትጨርስ፣ ሳያስበው በጥፊ አጮላት፡፡ ድንገት ወደቀች፡፡
‹‹ወይኔ… ልጄን!... ወይኔ ልጄን!›› አለች፤ ሆዷን ይዛ፡፡
ከጎረቤት ሰዎች እየተግተለተሉ መጡ፡፡
አቻምየለሽ ወድቃለች፡፡
‹‹ውይ ጉዴ! ውይ ጉዴ!›› አለች፤ አዲሷ የጎረቤት ተከራይ፡፡ መልስ የሰጣት የለም፡፡
‹‹… ወንድሜን ገደሉብኝ! ወንድሜን ገደሉብኝ?›› አለችና ተመልሳ ወጥታ ሄደች፡፡
አቻምየለሽ እያዞራት ብድግ ስትል፣ ሌላዋ ጎረቤት መጣች›…
“እንከተላት ይሆን እንዴ?... ወንድሟን መኪናው ውስጥ ገደሉት!›› አለች፤ በድንጋጤ ተውጣ አዞረው:: “ምን ዐይነት ጦስ!፣ ምን ዐይነት ሰበብ ነው!›› እያለ… ጓዳ ገብቶ አልጋው ላይ በጀርባው ዝብ አለ፡፡         

Read 2241 times