Print this page
Saturday, 17 August 2019 13:22

ኢህአዴግ በ11ኛው ሰዓት!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አቶ አባይ ወልዱ በወቅቱ የህወሓት ሊቀ መንበር ናቸው፡፡ አቶ አባይ በተመሳሳይ መልኩ ሃሳባቸውን ሲገልጹ፤ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭና መፍትሔው ተቀምጦ ያደረ ነው፣ አሁን አዲስ ነገር አልቀረበም፡፡ ባለፈው ክረምት (በ2006 ዓ.ም ክረምት ማለታቸው ነው) ይህንን ለማረምም በጋራ ሆነን ትግል ጀምረናል፣ ስለሆነም አሁን የደረስንበት ቦታ ሆነን መገምገምና የበለጠ ለትግል መነሳሳት መፍጠር ይገባል፣ dead end የሚል እንዲሁም 1994 ዓ.ም ላይ ነን፣ ከህዝብ ተነጥለናል ወዘተ. ከተባለ፤ በድርጅትም ሆነ በመንግስት፣ ሌት ተቀን በሥራ እየለፋ ያለው አመራር፣ ተስፋ ሰንቆ ወደ ፊት እንዳይጓዝ፣ እንቅፋት እንደሚሆን መገንዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አቶ አባይ ሲቀጥሉ፣ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ነገር እየተነሳ የስራ ጊዜያችንን እያባከንን ነው፣ በተደጋጋሚ frustration አለኝ የሚልም፣ የግሉ ችግር እንዳይሆን፣ ራሱን ተመልሶ ማየት አለበት፡፡ አቶ ዘርአይ፤ ወዳጄ ሲሆኑ ለምን ወረዱ እየተባለ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ አይደለም፣ ህወሓት የድርጅቱን ኮንፈረንስ በማካሄድ፣ ከዲሲፕሊን ውጪ አልተንቀሳቀሰም፡፡ የግጨው ጉዳይ ጊዜ ወስዷል፤ ነገር ግን አሁን ከብአዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀጠሮ ይዘናል፣ የግጨው ጉዳይ የመሬት ችግር ሳይሆን የትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ ችግር ውጤት በመሆኑ ውስጣችንን ማየት ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ አዲሱ ለገሰና አቶ በረከት ስምኦን፤ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ተሳታፊዎች በቀረቡ ሃሳቦች አልተስማሙም፡፡ የኢህአዴግ ኮር አመራር የችግሩን ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም ውስብስብነት አልተገነዘበም ወይም ለመገንዘብ አልፈለገም የሚል አመለካከት የያዙ ይመስላሉ:: በመሆኑም ክርክራቸውን ለመቀጠል ጥረት አድርገዋል፡፡
አቶ አዲሱ ለገሰ፤ በግብረ መልስ መልክ ሲናገሩ፤ ያለንበት ሁኔታ እየከበደ ነው፤ አመራሩ ለዚሁ ሁኔታ ብቁ ሆኖ እየጠበቀ አይደለም፤ መስመር ብቻውን ያለ ብቁ አመራር አያድነንም፣ ለምሳሌ ለአቶ ከበደ ‹ጫኔ “ከሃላፊነትህ እናስነሳሃለን›› ብለው የዛቱ ባለሀብቶች አሉ፡፡ ከባለሀብቶች ጋር የተሳሰሩ ሚኒስትሮች አሉ ይባላል፣ በመሆኑም ውስጣችንን መፈተሽ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን መጥፎ የሌብነት ስም በጋራ እየተጠራንበት ነው፣ ቤት የሰራም ከመንግስት ቤት ወጥቶ፣ በሰራው የግል ቤቱ ይግባ የሚሉ ነጥቦች አንስተዋል፡፡ በመጨረሻም አቶ አዲሱ ሲናገሩ፤ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም፣ ብአዴን በውስጡ ምንም አይነት ትግል ሳያደርግ እንደመጣ መታየት የለበትም፤ ብአዴን ህወሓትንም ሆነ የትግራይን ህዝብ defend ያደርጋል፣ ነገር ግን ገዢዎች በፈጠሩት ችግር፣ የአማራ ህዝብ በትምክህት መጠርጠር እንደሌለበት አሳሰቡ፡፡
አቶ በረከት ስምኦን ክርክራቸውን በግብረ መልስ ሲቀጥሉ፣ እኔ የመሰለኝን ሃሳብ ነው ያቀረብኩት እና Procedural issues  ማየት አይጠቅምም፣ አቶ አባይ ወልዱ ተመሳሳይ ሃሳብ መደጋገም ኢንቴንሽኑ ምንድነው ብለው ያነሱት፣ የኔ መነሻ፣ ጥራት ያለው ድርጅት እንዲኖረን ስለምፈልግ ብቻ ነው፡፡ ችግሩ በተደጋጋሚ ተነስቶ ለውጥ አለማምጣታችን፣ why ብለን መጠየቅ፤ ይህንንም መመለስ አሁንም ጠቃሚ ነው፣ ብዙ የኛ አይነት መስመር የያዙ አገሮች ችግር ውስጥ ይገባሉ፤ አሁንም ለወደፊትም መምራት የሚያስችል ፖለቲካዊ ህይወት የለንም፤ እንደ አመራር unified ባለመሆናችን፣ ለአደጋ እየተጋለጥን ነው አሉ፡፡
አቶ በረከት ሲቀጥሉ፤ እዚህ ቤትም ሆነ በብአዴን እያየነው ያለው ሁኔታ sense of urgency የለም፣ አሁንም reservation አለኝ፤ መተካካት ወደ ኋላ መመለስ የለበትም፤ ነገር ግን ሁላችንም የተሟላ አቅም ስለሌለን፣ ያለንን አቅም አዋህደን ካልተጠቀምን፣ ችግር ውስጥ እንገባለን፤ትምክህት በታየበት ልክ ትግል እየተካሄደ ነው፤ ከህወሓት መስመር ያፈነገጠ አባልን መታገልም፣ ትምክህተኛ መባል የለበትም የሚል ጨመሩ፡፡ በመጨረሻም፣ አቶ በረከት ሲናገሩ፤ የግጨው ጉዳይ the level of our problem ያሳያል፣ የግጨው ችግሩ build up እየሆነ መጥቶ massive ትጥቅ በአካባቢው ተሰባስቧል፤ አሁንም give and take መርህ ተከትለን፣ ጊዜ ሳንሰጥ እንፍታው፤ ብአዴን እና ህወሓት ወርቃማ ታሪክ የሰሩ ድርጅቶች፣ በዚህ የተነሳ ወድቀው ማየት ያሳዝናል፤ አሁንም ችግሩ ገና ነው፤ ሌላ ኃይል ብዙ ይጠቀምበታል በሚል አስተያየታቸውን አጠቃለሉ::
አሁንም የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባው ፍሬ አልባ ሆኗል፡፡ በአቶ ደመቀ መኮንንና በአቶ በረከት ስምኦን መካከል ከአስተሳሰብ ልዩነትም አልፎ ያልተፈለገ ንትርክና ጭቅጭቅ መከሰቱ ቀጥሏል:: እነ አቶ ደመቀና እነ አቶ በረከት በመካከላቸው በፈጠሩት ልዩነት ዙሪያ በብአዴን አመራር ውስጥ ክፍፍል እየሰፋ እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ነበር:: እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፤ ብአዴንም በውስጡ ተከፋፍሎ እየተፋጀ እንደሆነ ውስጥ ለውስጥ በሰፊው ይወራ ነበር፡፡ ክፍፍሉና መደጋገፉ በእነማን እንደሆነ፣ በኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በሚሰጡ ሃሳቦች ጭምር ለማየት አዳጋች አልነበረም፡፡
በብአዴን እና በህወሓት እንዲሁም ሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች በውስጣቸው የተፈጠሩ ክፍፍሎች፣ በኢህአዴግ ደረጃ እየሰፉ እንደሆኑ ምልክቶች ነበሩ፡፡ የተወሰኑ የህወሓት ነባር የተተኩ አመራሮችና እነ አቶ በረከት የመሳሰሉ አመራሮች፣ ተመሳሳይ አቋም ይዘው፣ በአዲሱ አመራር እምነት አጥተናል እያሉ መናገር የዘወትር ስራቸው ሆኗል፡፡ በአዲሱ አመራር እምነት አጥቷል፡፡ አዲሱ አመራርም የያዘውን ስልጣን ለመከላከል ምሽጉን አጠናክሮ መፋለሙን ቀጥሏል፡፡
አቶ ኃ/ማርያምና አቶ ደመቀ አብዛኛውን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይዘዋል፡፡ የአብዛኞቹን ነባር አመራሮች ኩነኔ ከመከላከልም አልፈው ለመቆጣጠር ጥረታቸውን ቀጥለዋል:: የፍልሚያው መነሻ ጥቂቶቹ፣ ሌብነታቸው እንዳይጋለጥ ለመከላከል እንዲችሉ፣ ስልጣናቸውን ለመጠበቅና ከፍ ለማድረግ የግድ እንደሆነባቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ሌላውም ለክብርና ለዝና ስልጣኑን ይፈልገው ነበር፡፡ አንዳንዶችም የተለያዩ ቅሬታዎችንና ቂም በቀሎችን መነሻ በማድረግ፣ ይጠቅመናል በሚሉት ጐራ በቋሚም ሆነ በጊዜያዊነትና ተለዋዋጭነት መቧደናቸው ቀጥሏል፡፡ በአድርባይነትና የድርጅቱ ውስጠ ጸረ ዴሞክራሲ ተግባር ታጅቦ፣ የቁልቁለት ጉዞው ፍጥነቱን ጨምሯል፡፡ በርከት ያለ ቁጥር ያለው የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር፣ ከኢህአዴግ እምነትና አላማ በተጻራሪ አቅጣጫ ቆሟል፡፡---
ምንጭ፡- (በብርሃነ ፅጋብ ከተዘጋጀው ‹‹የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ (2005-2010) የስብሰባዎች ወግ›› መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 3393 times
Administrator

Latest from Administrator