Print this page
Saturday, 24 August 2019 13:56

“የእኔ ምቀኛ ገና አልተወለደም”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ነገሬ ላለ ሰው፣ ሚኒባስ ታክሲዎቻችን ላይ የሚለጠፉት ነገሮች፣ አንድ ሰሞን ሲያሸማቅቁን ከነበሩት ዘለፋዎች ቀስ በቀስ እየወጡ ነው:: “የቤትሽን ዓመል እዛው!” አይነት መለስተኛ የተቃውሞ  ሰልፍ ሊያስወጡ የሚችሉ ነገሮች አልፎ፣ አልፎ በምክሮችና መልካም በሆኑ ቃላት እየተለወጡ ይመስላል፡፡ በእርግጥ ምን የመሳሰሉ የሚያረጋጉና ብሩህ ኃይማኖታዊ መዝሙሮችና ሰብከቶች እየተሰሙ፣ ዲያብሎስ እንኳን የሚቀናባቸውን ስድቦች የሚሳደቡትን እንዳልሰማን እያለፍን ማለት ነው፡፡ እናማ…አንድ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ምን የምትል ነገር ተለጥፋለች መሰላችሁ…“የእኔ ምቀኛ ገና አልተወለደም” አሪፍ አይደለች! ቢያንስ ይሄ ባለታክሲ በትንሽ ትልቁ ችግር ጣቱን ምቀኛ ላይ አይቀስርም፡፡ ሁሉም ባይሆን እንኳን ብዙ ነገሮች በምቀኞች በሚሳበቡበት፣ ምቀኝነት ከግለሰባዊ ባህሪይነት አልፎ ድርጅታዊ ሆኗል በምንልበት ጊዜ፣ ምቀኝነት በሀገር ደረጃ ሁሉ አለ እያልን በምንጠረጥርበት ጊዜ፣ ይህን መሰል ነገር  ማየትና መስማት አሪፍ ነው፡፡
እናላችሁ ዘንድሮ…ስለ ምቀኝነት የማይወራበት ስፍራ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሞራልና ስነምግባር፣ አይደለም መቀነስ፣ እየተንኮታኮቱ ነው በሚባልበት ዘመን፣ ስለ ምቀኝነት ብዙ ቢወራ ላይገርም ይችላል:: ግን…አለ አይደል… ለሁሉ ችግር ምቀኝነት እንደ ጆከር ካርታ እየተመዘዘ፣ በቀረችን ሰብአዊነት እንኳን ለሻይ አብረን መቀመጥ እያስቸገረ ነው፡፡
“ስማ፣ እንትናን መንገድ ላይ አይቼው፣ እሱ ሰውዬ ብቻውን እያወራ መሄድ ጀመረ እንዴ?!”
“ምን እባክህ፣ ወዶ መሰለህ…”
“ወዶ መሰለህ ማለት…”
“ምናምን አቅምሰውት ነው ይባላል፡፡”
“እነማን ናቸው?”
“ምን አይነት ጥያቄ ነው…ምቀኞች ናቸዋ!”
አራት ነጥብ፡፡ “ምቀኞች ናቸው…” ከተባለ በኋላ… አለ አይደል… “ለምን ተመቀኙት?”፣ “ምን አጣን ብለው ተመቀኙት?” ምናምን አይነት ‘ኮድ ያልተሰጣቸው’ ጥያቄዎች መጠየቁ ዋጋ የለውም፡፡ ዘንድሮ ለምቀኝነት ንድፈ ሀሳብ፣ ትንታኔ ምናምን ብሎ ነገር አያስፈልግም!
“አሁን ይቺን የመሰለች ምስኪን ልጅ፣ ገና ለገና አንዲት ቀሚስ ለወጠች ብለው ይሄ ሀሉ ምቀኝነት!?”
“ምነው፣ ምን አደረጓት?”
“መንገድ ላይ በመኪና ጭቃ ውሃ አያለብሷት መሰለሽ!”
“ኸረ እነሱንስ ይድፋቸው! ሰው ምነው እንዲህ ከፋ!”
ልብ በሉልኝማ… ይህ የሆነው እኛ ሁላችንም በጭቃ ውሀ በምንረጭበት መንገድ ላይ ነው! መኪና ውስጥ ያሉት ሰዎች ይወቋት አይወቋት፣ ያሽከረክር የነበረው ሰው፣ ሆነ ብሎ ለክፋት ወደ መንገዱ ጠርዝ ተጠግቶ ይሁን ወይም አስፋልቱ ሁሉ መለስተኛ ወንዝ ሆኖበት ይሁን… ማናችንም ማወቅ አንፈልግም::  ምክንያቱም ከእኛ በስተቀር ሁሉም ምቀኛ ነዋ!
አሪፍ ልብስ ለብሰን በለጭለጭ ካልን፣ ልብሱን የሸጠልን ሰው ሳይቀር ሁሉም ምቀኛ ነው፤ የሆነ ወፈር ያለ ረብጣ ካገኘን፣ ፈራንኩን የሚሰጠን የማናውቀው የባንኩ ገንዘብ ከፋይ ሳይቀር ሁሉም ምቀኛ ነው፣ መኪና ከያዝን ራዲያተሩን የሚፈትሸው መካኒክ ሳይቀር፣ ሁሉም ምቀኛ ነው፡፡
እናማ…ይሄ ሁሉንም ምቀኛ የማድረግ ልማድ… አለ አይደል… ከብዙ ነገርም ሳይጎትተን አይቀርም፡፡ የሆነ ነገር ለማድረግ የሚያስጨንቀን፣ ነገርዬው ‘ልክ ነው፣ ልክ አይደለም’ የሚል ነገር ሳይሆን፣ ምቀኞች ምን ይሉ ይሆን፣ ምን ያደርጉ ይሆን የሚሉት አይነት ነው፡፡
“አንቺ ምንድነው ይህን ያህል መሽቀርቀር…ከሩቅ እኮ ነው የምትታዪው!”
“ቢያምርብኝ ምናለበት፣ እኔ የማንንም መብት አልነካሁ…”
“ሰው የሚልሽን ስሚ! ሀገሩ ሁሉ ምቀኛ ሆኗል! ኋላ ነግሬያለሁ፣ እንደዚህ ለብሰሽ በዓይናቸው ቅርጥፍጥፍ አድርገው እንዳይበሉሽ!”
“የራሳቸው ጉዳይ…”
እናማ…አለ አይደል…ይቺ ልጅ ‘የራሳቸው ጉዳይ’ ብላ ከወጣች በኋላ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ከወንበር ወጣ ያለ ምስማር የጂንሷን ክር ሳብ ቢያደርገው…አለቀ፡፡ ምቀኞች የሚመጡበት ቢያጡ በዚህ መጡ! አሀ…ምስማሩ ብቅ ያለው በእነሱ ሟርተኛ አፍ ነዋ!
“የእኔ ምቀኛ ገና አልተወለደም” ያለው ባለታክሲ ይመቸውማ! ቀይ መብራት ጥሶ በተያዘ ቁጥር በምቀኛ ትራፊክ አያሳብብማ!
ደግሞላችሁ…በወዳጆች መካከል፣ በሚቀራረቡ ሰዎች መካከል በምቀኝነት የተነሳ ተፈጠሩ ስለሚባሉ ነገሮች ሁልጊዜም የምንሰማው ነው፡፡ “ገና ለገና ቤት ገዛ ብለው ይኸው ጓደኞቹ ሁሉ ጥምድ አድርገው ይዘውታል» አይነት ነገር ነው፡፡
ይቺን አፈ ታሪክ ነገር ስሙኛማ…ዲያብሎስ በሊቢያ በረሀ እያቆራረጠ ነበር አሉ፡፡ እናላችሁ…መንገዱ ላይ አረመኔዎች፣ አንድ ቅዱስ ባህታዊን ሲያስቸግሩ ተመለከተ፡፡ ባህታዊውን የሆነ ክፉ ነገር እንዲያደርግ ሊያሳምኑት፣ በሆነ ነገር ሊያበሳጩት ቢሞክሩም ምንም ፍንክች አላለላቸውም፡፡ ዲያብሎስም ሙከራቸውን ሲከታተል ከቆየ በኋላ ትምህርት ሊሰጣቸው ወሰነ፡፡ “እያደረጋችሁት ያለው የማይረባ ነገር ነው…ቆይ እንዴት ማበሳጨት እንደሚቻል እኔ አሳያችኋለሁ” አለና ወደ ባህታዊው ቀረበ፡፡ ወደ ጆሮው ጠጋ አለናም… “ወንድምህ የአሌክሳንድሪያ ጳጳስ ሆኖ ተሹሟል” አለው፡፡ ይሄን ጊዜ ባህታዊው በንዴት ፊቱ ሁሉ ተለዋውጦ የሚይዘው፣ የሚጨብጠው ጠፋው፡፡ ዲያብሎስም ወደ አረመኔዎቹ ዘወር አለና… “እንዲህ ነው የሚደረገው” ብሏቸው፣ መንገዱን ቀጠለ ይባላል፡፡
እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምቀኝነት በሽ ነው፡፡ እኛ ትንሽ ለጥጠነው ሲያስነጥሰንም፣ ሲያደናቅፈንም በምቀኝነት ላይ ብናሳብብም፣ እውነቱ፣ ምቀኝነት ወረርሽኝ የሆነ ይመስላል:: “ምቀኛ የሚያስደስተው እራሱ በሚያገኘው ሳይሆን፣ ሌላኛው በሚያጣው ነው” የምትል ነገር አለች:: በተለይ መላ ቅጡ የጠፋው የጎጥ ፖለቲካችን፣ ለምቀኝነት አዳዲስ አስከፊ ገጽታዎች እያላበሰው ነው፡፡
ኦስካር ዋይልድ ‘ዘ ሶል ኦፍ ማን አንደር ሶሻሊዝም’ በሚል መጽሀፉ ላያ ያሰፈራት ተብላ የምትጠቀስ ነገር አለች… “ማንም ሰው በጓደኛው መከራ ሊያዝን ይችላል፤ ግን በጓደኛ ስኬት ለመደሰት ንጹህ የሆነ ባህሪይ ያስፈልጋል፡፡”
ስሙኛማ…ሌላ የሚያስቸግር ነገር አለ:: እርስ በእርሳችን በምቀኝነት ላይ እርግማኑን የምናወርደውን ያህል ለአንድዬ አቤቱታ እናቅርብ ብንል፣ የሆነ ‘ቴክኒካዊ’ ችግር ሳይገጥመን አይቀርም::
አንድዬ፡- ”አሁን ደግሞ ምን አመጣችሁ፣ እርስ በእርስ ከመባላላት የተረፈ ጊዜ አገኛችሁ ማለት ነው!”
«አንድዬ፤ በጣም አጣዳፊ ችግር ገጥሞን ነው…”
“ለነገሩ…ሁሉንም መስመሮች ካለፋችሁ በኋላ አጣዳፊ ችግር ብሎ ነገር ለእናንተ አይሠራም::  እሺ… ምንድነው አጣዳፊው ችግር?”
“አንድዬ፤ ምቀኝነት መድረሻ እያሳጣን ነው”
“ምን አላችሁ? እስቲ ድገሙልኝ”
“ምቀኝነት መሄጃ እያሳጣን ነው…”
“እኔ አኮ እናንተ ሰዎች፤ አንዳንዴ ከአእምሯችሁ ምን፣ ምን ባጎድልባቸው ነው እንዲህ የሆኑት እላለሁ…”
“አንድዬ…  ይህን ያህል ምን ብናስቀይምህ ነው!”
“ራሳችሁ ‘ምቀኛ አታሳጣኝ’ እያላችሁ በተረት ስትለምኑ ኖራችሁ፣ ጭራሽ ምቀኛ መድረሻ አሳጣን ማለት ጀመራችሁ፡፡ የተመኛችሁትን አይደል እንዴ ያገኛችሁት! መጀመሪያ ተረታችሁን ለውጡና ያኔ እሰማችሁ ይሆናል፡፡»
‘ምቀኛ አታሳጣኝ፣’ የሚለውን ተረት ለመለወጥ የብሬክሲት አይነት ሪፈረንደም ነገር ይካሄድልን:: (ዘንድሮ የማይሰማ ‘ጉድ’ ስለሌለ እናጅብ ብለን ነው፡፡)
 “የእኔ ምቀኛ ገና አልተወለደም” ያለው ባለታክሲ ይመቸውማ! ትርፍ ጭኖ በተያዘ ቁጥር በምቀኛ ትራፊክ አያሳብብማ!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 2522 times