Saturday, 24 August 2019 14:12

ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አዲስ ብስራት!

Written by  በጥበቡ በለጠ
Rate this item
(0 votes)

ሔንዝ ሪትማን  ይባላሉ፡፡ በጀርመን አገር BAUVERBANDE. NRW በተባለ ድርጅት ዉስጥ ም/ስራ አስፈጻሚ ናቸዉ፡፡ ድርጅቱ በጀርመን አገር የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ማህበር ነዉ:: በስሩ ከ5ሺ በላይ አባላት አሉት፡፡ ስራውም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ያሉትን ባለሙያዎች የዕዉቀት ክህሎት በመስጠት መርዳት ነዉ፡፡
ሔንዝ ሪትማን ኢትዮጵያ ዉስጥ በተደጋጋሚ በመምጣት በኮንስትራክሽን ዘርፍ አያሌ ፕሮጀክቶችን ሰርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ከዩኒቨርስቲ የሚመረቁ የምህንድስና ተማሪዎችንና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ዉስጥ በልምድ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎችን፣ የተለያዩ ስልጠናዎችን  በመስጠት፣ ሙያዊ ብቃት እንዲኖራቸዉ የሚያስችል ፕሮጀክት ይዘው መጥተዋል፡፡ ይህን ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ጋር በመሆን አዳብረውት፣ አሁን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት ላይ ናቸዉ፡፡
ይህን የኮንስትራክሽን ተግባራዊ ዕውቀት በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስረጽ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸዉን ሔንዝ ሪትማን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ውይይታቸውም ስልጠናው በምን አግባብ መካሄድ  እንዳለበትና የወደፊት ተጨባጭ ውጤቶች ላይም ተነጋግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሔንዝ ሪትማን ሲናገሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዩኒቨርስቲና ከልዩ ልዩ ኮሌጆች የሚመረቁ ተማሪዎች የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ላይ ሰፊ ዕዉቀት ቢኖራቸውም፣ ተግባራዊ እውቀት ላይ ግን አናሳ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሳይኖራቸው በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የተሰማሩትም ኢትዮጵያዊያን፤ በንድፈ-ሀሳቡም ሆነ በተግባራዊ ትምህርቱ ብዙ ገፍተውበት ባለመሄዳቸው፣ ሁለቱንም ወገኖች በጋራ ተግባራዊ ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል:: ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቁት ተማሪዎችና በልምድ ለሚሰሩት ባለሙያዎች፣ በጋራ ተግባራዊ ትምህርት የመስጠት ፕሮጀክት፣ ወደ ኢትዮጵያ ይዘው መምጣታቸውን ሔንዝ ሪትማን ይገልጻሉ፡፡
በዚህ ስልጠና ውስጥ የሚካተቱት ትምህርቶች፣ አንድ የኮንስትራክሽን ኩባንያ እንዴት ተመስርቶ ያድጋል፣ የቢዝነስ ፕላኑ እንዴት ይሰራል፣ የገንዘብ አቅሙን እንዴት ማሳደግ ይቻላል፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃስ እንዴት ያድጋል በሚሉትና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ፣ በአለም አቀፍ ባለሙያዎች ስልጠናው እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ይህ ስልጠና አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከስልጠናው በኋላም አዳዲሶቹ ምሩቃን ተማሪዎች፣ የየራሳቸውን የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በጋራም ሆነ በተናጠል በመክፈት፣ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩበትን አጋጣሚ እንደሚያመጣ ሚስተር ሔንዝ ሪትማን አስረድተዋል፡፡
የዚህን ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ገንዘብ ከየት ታገኛላችሁ ተብለው የተጠየቁት ሔንዝ ሪትማን፣ ገንዘቡ ከጀርመን የገንዘብ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚገኝ ሲሆን የሚያስተባብረው ሴኳ/ Sequa/  የተባለው የጀርመን ድርጅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲም፣ የሀሳቡ ደጋፊ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በመጨረሻም በዚህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊያን የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባሻገር ለሀገርም በሙያው የዳበረ የኮንስትራክሽን ባለሙያ መፍጠር እንደሚያስችል አውስተዋል፡፡ በሂደትም ከአለማቀፉ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ የሚሆኑ ድርጅቶችንም ኢትዮጵያ ውስጥ ማብቃት እንችላለን ብለዋል፡፡

Read 2336 times