Saturday, 24 August 2019 14:08

‹‹ኢትዮ ስኳር የቀዩን ዝሆን ገናና ታሪክ ለመመለስ እየተጋ ነው››

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

- የአክሲዮን ዋጋ ከ10 ሺ ብር እስከ 50 ሚ.ብር ይደርሳል
         - የስኳር ምርት አዋጪ ሥራ ነው፤ ኪሳራ የለውም


          የወንጂ አካባቢ ተወላጆችና የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የቀድሞ ሰራተኞች ያቋቋሙት ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር፤ የወንጂና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎችን ከመንግስት ላይ ለመግዛት በዝግጅት ላይ መሆኑን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቢተው ዓለሙ ይገልጻሉ፡፡ መንግስት ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ከ10 በላይ የሚሆኑ የስኳር ፋብሪካዎችን ለግል ባለሀብቶች አዘዋውሮ ለማጠናቀቅ ማቀዱን አስታውቋል፡፡ ኢትዮ ስኳር፤ በቀዳሚነት ያነጣጠረው ግን የወንጂና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች ላይ ነው፡፡ ያለ ምንክንያት ግን አይደለም፡፡ ከእነዚህ ቀደምት የስኳር
ፋብሪካዎች ጋር የተለየ ቁርኝት ስላለን ነው ይላሉ - የአክሲዮን ማህበሩ አደራጆች፡፡ የቀዩን ዝሆን ገናና ታሪክ ለመመለስም ኢትዮ ስኳር እየተጋ መሆኑን አቶ ቢተው ጠቁመዋል፡፡ ለመሆኑ ‹‹ቀዩ ዝሆን›› ምንድን ነው? የጥንቱ ገናና ታሪክስ? ከጥቂት ወራት በፊት የጀመሩት የአክሲዮን ሽያጭ ከምን ደረሰ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር ቀጣዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እነሆ፡-


       ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር እንዴት ነው የተመሰረተው?
ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር ለመፈጠሩ ምክንያት የሆነው የመንግስት ለውጥን ወይም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ፣ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ያሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡ እርግጥ ከዚህ ቀደም ሀሳቡ በውስጣችን ነበር፡፡ አሁን ሀሳቡን እውን ለማድረግ ከላይ እንደገለጽኩት፣ መንግስት በስሩ ያሉትን የስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግል ዘርፉ የማዘዋወር ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ሲያሳውቅ ነው፣ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ የገባነው፡፡
መንግስት በስሩ 13 የስኳር ፋብሪካዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ እናንተ ያነጣጠራችሁት ግን ወንጂና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች ላይ ነው፡፡ ምክንያታችሁ ምንድን ነው?
ጥሩ! እኛ አክሲዮን ማኅበሩን ያደራጀነው የወንጂ ተወላጆች ነን፡፡ ወንጂ መወለዳችን ብቻ ሳይሆን በአገራችን የስኳር ኢንዱስትሪ ታሪክ የሚጀምርበትም ሥፍራ ጭምር ነው - ወንጂ::  አያቴም አባቴም በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ነው ሲሰሩ የነበሩት፡፡ እኔም ለዚህ ፋብሪካ ሶስተኛ ትውልድ ነኝ፡፡ ይህንን አክሲዮን ማኅበር ያቋቋሙት አብዛኞቹ ወንጂ የተወለዱ፣ ከፊሎቹ ደግሞ በእነዚህ የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ እስከ ከፍተኛ አመራርነት ድረስ ያገለገሉ የቀድሞ ሰራተኞች ናቸው፡፡ በዚያን ወቅት ወንጂ እንደ ምድረ ገነት የሚቆጠር አካባቢ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን አካባቢው በጉስቁልናው ወደር የማይገኝለት፣ እጅግ የሚያሳዝን ደረጃ ላይ መድረሱ  ቁጭት ፈጥሮብናል፡፡ ቀድሞ እነ ምድር ጦር፣ እነ መቻልና እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሳሰሉት ክለቦች፣ እዚያ ሄደው እግር ኳስ ይጫወቱበት የነበረ ገነት የሆነ ቦታ፤ አሁን ተራቁቶ ስናየው፣ ያንን የቀድሞውን ልምላሜ እንናፍቃለን፡፡ ያንን ልምላሜና የቁዩን ዝሆን የስኳር ታሪክ ለመመለስ ነው አክሲዮን ማኅበሩን ያቋቋምነው፡፡ በአሁኑ ሰዓትም አክሲዮኑን በጥሩ መልኩ እየሸጥን ነው፡፡
ወንጂን አሁን ለኪሳራ የዳረገው ምንድን ነው ይላሉ?
የችግሮቹ ዋና ዋና መንስኤዎች የምንላቸው በርካታ ናቸው፡፡ አንደኛው፤ ቀደም ሲል ፋብሪካዎቹ የራሳቸው የአሰራር ሥርዓትና ባህል ነበራቸው፡፡ ፋብሪካውንና አሰራሩን ይበልጥ ለማዘመን በሚል ሰበብ የአካባቢውን፣ የማህበረሰቡንና የድርጅቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱ፤ እንዲሁም ቀድሞ የነበረውን ሰራተኛ አበረታትቶና አቅሙን ገንብቶ ስራውን ማስቀጠል ሲገባ፣ ይህ ሳይደረግ መቅረቱ በመንስኤነት ይጠቀሳል፡፡ በሌላ በኩል፤ መንግሥት አገር ውስጥ ያለውን የስኳር ምርት ለማሳደግ ፈልጎ ተጨማሪ 10 ፋብሪካዎችን ገነባ። ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ውስን የስኳር ምርት ባለሙያዎች ወንጂ፣ መተሃራና ፊንጫ ይገኙ ስለነበር እነዚህን ውስን ባለሙያዎች ለ10 አዳዲስ ፋብሪካዎች እያነሳ ሲወስድ፣ የባለሙያ እጥረትም ተፈጠረ፡፡ እነዚህ ለወንጂ ስኳር ፋብሪካና ለአካባቢው መዳከም ምክንያት ነው ብለን እናምናለን፡፡
በአሁን ሰዓት ኢትዮ ስኳር አክሲዮን ማኅበር፤ አክሲዮኖችን በመሸጥ ላይ ነው፡፡ ማስታወቂያም በተለያዩ ሚዲያዎች እየለቀቃችሁ ነው፡፡ ወንጂና መተሃራ ስኳር  ፋብሪካዎችን ልትገዙ የምትችሉበት እድል ምን ያህል ነው? ሎጎውስ እንዴት ቀይ ዝሆን ሊሆን ቻለ?
ከሎጎው ብንጀምር፤ ልክ ነው ቀይ ዝሆን ነው፡፡ የቀድሞውን ወንጂ ስኳርን ይመስላል ግን አይደለም:: የእኛ ዋና ፍላጎትና ዓላማ፤ ያንን ዘመን መመለስ ነው፡፡ ያ የቀይ ዝሆን ዘመን ሲባል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣፋጭ የቀመሱ ሁሉ ሁኔታውን የሚያገናኙት፣ ከቀዩ ዝሆን ጋር ነው፡፡ ደስታ ከረሜላን ብንወስድ፣ ይህን ከረሜላ የሚበሉ ሰዎች፣ የከረሜላው ሽፋን ላይ ያለውን ቀይ ዝሆን አይረሱትም፡፡ እንግዲህ ያ የቀዩ ዝሆን ዘመን ማለት፣ ፋብሪካው ውጤታማ የነበረበት፣ አሁን እየታየ ያለው ጉስቁልናና ችግር ያልነበረበት፣ እኛም ልጅነታችንን በደስታ ያሳለፍንበት ዘመን ነው፡፡ ስለዚህ ቀዩ ዝሆን፤ የእነዚህ ስኬቶች ሁሉ ምልክት ነው፡፡ እኛም የቀዩን ዝሆን ታሪክ መመለስ ስንል፣ የዝሆኑን ምስል ብቻ አይደለም፤ ስኬቱን ታሪኩን ማህበረሰባዊ ትስስሩንና መስተጋብሩንም ጭምር እንጂ። ለዚህ ነው ሎጎውን ቀይ ዝሆን ያደረግነው፡፡
ወንጂን ልትገዙ የምትችሉበት እድል ምን ያህል ነው ላልሺው፣ ዕድሉ ጠባብ ነው የሚያስብል ነገር የለም፡፡ እኛ ተወዳድረን እንገዛለን ብለን ነው እየተጋን ያለነው፡፡ ከተወዳዳሪዎቻችን የተሻለ አቅም አለን ብለን እናስባለን፡፡
ከተፎካካሪዎቻችሁ በምንድን ነው  ነው የምትሻሉት?
አንደኛው፤ እኛ ይህንን ዘርፍ በደንብ እናውቀዋለን:: ተወልደን አድገናል፤ በፋብሪካዎቹ ውስጥ ሰርተናል:: አሁን ፋብሪካዎቹ ለምን እንደደከሙ እናውቃለን:: እንዴት አገግመው ወደ ቀድሞ ውጤታማነት ሊመለሱ እንደሚችሉም ጠንቅቀን እናውቃለን:: መንግስትም ስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግሉ ዘርፍ አዘዋውሮ የሚሸጣቸው’ኮ ምርታማነታቸው እንዲሻሻል ነው፡፡ ምርታማነትን ለማሻሻል ደግሞ በዘርፉ ልምድና እውቀት ያለው የሰው ሀይል ወሳኝ ነው፡፡ እውቀቱንም ልምዱንም በማሰባሰብ፣ ኢትዮ ስኳር በጥሩ ቁመና ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው ብለን በፅናት እናምናለን፡፡ መንግስትም ገንዘብን ብቻ ግብ እንደማያደርግ እርግጠኞች ነን፡፡ ለምን ቢባል፣ አንድ ኩባንያ ከፍተኛ ገንዘብ ከፍሎ ሊገዛው ይችላል:: ተመልሶ ውጤታማ ካልሆነና፣ ያ ገንዘብ ከውጭ ስኳር ለማስገባት የሚውል ከሆነ፣ መንግስት ኪሳራ ውስጥ ገባ ማለት ነው። ስለዚህ ምርታማነትን የሚያሻሽል ድርጅት፣ መንግስት በመፈለግ ላይ በመሆኑ፣ እኛ ለዚህ እንመጥናለን ብለን እናምናለን:: አሁን ባለው መረጃ፣ አገራችን 8 ሚ.ኩንታል አመታዊ ፍጆታ አላት፡፡ ከ3-4 ሚ.ኩንታል በአገር ውስጥ ይሸፈናል፡፡ ቀሪው ከ4-5 ሚ.ኩንታል ከውጭ ይገባል ማለት ነው፡፡ እነዚህን ክፍተቶች መሙላት የሚቻለው ስራ ላይ የነበሩት በሙሉ አቅማቸው ሲሰሩና አዳዲሶቹም ተጠናቅቀው ወደ ስራ ሲገቡ ነው፡፡
መንግስት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ፤ ስኳር ፋብሪካዎቹ በ6 ወራት ውስጥ ፕራይቬታይዝ ተደርገው እንደሚጠናቀቁ ጠቁሟል፡፡ እናንተ፤ መንግስት ለፋብሪካዎቹ የሚያቀርበውን ዋጋ በዶላርም ይሁን በብር በ6 ወር ውስጥ ከፍላችሁ ለመረከብ ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ? በቂ አቅም አላችሁ?   
አሁን የተባለውን ነገር መንግስት በይፋ ግልጽ አድርጓል፡፡ ፋይናንስ ሚኒስቴር፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ግል ተዘዋውረው  እንደሚያልቁ ገልጿል። ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግልጽ አስቀምጠውታል። ይሄ ነገር ያስፈለገው ለሶስት ነገሮች ነው፡፡ አንደኛው፤ ዋጋ ትመና አልተሰራምና ትመናው ይሰራል፡፡ ሁለተኛው፤ እነዚህ ኩባንያዎች ስኳር ኮርፖሬሽን በሚባል አንድ ተቋም ውስጥ ነው ያሉትና እያንዳንዱ ኩባንያ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ይደረጋል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ፤ የስኳር ተቆጣጣሪ አካል (Regulatory Body) ይደራጃል፡፡ ለነዚህ ሲባል ነው መግለጫው የወጣው፡፡ እርግጥ ነው ጊዜው አጭር ነው፡፡ እኛም  ለዚህ ስንል ነው ሰዎችን በትጋት እየጋበዝንና አክሲዮን እንዲገዙ እያደረግን ያለነው፡፡ እንዲህ አይነት ትልቅ አገራዊ እድል ከዘመናት በአንዱ አጋጣሚ የሚከሰት ነው፡፡ ፈረንጆቹ፤  ‹‹Once in a blue moon›› እንደሚሉት:: እናም ይህ ዕድል እንዳያመልጠን፣ ለመግዛት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ በእኛ አቅም የሚሸፈነው ይሸፈናል፡፡  ከእኛ አቅም በላይ ለሆነው የውጭ አገር አጋሮች ስላሉን፣ እነሱ እንዲሸፍኑት አድርገን እንገዛለን፡፡
ወንጂና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ነግረውኛል፡፡ በምን ያህል ጊዜና የገንዘብ ወጪ አገግመው ወደ ስራ ይገባሉ?
እኛ ጥናት አስጠንተናል፡፡ ለምሳሌ የወንጂን ብንወስድ፣ በሄክታር እስከ 180 ኩንታል ይገኝበት ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ 80 ኩንታል ወርዷል፡፡ በሄክታር እስከ 220 ኩንታልም የተገኘበት ወቅት እንደነበር ይነገራል፡፡ አሁን በሄክታር 80 ኩንታል ብቻ መድረሱ ምን ያህል እንዳሽቆለቆለ በቂ ማሳያ ነው፡፡ እኛ ፋብሪካውን ብንገዛው፣ ያለንን ልምድ ያካበተ የሰው ሃይልና ጥሬ ዕቃ ይዘን እንዲሁም ብቃት ባለው ባለሙያ እያሰራን ብናስቀጥለው፣ አሁን ካለው በ50 በመቶ ማሻሻል እንችላለን፡፡ በጥናቱ መሰረት፤ ወንጂ ከ3-5 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅም የማምረቻ ብቃቱ ላይ ማድረስ እንችላለን፡፡ በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዲችል 14 ሺህ ሄክታር መሬት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለን መረጃ፤ ፋብሪካው ያለው 9 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ነው:: ከዚህ ውስጥ 7 ሺህ ሄክታሩ በመንግስት የተያዘ ሲሆን ቀሪው የአካባቢው አርሶ አደር መሬት ነው። ስለዚህ 14 ሺህ ሄክታር መሬት ለማድረስ ተጨማሪ 5 ሺህ ሄክታር መሬት ያስፈልገናል ማለት ነው። ይህንን ለማድረግ አርሶ አደሩን አሳምኖ፣ ሸንኮራ ወደ ማምረት የመመለስ ስራ ይጠብቀናል፡፡
ከ40-60 ሺህ የሚደርስ የአካባቢውን ማህበረሰብ፣ የአክሲዮን ባለድርሻ ለማድረግ እየሰራን ነው ብላችኋል፡፡ እስቲ ሁኔታውን ያብራሩልኝ…
ሰራተኞችና አርሶ አደሮች ይሳተፉ ስንል በምክንያት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሲሳተፉ በባለቤትነት ስሜት በደንብ ይሰራሉ፡፡ ይሄ ምርታማነትንም ያመጣል፤ የኢንዱስትሪ ሰላምንም ያሰፍናል፡፡ አርሶ አደሩም ባለድርሻ ከሆነ ባለቤትነት ይሰማዋል፤ ፋብሪካውን ይጠብቃል ይንከባከባል፡፡ ይህን ሲያደርግ ሁለት አይነት ጥቅም ያገኛል፡፡ አንደኛ ከሸንኮራ ሽያጭ ይጠቀማል፣ ሁለተኛ ፋብሪካው ሲያመርት ባለድርሻ በመሆኑ ተጠቃሚ ነው:: ሶስተኛም፤ የስራ እድል የሚያገኝበት በመሆኑ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በሌላ በኩል እንደ አገር እውነቱን ስንነጋገር፣ መንግስትም ይሄንን ነገር በደንብ አስቦበታል ብለን እናምናለን፡፡ በሌላ በኩል፤ ኢኮኖሚያዊ አቅምና ሀይልም የሚመጣው በእንደዚህ ያለ መልክ ነው፡፡
አርሶ አደሩንና የአካባቢውን ህዝብ ባለአክሲዮን ለማድረግ ስናስብ፣ ባይችሉና አቅም ባይኖራቸውስ ብለን፣ ከአምስት ባንኮች ብድር አመቻችተንላቸዋል፡፡ ለ40ሺህ ሰው፣ የ800 ሚ. ብር ብድር (ለእያንዳንዳቸው 20ሺ ብር ማለት ነው) አመቻችተናል፡፡ ብድሩ በአምስት ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ ነው፡፡ ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ ለአርሶ አደሮች ያለ ኮላተራል (ያለ መያዣ) አበድራለሁ የሚል ቃል ገብቷል፡፡ ይህንን ወደ አፈፃፀም ወስደን ስራ እንጀምራለን፡፡
የአርሶ አደሩ ምላሽ እንዴት ነው? ደስተኛ ነው?
በመሰረቱ እኛ እንዲህ እናደርግላችኋለን አላልናቸውም፡፡ ማህበረሰቡ ‹‹እኛ የፋብሪካው ባለቤት መሆንና መሳተፍ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ዝቅተኛ ብላችሁ ያስቀመጣችሁትን ገንዘብ እንኳን አውጥተን አክሲዮን ለመግዛት አቅም የለንም፤ በምንችለው መጠን ለ10ም ለ20ም እየሆንን እያዋጣን እንገዛለን›› የሚል ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ይህንን ሃሳባቸውን መነሻ አድርገን፣ ፍላጐታቸውን አጢነን ነው፣ ከባንክ ብድሩን ያመቻቸንላቸው፡፡ በዚህም መንግስት ተጠቃሚ ነው፡፡ ፋብሪካው የእኛ ሊሆን ነው በሚል፣ ካለፈው አመት ጀምሮ፣ ሠራተኛው በደንብ እየሰራ ነው የከረመው፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡
በምታስነግሯቸው ማስታወቂያዎች ላይ የምትገዟቸውን ፋብሪካዎች ስም አትገልፁም፡፡ ሰው እንዴት ነው አክሲዮን እየገዛ ያለው?
ማስታወቂያው መለቀቅ ከጀመረ በኋላ የአክሲዮን ሽያጩ አበረታች ነው፡፡ እውነት ነው፤ የምንገዛቸውን ፋብሪካዎች ስም አልገለጽንም፡፡ እነዚህን ፋብሪካዎች ለመግዛት ፍላጐት ያለው ድርጅት ቢኖር እንኳን በሰው ንብረት ላይ “ይሄን ይሄን ልገዛ ነው” ብሎ መናገር ተገቢ ባለመሆኑ ነው የማንገልጸው፡፡ ይሄ ማለት ፍላጐታችንን አልገለጽንም ማለት አይደለም:: መንግስት በይፋ ጋብዞን፣ “የትኛውን ፋብሪካ ትገዛላችሁ” ብሎ 16 መጠይቆችን አስቀምጦልን፣ ከ1-3 ያሉ ምርጫዎቻችንን ገልፀናል፡፡ 1ኛ ፍላጐታችን ወንጂና መተሃራ ሲሆን እንደ ሶስተኛ አማራጭ፣ ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካ ብለን ገልፀናል፡፡ ኩራዝ አምስትንም በአማራጭነት ስናስቀምጥ ዝም ብለን አይደለም፤ ልምድ እንዳለን ነግረንሻል፡፡
ሸንኮራ አምርቶ የመሸጥ ፍላጐት አለን፡፡ በተለያየ ምክንያት ከስኳር ዘርፍ የወጡ ባለሙያዎችን አሰባስበን እንደምንሰራና ውጤታማ እንደምንሆን እርግጠኞች ነን፡፡ የስኳር ፋብሪካው ስም ባልተገለፀበት ሰው እንዴት ነው አክሲዮን የሚገዛው ላልሽው ግልጽ ነው፡፡ ስኳር አዋጪ ስራ በመሆኑ ነው፡፡ ስኳር ላይ ኪሳራ የለም፡፡ የገበያ ክፍተቱም በጣም ሰፊ ነው፡፡ የስኳርን ያህል ትርፋማ የሚሆን ሴክተር የለም፤ ምክንያቱም 90 በመቶ ጥሬ እቃ አገር ውስጥ አለ፡፡ ተረፈ ምርት ብዙ ሥራ አለው፡፡ ለዚህ ነው ስኳር ፋብሪካ፤ የፋብሪካዎች እናት ነው የሚባለው:: በተረፈ ምርቱ እንኳን እስከ 30 ዓይነት ምርቶችን ማምረት የሚችል ነው፡፡ ከስኳር ቀጥሎ ሞላሰስ አለ፡፡ ሞላሰስ ማለት ብዙ ነገር ነው፡፡ ኢታኖል አለ፤ ለከብት መኖ፣ የፕላስቲክ ምርት መሆን ይችላል፡፡ ሸንኮራ አኝከሽ የምትጥይው፣ ችቡድ መስሪያ ይሆናል፤ ሲነድ ደግሞ ሀይል ያመነጫል፡፡ በሞላሰስ ከብት ማደለብና የስጋ ምርትን በመጨመር የስጋን ዋጋ መቀነስ ይቻላል:: ብቻ ምን አለፋሽ… እጅግ አትራፊ ዘርፍ ነው፡፡ ከሰልና ወረቀት ማምረት ይቻላል፡፡ የሸንኮራው ጫፍ ለከብት መኖ ይሆናል፡፡ ጥቅሙ ተዘርዝሮ አያልቅም:: ለፋብሪካዎቹ ተብሎ የተቆፈሩ ኩሬዎች አሉ፡፡ እዛ ውስጥ አሳ ማርባት ይቻላል፡፡ ከረሜላ ፋብሪካም ሌላው የዚህ ዘርፍ ትሩፋት ነው፡፡ በሌላው አለም “ሹገር ስቴት” ነው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም ፋብሪካው ውስጥ የሰራተኛው መኖሪያ፣ ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያና በርካታ ነገሮች ያሉበት ትልቅ ቦታ ነው፡፡
በመጨረሻ-- እስቲ አክሲዮን መግዛት ለሚፈልጉ ጥቂት መረጃ ይስጡልኝ…
እኔ እንግዲህ የወንጂን ታሪክ ሳስብ ብዙ ነገር ነው የሚመጣብኝ፡፡ ለምሳሌ ሌላው ስኳርን በማንኪያ ነው የሚያውቀው፡፡ ነገር ግን ከጅምሩ አንስቶ ስኳር እስኪሆን ድረስ ያለውን ሂደት ማየት፣ በራሱ ሌላ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ወንጂን ያቆመው ሌላው ነገር፣ ጠንካራው ማህበራዊ ትስስሩ ነው፡፡ ማህበራዊ ትስስሩ የተፈጠረው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ስኳር ለማምረት የተፈጠረ ትስስር ነው፡፡ የስኳር ሰራተኛን ይዘሽ አቆይተሽ፣ የስራውን ባህሪና ሁኔታ ባህል እስኪያደርገው ድረስ ማስተማር አለብሽ፡፡ ወንጂ የነበረው አሰራር ይሄ ነው፡፡ አሁን ያንን ለመመለስ ነው እየጣርን የምንገኘው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አክሲዮን በመግዛት፣ የዚህ ታሪክ ተቋዳሽ እንዲሆን ጥሪ እያቀረብን ነው፡፡ በአሁን ሰዓት አክሲዮን በጥሩ ሁኔታ እየሸጥን ነው ያለነው:: የአንድ አክሲዮን ዋጋ 1ሺ ብር ሲሆን፤ በትንሹ አንድ ሰው 10 አክሲዮኖችን (10ሺህ ብር) መግዛት አለበት:: ትልቁ የአክሲዮን ሽያጭ ደግሞ 50 ሺህ አክሲዮን (50 ሚ.ብር) ነው፡፡ ይሄ የማይገኝ ዕድል ነው፤ ኑና  ግዙ እላለሁ፡፡  

Read 3225 times