Saturday, 31 August 2019 12:56

“የማትፈልገው ገንዘብ ካለህ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


           “የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል …በአገልግሎት መስጫዎች አካባቢ ኦምሌታቸውን ሲቀረጥፉ አርፈደው (ቅናት አይመስልብኝም!) በፈለጋቸው ሰዓት እየመጡ “ልዩ እንክብካቤ ይደረግልን” አይነት የሚያሰኛቸው ሰዎች አይገርሟችሁም! ስንተኛ ሰማይ ላይ ነን ብለው ነው የሚያስቡት?!--»
        
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰልፉ ረጅም ነበር…የመብራት ሂሳብ ለመክፈል:: ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ የቆሙ ሰዎች ነበሩ:: የሆነች ሸላይ ቢጤ ሴትዮ ትመጣለች፡፡ የመኪና ቁልፏን እያሽከረከች፣ ሶፍትዌር ተጽፎለት የተሰጣት በሚመስል የውሀ ልክ አይነት አረማመድ ቀጥታ ወደ በሩ መክፈያው በር አመራች፡፡ ጥበቃዎቹ ተሰልፋ ተራ መያዝ እንዳለባት ነገሯት፡፡ ታዲያላችሁ… የሆነ ካንሰርን ድምጥማጡን የሚያጠፋ መድሀኒት ልትፈለስፍ አርባ ሰባት ደቂቃ የቀራት ይመስል ኮስተር ብላ…
“በጣም አስቸኳይ ሥራ አለብኝ” አለች፡፡
 ቢሆንም፣ ተራ ሳትይዝ መግባት እንደማትችል ተነገራት፡፡ በተዘዋዋሪ አነጋገር ጥበቃዎቹ… “ይቺ ስልክ አስደውላ የእንጀራ ገመዳችንን ታስበጥስብናለች” አይነት እንዲሰጉ በሚያደርግ አይነት ደጋግማ፣ በጣም ከባድ ሥራ እንዳለባት ተናገረች፡፡ እንኳን ስጋት ሊያድርባቸው እነሱ በተራቸው…አለ አይደል… በ“አትረብሺን፣ ሥራችንን እንስራበት…” አይነት ኮስተር አሉ፡፡
“እባክሽ መግቢያውን ልቀቂልን” ተባለች፡፡
ወደተሰለፈው ህዝብ ዘወር ብላ አሁንም፣ “በጣም ከባድ ስራ ትቼ ነው የመጣሁት” አለች:: (ይህ አባባሏ…“እኛ እኛ ሥራ ፈቶች ነን!” ተብሎ ቢተረጎም፣ “የዘንድሮ ፖለቲካችን ‘ያጎናጸፈን ታለንት’ ነው” በሚል የባለቤትነት መብቱን እናስተላልፍ ነበር:: የምር ግን የሚያስፈራ ነገር ቢኖር “ሰላም አደርክ?” ያልነው ሰው…“እና ምን ሆኜ እንዳድር ፈልገህ ነበር!” እንዳይለን ነው፡፡ ይህን ያህል ነው የነገር ‘የውስጥ ለውስጥ ማሳበሪያ’ መንገድ የበዛው፡፡)
እናላችሁ… ሴትየዋ “በጣም ከባድ ስራ ትቼ ነው የመጣሁት” ስትል ዝም ብሎ የነበረው ሰው ሁሉ አጉረመረመ፡፡ “እኛም ስራ ትተን ነው የመጣነው” ተባለ፡፡ የታህሪር አደባባይ አመጽ አይነት ሊነሳባት መስሏትም ሊሆን ይችላል መኮሳተሯ ጠፋ፡፡ ይሀን ጊዜ ግን አንድ ሰው “ግዴለም፣ እንፍቀድላትና ትግባ፣ አንድ ሰው አይጎዳንም” አሉና ተፈቀደላት፡፡ ገብታ፣ ከፍላ ስትወጣ ግን አይደለም፣ “አመሰግናለሁ”፣ አይደለም፣ “እግዜር ይስጥልኝ” ማለት ዘወር ብላ እንኳን ሳታይ፣ ቁልፏን እያንቃጨለች ሄደች፡፡ የሆኑ ወጣቶች፣ ለመጻፍ ትንሽ የሚያስቸግሩ ነገሮች ጣል፣ ጣል አደረጉ፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል …በአገልግሎት መስጫዎች አካባቢ ኦምሌታቸውን ሲቀረጥፉ አርፈደው (ቅናት አይመስልብኝም!) በፈለጋቸው ሰዓት እየመጡ “ልዩ አንክብካቤ  ይደረግልን” አይነት የሚያሰኛቸው ሰዎች አይገርሟችሁም! ስንተኛ ሰማይ ላይ ነን ብለው ነው የሚያስቡት?! በተለይ እጅ ላይ መኪና ቁልፍ ካለችማ…“በሁሉም ስፍራ ቅድሚያ ይሰጠው” የሚል ‘የንጉሥ አይከሰስ’ ፈቃድ የተሰጣቸው ነው የሚመስሉት፡፡| ደግሞ ‘ዘንድሮ ማንም ለሚጫወትበት’ መኪና! ቂ…ቂ…ቂ… (ልጄ አልታወቀልንም እንጂ…ስንት ሀገር በቀል ‘አኔስቴዝያ’ አለን መሰላችሁ፡፡)
እናላችሁ…መተባበር፣ መተጋገዝ ምናምን የሚባሉት የአብሮ መኖር እሴቶች እየጠፉ ነው በሚባልበት በአሁኑ ጊዜ፣ የማይገባን ነገር ተደርጎልን እንኳን “አመሰግናለሁ…” ማለቱ ዳገት ይሆንብናል::  ምንም ይሁን ምን ለተደረገልን ትብብር አንዲት “አመሰግናለሁ…” የምትል ቃል ማውጣቱ ማንን ገደለ?!
ደግሞ እኮ ሰልፉ ላይ በአብዛኛው ደከምከም ያሉ እናቶችና አባቶች ናቸው የነበሩት፡፡
እዚሁ ቦታ ላይ ነው፣ ሴትየዋ ሄዳ ብዙም ሳይቆይ፣ አንዲት በጉልምስና ውስጥ ያሉ ሴት ይመጣሉ፡፡ እሳቸውም ቀጥታ ወደ በሩ ሄደው ቢሆን ካልገባሁ አሉ፡፡ ተሰልፈው ተራ እንዲይዙ ተነገራቸው፡፡ እስከዚያ ድረስ ፈታ ብሎ የነበረ ገጽታቸው በአንድ ጊዜ ዳመነ፡፡ “አሞኝ እኮ ነው፣ መቆም አልችልም” አሉ…እንደ በኪንግሀም ቤተ መንግስት ዘብ ቀጥ ብለው ነው እኮ!
በድጋሚ መሰለፍ እንዳለባቸው ተነገራቸው፡፡ ተራውን ወደሚጠብቀው ሰው ዞረው መለማመን ጀመሩ፡፡ በሸላዩዋ ሴት የተበሳጨው ህዝብ ግን አልሰማቸውም፡፡ አንዲት እናት “እኛም አሞናል” አሉ፣ ቁመናቸውም ያንኑ የሚሳይ ነበር፡፡ ሌሎችም “ማን ያላመመው አለና ነው!” አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ማኒፌስቶ የሚመስል ተቃውሞ አሰሙ፡፡
(እኔ የምለው…ሀሳብ አለን፣ የፖለቲካ ‘ቡድኖቻችን’ ገና የሀገራችንን ሁኔታ ‘እያጠናችሁ’ ቢሆንም፣ የሆነ ‘ማኒፌስቶ’ ነገር የማትበትኑልንማ! ችግር የለውም እኮ…ገጾቹን በሙሉ ባዶ አድርጋችሁ፣ “የምንቃወማቸውን ነገሮች ስንለይና ምን አይነት መስመር እንደምንከተል ስንወስን የሚሞሉ ገጾች” ብላችሁ ብትበትኑት እኛ ‘ችግራችሁን’ እንረዳላችኋለን፡፡ “ዝም ብለው አዳራሽ ማሞቅ…” እየተባላችሁ የፌስቡክ ፕሮፋይል ምናምን ነገር እንዳትሆኑ ለመጠቆም ያህል ነው፡፡  ቂ…ቂ…ቂ… “ወደው አይስቁ” የሚለው አሪፍ አባባል ኮፒራይቱ የማነው?)
እናላችሁ…ሸላይዋ ሴትዮ እንድትገባ ሀሳብ አቅርበው የነበሩ ሰውዬ… “ይልቅ ሰው ሳይበዛብሽ ሰልፍ ያዥ” አሉ፡፡ ሴትየዋ ግን ወይ ፍንከች፡፡ የሌለ ግድግዳ ለመደገፍ በሚመስል እጃቸውን እየዘረጉ መለማመናቸውን ቀጠሉ፡፡ እንባ ሊፈሳቸው ይመስል ፊታቸው ቅጭም አለ፡፡ (ወይ ‘ሪያሊቲ ሾው’ ነገር ማጣት!) እንደ ምንም እንዲገቡ ተፈቀደላቸውና ገቡ፡፡ ከፍለው ሲወጡ አንዲት ቃል ሳይተነፍሱ ዘወር ብለው የተሰለፈውን ሰው ያዩበት ፈገግታ፣ ምን ልበላችሁ፣ ‘ቆሽት’ የሚባለውን ነገር ድብን የሚያደርግ ነበር፡፡ አለ አይደል… “እኔ ልጅት፣ ሠራሁላችሁ!” አይነት ፈገግታ ነው፡፡ ደግሞላችሁ…ሲራመዱበት የነበረው ፍጥነት አይደለም መታመም፣ ‘ማስ ስፖርት’ እየሠሩ ያሉ ነበር የሚመስለው፡፡
የእውነት ምን ነካን! እድሜ ትልቅ ነገር አይደል እንዴ!
እኔ የምለው…እግረ መንገድ ይሄ የብድር ነገር…በዚሁ ከቀጠለ ለመተሳሰቢያ የሚሆኑ አቅም ያላቸው የሂሳብ ‘ማሽኖች’ ማግኘት እንዳንቸገራ!  ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ካገኘነው ስፍራ ሁሉ ብድር መውሰድ የምናበዛ ሰዎች እኮ አንድ መመሪያ አለችን… “ወይ አበዳሪ፣ ወይ ተበዳሪ ይሞታል” የምንላት፡፡ አለ አይደል… ተበድረን ዘወር ካልን በኋላ …“መክፈያው ጊዜ ሳይደርስ የእሷን መጨረሻ ካላሳየኸኝማ!” ብለን የምንለማመን ነው የሚመስለው፡፡ እናማ…ይቺ መመሪያ በሀገራት ላይም ትሠራለች እንዴ!? እንደው ቀጥ ያለውን ነገር አዙሬ፣ አሽከርክሬ ሳስበው፣ ከሀምሳ ምናምን ሀገራት መበደራችን ሲታወቅ ሁሉም “ከዚህ ሁሉ  ሀገር ወስደው የእኛን መቼ ሊመልሱልን ነው!” ብለው በየሀገራቸው ህዝቡ ከቀበሌ ጀምሮ ተወያይቶ ይወስን እንዳይሉ እሰጋለሁ፡፡ (ስሙኝማ…እናቶቻችንና እህቶቻችን አብሲት ከሚያዞሩበት በብዙ እጥፍ በበለጠ ፍጥነት ‘ነገር’ ማዞር የሚቻልበት ዘመን ላይ መድረሳችን፣ ዩ.ኤን.ዲ.ፒ. ምናምን ‘ኢንዴክስ’ ውስጥ ይካተትልንማ!)
በነገራችን ላይ ሀምሳ ነው ምናምን ከሚሆኑ ሀገሮች ተበድረናል ሲባል፣ ከገንዘቡ ባሻገር የሚያሳስበን፣ የትኛውም ሀገር ቢሆን ‘ለወለድ’ ምናምን ብቻ ብሎ እንደማያበድር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ…እኛ እኮ አበዳሪ ሲባል ከሶስትና አራት ሀገራት በላይ ያሉ አይመስለንም ነበር፡፡ ያ ሁሉ ሀገር እውነት የሚያበድረው ገንዘብ እየተረፈው ነው ወይስ የሆነ “ሿ…ሿ…” ምናምን ነገር አለበት?!
እኔ የምለው… ሀገራት ሲበዳደሩ…“ስሙ… የማትፈልጉት ገንዘብ ካላችሁ አንድ፣ ሀምሳ ሚሊዮን ዶላር ልታበድሩን ትችላላችሁ?” ምናምን ነው የሚባባሉት? አይ… ብዙ ነገሮች ግራ እየገቡን ስለሆነ ‘ግልጥና ግልጥ’ ይሁን ብለን ነው፡፡ 
ስሙኝማ…በዓል እየደረሰ ነው፡፡ መቼም ዘንድሮ የካላንደሩም፣ ከካላንደሩ ውጪም ያለ ‘በዓል’ ይዞልናል፡፡ የምር ግን…በዓል እኮ “ሪፈራል ካልተጻፈ” “ሜዲካል ቦርዱ ካልፈቀደ” የሌለባት አሪፍ ‘አኔስቴዚያ’ ምናምን ነገር ነች፡፡ እያስጨፈረች ብቻ ሳይሆን እያስለቀሰችም የተወሰኑ ቀናት ታደነዝዛለች..በበዶ ትሪ ቢሆንም ማለት ነው፡፡ ስንት ወር ሙሉ… “የዘንድሮ ኑሮ እንደው ብን ብለሽ ከአገር ጥፊ እያሰኘኝ ነው” ስንል ከርመን በዓል ሲመጣ ግን ፊታችን ይበራል፡፡ የምር እኛ ራሳችን ባልበላነው ቅባት የበዓል ሰሞን ፊታችን ማብራቱ የምር ‘መጠናት’ አለበት፡፡ ‘መጠናት’ እንደሁ…“አቋሙ ምንድነው?”፣ “የእነማን ደጋፊ ነች?” እየተባለ የለመድነው ስለሆነ እንችለዋለን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2470 times