Saturday, 31 August 2019 13:15

ማልዶ - ሁለት ማለዳ

Written by  ብሩክ
Rate this item
(9 votes)

ሙና የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸው አልቆ ሲለቀቁ፣ መውጫው በር አካባቢ አገኘችው። በሦስተኛው ክፍለ ጊዜ ላይ ቀድማ የነገረችው ቢሆንም ማስታወሷ ነበር።
‹‹እንዳትረሳብኝ ... አማርኛ ከኔ ትሻላለህ ብዬ ነው››
‹‹ለመቼ ነው የማደርስልሽ?››
አናሳ ዓይኖቿን፣ ቀይ ዳማ ፊቷ ላይ ዓይን የሚገባ ወዛማ አፍንጫዋን ይመለከታል።
‹‹ነገውኑ ...››
‹‹ቻ ... ው›› አላት። ፈገግ እያለች ሄደች።
ዓይናውጣነቷ የታወጀ ቢሆንም፣ መሽኮርመሙን ስትችልበት አያት።
....
‹ነገ ረቡዕ መሆኑ ነው ... እቴቴን ላሠራት እችላለሁ፣ ...አፍንጫዋ ... አፍንጫዋ...› እያለ እያሰበ፣ ወደ ቤቱ የሚወስደውን መንገድ ታጥፎ ያዘ።
እቤት ሲደርስ .....
የደጁን  የቆርቆሮ በር ገፍቶ ሲገባ፣ በረንዳ ላይ ጀርባቸውን ለሱ ሰጥተው፣ ከእናቱ ፊት የተቀመጡ እንግዳ ሴት ተመለከተ።
‹‹መጣህ...?›› አሉት እናቱ፣ ሲያዩት።  ‹‹ውብዬ ... ዘመዳችን ናት ሰላም በላት ና...››
ሴትየዋ ከተቀመጡበት ሳይነሱ ከወገባቸው ተጠምዘው፣ ዘወር ብለው ተመለከቱትና እጆቻቸውን እንዲሁ - እንደ ክንፍ ዘረጉት።
‹‹ውይይ ...ይ ... እሱ ነው እንዳትይኝ!... ና ና በሞቴ፣ ...  አድጎ የለም’ንዴ?! ... እኔ ስለየው’ኮ አንድ ፍሬ ልጅ ነበር››
እንግዳዋ ሴትዮ እያለፉ ሳሙት።
‹‹አወ’ከኝ?›› አሉ፣ ጭንቅላታቸውን ወደ ኋላ ሳብ አድርገው ...በትኩረት እየተመለከቱት።
አንገቱን በፀጥታ ደፍቶ ቆሟል ....
‹‹ውይ-ይ ይረሳ ይሆናል። ... አንቺዬ ተመዞ የለም’ንዴ!›› አሉና፣ ቀና ሲል አፍንጫቸውን ሲያካክኩ አያቸው።
‹‹የውልሽ እንግዲህ...›› ብለው አቆሙ እናቱ፤ በፈንታው ዘለግ አርገው ተነፍሰው።
‹‹ወይ ባሌ!...›› አሉ ሴትየዋ ተከትለው። ለምን እንዲህ እንዳሉ አልገባውም።
እናቱ ባጎነበሰበት እጇን ልካ ራስ ቅሉን እየደባበሰች መናገር ጀመረች።
‹‹የውልህ ልጄ፣ በሰው አገር አንተን ወልጄ - ስንት ግዜ እየታመምክብኝ ስሰቃይ እጎኔ ያለርሷ ወገን አላገኘሁም ነበር...›› እናቱ መቀጠል አልቻሉም። ወደ ማለቂያው የመጣው ገርዳፋና  እንክርፍ ድምፃቸው ቅርፅ አጥቶ፣ ክርር እያለ፣ ከጉሮሯቸው ማለፍ ሳይችል ቀረ / በአንደበታቸው መፍሰስ ሳይችል ቀረ። እቅፋቸው ስር እንደቆመ ቀና ብሎ (በድፍረት) የእንግዳዋን ሴት ፊት ተመለከተ። አፍንጫቸውን ዳበስ ዳበስ አድርገው በፈገግታ አዩት። ፍንጭታቸው ፈነደቀች፤ ጥቁር ጮራ! ለራሱም ለምን እንደሆነ አልገባውም  ግን  ደጋግሞ አፍንጫቸውን ይመለከታል። ቀና ሲል ዓይኑ ከዚያ ላይ ያርፍበታል።
ምክንያቱን ለጊዜው ጭንቅላቱ አልይዝ ሲልበት፣ በዚህ በኩል ሙናን በተመለከተ፣ ብቻውን ለመሆን ልቡ ቆማ ነበር።  ... እንዴት ያምልጥ ከእኒህ አሮጊቶች?
‹‹እንዴት ይወድሽ ነበር ያኔ...››
‹‹ታዲያስ... ስ-ስስ…›› እሴትየዋ ስር ቆሞ ስለነበር (እሳቸው ጎተቱት ወይስ እሱ ‹ተሳበ›? አያውቅም) ወደ ስስ - ስውር ፉጨት እስኪለወጥ የጎተቱትን የ‹‹ታዲያስ› ‹‹ስስ...›› ሰምቷል። ከቃል በፉጨት በኩል አድርጎ ወደ ትንፋሽ የተለወጠውን።
‹‹...ያማ ተነግሮ መቼ ያልቃል። የባልተቤቴስ  ቅናት!... ልክ እንዳንቺ እናትነትሽን የቀማሁሽ ይመስል አብሮሽ አልጫወት፣ አልውል ቢል አንዴ እንዳለቀስሻት!... ደሞ ትዝ ይልሻል፣ ይሄ ጅሉ ባሌ እያልኩ ሳበሽቀው፣ ያለቅሰዋል ይዞ...”
‹‹ሃ ሃ ሃ ሃ - ሃ!... ሁ ሁ - ሆ ሆ!... ማን ይረሳል?!... ምን መዋል ብቻ አዳሩስ? እኔ የሰራሁለትን መብላትም ትቶ!....”
‹‹ወይ ያ ሁሉ...›› እንግዳዋ ጀምረው ፀጥ አሉ፤ ሊያወጡት ብለው መናገር የማይችሉት፣ የማይፈልጉትን ነገር  መልሰው የዋጡት ነገር ያለ ይመስል።
ቀኝ እግሩ የሳሎኑን ቤት ደፍ አልፎ ሲገባ፣ ጆሮው ኋላ ሲቀር...
‹‹የኔዋስ አድጋ - አ!... ደርሳልኛለች’ኮ!...›› - እንግዳዋ ሴት፣ ሲሉ ሰማ።
 መቼ፣ እንዴት ከሴትየዋ ጋር ይህን ሁሉ እንዳሳለፈ ትዝ ሊለው አልቻለም፣ ሲሰማቸው ተገርሞ ነበር። ለጊዜው በሌላ ሌላ ጉዳይ ስለተወጠረ ሊሆን ይችላል። አሁን የቸኮለው የሙናን ደብተር ፊቱ ዘርግቶ፣ ከሷ ጋር በተያያዘው ሃሳብ ሁሉ ለመስጠም ነው።
ጢዝ-ጢዝዝ ከሚለው ዝንብና ከሴትየዋ ጉዳይ ለመፋታት ግን ትንሽ መልፋት ነበረበት። እንደ ምንም በግትርነት ትኩረቱን እዚህ አደረገ ። ታግሎ ሲያበቃ ...  የሙና ደብተር የመጀመሪያ ገፅ ላይ በዥንጉርጉር ቀለሞች የተጻፉ ጥቅሶችን አየ። አብዛኞቹ የፍቅር ጥቅስ ናቸው፤ ቀልድም አለበት። አግድም፣ ስላች፣ ተቆልምመው፣ ተንጋደው በተሰለፉ ሆሄያት...። በቀይ፣ በአረንጓዴ፣ በጥቁር፣ በሰማያዊ።
‹‹...››
‹‹…  ...››
‹‹... ... ...››
ለርሱ ይመስላል፣ በጎን። የፍቅር ቅኔ። እንደዚያ መሆኑ ተሰማው። የቤት ስራዋን መስራቱን ሳይተው ስለሷ ማሰቡን ቀጠለ። ይቺ ልጅ ምኑን ለከፈችው? ሴት ጓደኞቿን እያለች፣ እነሱ ክፍል፣ እነሱ ኮሪደር ስታዘወትር በዓይን ተዋወቁ፣ ተግባቡ። እነኛን ጓደኞቿን ሰበብ እያደረገች መመላለሱን ቀጠለችበት። ምክንያቱም እሱ ላይ ያነበበችው <ሁኔታ> ይሁንታ ነበር።
ሲነጋለት፣ የ‹እረፍት› እና የ‹ወደ ቤት›› ሰዐት ጠብቆ ደጋግሞ ጎበኛት፤ እንዳይጠፋበት አርጎ መልኳን በምናቡ እየቀረፀ ወደ ቤቱ ሲገባ፣ ሱስዋም እንዳይለቅ ሆኖ ከልቡናው እየሰረፀበት ሄደ። ልቡ ድም ድሙን፣ ትንፋሹ ‹እጥር እጥሩ›ን  ... ለመደ። የልጅ ትንሽዬ ነፍሱ፣ ከአቅሟ በላይ የሆነ አስማት ለክፏት፣ እሱን አውሬ ስታለምድ።
ውብሸት እሷን በህልሙ አይደለም - አያት ...
የፍቅር ሚስጢር፣ ሁልግዜ በሚሰራው በሱ ስሌት፣ አንዴ በተያዩ ማግስት፣ ሁለቴ ሦስቴ መገጣጠማቸው የተለመደ ሆነ።   --- -- - - ‹‹አዎን እንደሚባለው ፍቅር እኛ የፈጠርነው ሳይሆን አማልዕክት በአሰራራቸው የሚወጉን መሆን አለበት......
‹‹የበዓል ጊዜም ይሁን፥ መንግስት በብዙ አይነት ሰልፍ በጠራን ቁጥር፣ ከተማሪዎች ጋር ተቀላቅዬ፣ ከዩኒፎርም ለባሹ ሁሉ ጋ ስጎርፍ፣ ከዛ ሁሉ መአት መሀል ‹‹እሷን›› በቅርበት - ዞር ብል ከኋላዬ ወይም ድንገት ከፊቴ አያታለሁ ... ይገርመኛል። ፍቅር ያስገርማል!... ሁሌ ግርግር ውስጥ ጣምራዎቹን ያገጣጥማል።  ለነገሩ ልብ ተቀራራቢ ቦታ ላይ ከሰፈረ የአካል ተከትሎ ተቀራራቢ ካርታ ላይ መገኘት ምኑ ይገርማል?!››
ለትምህርት ቤት ግቢው አዲስ የሆነች ቆንጆ እንደሆነች ያውቃል፤ የበኩር እድሉ ነች።
 ............. ‹መቼ ነው የምስማት?...› .........
ሰውነቱ መዛል ጀምሯል። ከሁለት ለእናቱ የተተዉ ጥያቄዎች በቀር ሌሎቹን ሠርቶ ጨርሷል። ...የእንግዳዋ ሴት ስሞሽ መጣበት ... ጉንጩን ክብድ አለው።  ርጥበቱ፣ ቅዝቃዜው - አሁን አሁን መሰለው ... የአፏ ሙቀትና እርጥበት ... ከላይ ወዝ ችፍ ያለበት አፍንጫዋ ..  ወዙ ...  ትናንሽ ደብዛዛ ጤዛዎች .....
የተደገፈው ሶፋ ልስላሴ አባበለው።  እሹሩሩ ...  <ተኛብኝ፣ ተኛብኝ > አለው፣ ምቾት በጉያው አቅፎ። <ለእንቅልፍ፣ ለበለጠው እረፍት ካልሰጠሁህ...>    .... በእዝነ ልቦናው እንግዳዋ ሴት ‹‹ብዪና ሂጂ››፣ ‹‹አልበላም!›› ከእናቱ ጋር ሲባባሉ ይሰማዋል።
‹‹መ’ቶ አይሰናበተኝም እንዴ?... እኔም የደረሰች ካንተ የማታንስ ልጅ አድርሻለሁ ... በዪልኝ  (ድምፃቸውን ዝቅ አደረጉናም) - የታባቱ’ንስና ከሌላ ወለድኩበት!››
(<...ለሱ እንዳይሰማ ካልፈለጉ ለምን ድምፃቸውን ዝቅ አደረጉት?> ... ሰመመን ውስጥም ሆኖ ያስባል።)
የእናቱና የእንግዳዋ ሴትዮ ሳቅ፤ እየተቃቀፈ፣ እየተደራረበ፣ … እየተቀዳደመ ... እየተከታተለ ... መጥቶ እዚህ ድረስ ይሰማዋል - በትንሹ።
...ነውዝ ውስጥ ገባ።
ገልበጥ ብሎ ፊቱን ትራሱ ስር ቀበረ።
በሰመመን ... እናቱ ስትገባ ... ‹‹ይሄውልህ - ማር ይዛልን ... ሀገር ቤት ጠፍታ ሄዳ...›› ስትል ሰ-ም..ማት።
‹‹ውይ! ተኝቷል ልጁ...››
***
ጠዋት፣ ... መማሪያ  ክፍል ውስጥ ነው፤ ቲቸር ገሰሰ ይጮኻሉ።
እሱ አይሰማም። ከመጨረሻው ወንበር ተርታ ሆኖ፣ ዴስኩ ስር የራሱን ሥራ የያዘ ይመስላል።  መፃፊያ ጠረጴዛው ስር አጎንብሷል፤ አመሉ ነው። ቲቸሩ በሩ ሲንኳኳ ልፍለፋቸውን ገቱና ወደ በሩ ቀስ እያሉ ተራመዱ። የከፈቱትን በር ገርበብ አርገው እንደያዙ፣ አንገታቸውን ወጣ አድርገው ለመሰማት የራቀ ንግግር አደረጉ፤ መለስ አሉናም   “ውብሸት ... ውብሸት ደጉ?”’ እየተጣሩ ጠየቁ።
‹‹አቤት?›› አለ ካደፈጠበት ዴስክ ሥር ቀና ብሎ።
‹‹ተነስ ጊዜያችንን አትግደል ... ውጪ ሰው ይፈልግሃል!...››
ከዴስኩ ስር ያወጣውን ደብተር ይዞ ወደ ውጪ ወጣ - - ጠርጥሯል - - ወደ ጎን ሲመለከት (ልቡ ሶምሶማዋን ጀምራለች)፤ ሙና ከበሩ ጎን ግድግዳው ላይ ለጥ ብላ፣ ተደግፋ ፊት ለፊቷ ሜዳውን ትመለከታለች። ከመምጣቱ እንኳን ወዲያው አልዞረችም።
....
የተመሰጠ ፊቷን ፈዞ እየተመለከተ ጥቂት ሰከንዶች ጠበቃት - በራሷ ጊዜ ዞር አለችና አየችው፤ ዞር ብላ ስታየው ‹‹እንዴት መጣሽ?›› አላት እየተንሾካሾከ . . .
‹‹ሰራህልኝ?›› አለች፤ መልስ የማሻውን ጥያቄ ችላ ብላ።
‹‹አዎ.. ን - ግን ሁለት ጥያቄዎች ቀሩኝ››
‹‹አሁን እንሠራዋለን በቃ ... ሜዳ እንውረድ›› ቀልጠፍ አለች በስሱ።
ወደ ኋላው መለስ ባለው በር ተመለከተ፤ መምህሩም ተማሪዎቹም በውል አይታዩትም። (አይታዩኝም ማለት አያዩኝም ሆነ።) ከመቸው መጋል የጀመረው የመምህሩ የስሜት ድምፅም ተሰማው።
ከበረንዳው ደረጃ ወርደው ተንደረደሩ። ተማሪዎች ለእረፍት ክፍለ ጊዜ ከሚራወጡበትና ስፖርት ትምህርትን በተግባር ከሚማሩበት ሰፊው ሜዳ ገብተው፣ ሰፋ ያለ ትልቅ የአሸዋ ድንጋይ ላይ ተጠባብቀው ተቀመጡ፡፡  ደብተሩን የጭኖቻቸው ከፋይ ላይ ዘረጉት።  ደብተሩን ግማሽ ግማሽ፣ ጭኖቻቸው ላይ ዘረጉት።
ሙና ‹‹ቆይ!›› ትልና በፌስታል የተጠቀለለ ነገር ታወጣለች።
‹‹ምንድ’ነው?›› ይላታል- በትከሻዋ ላይ።
‹‹ማር ነው  ... እንዴ መጀመሪያ  ...እ››
በአመልካች ጣቷ ከማሩ ዝቃ ማር ያንዠረገገ ጣቷን ወደ አፉ አመጣች። ማር የለበሰ ጣቷን አብሮ መምጠጡ/መላሱ  ተመቸው። ጣቷ ይጣፍጣል...።
የማሩና የጣቷ ወሰን የተጣረሰ መሰለው። ጣቷም አብሮ ማር ማር፣ ማሩም እጇን እጇን ያለው መሰለው።
እሱም ለሷ - ልክ  እንደርሷ እያደረገ - -።
በኋላ - - ቀና አለች። ቀና አለ። ተያዩ። ልቦቻቸው ‹ብርር-ርር› አሉ። ቀድማ አፈረችና ደብተሩ ላይ አቀረቀረች። በትከሻዋ ላይ ደገፍ አላት...። አፍንጫው ፀጉሮቿ መሀል . የፀጉሯ ቅባት ሸተተው። የፀጉሯ ሽታ...። እንዳቀረቀረች ወደ ታች ከምታመለክተው አፍንጫዋ ላይ ወዝ ተንቸፍችፎ ተመለከተ...፣ በከንፈሮቹ የአፍንጫዋ ጤዞች ላይ ወረደባቸው ..ሊያፈራርሳቸው፣ እንደ ነፋስ።
ደብተሯ ከጉልበቶቻቸው ስር ... ከመሃል - ተንሸራቶ ወደቀ፣ ነፋስ ገላለጠው። አላዩም፣ አልሰሙም።
የት እንዳሉም፣ ምን ሊያደርጉ እንደሆነ አያውቁም።
... ብቻ ተጠጋጉ፣ ተቀራረቡ፣ ተነካኩ...።
‹‹መፈላለጋቸውን›› ብቻ ከውስጣቸው እያዳመጡ።
***
ረቡዕ ጠዋት፡-
‹‹ውቤ ... ውቤ’ኤ!  ኧረ ውብሸት!››
ከአልጋው ነቃ ብሎ ተቀመጠ።
‹‹አንተን’ኮ ነው ... እንዲ’ነች’ና!... አትነሳም?!››
‹‹ኧ - አቤት፣ እም...›› ዓይኖቹን እያሻሸ።
‹‹ተነስ’ንጂ... ትምህርት ቤት እንዳይረፍድብህ፤ ዛሬ ደግሞ አነጋህ ... ስፖርቱም ቀረ...››
‹‹አቦ - በቃ እሺ›› አለ፤ ከደረቱ ርቆ ባልተሰራጨ ድምፅ።
.....
‹‹ሠራሽልኝ?›› ጠየቃቸው ጮሆ፤ ድንገት እንደ መባነን ብሎ።
‹‹ውይ ልጄ... እባክህን ከዚያች እንግዳችን ጋር ሳወጋ አመሸሁ አይደል...፣ ከዛም ሥራ ነበረብኝ፣ ጉድ ጉድ ስል ረስቼው - መኝታዬ ሄድኩ››
‹‹የስ-ስስ!›› አለ ድምፁን ቀንሶ፣ በቀስታ ተንፈስ ብሎ።
 .....  
‹‹ደግሞ ስነግርህ የምትጽፈው አንተ ተኝተህ እንዴት ሆኖ? .... የሚያነብልኝስ ማን ሆነና?!››
‹‹አዎ፣ አዎ››  ... ጥድፍ! (አለ ተስገብግቦ)
....
ተስፈንጥሮ ተነሳና የክፍሉን መስኮት ከፍቶ ቆመ። - - ያደረ ህልሙን ለማማጥ ... የረቡዕ ጠዋት ህዋ ላይ ዓይኑን አማተረ።
.... ...
እናቱ ከጓዳ ... ‹‹የዛሬው ቁርስ ልዩ ነው... እንግዳችን ከሃገሯ ማር አመጣችልን’ኮ ... ሳልነግርህ...›› ... ከእዚያ በኋላ ምን እንዳሉ አልተሰማውም። ...
መስኮቱ ላይ ለመቀመጥ ሲመቻች የነበረው ሰውነቱ - ተያያዘ።
ዓይኖቹ ፈጠጥ ብለው ተርገበገቡ።
...
. . . . እናም ፈገግ አለ።
(ለአዳም ረታ መታወሻ ይሁን።)
ውሉድ - ያቦካው - ወንጌል
ምሽት 01 : 04  ...
መለስ ባለው ቀይ መጋረጃ ታጥፎ በላዩ ከተጣለበት በር:: ቀዘቃዛ ነፋስ እየገባ ቆዳውን እንደዶሮ ገላ ሽፍ ማድረግ በጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ይኽንንም ቢገነዘብም እስካሁን በሩን መለስ ለማረግ አልተነሳም።
አልፎ አልፎ ብቻ ከሚጫጭርበት አጀንዳ ላይ ቀና እያለ ወደ በሩ ይመለከታል። ከእናቱ ሕልፈት በኋላ ቅያሜውን አሳድሮበት ለነበር አባቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆዱ መረበሽ ጀመረ፡፡
ወላጅ አባቱ ________ ከጓደኞቹ ጋር የጫት ነዶ ሲገራርዝ ያመሽና አራት ሰዐት መዳረሻ ይገባል። ...
አሁን ግን ለአራት ሰዐት ሶስት ደቂቃ ብቻ እየቀረው ሆዱ ተንቦጫቦጨበት፡፡ ባር ባርም ያለው መሰለው፡፡
ያሟረተ መስሎታል፤ የተነበየም።
ደሙን በሰውነቱ የገባው ፍራት አጓጉሎት በምሽትና በሌሊት መሀል ተነስቶ ወጣ።
መንደሩ ፀጥታን አንግሷል። ምድር ፀጥታ ሲውጣት፣ ሰማይ ደሞ ሕይወት የሚዘራበት ጊዜ ነው። የነፍሳት ጭርጭርታ ... የውሾች ማላዘን ... ከዚ ጋርም ቅልቅል፦ መነሻቸው ያልተደረሰበት፣ መኖራቸው የተጠረጠረ ድምፆች ... በመኖርና ባለመኖር መሀል ያመነታ ህላዌ ። ሹክሹክታ .. የነፋሱ - የቅጠሎቹ ነው!፣ የሰው ነው - የመናፍስት!  ... ግራ መጋባት። ፍርሐት።
ጆሮው ልቡን ከፍቶ ለመርዶ የቸኮለ ይመስለዋል። ማሟረትስ የለብኝም ብሎ ቀልቡን እንዳያረጋም እየተነበየ ያለም ይመስለዋል።  ...
ከጓደኞቹ ከነከድር ዘንድ አለመኖሩ ሲነገረው ... እላይ ሰፈር ሄደ ... እግሩን እየተከተለ፡ እንጂ እግሩን አልመራውም፡፡ ደመነፍሱ ግን መሄድ አለበት እየመራ ወሰደው ‘ንጅ ... .... ...
የአባቱ _________ ያ ቀውላላ ቁመት ደሙን ዘርቶ መንገድ ወድቆ እተዘረጋበት። .....
በሕሊናው ፅፎ የጨረሰውን፣ በእጁ ደምስርና በብዕሩ ግን መውረድ ጀምሮ ያላለቀውን - ፅንስ፣ ችግኝ - ፈራው...። ፈራ፣ ሰጋ።
የክየና ውቃቢው ምሱን ቢያገኝም፥ የመፃፍ መንፈሱ ንቃት ንቃት ቢለውም፣  ልቡ ግን እቅት እቅት አለው።
ከላይ የመጣበትን ይዘት በስሜቱ ለአጭር ልብወለድነት እያቀደው ይነብር እንጂ በእጁ በድንገት ይሸረካክተው ጀመር፡፡ አፉ አስገብቶ በጥርሶቹ አኛኘከው።
በመጀመሪያ ቃል ነበር ..  ቃልም በሚፈጥረው በደራሲው ዘንድ ...  ሁሉም በእርሱ ሆነ።
ታህተ - ሕሊናው እየመራው ገፀባህሪ ሰራ:: የሰራት ገፀባህሪይት በእናቱ መላ ባህሪይ አቋም ላይ የተመሰረተች መሆኗ ለራሱ ሳይታወቀው። ዳራውን ሳይረዳ።
አሁን ይገንዘበው እንጂ ያኔ ከሙሉ ፈጠራነት ውጪ ሆኖ አልታየውም። ....
የድርሰቱ ምትሓት ... ትንብይ ወይ ፍጥረት ፣ ነገን መስራት ወይስ ነገን ማየት?
ያኔ ገና በታዳጊነቱ፥ በአስራ ሁለት አመት እድሜው እፃፈው ድርሰት ውስጥ እንዳለችው ሴት ሆና እናቱ ታዳጊውን ፀሀፊ ትታ ሞተች።
ቀና አለና ወደ በሩ ተመለከተ። ...
አባቱ ________ ዘለግ ባለ ቁመናው የተደፋ አንገቱን አስግጎ ገድ - ገድ እያለ ገባ።
የተገፋው በር ... ወደ ቦታው እስኪመለስ ማማጡን ያዘ። ...
ሌሊት 04 : 14
ለትንሹ ለታዳጊው እኔ
14 / 06 / 2006
ድሬደዋ -ምሽት


Read 3086 times