Saturday, 16 June 2012 09:07

በሽታና መድሃኒቶች ሲለማመዱ…

Written by  - መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

“በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትም፤

መድኃኒቱን የደበቀ በሽተኛውን አያድንም፤ መድኃኒቱን የለመደኸ፣ በሽታ አይድንም!”

“ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል”

ሼክስፒር - ሐምሌት

(ትርጉም - ፀጋዬ ገ/መድህን)

ጭንቅላቷን ከተኛችበት ትራስ ላይ ቀና ማድረግ ተስኖአታል፡፡ ትኩሳቷ እንደ እሳት ያቃጥላል፡፡ ፊቷ በላብ ተጠምቋል፡ ከተኛችበት አልጋ ላይ ሆና ታቃስታለች፡፡ በቶንሲል ህመም ሣቢያ አልጋ ላይ ከዋለች ስምንተኛ ቀኗ ነው፡፡እየደጋገመ የሚነሳባትን የቶንሲል ህመም ለማስታገስና ከበሽታዋ “ለመፈወስ” ለወትሮው እምብዛም አትቸገርም ነበር፡፡ ከጐረቤቷ ካለው ፋርማሲ እየገዛች የምትወስደው መድሃኒት ፈጣን “ፈውስ” ይሰጣት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ መድሃኒት መዋጥ ባትወድም መርፌ ከመወጋት ይሻለኛል ስለምትል፣ ባመማት ጊዜ ሁሉ የምትወስደው ሽሮፕ ወይንም የሚዋጡ መድሃኒቶችን ነው፡፡

ከህመሟ የመሻል ምልክቶችን ስታገኝ መድሃኒት መዋጧን ወዲያው ታቆማለች፡፡ የቶንሲል ህመሟ ከሣምንታት ባልዘለለ ጊዜ እየደጋገመ ቢመላለስባትም መድሃኒቶችን ስትጀምር ቶሎ ይሻላት ነበር፡፡ አሁን ግን ጠንክሯል፡፡ በሽሮፑም በሚዋጥ ክኒኑም ህመሟን ለማስታገስ ጥረት ብታደርግም አልተሳካላትም፡፡ የጉሮሮዋ እብጠት ጨርሶውኑ ምግብ መዋጥ ከልክሏታል፡፡ ፋርማሲስቱ ጐረቤቷ “በሽታሽ መድሃኒቱን ተለማምዷል፡፡ ስለዚህ ወደ ሆስፒታል መሄድ አለብሽ” ብሏታል፡፡ ህመሟ ከአቅሟ በላይ ሲሆንባት ከመንደራቸው ከፍ ብሎ ወዳለው የግል ክሊኒክ አመራች፡፡ ሐኪሙ ምርመራውን ሲያጠናቅቅ መድሃኒት አዘዘላት፡፡ የታዘዘላትን መድሃኒት ለቀናት ዋጠች፤ ከህመሟ የመሻል ምልክት ግን አላየችም፡፡ ተጨነቀች፡፡ ሐኪሙ በቀን 3 ጊዜ እንድትውጥ ያዘዘላትን Amoxicillin ባለ 500 ሚ.ግ መድሃኒት በስልጣኗ በቀን አራት ጊዜ መውሰድ ጀመረች፡፡ አሁንም ምላሽ የለም፡፡ ሁኔታዋ ያሳሰባቸው ቤተሰቦቿ ወደ ሆስፒታል ይዘዋት ሄዱ፡፡ ምርመራውን ያካሄደላት ዶክተር ስለቀድሞ የህክምና ታሪኳ ጠይቆና የታዘዘላትን መድሀኒት አይቶ፣ በሽታው መድሃኒቱን ስለተለማመደ በምትወስደው መድሃኒት ፈውስን ማግኘት እንደማትችልና የተለየ ህክምናና ክትትል እንደሚያስፈልጋት፤ ለዚህ ደግሞ ሰፋ ያለ ጊዜና ተጨማሪ ወጪ እንደሚያስፈልጋት ነገራት፡፡ በህመሟ ሳቢያ አልጋ ላይ ከዋለች ጀምሮ የተዘጋውን እና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮዋን የምትገፋበትን የሸቀጥ ሱቅ እንደ ሃሳቧ ቶሎ መክፈት አለመቻልዋ የመርዶ ያህል ከበዳት፡፡ በመጨረሻ የጤናዋ ጉዳይ አሳሰባትና ከሆስፒታሉ የታዘዘላት መድሃኒት ገዝታ በአግባቡ መውሰድ ጀምራለች፡፡ መድሃኒቱን በታዘዘላት መጠንና ሁኔታ ሳታቋርጥ መውሰድ እንዳለባት ከሐኪሟ ተነግሮአታል፡፡ ህመሟ ቢታገስላትም እንኳን የታዘዘላትን መድሃኒት ሳትጨርስ እንደማታቋርጠው ወስናለች፡፡ መድሃኒት ጀምሮ ማቋረጥና ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መውሰድ የሚያስከትለውን ችግር አይታለችና፡እንደዚህች ወጣት በርካታ ህሙማን በየዕለቱ ለሚያጋጥሟቸው “ቀላል” የተባሉ ህመሞች:- ቶንሲል፣ ሆድ ቁርጠት፣ ራስ ምታትና ጉንፋን፣ በፈቃዳቸው መድሀኒቶችን ለራሳቸው አዘው ከየፋርማሲው እየገዙ ይጠቀማሉ፡፡ መድሃኒቶቹ ህመማቸውን ካስታገሱላቸው በኋላ መውሰዳቸውን ያቋርጣሉ፡፡ ይሄ ደግሞ መድሃኒት የተለማመደ ቫይረስ እንዲራባ በማድረግ ከፍተኛ የጤና ችግሮችን ያስከትላል፡፡ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ትርጓሜ፤ መድሃኒቶች የሚባሉት ለህመምተኞች በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅተው በሽታን ለመከላከልና ለማከም የሚያገለግሉ ኬሚካሎች ናቸው፡፡

 

ሁሉም መድሃኒቶች የጐንዮሽ ጐጂ ባህርያት አሏቸው፡፡ እነዚህ የጐንዮሽ ጉዳቶች ከቀላል እስከ ከፍተኛ ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ መድሃኒቶቹ በጥቅም ላይ የሚውሉትም የሚያስከትሉት የጐንዮሽ ጉዳት ከሚሰጡት ጥቅም አንፃር ሲወዳደር አናሳ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ለህመምተኛው መድሃኒቶችን የሚያዙ ሐኪሞችም ሆኑ መድሃኒት የሚያድሉ ባለሙያዎች፤ መድሃኒቶቹ የሚያስከትሉትን የጐንዮሽ ጉዳቶች ለህመምተኛው በግልጽ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ  መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከዩኤስኤድ፣ ኤምኤስኤችና ኤስፒኤስ ጋር በመተባበር የፀረ ተህዋስያን መድሃኒት መላመድና የሚያስከትሉትን የጤና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አስመልክቶ በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት ለጋዜጠኞች ስልጠና አዘጋጅቶ ነበር፡፡ፀረ ተህዋስያን መድሃኒት የሚባሉት በቫይረስ፣ በባክቴሪያ፣ በፈንገስና በፕሮቶዞዋ አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግሉ መድሃኒቶች ናቸው፡፡የመጀመሪያው ፀረ -ተህዋስ መድሃኒት (ፔንስሊን) እ.ኤ.አ በ1929 ዓ.ም አካባቢ ከተፈረከበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በእነዚህ ፀረ ተህዋስ መድሃኒቶች ድነዋል፡፡ ይሁን እንጂ መድሃኒቶቹ አንድም አዳዲስ የፀረ - ተህዋስያን መድሃኒቶች ግኝት እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ ወዲህ በጣም በመቀነሱ፣ አሊያም የሰው ልጅ የተገኙ ፀረ ተህዋስያን መድሃኒቶችን በአግባቡ ተጠቅሞ ለሚከተለው ትውልድ ማስተላለፍ ባለመቻሉ፣ ከጥቅም ውጪ እየሆኑ፤ ዓለም ወደ ቅደመ - ፀረ - ተህዋስያን መድሃኒቶች ግኝት ዘመን እንዳትገባ ሥጋት እንደሆነባት ከኢትዮጵያ መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ክስተት እንደ ኢትዮጵያ ላሉና የበሽታ ስርጭቱ ከፍተኛ ለሆነባቸው ታዳጊ አገራት ትልቅ አደጋ ነው፡፡ በአገራችን ለተለያዩ በሽታዎች መንስኤ በመሆን ለበርካቶች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሚሆኑት በሽታዎች የሚፈጠሩት በማይክሮ ኦርጋኒዝምስ (ፈንገስ፣ ፓራሳይት፣ ቫይረስና ባክቴሪያዎች) የሚከሰቱ በሽታዎች ናቸው፡፡ ለእነዚህ በሽታ አምጪ ተህዋስያን ማከሚያነት ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት ፀረ - ተህዋስያን መድሃኒቶች ዛሬ ከተህዋስያኑ ጋር በመላመዳቸው ከበሽታ የመፈወስ አቅማቸውን አጥተዋል፡፡ የፀረ ተህዋስያን መድሃኒቶች መላመድ በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን ለማከምም ሆነ ለመከላከል ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው አንድ ፀረ ተህዋስ መድሀኒት በቀድሞው መጠን ወይም ከዚያ በላይ በሆነ መጠን ተሰጥቶ ተዋህስያኑ የማይሞቱ ወይም መራባታቸው የማያቆሙ ከሆነ ተህዋስያኑ መድሃኒቱን ተላምደዋል እንደሚባልና ሂደቱም የፀረ - ተህዋስያን መድሃኒቶች መላመድ (Antimicrobial Resistance) ተብሎ እንደሚጠራ የባለስልጣን መ/ቤቱ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ፀረ ተህዋስያን መድሃኒት መላመድ በሁለት መንገዶች ይከሰታል፡፡ የመጀመሪያው የፀረ ተህዋስያን መድሃኒቶች በሚወሰዱበት ወቅት በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙትን በሽታ አምጪ ተህዋስያን ይገድሏቸዋል፡ አንዳንዶቹን ደግሞ እድገታቸውን ይገቱአቸዋል፡፡ በዚህ ወቅት በሽታ አምጪ ተህዋሳቱ የመድሃኒቱን ኬሚካላዊ ባህርይ እንደሰው ያጠናሉ፡፡ ከዚህ በኋላም መድሃኒቱን ለመቋቋምና ከጉዳት ለመዳን በሪቮሌሺን ሲስተም መለወጥ ይጀምራሉ፡፡ መድሃኒቱንም ይለምዱታል፡፡  በዚህ ጊዜም መድሃኒቱ ጥቅም አልባ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ አይነቱ በሽታዎች ከመድሃኒት ጋር የመላመድ

ሲስተም (ሬዚስታንስ) ይባላል፡፡ ሌላው የበሽታዎች መድሃኒትን የመላመድ ችግር የሚከሰተው ለመድሃኒቶች ጥገኛ በመሆን /በአዳፕቴሽን/ የሚመጣ ችግር ነው፡፡ በተለይ የአእምሮ ህሙማንና ከእንቅልፍ ችግር ጋር የተያያዙ መድሃኒቶች ከሐኪም ትእዛዝ ውጪ ሲወሰዱ አሊያም ሱስ አምጪ የሆኑ መድሃኒቶች በተደጋጋሚ ሲጠቀሙ ለእነዚህ ኬሚካሎች ጥገኛ ይኮናል፡፡ ከእነዚህ ኬሚካሎች ውጪ ጤናማ ህይወትን መምራትም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የዚህ ችግር ተጠቂ የሆነ ሰው ከእነዚህ ኬሚካሎች ጋር ያለው ወዳጅነት እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሚወስደውም መጠን (ዶዝ) እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በሒደትም ኬሚካሎቹ በዚህ ሰው ላይ ሙሉ በሙሉ ሊሰሩ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሂደቱም አዳብፕቴሽን በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ችግሮች ሊከሰቱ የሚችሉትም አግባባዊ ባልሆነ የመድሃኒት አጠቃቀም ነው፡ በትክክል ተመርምሮ ምንነቱ ለተረጋገጠ በሽታ ትክክለኛው መድሃኒት በትክክለኛው ጊዜና መጠን ሳይሰጥ፣ አግባባዊ የመድሃኒት አጠቃቀም መኖሩን ያመለክታል ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሚወሰድ መድሃኒት ፤ አግባባዊ ያልሆነ ነው እንላለን፡፡ ይህም የመድሃኒት መላመድን አስከትሎ ህይወትን ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ በአንድ ወቅት የተለያዩ አይነት ኢንፌክሽኖችን ለማዳን ከፍተኛ ጠቀሜታ የነበረውና በስፋት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ፔኒሲሊን የተባለው መድሃኒት የማዳን ችሎታው አጠራጣሪ ሆኗል፡ ይህም መድሃኒቱን ሊቋቋሙ የሚችሉ ባክቴሪያዎች እየተባዙ በመምጣታቸው ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ሌላው መድሃኒትን ስለተላመዱ በሽታዎች ምሳሌ ሊሆን የሚችለው የ MDR ቲቢ ነው፡፡ ይህ በሽታ ከመደበኛው የቲቢ በሽታ የሚለይበት ምክንያት በህመምተኛው ውስጥ የሚገኙት የበሽታ አምጪ ተህዋስያን፤ መድሃኒቶችን የተላመዱ በመሆናቸውና በመደበኛ ህክምና ሊድኑ የማይችሉ በመሆናቸው ነው፡፡ አንድ የ MDR TB ህመምተኛ ከህመሙ ለመፈወስ እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ ህክምናዎችን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ህክምና ዛሬ በአገራችን በሦስት ቦታዎች ብቻ የሚሰጥ ሲሆን ሁለቱ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታልና በአለርት ህክምና ማዕከል፣ከአዲስ አበባ ክልል ውጪ ደግሞ በጐንደር ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ነው፡፡ የዚህ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች በሽታውን ለሌሎች ለማስተላለፍ እጅግ ፈጣኖች ሲሆኑ ወደ ጤነኛው ሰው የሚተላለፈውም በሽታ መድሃኒትን የተለማመደ ቫይረስ (MDR TB) ነው፡፡ የኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች የሚወስዱዋቸው ፀረ ኤች አይቪ መድሃኒቶችም ከበሽታው (ከቫይረሱ) ጋር በመላመዳቸው ምክንያት ለህሙማኑ ምንም ጠቀሜታ አለማስገኘታቸውንና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉ የኤች አይቪ ህሙማን በአብዛኛው የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ሕሙማን መንከባከቢያ ማዕከል መሥራች አቶ መስፍን ፈይሳ ይገልፃሉ፡እንደ አቶ መስፍን ገለፃ ህሙማኑ መድሃኒቱን የሚያገኙት ከሆስፒታሎች ብቻ በመሆኑና ሆስፒታሎቹም ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የኤችአይቪ ህሙማን ቀድሞ መድሃኒቱን ይወስዱበት ከነበረው ሆስፒታል የሪፈር ወረቀት ካላመጡ በስተቀር መድሃኒት ስለማይሰጧቸው፣ አብዛኛዎቹ ህሙማን መድሃኒታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡ ወይንም ደግሞ እንደ ጀማሪ በመሆን ቀደም ሲል ይወስዱት ከነበረው መድሃኒት የተለየ ይወስዳሉ፡፡ ይህ ሁኔታም ቫይረሱ መድሃኒቶችን በቀላሉ እንዲላመድ ያደርገዋል፡ በmsh /Management science for health/ የመድሃኒት አጠቃቀምና የፀረ ተህዋስያን መድሃኒት በጀርሞች መላመድ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ጤናው አንዱዓለም፤መድሃኒቶች በጀርሞች መለመዳቸው ሊታወቅ የሚችለው በላብራቶሪ ምርመራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ህመምተኛው በራሱ ላይ ከሚያያቸው ለውጦች ተነስቶ መድሃኒቱን በሽታው ተለማምዶታል ማለት እንደማይችልም ይገልፃሉ፡፡ የኤች አይቪህሙማን ቫይረሱ መድሃኒቱን ተለማምዶታል ለማለት የሚቻለው የሲዲ ፎር ቁጥራቸው ለውጥ ከሌለውና ቫይራል ሎዱ/በሰውነታችን ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን/ ካልቀነሰ ወይንም ባለበት ከቆመ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትክክለኛው ምርመራ ሊታወቅ ይገባል፡ የኤች አይ ቪ ህመምተኛው የሚወስደው መድሃኒት ለወራት ብሎም አመት ድረስ ለውጥ ላያመጣ ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የህመምተኛው የመድሃኒት አወሳሰድ፣ የአመጋገብ ሁኔታው፣ ከደባል ሱሶች የፀዳ መሆን አለመሆኑ ተፅዕኖ አለው፡፡ ስለዚህም መድሃኒቱ በሽታውን ተለማምዷል አልተለማመደም ለማለት የግድ የላብራቶር ምርመራ ማድረግ ወይንም የህክምና ባለሙያዎችን ማናገር ያስፈልጋል፡፡ በግል ስሜትና ፍርሃት ብቻ መድሃኒቱን ተለማምዷል ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ የፀረ ተህዋስያን መድሃኒቶች መላመድ ዋንኛ መነሻው አግባባዊ ያልሆነ የመድሃኒት አጠቃቀም ነው ከተባለ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ህብረተሰቡ በመድሃኒት አጠቃቀሙ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሃኪምን ሳያማክሩ መድሃኒት መውሰድ፣ መድሃኒቶችን በጋራ መጠቀም (ለአንዱ የተሰራለት መድሃኒት ለሌላውም ይጠቅማል ብሎ ማሰብ) መድሃኒት ሳያልቅ መቋረጥ፣ በልዩ ልዩ ማህበራዊ ሰበቦችና ሃይማኖታዊ  ጉዳዮች ሳቢያ የመድሃኒት አወሳሰድ ሥርዓትን ማዛባት፤ በህብረተሰቡ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው! በሀኪሞችና በፋርማሲ ባለሙያዎች ዘንድ ደግሞ የተሳሳቱ መድሃኒቶችን የማዘዝና የመስጠት፣ ስለ መድሃኒቱ አወሳሰድ ለህመምተኛው በበቂ ሁኔታ አለማስረዳትና፣ ህመምተኛው መድሃኒቱን በሚወሰድበት ጊዜ ሊከተሉ የሚችሉትን የጐንዮሽ ጉዳቶች ህመምተኛው እንዲያውቅ አለማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ህመምተኛው መድሃኒቱን ጀምሮ በማቋረጡ ምክንያት ሊፈጠሩበት ስለሚችሉ ችግሮች በአግባቡ ሊነገረው ይገባል፡፡ በተገቢው የመድሃኒትአይነትና በትክክለኛው አወሳሰድ በቀላሉ ሊድን የሚችለው በሽታ ሌሎች ውድና አስከፊ ጐጂ ባህርይ ያላቸው መድሃኒቶችን ለረጅም ጊዜ እንድንጠቀም ሊያስገድደን፣ ህክምናውንም ውስብስብና አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላልና ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ፅሁፌን የማጠቃልለው ሰሞኑን በሰማኋት ቀልድ መሰል ዕውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ኰሎኔሉ ቆፍጣና የደርግ ወታደር ናቸው፡፡ መርካቶ አካባቢ ከሚገኝ አንድ የጓደኛቸው ሱቅ ውስጥ ከወዶቻቸው ጓደኛሞቹ እየተገናኙ ይጫወታሉ፡፡ ስለ ምርጫ፣ ስለ አገር ፍቅር፣ ስለ ኑሮ ውድነት፣ ስለ ቀድሞ ታሪክ ሁሌም ይወራል፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሚያነቧቸው የግል ጋዜጦች የሚያነቧቸው ናቸው፡፡ እኚህ የደርግ ኮሎኔል ከሌሎች ጓደኞቻቸው የሚለዩበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ በወቅቱ ይታተሙ የነበሩ የግል ጋዜጦችን ሁሉንም ይገዛሉ፡፡ ያነባሉ፡፡ ይህ የእኚህ ኮሎኔል የዕለት ተዕለት ህይወት ነው፡፡ ተዛንፎ አያውቅም፡፡ “ይህንን ሁሉ ጋዜጣ የሚገዙትና የሚያነቡት ለምንድነው? ብሎ ለጠየቃቸው ሁሉ “ጋዜጦቹን አንብቤ አንብቤ ሳበቃለሽ ብዬ ያለሃሳብ እተኛለሁ በሽታዬን ማስረሻ መድሃኒቶቼ ናቸው” ነበር መልሳቸው፡፡ ከጊዜ በኋላ ኮሎኔል የሚገዟቸውን ጋዜጦች ከቀን ወደ ቀን እየቀነሱ መጡና አንዲት ጋዜጣ ላይ ብቻ የሙጢኝ አሉ፡፡ ሁኔታቸውን የታዘበው የቀድሞ ጠያቂ፣ ሌላ ጥያቄ ይዞላቸው ቀረበ፡፡ “ኮሎኔል፤ ምነው ምን ሆኑ አንድ ጋዜጣ ብቻ ሆነ የሚገዙት?” ኮሎኔሉ ሲመልሱም፤ “ጋዜጦቹን እንደ መድሃኒት ሰውነቴ ለመዳቸው፡፡ ደህና እንቅልፍ አልሰጥ አሉኝ፡፡ ይመጣሉ ያሏቸው አይመጡም፡፡ እንዲህ ሊሆን ነው ያሉት አይከናወን ተስፋ ብቻ! ከህመሜ አልፈውስ አሉኝ!”

 

 

 

 

Read 10247 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 13:39